Monday, 05 March 2012 14:02

የጊዮርጊስ እና የቡና የአፍሪካ ታሪክ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡና በአራት የአፍሪካ ውድድሮች የመሳተፍ እድል አግኝቷል በአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ በ1985 የኢትየጵያ ሻምፒዮን መሆኑን ተከትሎ በ1990 ተሳትፏል፡፡ በዚህ እስከ አሁንም ብቸኛ ሆኖ በተመዘገበለት ተሳትፎው እስከ ሁለተኛ ዙር ለመዝለቅ የተሻለ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ በመጀመሪያው የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታው ሴይንት ማይክል ዩናይትድ ጋር ነበር የተገናኘው፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ በተቀናቃኙ ሜዳ 1ለ0 ተሸንፎ መመለሱ የማለፍ እድሉ ስጋት ውስጥ ቢገባም በመልሱ ጨዋተ በፍፁም የበላይነት 8ለ1 በማሸነፍ አለፈ፡፡ በዚህ ጨዋታ በወቅቱ የሀገሪቱ ምርጥ ተጫዋች እንደሆነ ይነገርለት የነበረው አሰግድ ተስፋዬ ብቻውን አምስት ኃይሎችን በማስቆጠር አስገራሚ ብቃት አሳይቷል፡፡ በቀጣዩ የአንደኛ ዙር ማጣሪየ ከግብፁ አልአህሊ ጋር ተገናኘ፡፡ አል-አህሊ በአፍሪካ ስመገናና የሆነና የክፍለ ዘመኑ የአፍሪካ ምርጥ ክለብ ተብሎ የተመረጠ መሆኑ የቡና እጣ ፈንታ ከአል-አሃሊ አያልፍም ተብሎ ነበር፡፡

በመጀመሪያው የአዲስ አበባ ጨዋታ አንድ አቻ በመልሱ በካየሮ ኢንተናሽናል ስታድየም በተካሄደው ጨዋታ ደግሞ ሁለት አቻ ተለያዩ፡፡ ከሜዳው ውጭ ሁለት አቻ የተለያየው ኢትዮጵያ ቡና ከሜዳ ውጭ የተሻለ ጎል በማስቆጠሩ ወደ ሁለተኛው ዙር አለፈ፡፡ በሁለተኛው ዙር ከታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስ ጋርተገናኘ፡፡ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ሁለት አቻ የተለያየው ቡና በመልሱ ጨዋታ ከሜዳው ውል 6ለ1 በመሸነፍ 8ለ3 በሆነ ድምር ውጤት ከውድድሩ ተሰናብቷል፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ ቡና በዚህ ዓመት ያስመዘገበው ውጤት የኢትዮጵያ ክለቦች ለመጨረሻ ጊዜ ያስመዘገቡት የተሻለ ውጤት ለመሆን በቅቷል ባለፋት 12 ዓመታት የተሳተፋት ቅ/ጊዮርጊስ፣ መብራት ሀይልና ሀዋሳ ከነማ ከአንደኛው ዙር በላይ ማለፍ አለቻሉም፡፡’

 

 

ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅ/ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ በውጤታማነቱ የሚጠቀስ በመሆኑ ለበርካታ ጊዜ በኢንተርናሽናል ውድድር መሳተፍ የሚያስችለው ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በዚህም ከሌሎች የኢትዮጵያ ክለቦች በተሻለ ሁኔታ በአፍሪካ ውድድሮች ላይ ተሳትፏል፡፡ ቅ/ጊዮርጊስ በአህጉር አቀፍ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈለው እ.ኤ.አ በ 1967 1959 ነበር፡፡

በወቅቱ የአፍሪካ ሻምፒዮን ክለቦች ዋንጫ ተብሎ ይጠራ በነበረውና በአሁኑ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ሲሆን በታሪኩ የተሻለ ውጤት ያስመዘገበበት ውድድር ነበር፡፡ በመጀመሪያው ዙር የኡጋንዳው ቢቲማስቲክ ማሱን ራሱን ከውድድሩ በማግለሉ ጊዮርጊስ በቀጥታ አለፈ፡፡ በሁለተኛው ዙር የግብፅን ኦሎምፒክ አሌክሳንዴርያን 5ለ2 በሆነ ድምር ውጤት በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜው አለፉ ለፍፃሜ ለማለፍ ከዴሞክራቲክ ኮንጎው ቲፒ ኢንግልበርት የአሁኑ ቲ.ፒ ማዜምቤ ጋር ተገናኝቶ 4ለ3 በሆነ ድምር ውጤት ተሸንፎአል፡፡ አዲስ አበባ ላይ 2ለ1 ቢያሸንፍም ኪንሻሳ ላይ 3ለ1 በመሸነፉ ነው ለፍፃሜ የማለፍ እድሉ ያልተሳካው፡፡ አሸናፊው ኢንግልበርት በፍፃሜ ጨዋታውም በማሸነፍ የአመቱ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ በቀጣይ አመታት 1968 እና 1969 በመጀመሪያው ዙር ተሰናበተ በ 1972 በሁለተኛው ዙር ማለፍ አልቻለም፡፡ በ 1976 በመጀመሪያ በ 1986 በሁለተኛው ዙር ከውድድሩ ወጣ፡፡ በ 1991 1983 በኢትዮጵያ በነበረው የመንግስት ለውጥና አለመረጋጋት ምክንያት ራሱን ከውድድረ አገለለ፡፡ በ 1992 እና በ 1993 ቅድመ ማጣሪያ በነበረባቸው ውድድሮች አልተሳካለትምና ወደ አንደኛ ዙር እንኳን አልደረሰም፡፡ ከዚህ አመት በኃላ የወድድሩ ፎርማትና ስያሜ ተለወጠ፡፡

ከ1997 ጀምሮ ይህ ውድድር የአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ በሚል ስያሜ ተተካ፡፡ በመጀመሪያው ውድድር በመጀመሪያው ዙር ከውድድሩ ተሰናበተ፡፡ ከግብፁ ታዋቂ ክለብ ዛማሊክ ጋር የተገናኘ ሲሆን ግብፅ ላይ 2ለ0 ተሸንፎ በመልሱ ጨዋታ አንድ አቻ ተለያይቶ 3ለ1 በሆነ ድምር ውጤት ተበልጦ ነበር ማለፍ ወደ ሁለተኛው ዙር ማለፍ ያልተቻለው፡፡

ቀጣይ ተሳትፎውን ያገኘው በ 2000 ነበር በቅድመ ማጣሪያው የኡጋንዳውን ቪላ ካምፓላን 5ለ2 በሆነ ድምር ውጤት ረትቶ አለፈ፡፡ከሜዳው ውጪ ካምፓላ ላይ ሁለት አቻ ተለያይቶ በመልሱ ጨዋታ ደግሞ 3ለ0 አሸንፎ ነበር ውጤታማ የሆነው፡፡ በመጀመሪያው ዙር በቪታሎ ቡሩንዲ በመሸነፉ ጉዞው አልረዘመም፡፡ ከሜዳው ውጭ 2ለ2 አቻ ቢለያይም በሜዳው 2ለ1 መሸነፉ ነበር ከውድድሩ ላለመዝለቁ ምክንያት የሆነው፡፡ በቀጣዩ አመት 2001 ከኬንያ ተስካር ጋር የተገናኘ ሲሆን አዲስ አበባ ላይ 1ለ1 ኬንያ ላይ ደግሞ ያለግብ አቻ ተለያዩ፡፡ ከሜዳ ውጭ ባገባ በሚለው ህግ መሰረት ተስካር አላፊ ጊዮርጊስ ወዳቂ ሆኑ፡፡

በ2003 ለአራተኛ ጊዜ የመሳተፍ እድል ባገኘበት ወቅትም ቅድመ ማጣሪያውን ማለፍ አልቻለም፡፡ ኡጋንዳ ላይ 1ለ0 ቢያሸንፍም አላለፈም፡፡ ምክንያቱም አስቀድሞ አዲስ አበባ ላይ 3ለ1 ተሸንፎ ነበርና፡፡ በቀጣይም ውድድር 2004 ላይ ደግሞ በሱዳኑ አልሂላል አምደርማን ተሸንፎ በመጀመሪያ ዙር ከውድድሩ ተሰናበተ በመጀመሪያው ጨዋታ በሜዳውና ደጋፊው ፊት አዲስ አበባ ላይ 2ለ1 ተሸንፎ ስለነበር ካርቱም ላይ አንድ አቻ መለያየቱ ሊያሳልፈው አልቻለም በእነዚህ ሁለት አመታት ከሜዳው ውጭ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ቢችልም በሜዳው አለመጠቀሙ ጎድቶታል፡፡

በ2006 አወዛጋቢ የውድድር ዘመን ያሳለፈበት ነው በመጀመሪያው ዙር ከግብፅ ኢንፒ ENPPI ጋር ነበር የተገናኘው፡፡ ይህ ክለብ በወቅቱ በአረብ ሻምፒዮንስ ሊግ ለፍፃሜ የበቃ ስለነበር ጨዋታው ጠንካራ ይሆናል የሚል ግምት አድሮ ነበር፡፡ ይሁንና ከሜዳው ውጭ 0ለ0 በመለያየት በሜዳው ደግሞ 1ለ0 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈ፡፡ በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ የጋናውን ኸርትስ ኦፍ ኦክል 4ለ0 አሸነፈ፡፡ ይህ በኢንተርናሽናል ውድድር ታሪኩ ታላቅ ድል ስለነበር በቀጣይ ተስፋ ተጣለበት፡፡ በመልሱ ጨዋታ ግን ያልተጠበቁ ክስተቶችን አስተናገደ፡፡ ከሆቴል ጀምሮ የደረሰበት እንግልት እስከ ሜዳ ዘለቀ፡፡ የእለቱ ዳኛ አወዛጋቢ ውሳኔዎችንአሳለፉ፡፡ ባለሜዳዎቹ 2ለ0 መሩ የፍፁም ቅጣት ምትም አገኙ በዚህ ወቅት በደሉን መቋቋም ያልቻሉት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች የኦህንጃን ስታድየምን ሜዳን ጨዋታው ሳይጠናቀቅ አቋርጠው ወጡ የውድድሩ አስተዳዳሪ ፊፋ ውሳኔም ወደ ጋናው ክለብ ተጋዘ፡፡ ቅ/ጊዮርጊስ ወድቆ ኸርትስ ኦፍ ኦክ እንዲያልፍ ተደረገ፡፡

በተከታዩ አመት 2007 የመጀመሪያውን ቁጭት ይዘው አዲስ አበባ ላይ የኮንጎ ብራዛቪሉን ኤቶል ዲ ኮንጎን ያስተናገዱት ጊዮርጊሶች 1ለ0 አሸነፉ፡፡ በመልሱ ጨዋታ 2ለ0 መሸነፋቸው ግን ህልማቸውን አጨናገፈባቸው፡፡ የመጨረሻዎቹ ቡድኖች ላይ ገብተው ኤቶልን ከመግጠማቸው በፊት ከሱፐር ኤስከም ጋር ተደልድለው ነበር፡፡ ይሁንና የማላዊው ክለብ ራሱን በማግለሉ በቀጥታ አለፉ፡፡

በቀጣዮቹ ሁለት አመታትም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ በተፈጠረው ውዝግብ ምክንያት ፊፋ ሀገሪቱን ከማንኛውም ኢንተርናሽናል ውድድር ማገዱ ክለቦቻችንንም ይመለከታልና ቅ/ጊዮርጊስም መሳተፍ በነበረበት 2009 ሣይሳተፍ ቀረ፡፡ የተፈጠረው ችግር ተቀርፎ እገዳው መነሳቱ በ 2010 ወደ ውድድር እንዲመለስ አስቻለው የተደለደለውም ከሱዳኑ ኤልሜሪክ ጋር ነበር፡፡ የመጀመሪያው ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ሲካሄድ ሜሪኮች መምራት ችለው ነበር መሐመድ ናስር በጭንቅላት በመግጨት ያስቆጠራት ግብ ግን ባለሜዳውን ነጥብ አጋራች፡፡ የመልሱ ጨዋታ በኤልሜሪክ ስታዲየም ሲደረግ አዳነ ግርማ ቅ/ጊዮርጊስን መሪ አድርጓል፡፡ ማሪኮች ሥስት ግቦችን በማስቆጠራቸው ጊዮርጊስን ጥለው ማለፍ ቻሉ፡፡

ምንጭ ኢትዮፉትቦል ድረገፅ

 

 

Read 2221 times Last modified on Monday, 05 March 2012 14:06