Monday, 08 August 2016 06:06

…“የባልና ሚስት አለመግባባት እና የፍቺ ምክኒያቶች”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ በአዲሱ ደረሰ
Rate this item
(34 votes)

(ካለፈው ሳምንት የቀጠለ)
        “የባልና ሚስት አለመግባባት እና የፍቺ ምክኒያቶች” በተባለው በአቶ አበበ መጽሃፍ ውስጥ ሌላኛው የፍቺ ምክኒያት ተብሎ የተጠቀሰው የድንግልና ጉዳይ ነው፡፡ እንደኢትዮጲያ ባሉ አክራሪ ሃይማኖተኝነት በሚበረከትባቸው አገሮች ድንግልና እንደቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ብዙ ጥንዶች የመጀመሪያቸውን የግብረ ስጋ ግንኙነት እንዲያደርጉ የሚጠበቀው በጋብቻቸው ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን ሚስት ድንግል ሆና ካልተገኘች መጥፎ ስሜት በወንዱ ላይ ሊያሳድር ይችላል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ይህ በባል ላይ የሚፈጠር መጥፎ ስሜት በትዕግስት ታልፎ  ወደ ተሳካ ጋብቻ ሊያመራ ቢችልም በሌሎች ብዙ አጋጣሚዎች ግን ጥንዶቹን በተጋቡበት ቀን ለፍቺ የሚዳርግ ምክኒያት ነው፡፡ በዚህ ምክኒያት ለፍቺ ሊዳረጉ የሚችሉ ጥንዶች ሊያስተውሏቸው ስለሚገቡ ሁለት እውነታዎች ይጠቁማል መጽሃፉ፡፡
የመጀመሪያው እውነታ ሴቷ ድንግል ሆና አልተገኘችም ማለት ከዚያ በፊት የግበረ ስጋ ግንኙነት አድረጋለች ማለት ብቻ እንዳልሆነ ነው፡፡ ሳይንሱ እደሚለው ሴቶች ከግብራ ስጋ ግንኙነት ውጪ ድንግልናቸውን ሊያሳጣቸው የሚችሉ ብዙ ምክኒያቶች ሊኖሩ እንደሚቸሉ ነው፡፡ ወንዱ በድንግልና አለመኖር ምክኒያት ሴቷን ለመፍታት ከመወሰኑ በፊት ይህንን እውነታ ሊያጤነው ይገባል ይላል መጽሃፉ፡፡
ሌላኛው እውነታ ድንግልና በአንድ ጊዜ የህክምና ምርመራ ብቻም የማይረጋገጥበት አጋጣሚ መኖሩ ሊጤን ይገባል- እንደመጽሃፉ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ድንግልና አለመኖርን ያስተዋሉ ጥንዶች ወደህክምና ምርመራ በማምራት ምርመራውን ካካሄዱ በኋላም የድንግልና አለመኖር ቢነገራቸውም እንኳን ምርመራውን በተደጋጋሚ፤ በተለያየ ጊዜ እና በተለያየ ቦታ ሊያርጉ እንደሚገባ እና ለዚህም የተሸሉ የሚሆኑት ባለሞያዎች የጽንስና ማህጸን ሃኪሞች መሆናቸውን ልብ እንዲሉ ጸሃፊው ያሳስባል፡፡
የልጅ መኖርን መደበቅ ሌላኛው በመጽሃፉ ላይ የተነሳው የፍቺ ምክኒያት ነው፡፡ ባል ወይም ሚስት አንድኛቸው ላንድኛቸው በግልጽ ያላሰወቁት ልጅ መኖር አንድ ትልቅ የፍቺ ምክኒያት ሊሆን ይችላል። ልጅ የተወለደው ከትዳር በፊት ወይም ከትዳር በኋላ ሊሆን ቢችልም ከትዳር በኋላ የተወለደ ልጅ በባልና ሚስት መካከል ያለውን ችግር የተወሳሰበ ሊያደርገው እንደሚችል መጽሃፉ ያብራራል፡፡
በርግጥ አንዳንድ ግለሰቦች የባላቸውን ወይም የሚስታቸውን ከትዳር ውጪ የተወለደን ልጅ እንደልጃቸው አድርገው አሳድገው ለወግ ለማረግ የሚያበቁ እንዳሉ ሁሉ የልጅ መኖርን ስነልቦናቸው አልቀበል ብሎ ወደፍቺ ማምራትን እንደ አማራጭ የሚወስዱ ብዙ ግለሰቦች አሉ፡፡ የልጅ መኖርን እንደትልቅ የፍቺ ምክኒያት የሚወስዱ ግለሰቦች ስነልቦና ለመረዳት እንደሚቻለው የልጅ መኖር በራሱ ብቻ ሳይሆን “ይሄ ካለ ሌላ ብዙ ጉድ ይኖራል” የሚል አመለካከት ሲሆን ከትዳር በፊት ያለ የልጅ መኖርና ይህንንም ደብቆ ማቆየት በጥንዶች መካከል ያለን መሰረታዊ መተማመንን ያናጋል ይላል ጸሃፊው፡፡ በአብዛኛው የልጅ መኖር የሚደበቅበት ምክኒያት ትዳርን ሊያናጋ ይችላል በሚል ፍራቻ ሲሆን ልጅ መኖር ብቻ ሳይሆን ስለጉዳዩ የትዳር አጋርን መደበቅ ችግሩን እጅግ ውስብስብ ሊያደርገው ይችላል፡፡ የልጅ መኖርን ውስብስብ ከሚያደርጉት አጋጣሚዎች አንዱ ደግሞ ሞትና እርሱን ተከትሎ የሚመጣ የውርስ ጥያቄ ነው። ከዚህ ቀደም ብሎ ለማይታወቅ ልጅ የውርስ መብትን ለማስጠበቅ ለሌላኛው አካል ለመቀበል ከማስቸገሩም በላይ “…ከጋብቻ ውጪ የሚወለዱ ልጆች ሊጋደሉ ይደርሳሉ፡፡” ይላል ጸሃፊው ልምዱን ሲያካፍል፡፡
“ልጅ የለንም፤ 18 አመት አብረን ስንኖር ይሄ ምክኒያት አላፋታንም፤ የወር አበባዬ ከቆመ በኋላ ግን ጠላኝ፤ ሴት አልመስል አልኩት…”
ይህንን ያንዲት ሴት ልምድ ያካፈለው ጸሃፊው ማረጥ ሌላኛው የፍቺ ምክኒያት እንደሆነ ለማስረዳት ነው፡፡ የዚችን ሴት ባል ጸሃፊው አናግሬው ይህንን ነገረኝ ይላል፤
“… ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚገርም ሁኔታ ባህሪዋ ተለወጠ፤ በወጣው በገባው ቁጥር ጭቅጭቅ ነው፤ለምን ጃኬትና ጅንስ ትለብሳለህ ትለኛለች፤ ይህ ሁሉ እራስ መጠበቅ ምን ለመሆን ነው ትለኛለች…”
ከዚህ ታሪክ የምንረዳው ማረጥ ወንዱ ላይ የሚፈጥረው መጥፎ ስሜት ብቻ ሳይሆን ሴቷ ገና ለገና እዚህ ሁኔታ ውስጥ ስላለው እነደድሮው ላላስደስተው እችላለው፤ ሌላ ሴት ጋር ለመሄድ ሊፈልግ ይችላል የሚለው ስሜት ባህሪያቸውን አስቸጋሪ ሊያደርገው እንደሚችል ነው፡፡ ማረጥ ተፈጥሯዊ ዑደት መሆኑን መቀበልና በዚህ ረገድ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በግልጽ ከባለሞያ ጋር በመወያየት ሊፈቱ እንደሚገቡ መጽሃፉ ይጠቁማል፡፡
ጸሃፊው በመጽሃፉ የፍቺ ምክኒያቶችን ብቻ ሳይሆን የፍቺ ውጤቶችንም አካፍሏል፡፡ በመጽሃፉ ሶስተኛው ክፍል በልምድና በንባብ አገኘኋቸው ያላቸውን የፍቺ ውጤቶች በተለያዩ ርዕሰ አንቀጾች ስር አስቀምጧል፡፡
ከፍቺ ውጤቶች አንዱ ልጅን ወይም ልጆችን ለብቻ ማሳደግ ነው፡፡ የውጪ አገር ጥናት ጠቅሶ መጽሃፉ ሲያብራራ ከ10 ህጻናት መካከል 3ቱ ከአንድኛው ወላጅ ጋር ብቻ የሚያድጉ ናቸው፡፡ በኢትዮጲያ ይህንን በግልጽ የሚያሳይ ጥናት ባይገኝም፤ ብዙ ወንዶች ልጆቻቸውን ለብቻቸው የሚያሳድጉ ቢኖሩም ቁጥሩ ግን የሴቶች ያይላል ይላል፡፡
“… 3 ልጆች ወልደናል፡፡ እሱ ሌላ አግብቶ ሁለት ወልዶ መጠጥ አቁሞ በሰላም እየኖረ ነው፡፡ አኔ ልጅ በማሳደግ ብቻዬን እየተንገላታው አለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እግዚያብሔር ምነው ትዕግስቱን ሰጥቶኝ ችየው በነበረ እላለው፡፡ 3 ልጅ ብቻ ማሳደግ በጣም በጣም ከባድ ነው፡፡…” ትላለች ጸሃፊው ታሪኳን አካፈለችኝ ያላትና በባሏ ጠጪነት ምክኒያት ትዳሯን ከፈታች በኋላ ልጆቿን ለብቻዋ ለማሳደግ የተገደደች ሴት፡፡
የፍቺ ውጣ ውረድ በዚህም ብቻ የሚገታ አይደለም። የወሲብ ስሜት ማጣት ሌላኛው የፍቺ ውጤት ሊሆን እንደሚችል ጸሃፊው ያስረዳል፡፡ ጥንዶች ከተፋቱ በኋላ ወንዱም ትሁን ሴቷ ለጥቂት ጊዜ ወይም ለረጅም ጊዜ የወሲብ ስሜት ላይኖራቸው ይችላል፡፡  
“ከባለቤቴ ጋር ከተለያየን ሶስት አመት ገደማ ሆኖናል። በዚህ ጊዜ ከ4 ወንዶች ጋር ለመውጣት ሞክሪያለው፡፡ በጣም የሚገርመው ሴክስ የበለጠ እየጠላው ነው የመጣሁት፡፡ ሌላው የሚገርመው አንደኔ የተፋታች ጓደኛ አለችኝ፤ ከሷም ጋር ስናወራ ተመሳሳይ ስሜት ነው ያላት፡፡” ትላለች አንድ ጸሃፊው አናገርኳት ያላት ባለታሪክ፡፡እንደዚች ባለታሪክ ከሆነ ሰዎች ከተለያዩ ግለሰቦች ጋር አብሮ የመሆን ልምድ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከፍቺ በኋላ የወሲብ ስሜቷ ጭራሹኑ ሊሞት የቻለው እንደባለታሪኳ እሷና ተመሳሳይ ታሪክ ያላት ጓደኛዋ በህይወታቸው የሚያውቋቸው የፍቅር አጋሮች የቀድሞ ባለቤቶቻቸው በመሆናቸው ጭምር ነው፡፡
“የሆነ ጊዜ ላይ ልጆቼ ትዝ ይሉኛል፤ ድንገት ይናፍቁኛል፤ ከዚያም ትምርትቤታቸው ወይም እናታቸው ቤት ሄጄ አያቸዋለው፡፡ ላያቸው ካልቻልኩ ግን ስራ መስራት አልችል፤… ስሜቱ ከባድ ነው…” ይላል አንድ ጸሃፊው የጠቀሰው ባለታሪክ የፍቺን ጉዳት ሲያብራራ፡፡
ፍቺ ጥንዶች ላይ ከሚያስከትለው ጠባሳ አንዱ ልጆችን መናፈቅ ነው፡፡ ምንም እንኳን ልጆቻቸውን በናፈቁ ቁጥር የማግኘትና ናፍቆታቸውን የመወጣት እድሉ ያላቸው ግለሰቦች ያሉ ቢሆንም ሌሎች ብዙዎች ግን ከትዳር አቻቸው ጋር ተለያይተው በመኖራቸው ምክኒያት ያጧቸውን ልጆቻቸውን በተለያየ ምክኒያት ማግኘትም ማየትም የማይችሉ እንዳሉና ይህም ስነልቦና ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽዕኖ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መጽሃፉ ያብራራል፡፡ ፍቺ ከተፈጸመ በኋላ ጥንዶች ህይወታቸውን ለየብቻቸው ይመሯታል ማለት ላይሆን ይችላል። እንዳውም ብዙ ፈት ግለሰቦች ከጥቂት ጊዜ በኋላ ህይወትን የሚጋሯቸው ሌሎች ግለሰቦችን ሲፈልጉና መልሰውም ሲያገቡ ይስተዋላል፡፡ ከፍቺ በኋላ የተፈጸመ ትዳር የመጀመሪያው ትዳር የፍቺ ምክኒያት ተጽዕኖ ነጻ ሊሆን አለመቻሉ ሌላኛው የፍቺ ውስብስብ ነው- እንደጸሃፊው፡፡
በአሜሪካን አገር የተደረገን ጥናት ጠቅሶ ጸሃፊው ሲያብራራ ከፍቺ በኋላ የተፈጸመ ትዳር የመፍረስ እድሉ 62 በመቶ እንደሚደርስ ይናገራል፡፡ የመጀመሪያው ፍቺ የተፈጸመው ባለመተማመን ከሆነ፤ ያለመተማመን ሁለተኛውንም ትዳር አንኳኩቶ የመምጣት እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ የመጀመሪያ ትዳራቸውን በቤተሰብ ጣልቃ ገብነት የፈቱ ግለሰቦች የሁለተኛውን የትዳር አጋራቸውን ጥቃቅን ቤተሰባዊ ግንኘኑነቶች በማጋነን “ይቺኛዋም ጣጣዋ ብዙ ነው” በሚል አስተሳሰብ የመጠመድ እድላቸው ሰፊ ነው፡፡
“የችግሩ አዙሪት እንደዚህ በመሆኑ እዝኛለው…” ይላል አንድ እማኝነቱን ለጸሃፊው የሰጠ ባለታሪክ፡፡
ሌላው ፍቺ ልጆች ላይ የሚኖረው ጠባሳ ነው። ፍቺ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ላሉ ልጆች የሚኖረው ስነልቦናዊ ተጽዕኖ አይካድም፡፡ ጸሃፊው ይህንን ለማብራራት በተለምዶ ልደታ ፍርድቤት እየተባለ በሚጠራው መግቢያ በር አካባቢ ተለጥፎ አየሁት ያለውን ጽሁፍ “የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍድር ቤት የዳኛ ምክር ፍቺ ለሚፈጽሙ ወላጆች” በሚል ርዕስ ስር አከፍሏል፡፡
እንደጸሃፊው እስከ 3 አመት ድረስ የሆኑ ህጻናትን በተመለከተ ጽሁፉ የሚከተለውን ያስቀምጣል፡-
በዚህ እድሜ ያሉ ህጻናት በህይወታቸው በጣም ጠቃሚ በሚሉት ሰው የመከዳት ስሜት ይሰማቸዋል፤
ይህ የመከዳት ስሜት ልጆች ከሰዎች ጋር ባሏቸው ግንኙነቶች ላይ የመተማመን ስሜታቸውን ስለሚያጠፋው፤ ልጆቹ ከሰው ጋር ባላቸው ግንኙነት ላይ በአሉታዊ መልኩ ተጽዕኖ የሚያሳድር ይሆናል፡፡
ይላል ጸሃፊው በቀጥታ ጠቅሶ ያስቀመጠው ጽሁፍ፡፡ ጽሁፉ ትኩረቱን ያደረገው እስከ ሶስት አመት በሆናቸው ልጆች ላይ ብቻ ሳይሆን እድሚያቸው ከ3-5፤ 6-8፤ 9-10፤ 11-13፤ እና እድሚያቸው ለ13 አመት በላይ በሆናቸው ወጣቶች ላይ የወላጆች ፍቺ የሚያስከትለውን የስነልቦና ተጽዕኖ ጭምር ነው፡፡
መልካም ሳምንት፡፡

Read 23568 times