Monday, 08 August 2016 06:16

ለ35 ቀናት የዘለቀው ዓለም አቀፍ የሥነጥበብ መርሃ ግብር

Written by  -ሚፍታ ዘለቀ-
Rate this item
(0 votes)

--- ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ በመቶ ዓመት የህይወት ዘመኑ አንዴ እንኳ ፎረም (Forum) የሚባል ነገር አድርጎ ያውቃል? በየትኛው እድሜው ላይ ነው የተለያየ ድምፅ ያላቸው ሠዓሊያን በአንድነት የመከሩት?----;
   ጊዜ እና (Asiko 2016)
‘ሥነ-ጥበባችን አላደገም!’፤‘መንግስት ለሥነ-ጥበብ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል!’ የሚሉ እንዳሉ ሆኖ፣ ‘መንግስት ተገቢውን ትኩረት ለሥነ-ጥበብ ነፍጓል!’፤ ‘ባለሀብቱ ሥነ-ጥበብን አይደግፍም፣አይገባውም፤ እንዲያው ለታይታ (ልታይ ልታይ ለማለት) ካልሆነ በቀር ሥዕል ከቻይና አስመጥቶ፣ ግድግዳው ላይ ይሰቅላል እንጂ የሀገሩን ሥነ-ጥበብ ዞር ብሎ አያይም!፤ኅብረተሰቡ ሥነ ጥበብን አያዘወትርም፤የህይወት ዘዬው እንዲሆን አይጥርም!፤ወደ ጋለሪዎችና ወደ ሙዚየሞች በመሄድ ትርፍ ጊዜውን አያሳልፍም፣ በሥነ ጥበብ አይዝናናም...!’፡፡
 ‘ሠዓልያን  በአስማት ነው የሚኖሩት፤የልፋታቸውን ዋጋ አያገኙም!’፣ ‘የግብር አሰባሰቡ የሠዓልያንን የኑሮና የሥነ-ጥበብን ኢኮኖሚያዊ አካሄድ ያልተከተለ ነው!፤ ‘ዞር ቢሉ እዬዬ… እህ ቢሉ ዋይታ ሆኖዋል - የእኛ ነገር!’ ከሚሉ አስተያየቶችና አመለካከቶች ጀምሮ በሥነ-ጥበብ ማኅበረሰቡ ውስጥም መከፋፈልን የፈጠሩ፤ ጎጦችን ያበጁና ምሽጋቸውን ቆፍረው ብቅ እያሉ የሚታኮሱ፤ ጦርነቱ ጋብ ሲል ከምሽጋቸው ጀርባ ያነጣጠፏት አጎዛ ላይ እየተንከላወሱ ‘የታባቱ ሰራሁለት!፤ አስታጠቀችው!’፤ ‘አስገባላት- አስገባችለት - ልኩን ነገረው!’ ከማለት የማይዘሉ፣ ሂሳዊ አተያይ የጎደላቸው አስተያየቶችን ከመሰናዘር እስከ ‘ሠዓሊ የታለ? ሀገራችን ውስጥ ፋይዳ ያለው የሥነ-ጥበብ አቅጣጫ የት አለና?፤ የማኅበረሰቡ፣የከተማይቱንና የሀገሪቱን ዘመንኛ አኗኗር የሚያትት፣ የሚያሄስና የሚተች ሥነ-ጥበብም ሆነ ሠዓሊ፤ድምፅ አልባ በሆነበት ዘመን ስለ የትኛው ሥነ-ጥበብ ነው የምንነጋገረው? አብስትራክት ብሎ ቀለም መለቅለቅ፤ ምስላዊና ምስል አልባ እያሉ ማደናገር ነው እንዴ ሥነ-ጥበብ?’ … ወዘተ እንዲሁም ውዝፍ ጥያቄዎችን መመለስ ይቅርና በጥያቄዎች ላይ የመነጋገር ፈቃደኝነት በሌለን በዚህ ዘመን … በዚህ ወሳኝ ጊዜ ነው አንድ አበይት አህጉራዊ ይዘት ያለው ዓለም አቀፍ መርሃ-ግብር፣ በመዲናችን ለ35 ቀናት ተደርጎ የተጠናቀቀው፡፡
Asiko: አሲኮ… የዚህ በየዓመቱ የሚደረግ መርሃ ግብር ጠንሳሽና ዘንድሮም ለስድስተኛ ጊዜ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ያደርገው CCA Lagos የተሰኘው መቀመጫውን በናይጄሪያ ሌጎስ ያደረገ የሥነ-ጥበብ ተቋም ነው፡፡ የተቋሙ መስራችና የመርሃ-ግብሩ የደም ስር ደግሞ ተናግረው ሊደመጡ ከሚችሉ ምርጥ አምስት ወይም ሶስት አፍሪካዊ የሥነ-ጥበብ አጋፋሪዎችን (curator) ብንጠራ ስሟና ተግባሯ ሊተነተን ከሚችሉት ጥቂቶች መሃል የሆነችው Bisi Silva ነች፡፡ ታላቅ አፍሪካዊ ራዕይ አንግቦ፣ባለ ራዕዮችን ሲያበራይ፣ ሲያበረታታና ሲያንጽ የቆየው ይህ መርሃ-ግብር፤ተራው ለመዲናችን ሆኖ ሰነባብቶ ነበር፡፡
በዘንድሮም የAsiko መርሃ-ግብር፣ከአስር አፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ አስራ ሁለት ወጣት ሠዓሊያንና አራት የሥነ-ጥበብ አጋፋሪዎች (Curators) የተሳተፉ ሲሆን ከኢትዮጵያ የዚህ ፅሑፍ አቅራቢን ጨምሮ ሶስት ሠዓልያን ማለትም፡- ሩት አድማሱ፣ ክብሮም ገ/መድህንና ኢዮብ ኪታባን ተሳትፈዋል፡፡ ለመሆኑ ASIKO ምን ምን ይል ነበር? የኔን የጣዕም ልኬት እንካችሁ፡፡
Asiko -ጊዜ፡- በናይጀሪያው ዮሩባ ቋንቋ  ASIKO ማለት ጊዜ ማለት ብቻ ሳይሆን  ‘ጊዜው አሁን ነው!’ እንደ ማለት ነው፡፡ በርግጥም ማንኛውንም ሥነ-ጥበባዊ ጥያቄ ለማንሳትም ሆነ ለመነጋገር … ለመነጋገር ብቻም ሳይሆን ለመመለስ የሚያስችለን ጊዜ አሁን ነው፡፡ የአፍሪካን በተለይም የኢትዮጵያ ከላይ የተብለቀለቁት ሀሳቦችና ጥያቄዎችን መጠየቂያ ጊዜው አሁን ነው፡፡ በአስቸኳይ መልስ መስጠት ባንችል እንኳ የንግግር መጀመሪያው ጊዜ አሁን ነው፡፡
የASIKO ዋነኛ ትኩረት ጊዜ ነው፡፡ አፍሪካዊ ማንነት፣ መሰረትና ግብ ያለው የሥነ-ጥበብ ህላዌ መከሰት ያለብን አሁን ነው፡፡ ማድረግ የምንችለውም አሁን ነው፡፡ ጊዜው በእርግጥም አሁን ነው፡፡ በመርሃ ግብሩ፣ተሳታፊያን ጥያቄዎችን እንዲያነሱ ይጋበዛሉ፡፡ ፅንሠ-ሃሳባዊ፣ ቲዎረቲካልና ተጨባጭ ልምድን መሰረት ያደረጉ ውይይቶች፣ንባቦችና ትችቶች ከመላው ዓለም በመጡ ባለሙያዎችና መምህራን ይቀርባሉ፡፡ ተሳታፊያን ከራሳቸው ዓውድ ጋር በማሰናኘት የራሳቸውንም ሆነ የሃገራችውን የሥነ-ጥበብ አቅጣጫ እንዲፈትሹ እድል ያገኛሉ፡፡ከምንም በላይ ደግሞ ይህን የማድረጊያው ጊዜ አሁን እንደሆነ አቅራብያኑ የሚደረድሩት አመክንዮ፣በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ ይመለከተናል፡፡ ዓለም የደረሰበት ሥነ-ጥበባዊ ርቀትና ርቅቀትን በሚዳስሱ ትምህርታዊ ገለፃዎች፣ ውይይቶችና ሂሶች አማካኝነት ተሳታፊያን ያሉበትን ቦታ እንዲያጤኑ፣ አጢነውም አንገብጋቢው ጊዜ አሁን መሆኑን እንዲገነዘቡ ያስችላል - መርሃ-ግብሩ፡፡
ጊዜ- አሁን ኢትዮጵያ፡- የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ‘ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም!’ እንደሚባለው አይነት ሆኖ፣ ነገር ግን ደፋርም ጭስም መሆን አቅቶት የተገተረ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያን የተመለከተ ይቅርና የግለሰብን ሥነ-ጥበባዊ አቅጣጫ አንስተን ለመነጋገር፣ለመከራከር፣ ለመተቻቸት አቅም የሌለን የፈሪዎች ስብስብ በመሆናችን፣ ሁላችንም ጥጋችንን ይዘን ብቻ ነው ምሽጋችንን የምንቆፍረው፡፡
 በዚህ ፅሑፍ መግቢያ ላይ መንግስትን፣ ባለሃብቱንና ኅብረተሰቡን ተጠያቂ የሚያደርጉ ሃሳቦችና ጥያቄዎችን ደርድሬያለሁ፡፡ እነዚህን ተጠያቂ አካላት ተጠያቂ ከማድረጋችን በፊት የኛ የሥነ-ጥበብ ማኅበረሰቡ አካላት ተጠያቂነትስ እስከ የት ድረስ ነው?… እሺ መንግስትም ሆነ ባለሃብቱና ኅብረተሰቡ ለሥነ-ጥበብ ደንታ የሌላቸው ከሆነ፤ በምን አይነት መልኩ ነው ደንታ እንዲኖረው ማድረግ የሚቻለው?.. ምን አይነት ጥረትስ ከኛ ከሥነ-ጥበብ ማኅበረሰብ ይጠበቃል...? በምን መልኩ ነው ኃላፊነታችንን መወጣት የምንችለው?… ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ በመቶ ዓመት የህይወት ዘመኑ አንዴ እንኳ ፎረም (Forum) የሚባል ነገር አድርጎ ያውቃል? በየትኛው እድሜው ላይ ነው የተለያየ ድምፅ ያላቸው ሠዓሊያን በአንድነት የመከሩት? ልዩነት ያላቸው አመለካከቶችና ፍልስፍናዎች በየትኛው መድረክ ላይ ተገናኝተው ነው የተከራከሩትና የተደማመጡት?… ያው ያቺ የፈረደባት ምሽግ አለች፤ከሷ ወጣ እያሉ ተኮስ አድርገው እዚያው ያነጠፏት አጎዛ ላይ ከመንከባበል ውጪ መቼ ነው ቀና ብለን በግልፅነት የተነጋገርነውና የምንነጋገረው? መነጋገር ያለብን አሁን ነው፡፡ አሁን ካልሆነ ደግሞ የሻገተው እየበሰበሰ፣ ያልሻገተውና ንፁሁም በሻገተው እየተመረዘ ነው የሚቀጥለው፡፡ ካልደፈረሰም አይጠራም፡፡ ካልጠራም አይጠራም፡፡ አይጠራምም፡፡ መንግስትን፣ባለሃብቱን፣ ሰፊው ማኅበረሰብም ሆነ ዓለም አቀፍ የሥነ-ጥበብ መድረኮችን መጥራት፣መሳብም ሆነ መቀላቀል አይቻልም፡፡
ASIKO-የሥነ ጥበብ ታሪክ ፡- ሥነ-ጥበብ በደፈናው ሊገናዘብ የሚችል ዓለም አይደለም፡፡ የአንድ ግለሰብ ሠዓሊ ዓውድ ካልተጠና፣ የተነሳበትንም ሆነ የሚሄድበትን ለማወቅ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ይህንን ሁኔታ በሃገር ደረጃ ስንወስደው ደግሞ መሰረቱ ያልተጠና ሥነ-ጥበብ መድረሻውን ይቅርና መለያውን  ለማግኘት አዳጋች ነው፡፡ በአንድ መቶ ዓመት ዘመናዊ የኢትዮጵያ የሥነ-ጥበብ ታሪክ ውስጥ አንድ አንኳን በሀገራችን አጥኚዎች የተፃፈ የሥነ-ጥበብ ታሪክ መፅሃፍ የሌለን ኩሩዎች ነን፡፡ እርግጥ ነው የሥነ-ጥበብ ት/ቤታችን (አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት አ.አ.ዩ) ሠዓሊያንን እንጂ የሥነ-ጥበብ ምሁራንን ወይም አጥኚዎችን አላፈራም፡፡ የሥነ-ጥበብ ታሪካችንን አስተካክለን የፃፍን ቢሆን ኖሮ ማህበረሰቡም፣ መንግስትም፣ ባለሃብቱም ሆነ ማንኛውም ባለድርሻ አካል የሚንጠላጠልበት ጅራት ይኖረው ነበር፡፡ መንጠላጠያም ብቻ ሳይሆን የመገንዘቢያ፣ የመረጃ መሰረት ይኖረው ነበር፡፡ የሥነ-ጥበብ ታሪካችን አለመፃፍ ተፅዕኖ የሚያመጣው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፍ ተሳትፎአችን ጭምር ነው፡፡ የተጠና፣ የታሰሰ፣ የተተቸ፣ የተመረመረ የሥነ-ጥበብ ታሪክ የሌለው ሀገር፤ሥነ-ጥበባዊ ድምጹ አይሰማም፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያ የምትነሳው በግለሰብ ሠዓልያን ሀገርነት እንጂ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብን በማንሳት አይደለም፡፡
የሥነ-ጥበብ ታሪካቸውን ፈትሸው ያጠኑ ሃገራት፣ አሁን ያሉበትን ቦታ ይዘው እንዲቀመጡ አስችሏቸዋል፡፡ የሥነ-ጥበብ ታሪካችንን ችላ ያልነውም የት እንዳለንና የትም እንደሌለን እናውቃለን፡፡ ጊዜው አሁን ነውና ኮስተር ቆፍጠን ብለን ታሪካችን ላይ መረባረብ ያለብን ጊዜ ይኸው ነው፡፡ አዲስ ታሪከ መስራትም የምንሻ ከሆነ ያሳለፍነውን በሚገባ ሰንደን አጥንተን ሊሆን ይገባል፡፡ እንዳው በግርድፍ ‘ወደፊት!’ ብቻ የምንል ከሆነ ብዙ እምንረግጠው እምንጨፈልቀው- እምናበላሸው ይበዛል፡፡ ስለ ዛሬው- ስለ አሁኑ የምንነጋገር- የምናጠናና የምንጽፍ ከሆነም ትኩረታችን የተገራ፣አተያያችን የሰላ መሆን ይኖርበታል፡፡
የAsiko ሌላኛው ጣዕም፤ታሪክና የሥነ-ጥበብ ታሪክ ነበር፡፡ በተለይም የናይጄሪያዊው CHIKA OKEKE-AGULU: Postcolonial Modernism: Art and Decolonization in Twentieth-Century Nigeria የተሰኘው መፅሐፍ የመርሃ-ግብሩ ዋንኛ ንባብ ሆኖ፣ በየሳምንቱ ጊዜ ተመድቦለት፣በጥልቀት ውይይት የተካሄደበት ሲሆን መፅሐፉ በ1960ዎች የናይጄሪያ ዘመናዊ ሥነ-ጥበብን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ዘመናዊ ሥነ-ጥበብን የሚዳስስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ፤ ከአፍሪካ ሥነ-ጥበብ ተገንጥሎ መታየት ብቻም ሳይሆን የኢትዮጵያ የሚባል ሥነ-ጥበብ መኖሩም ራሱ ከነጭራሹ የተዘነጋ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ አይነቱ ውዝግብ መፈጠር የተለያዩ ምክንያቶች ሲኖሩ በቅኝ ግዛት አለመገዛታችን አንደኛው ነው፡፡ ምዕራባውያን የአፍሪካን ሥነ-ጥበብን ሲያጠኑ፣ለራሳቸው ፍላጎትና ፕሮፖጋንዳ የሚመቻቸውን አንጻር ብቻ ወስደው እንደሚያጠኑ ግልጽ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ራሳችን በሥነ-ጥበቡ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዘርፎች ማለትም በታሪክ፡ በዘር፡ በፖለቲካና በማሕበራዊ መስተጋብሮች ከአፍሪካ ልዩ እንደሆንን የምንቆጥረውና በዚህ ልዩነታችንም ሥነ-ጥበባችንን ከአፍሪካ መለየታችን ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡ ሁሌም ቢሆን ልብ የማንለውና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በተለይ በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ከጥንት ጀምሮ ያዳበረችው የቤተክርስቲያን ሥዕል አሳሳል ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ-ጥበብ መነሻ ብቸኛው ወኪል አድርገን መውሰዳችን እንዲሁም የደቡብ፣ የምዕራብና የምስራቅ የሃገሪቱ ሥነ-ጥበባዊ ተዋጽኦዎች ከአፍሪካ የሥነ-ጥበብ መለያዎች ጋር ያላቸውን ተዛምዶ በማጥናትና በማሰናኘት፣ ለሥነ-ጥበብ ታሪካችንና ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ-ጥበብ ያበረከቱትን ጉልህ ሚና በታሪክ ድርሳናችን አለማካተታችን ለመዘንጋታችን ዋንኛ መንስኤ ይመስለኛል፡፡ ሆኖም፤ የCHIKA OKEKE-AGULUው አይነት ይዘት ያላቸው መፅሐፍት፤በኢትዮጵያ አውድ በራሳችን የሥነ-ጥበብ ታሪክ ምሁራንና አጥኚዎች ተፅፎ ቢሆን ኖሮ ሥነ-ጥበባችን ዛሬ የቆመበት ዳገት ላይ አይለግምም ባይ ነኝ!!!
ASIKO -ደግነት፡- ደግነት በተለያ መልኩ ይገለፃል፡፡ ደግ መሆን የሚባዛ እንጂ የማያቋርጥ ፍስሰት መሆኑን ለመረዳት ASIKOን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከመላው ዓለም የተውጣጡ የአስራ ሶስት ሀገራት ሃያ ሰባት ሥነ-ጥበባዊ ሰብዕናቸው የዳበረ፣ ልምዳቸው የካበተ፣ እውቀታቸው የጠለቀ መምህራንና አቅራቢዎች የASIKOን ፍሬ ለማብዛት፤ የወጣት አፍሪካውያንን ልምድና እውቀትን ለማጎልበት በፍቃደኝነት ብቻ ሳይሆን አብዛኛዎቹ የራሳቸውን ወጪ ሸፍነው እዚህ መዲናችን በመገኘት የተቻላቸውን ሁሉ ደግነት ሲለግሱ ነበር፡፡ እውቀት፣ ጥበብና ትጋት በደግነት ሲታጀቡ ግባቸውን ይመታሉ፡፡ የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች እርስ በእርስና ከታጋባዦች ጋር የሚያደርጉት የልምድ ልውውጥና መስተጋብር ሁሉ፣ እውቀትና ጥበብ እንዲሁም ትጋት ብቻ ሳይሆን ደግነት ሲታከልበት ብዜቱ እንደሚጨምርና የትየለሌ እንደሚደርስ አመላካችና አስተማሪ ነበር!... ደግነት… በጣም abstract ነገር ቢሆንም እንዲህ ባሉ መድረኮች ግን ተጨባጭነቱን ማየት ይቻላል፡፡ የምንሰራው ሁሉ ትንሽ ደግነት ካለው ረዥም ርቀት መጓዝ ይቻለናል- ለዚህ ደግሞ ASIKO ምሳሌ ነው፡፡
ASIKO-ድንበር መግፋት፡- ‘ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ!’ ይባላል፡፡ እኛ ሃገር ለሥነ-ጥበብ ማነቆዎች ዋነኞቹ መገለጫ፡ ቁልፍና ሚስጥራዊ ቃላቶች በዚህ አባባል ውስጥ የተሸሸጉ ይመስላል - ባለቤት - ንቀት -አጥር- ንቅነቃ፡፡ ‘የምሰራው እኔ! የሥዕሉ ባለቤት እኔ- ምን ቢንቀኝ ነው የራሱን አጥር ዘሎ የኔን እሚነቀንቀው?’ የሚል ድክመትን በማስወገድ፣የሚሰራውን ሥራ ለትችት ማጋለጥ የAsiko ባህል ነው፡፡ ትችት ሥራን ለማሻሻል የሚጠቅም መሳሪያ መሆኑንና ትችት ሲሰጥ ክፍተቶችን ለመድፈን ማዋል፣ ከቆምንበት ብቻ ሳይሆን ሙጥኝ ብለን ከቆምንበት ትንሽ ፈቀቅ በማለት አማራጮችን እንድናስስ፣ ያደርገናል፡፡ ማስተካከያዎችን እንድንከስት፣በዚያውም የተሻለ የብቃት ደረጃ ላይ እንድንገኝ የሚያስችል ድንበር መግፋት - ሌላኛው የAsiko መለያ ነው፡፡ ‘የምገፋው ድንበር የለኝም- ለስራዬ በቂ ጥናትና ምርምር አድርጌአለሁ- በቆምኩበት የተብቃቃሁ ነኝ!’ የምንል ከሆነም፣ምክንያታችንን አስቀምጠን ማሳመን ይጠበቅብናል፡፡ ታዲያ የትኛውን ድንበር ገፍተን፣ የትኛውን ጥግ አስሰን ነው ጥያቄዎችን ብቻ ደርድረን፤መንግስት፣ባለሃብትና ማህበረሰብን የምንወቅሰው? እልፍ የቤት ስራ! ቸር እንሰንብት!     

Read 856 times