Monday, 08 August 2016 05:59

ግብጻውያን የወርቅ ጥሎሽ እንዲቀር ዘመቻ ጀምረዋል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የወርቅ ዋጋ መናር ለትዳር ፈላጊ ወንዶች ፈተና ሆኗል ተብሏል
     በግብጽ የወርቅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየናረ መምጣቱን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ወንዶች ለሚያገቧት ሴት የወርቅ ጥሎሽ የሚሰጡበት ባህላዊ ልማድ እንዲቀር ለማድረግ የተጀመረው ዘመቻ ተቀባይነት እያገኘ መሆኑን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ሻብካ በተባለው የግብጻውን ባህላዊ የሰርግ ልማድ መሰረት፣ አንድ ወንድ ሊያገባት ለሚፈልጋት ሴት የወርቅ ጌጣ ጌጦችን መስጠት እንደሚጠበቅበት የጠቆመው ዘገባው፣ አሁን አሁን ግን የወርቅ ዋጋ እየናረ መምጣቱ ለትዳር ፈላጊ ወንዶች ፈተና መሆን መጀመሩን ገልጧል፡፡በግብጽ የአንድ ግራም ባለ 24 ካራት ወርቅ ዋጋ 50 ዶላር ያህል መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፤ይህም የትዳር ፈላጊ ወንዶችን አቅም እየተፈታተነ በመሆኑ በማህበራዊ ድረገጾች የወርቅ ጥሎሽ ባህሉ እንዲቀር ዘመቻ እንዲጀመር ምክንያት መሆኑን አስታውቋል፡፡ ዘመቻው መጀመሩን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ግብጻውያን፣ልማዱ አንዲቀር ድጋፋቸውን ማሳየታቸውን የጠቆመው ዘገባው፤የዘመቻው ደጋፊዎች በወርቅ ምትክ ብር ወይም ሌላ ውድ ያልሆኑ ጌጣጌጦች በጥሎሽ መልክ ቢሰጥ መልካም ነው ሲሉ አስተያየታቸውን እንደሰነዘሩ ገልጧል፡፡የወርቅ ጥሎሽ እንዲቀር ድጋፋቸውን የሰጡ አብዛኞቹ የዘመቻው ተሳታፊዎች ወንዶች ቢሆኑም፣በርካታ ግብጻውያን ሴቶች ይህንን ሃሳብ በመደገፍ ከወንዶች ጎን መሰለፋቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

Read 1205 times