Monday, 08 August 2016 06:17

ውቢቱ ከተማ - ድሬ ደርሶ መልስ

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

 የጉዞ ወግ
       በጉዟችን ዋዜማ ስለ ድሬ ዳዋ ለብዙ አመታት የተዜሙና የተባሉ አብዛኞቻችን የምናውቃቸውን ውዳሴዎች ሳወጣና ሳወርድ ነበር፡፡ ‹‹የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም›› አባባል ለድሬ አይሰራም አልኩ። ቀላል ጓጉቻለሁ እንዴ! አብሮም ደግሞ የመጓዝን ፋይዳና ትሩፋትም ሳስብ ቆይቻለሁ፡፡ ስለ አንድ ጉዳይ ያለንን የተለያየ ግንዛቤም እንዲሁ፡፡ ለምሳሌ ‹‹እርግብ›› BIRD የሚል በትልልቅ ፊደላት የተፃፈ ቃል ለአብሳዩ (ሼፍ)፤ በቢላዋ ተበልታ ለጥብስ የተዘጋጀች። ለቀራጺው በድንጋይ የተቀረጸች። ለሰአሊው ደግሞ በሰማይ ላይ የምትበርር ነጭ እርግብ-ምስልን በአእምሮ ሊከስት እንደሚችል ባንድ ወቅት በኮሙዩኒኬሽን መጽሐፍ ውስጥ ያነበብኩት የምሁራን ትንታኔ ሽው አለኝ፡፡ ‹‹አቦ ተዉና!›› ብዬ ብርድ ልብሴ ውስጥ ገባሁ፡፡
ማለዳ ጉዟችንን በምስጋና ጀመርን፡፡ ‹‹ምን ያህል ጊዜ ይወስድብናል›› አልኩት የረዥም ጊዜ የማሽከርከር ልምድና ብቃት ያለውን የአውቶሞቢላችንን ዘዋሪ ወጣት፡፡ ‹‹ዱሮ ፒስታ መንገድ ሳለ በሁለት ቀን። ከዚያ አስፓልት ሲሰራ በአንድ ቀን ይገባ ነበር፤ አሁን ግን ግማሽ ቀን›› አለኝ አብርሃም፡፡ ‹‹እንዴት ባክህ!›› ማርሹን እየቀያየረ ‹‹ላሳይህ አይደል...›› አለ፡ አሳየኝም፡፡ አዲስ በተሰራው የኤክስፕረስ መንገድ አቋርጠን ናዝሬት ደረስን፡፡ አዋሽ ፓርክ ስንደርስ ፎቶ ሲነሱ የሚቆጡት ዝንጀሮዎች ፈገግ አሰኝተውኛል፡፡ ስንቃረብ አመታዊ ክብረ በአሉን አስመልክቶ የተዘጋጁ ‹‹ዝግታ›› SLOW የሚሉ ጽሑፎች በየአስፓልቱ ላይ ተጽፈው ይታያሉ፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ጥሩ ነው፤ በየመንገዱ ዳር የሚታዩት የትራፊክ አደጋ ትእይንቶች እጅግ ዘግናኝ ናቸው፡፡ የፖሊሶች ጥንቃቄና ትህትና የተመላበት ፍተሻና ተጨማሪ የተማሪዎች ትራፊክ መሰማራታቸውም መልካም ነው፡፡ ምሳችንን ደንገጎ ስር በልተን ብዙም ሳንቆይ ከናፈቅናት ድሬዳዋ ከተማ መሰስ ብለን ገባን፡፡በመጀመሪያ የደረስንበትን የከተማዋን መንደር ዙሪያ ገባ ስቃኝ፣ ከአንድ የመካከለኛው ምስራቅ ከተማ ጋር ተመሳሰለብኝ ልበል... አዎን  ከነዐን፡፡ በከነዐን ምድር ፍልስጤም ከተማ ያየሁት አይነት ባመዛኙ የእስልምና ኃይማኖት እምነት ተከታዮች ህዝቦችን አለባበስ፡ ፍየሎቹ፡ ግመሎቹና የድንጋይ ቤቶቹ አሰራር፡ በተለይ ደግሞ በገንደ ጋራ ዳገት ላይ የተገጠገጡት መኖሪያዎች፡፡ በፍልስጤም ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደባት ቤተልሄም ትገኛለች፤ በድሬዳዋ የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ ያበሰረው የሊቀ መልአኩ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን፡፡ያረፍንበት ዘመናዊ ሆቴል ‹‹ሲየስታ›› ባለቤቶች የሱማሊ ብሄር ሰዎች ናቸው፡፡ ዋና ማለት ነው ትርጉሙ ብለውኛል፡፡ በላቀ ደግነት ያስተናገዱን የሆቴሉ ሰራተኞች ኃላፊ ወጣት ስም ደግሞ ሂቦ ነው፤ ትርጉሙ ፀጋ፡፡ ረድኤትን ጥየቃ እንደ መምጣታችን በጸጋ መስተናገዳችን መልካም ነው መቸም፡፡
 በሆቴሉ ካገኘናቸው ሱማሌዎች ጋር ባጭር መግባባት፣ በ16ኛው ክ.ዘ ከደቡብ ምስራቅ አዳል በብርቱ ተነስቶ እስከ ላስታ ተጉዞ ስለነበረው  መሀመድ ኢብን ኢብራሂም አልጋአዚ ለማውራት ጊዜ አልፈጀብንም፤ የ‹ግራኝ›ን ቅጽል እየጨመርንም እየነቀስንም፡፡ ይህንን አይነቱን ከነልዩነቶቻችን አንድነታችንን የምናጠብቅበትን የመቀራረብ መንፈስ መሰለኝ - UNITY IN DIVERSITY የሚለን ዘመኑ። DIVERSITY IN UNITY የሚባልም አለ ልበል... ድሬ ዳዋን ማዕከል በማድረግ ከሸለቆው Rift valley በስተምእራብ እስከ ሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ፡ ጎንደር፡ ጎጃም፡ ሸዋ፤ እስከ ምስራቅ ኢትዮጵያ ጫፍ ደግሞ ሀረር፡ ጅግጅጋ፡ ኦጋዴን ከመኖራቸው ያለፈ ስለ ኢትዮጵያዊያን ሶማሊ ህዝቦች የቅርብ እውቀት የለኝም፡፡ ‹‹የመሀል ሀገር ሰው›› ነኛ፡፡ አሁን ግን በተለይ በየክፍላችን ገብተን በኮሪደሩ ላይ ጮክ ብሎ የሚሰማው የሱማሊኛ ቋንቋ ንግግር በፀጥታ ሲዋጥ፤እኔም ስለ ሱማሊ ህዝቦች ማውጠንጠን ያዝኩ፡፡ ‹‹ጸጥታ፡ ፍጹም የሆነ እርጭታ። በል የሚያሰኝ ለስንኝ ቋጠሮ፡ለቅኔ ዘረፋ በርታ እያለ እሚያበረታታ!›› እንዲል በአንድ ተዋናይ ገጸ ባህሪው አንደበት ሩሲያዊው ደራሲ ማክሲም ጎርኪ The Lower Depth በተሰኘ ተውኔቱ፡፡ እነሆ የሲየስታ ወንዝ ላይ ዋና . . .
ከ50 አመታት በፊት የታተመው የሪቻርድ ግሪንፊልድ ETHIOPIA - A new political History  መጽሐፍ ውስጥ ከሱማሊያ ምድር ወደ ኢትዮጵያ የተደረጉትን የሕዝብ ፍስሰቶች ሲገልጽ... ‹‹አንደኛቸው ከሶማሊያ አምባ Somali plateau ተነስተው አስከ አፋርና ደንከል፤ ሁለተኛዎቹና ከሰፊው የኦሮሞ ብሄር ጋር የተዋሀዱቱ ወደ ምስራቅና ደቡብ፤ ሌላኛዎቹ ደግሞ ከብቶቻቸውን እየነዱ መጥተው ሰፍረው ባህላቸውን እንደጠበቁ አሁን ድረስ ያሉትና ከመካከላቸውም ከባንቱና ኦሮሞ ህዝብ ጋር የተቀላቀሉ ናቸው›› ይላል። ‹‹አንዳንዶቹ የምስራቅ ባሬንቱ የኦሮሞ ጎሳዎች ባህል ከጎረቤቶቻቸው ከሱማሌዎች ባህል ጋር አንድ ስለሆነ የሱማሌ ዘር አቆጣጠር ወስደው፣ ሱማሌዎቹ ራሳቸው እንደ ኦጋዴን ሱማሌ ቤተሰብ አባል ይቆጥሯቸዋል፡፡ የኦሮሞዎቹ የከረዩ ጎሣ ደግሞ የጎረቤቶቻቸውን የአፋሮችን ባህል ወርሰዋል ተብሎ ተነግሯል›› የሚለን ደግሞ በአቶ ሚሊዮን ነቅንቅ ‹‹ትልቋ ኢትዮጵያ የብዙ ነገዶች ማኅበረሰብ›› በሚል ርእስ ተተርጉሞ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ያሳተመው የዶናልድ ሌቪን Greater Ethiopia መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሱማሊ ሕዝቦች እንደ ሶማሊያ ሱማሊዎች በቅኝ ግዛት ስር አልወደቁም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ናቸዋ፡፡ ወይም በሌላ አገላለፅ፤ ከሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል የኛዎቹ ሱማሌዎች፣ ኢትዮጵያ በክርስቶስ ሰምራ ተመስላ በሉአላዊ ክንፎቿ አዝላ ያወጣቻቸውና በታዛዋ ያስጠለለቻቸው ሕዝቦቿ ናቸው፡፡ በርግጥ የገፈቱ ቀማሾች ሱማሊያዊያን ሕዝቦችም ሆኑ መላው አፍሪቃዊያንና የአለም ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ያሳዝናሉ። የነጻነት ብርሃን ይፈነጥቅላቸው ዘንድ በአድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል ብስራት የአርነት ቀንዲል ሆና የምትመጣው አሁንም ኢትዮጵያ መሆኗ ሌላው ውብ ታሪካዊ ቅርሳችንና እጹብ ድንቅ  ኩራታችን ነው፤ ግን አጉል ኩራት (Vain pride) ሳይሆን ነው ታዲያ፡፡ በተረፈ የሶማሊያ ምድር የቅኝ ግዛት ቀንበሩ ምን ያህል የበረታባት እንደነበረች ለማስረጃነት አንዲቱን ሀገር ብቻዋን እንዴት ለሶስት ተቀራምተዋት እንደነበር ማስተዋል ብቻ ይበቃል... French Somali land, Italy Somali land, Britain Somali land. ኢትዮጵያ በወቅቱ በአውሮጳዊያኑ ዘንድ የተሰጣት ስያሜ ‹‹የጎን ውጋት›› (Bad neighbour) የሚል ነበር፤ የራሷን ሉአላዊነት በጽናት ከማስጠበቅ አልፎ የነጮቹ ምስራቅ አፍሪቃን የመጠቅለል የቅኝ ግዛት እቅድ በጎረቤቶቿም ላይ እንዳይፈጸም ደንቃራ ስለሆነችባቸው፡፡ መላዋን አፍሪቃን ለመቀራመት ጀርመን ላይ በ1984/5 እ.ኤ.አ ያደረጉት የBerlin Conference ሴራ እንዳይተገበርም እንዲሁ፡፡ ሶማሊያን ለሶስት ቆራርሰዋት ከነበሩት ሀገራት ጋር ኢትዮጵያ የነበራትን ግንኙነት በጨረፍታ እንይ . . .
የናፒየርን የግዛት ማስፋፋት እቅድ ተከትሎ አውሮጳዊያኑ በፖለቲካ ጉዳይ እጃቸውን ከማስገባት የታቀቡ መስለው በንግድና መሰል አቀራረቦች መልካቸውን እየለዋወጡ በተገዳደሩ ቁጥር ኢትዮጵያዊያንም በዚያው ልክና ባለፈም መጠን አጸፋውን እየሰጡ ቆይተዋል፡፡ ከአጼ ቴዎድሮስ በኋላ አጼ ዮሀንስ በተለይ በአባይ ወንዝና የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ከቋመጠችው ከእንግሊዝ ጋር ዲፕሎማሲውን ማጠናከር ሲጀምር፣ አሳቻ ሁኔታ እየጠበቀች ኢጣሊያ ላደረገችው ተደጋጋሚ የጥቃት ሙከራ የራስ አሉላን ክንድ እየቀመሰች ከርማ፤ አጼ ምኒልክ ከናካቴው አድዋ ላይ ድባቅ መትቶ ገላገላት። በምኒልክ ዘመን ፈረንሳይ የድሬዳዋ ጅቡቲን የባቡር መንገድ ስራ እንደ እጅ መንሻ (political weapon) አድርጋ ስትመጣ እናገኛታለን፡፡ ልጅ እያሱ ወደ ምስራቅ ተጉዞ ድሬዳዋንና የፈረንሳይ ሱማሊላንድን ካየ በኋላ፣ ውሎ አድሮ በ1950ዎቹ አብዮተኛ በገርማሜ ነዋይ የተመራውን ጦር ጅግጅጋ ላይ ያቋቁማል፤ እርግጥ ነው ልጅ እያሱ ኃይማኖታዊ አቋሙ አሻሚ ሆኖ ያልፋል፡፡ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ  የአድዋን ሽንፈት ለመበቀል 40 አመታት ቆጥሮ በመጣው የጣሊያን ወረራ ወቅትም፡ ከጠላት ወረራ በፊትም በኋላም ከአዲሳባ እስከ የምስራቅ ሀረርጌ ጫፍ ‹‹ኃይማኖት የግል፤ ሀገር የጋራ›› እያሉ  መመላለስ ይቀጥላል፡፡ንጉሡን ከዙፋን ያወረደውና የኢትዮጵያንና መላ ሕዝቦቿን አንድነት ለማስጠበቅ መከራውን ያየው የደርግ መንግስት መሪ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያምም፤ ከዚያው ከሀረር ጦር ሰፈር ተነስቶ ነው የሚመጣው፡፡ እንግዲህ ከዚህ ሁሉ በኋላ  ከኢህአዴግ ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ ህዝቦችና ብሄር ብሄረሰቦች ህገ መንግስት›› ዘመን እንደርሳለን። ታዲያ የእነዚህ ሁሉ ከአዲሳባ የምስራቅ ኢትዮጵያ ድንበር ጫፍና ጅቡቲ ድረስ መንሸራሸሮች መዳረሻ ከተማ በሸለቆው መካከል ጉብ ያለችውና በኢትዮጵያ ታሪክ ቀደምት የባቡር ትራንስፖርት ተጠቃሚ የነበረችው ውቢቱ የድሬ ከተማ መሆኗን ልብ ይሏል፡፡ Dira Dawa - the railway town on the floor of the rift valley.
በነገራችን ላይ ከላይ ከተዘረዘሩት ገዢዎች መኻከል፤መርስዔ ሀዘን ወልደ ቂርቆስ በ‹‹የሐያኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ›› መጽሐፋቸው ውስጥ የልጅ እያሱን ወደ ሀረር ጉዞ፣ ከአንዲት ቆንጆ ሴት/ጥሩወርቅ አሊጋዝ ፍቅርና ‹‹የከተማው ወሬ›› ጋር አሰናስለው ያቀረቡበትን የፍቅር ድርሳን በእጅጉ ተመስጬበታለሁ፡፡ አንዳንዶቹ የታሪክ ጸሀፍት፤ የልጅ እያሱን ፍቅረኛ ሴቶችና የልጆቻቸውን ቁጥር ይቆልሉታል፡፡
በሌሊቱ ጸጥታ ውስጥ ጎልቶ በተሰማው የአዛን ድምጽ መነሻ ደግሞ፤ ከመስኮቴ ባሻገር ምስራቅ አድማስ ላይ እንኮይ መስላ የወጣችውን የንጋት ጀምበር ፎቶ አንስቼና በቀዝቃዛ ውኃ ለቅለቅ ብዬ ለቁርስ የሆቴሉን ደረጃ ስወርድ ካገኘኋቸው ሱማሌ ወጣቶች ጋር ስለ ቢላል አል ሀበሺ ፡ ኡሙ አይመን አል ሀበሺ፡ የመጀመሪያዋ ሂጅራ ከቁሬይሽ ወደ ኢትዮጵያ ስለመሆኗ፡ ስለ አልነጃሺ መስጂድ... አወጋን፡፡ በመጨረሻም በአለም ዋንጫ ዝግጅት ላይ ያቀነቀነውን የሱማሊያዊውን ድምጻዊ የኬነንን ዜማ አስታውሰንም በጋራ አንጎራጎረን ተሰነበባበትን፡፡
(ከዘመናት ታሪካችንና በተለይ በደርግ ዘመን ድንበር ለማስከበር ብዙ ሺ ጀግኖች በሰማዕትነት የወደቁበት የኢትዮጵያና ሱማሊያ ጦርነት በፈጠረውና ትቶት ባለፈው አመለካከት፡ ከዚያም ወዲህ በተከሰቱ አለመግባባቶች ሳቢያ እንደኔ ያለ ‹‹የመሀል ሀገር ሰው›› ሱማሌን ሁሉ በአሉታዊ ስሜት እንዲያይ ተገድዶ ቢኖር አያስገርምም፡፡ የሶማሊያ ሱማሌንና የኢትዮጵያ ሱማሌን ለይቶ የማወቅ ተሞክሮ በሌላ ጊዜና ሁኔታም ውስጥ መሰል የፍረጃ አመለካከት እንዳይፈጠር ለማጥራት ይረዳም ይሆን እንጃ...) ከአዲሳባ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ድሬ ተነስተን  ወደ ቁልቢ (ነጭ ሽንኩርት ማለት ነው ብሎኛል ያካባቢው ተወላጅ ወዳጄ ብዙነህ ሰይፉ) ገብርኤል ንግስ መንገድ ላይ ሆነን፤ አባ ጎርጎርዮስ በ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ›› መጽሀፋቸው  ስለ የመላእክት ክብርና ምልጃ ሲጽፉ፤ የምልጃ ትምህርት ሐዋርያዊ ውርስ (Apotiolic Succession) መሆኑን ጠቅሰው ያሰፈሩት... ‹‹መላእክት ረቂቃን ፍጥረታት ናቸው። በእግዚአብሔርም ፊት በባለሟልነት የሚቆሙ ናቸው፡፡ የእግዚአብሔርን ኃይል ለመግለጥ የሚላኩ ናቸው፤ የእግዚአብሔርን ምህረትና ይቅርታ ለሰው ልጅ፣ የሰውን ልጅ ትሩፋትና ማንኛውንም በጎ ሥራ ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ ከዚህም ሁሉ ጋር በክርስትና ታሪክ ውስጥ የእግዚአብሔር ምስጢር ተካፋዮችና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ናቸው፡፡ በመጀመሪያ አምላክ ሰው ሊሆን ነው ብሎ የምስራች የተናገረ የእግዚአብሔር መልአክ ነው፡፡...›› ይላል፡፡
እነሆ እኛም የክርስቶስን መወለድ ብስራት ካበሰረውና በየአመቱ ታህሳስና ሀምሌ 19 ቀን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ምእመናን በሚታደሙበት፣ ሙሉ ለሙሉ የቤተ ክርስቲያን ስርአትና ያልተበረዘ መልክ በሚንጸባረቅበት ሁናቴ በታላቅ ድምቀት በሚከበረው የቁልቢ ገብርኤል ንግስ ላይ ተገኝተን ምስጋናና ጸሎታችንን አድርሰን ተመለስን። ከምዕመናኑ መካከል ስእለታቸውን በወረቀት ጽፈው የሚያኖሩትን ሳይ ደግሞ በቅድስቲቱ ኢየሩሳሌም ከተማ፣በነጭ እጀ ጠባብ የሀገር ባህል ልብሴ ላይ በሳባ ጥለት የተከፈከፈ ጥቁር ካባ ደርቤ፡አናቴ ላይ ከእብራይስጥ ጽሁፍ ጋር የዳዊት ኮከብ ምልክት ያለበት ነጭ የአይሁድ ቆብ (ኪፓ) አድርጌ፣በጥንቲቱ ኢየሩሳሌም ከተማ Old Jerusalem City የተቀደሰው ግድግዳ Waiting Wall ስር ቆሜ  በወረቀት ላይ የከተብኩትን ስእለቴን አኑሬ ስመለስ፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም Barack Obama በስፍራው ተገኝተው እንዲሁ ማድረጋቸውን ሰምቼ እንደነበር ትዝ አለኝ፡፡ (ኦባማ ሴናተር እያሉ ድሬዳዋ ከተማን ጎብኝተውም ነበር፡፡ ማን ያልጎበኛት ወይም ሊጎበኛት የማይፈልግ አለ ይሆን፤ይቺን የፍቅር ከተማ...)  
‹ከሀርጌሳ አካባቢ የሚመጡ ሙስሊሞች አውቃለሁ፡ በየአመቱ አዳዲስ ስጋጃዎችን እያነጠፉ ገብርኤልን ይለማመናሉ› ያካባቢው ተወላጅ ወዳጄ ስለ ቁልቢ ገብርኤል ንግስ ሲያጫውተኝ በጣም ተገርሜ ነበር የማደምጠው፤ ከአጥቢያው ራቅ ብሎ የሚገኘው ትልቅ ዋርካ ዛፍ መጠሪያ ደግሞ በኦሮሚፋ ‹‹ሐጃ ፈጅ›› ይባላል ሲል  ጨመረልኝ - ትርጉሙ ‹‹ጉዳይ ኮቻሚ››፡፡  እየራቅን ስንሄድና ወደ ከተማው ስንጠጋ፤ ያካባቢውን ዙሪያ ገብ ስቃኝ፤ ከንግስ መልስ በቁልቢ ከተማ የገብርኤልን ዝክር ከሚያወጡትና ክርስቲያኑንም እስላሙንም በክብር እየጋበዙ ከደማቸው በተጣባው የእንግዳ ተቀባይነት ባህርያቸው ‹‹ካላደርክ አንለቅህም›› ያሉኝን የወዳጄን ቤተሰቦች ሰፊ ጊቢ፡ መላ መንደሩንና መንገዱን ሁሉ ሳስተውል፡ በአሉን እንደ ክርስቲያኑ ሕዝብ ከሙስሊሙም መካከል በጋራ የሚያከብሩ አሉ። ኢየሩሳሌምን እንደ ቅዱሱ ግድግዳ በዚህም አሰብኳት፤ የአይሁድ፡ የክርስቲያን እና የእስልምና ኃማኖቶች መገኛ ናትና፡፡
አባ ጎርጎርዮስ፤ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከሮማ ካቶሊክም ጋር በተዋወቀችበት መድረክ በጋራ ለውይይት ተቀምጣ በፍሎሬንስ ጉባኤ  የተስማማችበትን ‹‹በእምነቶች መካከል  ያለውን ጥላቻና ክፉ አስተሳሰብ ለመክላት ቤተ ክርስቲያን ‹‹በትክክለኛ አላማው›› ትቀበለዋለች የሚሉንን የኢኩሜኒዝምን (Ecumenism) ታሪካዊ ንቅናቄ አይነት ሰላማዊ አላማ ያላቸው ቀና አስተሳሰቦች፤ እድገትና ስልጣኔን ተከትለው ለተጋረጡብን የእለት ተእለት ተግዳሮቶች መፍትኼ ማግኛ ይሆኑ ዘንድ በዘመኑ ጥያቄ ልክ ሰፋ፡ ዳበር ማለት ቢችሉ ብዬ ተመኘሁ፡፡
 እስከ ‹‹ዋናው ጉዳይ ሰው ነው›› ሉላዊ ቅኝት (Global thinking) ለጠጥና ‹‹ኃይማኖት ሁሉ ጥሩ ነው፤ ሰዎችን ጥሩ እንዲሆኑ እስከሰበከ ድረስና ››every religion is good if it teaches the people to be good.” ባሻገርም....ቦርቀቅ ቢልስ፡ ለጋራ የሚበጅና ለበጎ ብቻ ይሁን እንጂ፡፡ ወንጌሉም የሚያስገነዝበንን ... የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ በክብር ዙፋኑ ተቀምጦ፣ በጎቹን ከፍየሎቹ ሲለይ የሚናገረውን ‹‹እውነት እላችኋለሁ፡ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት›› (ማቴ 25፤31-31)፡፡ በሰማዕታት ደም ከተከተበው ከሀገራችን ሕገ መንግስት የኃይማኖት ነጻነት ትሩፋት ጋር የትየለሌ ጥንታዊና ነባር ሀገረኞችና ዘርፈ ብዙዎቹን (የየግለሰቡንምና ኢ አማኒውንም ሁሉ) እምነቶች ጨምሮ፤ ‹‹ዳግማዊት ኢየሩሳሌም›› የምንላት ኢትዮጵያ፤በረዥም ዘመናት ታሪኳ የአይሁድ፡ የክርስትና እና የእስልምና ኃማኖቶች መኖሪያ መሆኗን መካድ አይቻልምና፡፡ ወደ ድሬ ስንመለስ፤ ስለ ቅድስቲቱ ምድር የተቀነቀነውን Revalation in Jerusalem ዜማ አንጎራጉር ነበር... You can see Christians, Jews and Muslims living together and praying ... ክርስቲያኑም፡ ይሁዲውም፡ እስላሙም በጋራ የሚኖሩባትና የሚጸልዩባት- ኢየሩሳሌም፡፡
ከድሬዳዋ መንደሮች ጥቂት ያህሉን ብቻ ተዟዙረን ጎበኘን፡፡ በዛፎቿ ጥላዎች ስር ተንሸራሸርን፡፡ የፍየል ስጋና የድንች ጥብስ፡ ትኩስ ፍራፍሬዎችና መለዋ፡ ሙሸበቅ በላን፡ ትኩስ ጭማቂና ወተት ጠጣን፡፡በከተማዋ የመጀመሪያው ነው ከሚባለው ህንፃ ፊት ለፊት ከዚራ ላይ የቆመውና ከእምነ በረድ ተፈልፍሎ የተሰራው ሀውልት ግሩም ድንቅ ነው፡፡
 ዛሬ በባጃጅ የተተኩትንና ለዘመናት ሲያገለግሉ የኖሩትን የባለጋሪውንና ፈረሱን ውለታ ጠቋሚ ህያው ማስታወሻ ነውና፡፡ ከዚህ በፊት ጉልህ ስፍራ ነበረው፤ አሁን ተሸሸገ እንጂ የሚባለውም የባቡር ፉርጎ ተመሳሳይ ክብርና ስፍራ ሊሰጠው ይገባ ይመስለኛል፡፡
የባለጋሪውን ሀውልት የምናደንቀው ባረፈበት ረቂቅ የጥበብ አሻራ ብቻ አይደለም የከተማዋን ነባር መልክ ጠቋሚነቱ የሚገዝፍ ይመስለኛል፤ ከዚያ ነው የቀራጺው ጥበብ የሚመጣው፡፡  ምክንያቱም ሀውልቶች (Monuments) ያለፈውን ትውልድ ከመጪው ትውልድ የሚያስተሳስሩ የብረት ድልድዮች ናቸው ነው የሚባሉት - Monuments are the grappling-irons that bind one generation to another. በመኖሪያ ቤታቸው ፍራሽ ዘርግተው ከጠበቁን ድሬዎች ቤት አርሂቡ ተብለን፣እግራችንን አጥፈን ተቀመጥን፡፡
  የሰዉ ደግነት ያጥንት ነው፤ ያንገት አይደለም ለማለት ነው፡፡ በቃ ደግነት ባህርያቸው ነው፡፡ በቤትም በመንገድም፡፡ ድሬ የሚኖርባት ብዙ አይነት ብሄርና የተለያየ ሀገር ተወላጅ ነው፡፡
 ሎሬት ጸጋዬ፤ ‹‹ድሬዳዋ›› በሚለው ግጥሙ ይህንኑ ሲገልጽ፤‹‹ድሬዳዋ ቁልቢ በር፤የስንቱ ዘር የእኩል ሀገር፤ ድሬ ዳዋ ድሬ ዳዋ የምስራቅ ሀገር ጥላዋ፤ ላገር ጎሳ ድምር ጽዋ፤ኅብረ ጠባይ ማጥለያዋ›› ይላታል፡፡ ሁሉ ስለ ድሬ የራሱ ትዝታና ታሪክ አለው፡፡ ድሬን ገልጾ ለመጨረስ አይደለም ቆንጥሮም ለመተረክ ከባድ ነው፡፡ እና ምንድነው የሚሻለው...በሌላ ጊዜ ለመመለስ ቃል መግባት እንዲሁም ለመመላለስ፡፡ምሽት ላይ ዘና ብለን ከታደምንበት ሞቅ ያለ መዝናኛ ስፍራ ውስጥ ሳለን ዝናብ ማካፋት ጀመረ፡፡ ድንገት ተስፈንጥሬ ተነስቼ ወደ መንገዱ ወጣሁ፡፡ ግራ የተጋቡት ጓደኞቼ ተከተሉኝ፡፡ መሄድ የፈለግሁበት ስፍራ አሁን ካለንበት ይርቃል፡፡ ቅድም ድልድዩ ላይ ቆሜ ሰፊውን የጎርፉን መውረጃ ጉድጓድ እንደ ባላጋራ ቁልቁል ትክ ብዬ ሳየው፤ ‹‹ተው ያዞርህና ትገባለህ ›› ብሎ ራቅ አድርጎኝ ነበር አንድ የደቻቱ ሰፈር ሰው፡፡ እዚህ አካባቢ ያሉ ሰዎች ያ ዘግናኝና እጅግ ሰቅጣጭ፣ የሺዎችን ምስኪን ህይወት የበላ የጎርፍ አደጋ ሰለባ ባይሆኑም ከዝናብና ጎርፍ ጋር የተሰናሰለ ክፉ ትዝታቸው ነው፡፡
ባገር የሚመጣ ጥቃትና ጉዳት፣መከራና ሀዘኑ የጋራ ነውና። ይህንንም ስጋት ቀን ፍራሽ ላይ ሆነን ካፊያ ሲጀምር በነዋሪዎቹ ፊት ላይ አጥልቶ በነበረው የስሜት ጭጋግ አስተውያለሁ፡፡ ዝናብ ስለዘነበም ብቻ ጎርፍ ይከሰታል ማለትም ግን አይደለም፤ ምናልባትም ድሬ ላይ ሳይዘንብ ጥቂት ኪሎሜትሮችን ርቀው ከሚገኙ አጎራባች ከተሞች የዘነበው ዝናብ ነው የጎርፍ መዘዙ ለድሬ የሚተርፈው ይባላል፡፡
እናም እኒህን በእንስፍስፍ ፍቅራቸው፣ እንግዳ ተቀብለው በማስተናገድ የሚወደዱትን ደጋግ ሰዎቿን የሚሰለቅጠው፡፡ ‹‹ባለፉት ዘመናት በመንግስት ይደረግ የነበረና አሁን የቆመ መፍትኼ ነበረው›› የሚባለው እውነት ነውን?....ከሆነስ ምንድነው?....እናስ የድሬዳዋና እያሰለሰ ብቅ የሚለው የዚህ ጎርፍ ስጋት ጉዳይስ እስከ መቼ ይሆን የሚቀጥለው?....ዘላቂ መፍትኼስ የለውምን?....
ከተማዋን ስናቋርጥ በምድር ባቡር መስሪያ ቤት አጥር ግምብ ላይ የተደረደሩትን ከ7ሺህ አመታት በፊት የነበሩ የዋሻ ውስጥ የጽሑፍ ቅርሶችን ምስሎች አየሁ፡፡ አሁን ደግሞ ድሬን ከጥንታዊቷ ግሪክ ጋር ለማመሳሰል ዳዳኝ፡፡ ይህቺ ሀገር ሺሊማን ሳትፈልግ አትቀርም አልኩ፡፡ ሄንሪክ ሺሊማን በሆሜር ኢሊያድ ድርሰት፤የትሮይ ጦርነት ገድል ውስጥ ያነበባትን የትሮይ ከተማ ከግሪክ ምድር ስር ቆፍሮ አውጥቶ፣ከተረትነት ያላቀቃት ጀርመናዊ አርኪዮሎጂስት ነው፡፡
ጓደኞቼ በኔ መሻት ቀን በአንግድነት የነበርንበት ቤት አደረሱኝ፡፡ የአስፓልቱ ላይ ወራጅ ጎርፍ ድሬ ስደርስ ባጠለቅኩት ሸበጤ ስር ተረከዜን እያራሰኝ ገባሁ፡፡
ከተወለደች አንድ ሳምንት ከሞላት ህጻንና እናቷ አራስ መኝታ ስር ተቀምጬ፤ ባብዛኛው ስለተለያዩ የህይወት ጉዳዮች እያነሳን ስናወጋና ስንስቅ፡ ህጻኗን ስናጫውት፤ አልፎ አልፎ ግን፡ በየመሀሉ ትዝ ሲላት፤ እናቲቱ አሁን ካለንበት መኖሪያ ቤታቸው ጀርባ ስላለው ጎርፉ ስለሚወርድበት ስፍራና ቀን ከታላቅ እህቷና የቤተሰቡ አባላት፡ከጎረቤቶችም ነዋሪዎች በመጠኑ የሰማኋቸው አይነት ስለ አሰቃቂው የድሬ የጎርፍ አደጋ ልብ የሚነኩና አንጀት የሚያንሰፈስፉ ታሪኮችን ስታወራልኝ ጎህ ቀደደ፡፡
ከአራት ቀናት አጭር ቆይታ በኋላ ውቢቱን ከተማ ሳልጠግባት ወደ አዲሳባ ለመምጣት አይሮፕላን ውስጥ ቁጭ ብዬ ‹‹የድሬን ምድር አየኋት፤ እድለኛ ነኝ›› አልኩ፡፡ ብርቅ ቢሆንብኝ አይደንቅም፡፡ ከሰፈራችን ልጆች በልጅነታችን በዝና የሰማናትን ድሬን ለማየት እድሉ (‹‹ዲቪዋ››) ካልደረሰን፤ብር ሰርቀን መምጣት ካልቻልነውም መካከል ነኝ፡፡ ዘንድሮ ፍቅር አክንፎ አመጣኝ ልበል...፡፡ በእንግድነት ለተቀበላችሁኝ ድሬዎችና ጉዞዬ እንዲሳካ ላደረጋችሁ ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡ በተለያየ ሞያ ላቅ ያለ ስኬትን የተቀዳጁ እጅግ ብዙ ታላላቅ ሰዎች ከድሬዳዋና ከምስራቅ ኢትዮጵያ ወጥተዋል፡፡ ባንፃሩም በታሪክ ውስጥ ብዙ የውጪ ሀገር ሰዎችና እልፍ አእላፍ ኢትዮጵያዊያኖች፡ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ድሬን አይተዋታል፡፡ እንደኔ በእንቶ ፈንቶ ወሬ አልተጠመዱም እንጂ፡፡ ከበርካታ ጀግኖቹ መካከል አባ ነፍሶን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከሊቆቹ  አንድ ለመምዘዝ ያህል ደግሞ፤ በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ጸሐፌ ተውኔት የሆኑትና ዘመናዊ ትምህርታቸውን በሩሲያ ቀስመው በጊዜው በሚኒስትር ማእረግ የተሾሙት ብላታ ግርማቸው ተክለ ሀዋርያት፤ ባንድ ወቅት ወደ ድሬ ብቅ ብለው ሰንብተው በነበረ ጊዜ ነው፤ በወቅቱ ሀገሪቱና ገዢዎቿ በእርስ በርስ ቁርሾ ይታመሱበት ለነበረው ጉዳይ  በዘመኑ ድንቅ የተሰኘና በባእዳኑ የታሪክ ጸሐፍት ዘንድም ሳይቀር፤‹‹ያመዛኙን አዛውንት ኢትዮጵያዊያንን ባህርይ የሚያንጸባርቅ ምክር ;typical attitude of many older Ethiopians# ተብሎ የተወደሰላቸውን ኗሪና ህያው ኢትዮጵያዊ መፍትኼ ጨርጨር ላይ በተሰየመ ጉባኤ ተገኝተው የተናገሩት፤ እንዲህ ሲሉ.... ‹‹ልዩነቶቻችን የየራሳችን ጉዳዮችን ናቸው፤ ሀገራችንን በተመለከተ ግን ሁላችንም አንድ ነን፡››በትሁትና ቀልጣፋ የመስተንግዶ ባለሙያዎቹና በተሟላ የበረራ አገልግሎቱ የሚታወቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሮፕላን፣የድሬን መሬት ሲለቅቅ የጆሮ ማዳመጫዬን ሰካሁ፡፡ በመሳሪያ የተቀነባበረ ሙዚቃ ኩልል ብሎ ይሰማኝ ጀመር . . .
‹‹ኢትዮጵያ ሀገሬ፡ መከታ ጋሻዬ፤
 ለኔ መመኪያ ነሽ፡ የልቤ መኩሪያዬ››

Read 2515 times