Monday, 08 August 2016 06:28

አቶ አሰፋ ጫቦ፤ እራሣቸውን ከተጠያቂነት ነፃ አወጡ !

Written by  ማርቆስ ተስፋዬ
Rate this item
(7 votes)

አቶ አሰፋ ጫቦ፤ እራሣቸውን ከተጠያቂነት ነፃ አወጡ ያልኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ባለፈው
ሐምሌ 2፣ በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፤ “ የ60ዎቹ ፖለቲከኞች ንስሃ መግባት አለባቸው“ በማለታቸው ነው፡፡ አቶ አሰፋ ጫቦ፤ ንስሀ ግቡ የሚሉን፣ እሳቸው በ1960ዎቹ የት ነበርኩ ሊሉን ነው - የኔ ጥያቄ፡፡ እስከማውቀው ድረስ አቶ አሰፋ፤ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነበሩ፡፡ እንደውም በለውጥ አራማጅነት ኢጫትን ወክለው ግንባር ቀደም የፖለቲካ ተሣታፊ ነበሩ፡፡ ይኸንኑም ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ፤ “እኛና አብዮቱ “ ብለው በሰየሙት መጽሐፋቸው፣ ገጽ 237 ላይ፣ አቶ አሰፋ ጫቦ፤ ከአቶ ባሮ ቱምሳና ከአቶ ዘገዬ አስፋው ጋር ሆነው፣ በኢጫት ተወካይነታቸው ከደርግ ጋር እንደ መኢሶን አብረው ይሠሩ እንደ ነበር ገልፀዋል፡፡ ሀቁ ይኸ ሆኖ ሳለ፣ እንዴት ነው እሣቸው ነፃ ወጥተው፣ ሌሎች የወቅቱ ፖለቲከኞች ንስሀ የሚገቡት?  የ1960ዎቹ ፖለቲከኞች በጅምላ ይቅርታ መጠየቅ ካለብን ደግሞ አቶ አሰፋም ከኛው ጋር አብረው ለምንድን ነው የማይጠየቁት? ክፋቱ ደግሞ እርሣቸው እንዲህ ዐይነት የጅምላ ተጠያቂነት አይወዱም፡፡ እንዴት አወቅህ?  አትሉኝም፡፡ ጋዜጠኛው በቃለ መጠይቁ ወቅት ፤“አብዛኛው የናንተ ዘመን ፀሐፊዎች፣ ያለፈ ስርአትን ወቃሽ ናቸው፡፡ በየዘመናቱ በነበሩ መንግሥታት የተሠሩ በጎ ነገሮችን ለማንሳት ለምን አይሞከርም?“ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ “መውቀስ ካልነውም መላ ያለው፤ማስረጃ ያለው ወቀሳም ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ጅምላ ወቀሳ ከሆነ ደግሞ ወቀሳውንም ወቃሹንም ከፍቶ ማየቱ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ማለትም፣ “ለመሆኑ አንተ ማነህ ?”፣ ከነማን ጋር ነበርክ?” ያኔስ የት ነበርክ ?” ፣ “ምን ምን ሰራህ ?” “ምን ምንስ መስራት ሲገባህ ሳትሰራ ቀረህ ?” ፣ በምን ምክንያት ?” ፣ ሌላው አይን ውስጥ ያለውን ትቢያ ማሳየት ብቻ ሳይሆን አንተስ አይን ውስጥ የተጋደመውን ግንድ ምን እናድርገው ?” ማለቱ ጥሩ
ይመስለኛል፡፡ “ ብለው ነበርና ነው፡፡ አቶ አሰፋ፤እርሳቸውን የሚያካትት ጥያቄ ሲመጣባቸው ግን እንደዚህ ዐይነት ዝርዝር ማጣራት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ተጠያቂነቱ ሌሎችን የሚመለከት ነው ብለው ካሰቡ ደግሞ ፤  “መኢሶንና ወዝሊግን ከተከሳሾች መዝገብ ውስጥ ማስወጣት ያለብን ይመስለኛል፡፡ ቀይሽብር ነጭሽብር ተብሎ የኢትዮጵያን ቀጣይ ትውልድ በፈጀውና የደርግ አባላትንም እርስ በርስ በማባላት የተጫወቱትን
ሚና ሌሎች የጻፉት እንደ ተጠበቀ ሆኖ ፤ ፍቅረሥላሴ ወግ ደረስና ፍሰሀ ደስታ ደህና አድርገው
ገልጠውታል፡፡ ያም ሆኖ ፣ መኢሶኖች በተለየ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥተዋል፡፡ መንግሥቱ
ኃይለማርያም፤ የመኢሶንን መሪዎች አርደዋቸዋል፡፡ ከዚህ በላይ የሚከፈል ዋጋ ሊኖር ስለማይችል ፣
ከደርግ ጋር በማበር የፈጸሙትን ወንጀል መዝገብ ዘግተን ፣ ወደ መዝገብ ቤት በቋሚነት መመለስ
ያለብን ይመስለኛል ፡፡” ይሉናል፡፡ አቶ አሰፋ፤ በኛ ላይ ሲፈርዱ፤ለመሆኑ እኔ ማን ነኝ ? ከነማን
ጋር ነበርኩ ? የት ? ምን ምን ሠራሁ ? ወዘተ. የሚሉትን ጥያቄዎች ለራሣቸው አላቀረቡም፡፡
በደፈናው ወዝሊግና መኢሶን ከደርግ ጋር አብረው የሠሩ ወንጀለኞች መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
ይኸ አስተያየት ደግሞ፣ የሕግ ምሁሩና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም
ተግባራዊነት አብረውን የታገሉት የአቶ አሰፋ ጫቦ አልመስልህ አለኝ፡፡ አቶ አሰፋ፣መቼም አብረን አልታገልንም እንደማይሉኝ ተስፋ አለኝ፡፡ መኢሶን እንኳን የኢትዮጵያን ቀጣይ ትውልድ ሊፈጅ ይቅርና እርስዎ እንደሚሉትም፣ ደርጎችንም እርስ በርስ አላባላቸውም፡፡ ይኸንን ዐይነት ክስ መኢሶን ላይ ከእርስዎ በፊት ያቀረቡት ኮ/ል ፍሥሐ ደስታ ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህንን በደርግ ውስጥ ሲተገብሩ የነበሩት እራሳቸው ኮሎኔሉ ነበሩ እንጂ መኢሶኖች አልነበሩም፡፡ ይኸንን ስል እርሳቸው ይኸን ሥም እኛ ላይ ሊለጥፉት እንደፈለጉት፣ እኔም እርሳቸው ላይ ለመለጠፍ ፈልጌ ሳይሆን፣ ከማስረጃ ጋር ነው የማቀርብልዎት፡፡ መቼም መጽሐፋቸውን እንብቤያለሁ ብለውኛል፡፡ ያስታውሱ እንደሆን “አብዮቱና ትዝታዬ” በሚል በጻፉት መጸሐፋቸው ገጽ 222 ላይ፤ሰሚ አላገኙም እንጅ ለነዓለማየሁ ኃይሌ ፤“ ለመሆኑ (መንግሥቱን ሥልጣን እንዳይዝ) እናስቆማለን ስትሉ ዘመቻ ክፍሉን፣ መረጃ ክፍሉንና ጦሩን በእጃችሁ ሳትይዙ የምታደርጉት መሯሯጥ ተመልሶ እናንተን የሚጎዳ አይሆንም ወይ ? በስሜትና እልህ ከመጋባት
ይልቅ ለምን በጥሞና አትነጋገሩም አልኳቸው“ አይደለም እንዴ ያሉን፡፡ ኮሎኔሉ በዚህ በኩል መንግሥቱን ለማስመታት ይኸንን ይመክሩና፣ መለስ ብለው ደግሞ መንግሥቱን ፣ እርስዎ ሰውዬ ሥልጣንዎን አይፈልጉትም ወይ እያሉ ያስበረግጓቸዋል፡፡ መኢሶን እንደዚህ ውስጥ ውስጡን ማዋሸክ ልማዱም አይደለም፡፡
መኢሶን ስለ ደርግ ያለውን አስተያየት ማወቅ ፈልገው ከሆነ፣ መኢሶን፣ ደርጉ በአብዮቱ እስከ መጨረሻው ዘልቆ እንደማይሔድ በድብቅ ሳይሆን በግልጽ በልሳኑ ላይ እንዲህ ሲል አሳውቆ ነበር  ‹‹የኢትዮጵያ መለዮ ለባሽና ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ፤ ለአብዮቱ እስካሁን ያደረጉት አስተዋጽኦ በጣም ከፍተኛ መሆኑንና ወደፊትም ብዙ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ቢያምኑም፤ እነዚህ ኃይሎች እንዳሉት፣ እስከ መጨረሻው ለአብዮቱ ይቆማሉ በሚለው የሕልም እንጀራ ድርጅታችን ፈጽሞ አያምንበትም፡፡ በደርጉ ውስጥም ሆነ በመለዮ ለባሹ ውስጥ ያሉት አብዮታዊና ፀረ-አብዮታዊ
ኃይሎች ሠልፋቸውን ለይተው የሚፋፉበት ወቅት በእርግጥ ይመጣል፡፡ ለዚህም ነው፤ የኢትዮጵያ ሠፊ ሕዝብ በየእለቱ ይበልጥ መንቃት፤ መደራጀትና መታጠቅ ያለበት፡፡ “(መኢሶን በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮት ውስጥ፤ ሰሕድ ቁጥር 50 ጥር 30፤ 1969 ይመለከቷል)
 ይኸ ደግ ማርክሳዊ የመደብ ቅራኔ ትንታኔ እንጂ ደርጉን እርስ በርሱ ለማጋጨት ታስቦ የተሰነዘረ
አይምሰልዎት፡፡ መኢሶን የኢያጎን ባህሪ የተላበሰም ድርጅት አልነበረም ፡፡ አባሎቹ ቢታሙ እንኳን  
በሀገር ወዳድ ምሁርነታቸው ነው፡፡ አቶ አሰፋ፣ ደርጉ ፀረ-አብዮት አዝማሚያ ሲይዝ፣መኢሶን ከደርጉ መለየቱን ያውቃሉ? እርስዎ ግን በዚያን ጊዜም ከደርግ ጋር አብረው መሥራትዎትን ቀጥለው ነበር፡፡ ይብስ ብለው ደግሞ አሁን ፣ መኢሶንን ከደርግ ጋር ሠራ ብለው መወንጀል ጀመሩ፡፡ መኢሶን በዋናነት የአብዮቱ ጠላቶች ብሎ ከፈረጃቸው ኃይሎች ጎን ለጎን፣ ከደርጉም ጋር በመለስተኛ ደረጃ ሲታገል እንደ ነበረ አሁን ላይ ሻምበል ፍቅረሥላሴም ሆነ ኮ/ል ፍሥሐ ደስታ በመጸሐፋቸው ውስጥ በግልጽ አስቀምጠውታል፡፡ ስለዚህ መኢሶንና ደርግ ትውልድ አጠፉ የሚለው አነጋገርዎ፣ አድማጭም የሚያገኝ አይመስለኝም፡፡ አሁን ደግሞ ደርግና መኢሶን እጅና ጓንት ነበሩ የሚለው የሀሰት ፕሮፓጋንዳ  በደርጎቹ በራሣቸው እንዳልነበርን ተመስክሯል፡፡ መኢሶን በአብዮቱ ወቅት የሠራውን ማወቅ ከፈለጉ ፣ ጥቂቶቹን ልጥቀስልዎት፡፡ መኢሶን ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ሚያዚያ 13 ቀን ፣ 1968 ዓ.ም  የታወጀውን “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም “  ተግባራዊ ለማድረግ በታገለበት ወቅት፣ ሕዝብን አንቅቷል፣ አደራጅቷል፡፡ እስከተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሕዝቡ እንዲታጠቅ ጥረት አድርጓል፡፡ መኢሶን እጅና ጓንት ሆኖ
የታገለው ከኢትዮጵያ ሠፊ ሕዝብ ጋር እንጅ ከደርግ ጋር አልነበረም፡፡ ከደርግም ጋር የነበረው ትስስር የተበጠሰው በዚሁ የተነሣ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ በተረፈ ፣ ስለ መኢሶን ማንነት ሀቁን የመሰከሩትን የሠደድ አባል የነበሩትን የገሥጥ ተጫኔን ምስክርነት ላቅርብልዎት ፡፡ ገሥጥ ተጫኔ፣ መኢሶን ምን ያህል የሕዝብ ተቀባይነት እንደነበረውና ከደርግ ጋር ያደረገውን ተጋድሎ በሚቀጥለው መልኩ ነሐሴ 1996 ዓ.ም “ነበር” በማለት ባሳተሙት መጽሐፋቸው ገጽ 237 ላይ ገልጸታል፡-“ የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት ካድሬዎች ፣ በተለይም የመኢሶን ካድሬዎች፣ ሕዝቡን የማንቀሳቀስ ፈጣን ችሎታቸውን ካሳዩበት የቅስቀሳ ተግባራቸው ይህ ዋናው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ገበሬው ከማሳው የሰብል  ስብሰባውን ፣ ወዝአደሩ ከፋብሪካው የምርት ተግባሩን፣ የመንግሥት ሠራተኛው ከቢሮው የአገልግሎትና የአስተዳደር ሥራውን ሌላውም
የከተማው ነዋሪ ለዕለት ጉርሱ፣ ለዓመት ልብሱ የሚማስንበትን ትቶ በነቂስ ነበር የወጣው“  ገሥጥ እንደ እርስዎ መኢሶንን ትውልድ የፈጀ ብለው ሳይሆን የሚኮንኑት፣ በትግሉ ወቅት መኢሶን ያበረከተውን አስተዋጽኦ በተመለከተም ከፍ ብዬ በጠቀስኩት መጸሐፋቸው ገጽ 275 ላይ፤ መኢሶን በሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ ቤት መቋቋም ሰበብ ከደርግ ጋር ከተወዳጀበት ጊዜ አንስቶ ከሞላ ጎደል ለሁለት ዓመት ያህል ለአብዮቱ ሂደት መቃናት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን አውቃለሁ፡፡ ለምሣሌ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም እንዲወጣ፤ የአብዮቱ ወገኖች ነቅተው በየፈርጃቸው ተደራጅተውና ታጥቀው እንዲታገሉ፣ የኤርትራ ጉዳይ በውይይት መድረክ እንዲፈታ ጥረት ካደረገባቸው ብሔራዊና አብዮታዊ ጉዳዮች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ እንደነበሩ አስታውለሁ“  ብለው ነው የመሠከሩት፡፡ እንግዲህ እርስዎ እራስዎ እንዳሉት፤ በመረጃ አስደግፈን ከተወያየን፣ ስለ መኢሶን ያለው ሀቅ ይኸው ነው፡፡ ሌላው አሉባልታ ነው፡፡ በተረፈ በአብዮቱም ጎራ የተሰለፉትም ሆኑ ወይም ደግሞ በፀረ-አብዮቱ ፣ሁሉም አንድ ላይ ንስሀ ይግቡ፤ ለሰሩት ወንጀል ያሉት ፣ አንድ ገጠመኘን አስታወሰኝ፡፡ ገና ሁለተኛ ዲግሪዬን ይዤ፣ በ1967 ዓ.ም ከውጭ ሀገር እንደመጣሁ፣ ሥራ የተቀጠርኩት ፍትሕ ሚኒስቴር ውስጥ ነው፡፡ ጊዜው የፍየል ወጠጤ የሚዘፈንበት ወቅትም ነበር፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ ብቃት የላችሁም ተብለው ከዳኝነት የተባረሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ዳኞች ለውጡን ተገን አድርገው፣ “ያ አድሃሪ መንግሥት አላግባብ ከሥራችን አባረረን” ብለው በፕሬዜዳንቱ ቢሮ ለእንባ ጥበቃ ጽ/ቤት አቤቱታ ያቀርባሉ፡፡ እንባ ጥበቃ ጽ/ቤቱም አላግባብ ስለተባረሩ ወደ ሥራቸው መልሷቸው ብሎ፣ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ደብዳቤ ይጽፋል፡፡ ሚኒስትሩ በተራቸው፣ ችሎታ ስለሌላቸው ፈጽሞ አይመለሱም ብለው ለደርግ መልስ ይጻፍ ብለው ያዛሉ ፡፡ ጥያቄው አሁን ማን ደፍሮ ያችን ደብዳቤ ይጻፋት የሚለው ሆነ፡፡ አሁን ሁሉም ስለፈሩ፣ ቆይ ይኼ አዲሱ ልጅ አለ አይደለም ወይ ? ለምን እርሱን አናጽፈውም ይሉና፣ እኔ ደብዳቤውን እንድጽፍ ይታዘዛል፡፡ እኔም ዳኞቹ በምን ምክንያት እንደ ተባረሩ ስለማውቅ፣ የግል ማኅደራቸው ይቅረብልኝ እላለሁ፡፡ ቀርቦልኝ ስመለከተው ፈጽሞ የሕግ ዕውቀትም የሌላቸው መሆናቸውን እረዳለሁ፡፡
አንደኛው ከአምቦ የተባረሩት ዳኛ፣ላም በቂም በቀል ሆን ብላ አድብታ ሰው ወግታ ገላለች ተብላ በዐቃቢ ሕግ የወንጀለኛ ሕግ አንቀጽ 524 ተጠቅሶባት፣ ክስ ተመሥርቶባት ችሎት ስትመላለስ የነበረች ነች፡፡ ዝርዝሩ አስቂኝም ነው፣ ላሟም ታሳዝናለች፡፡ ሁለተኛው ዳኛ ደግሞ የአቶ አሰፋ ጫቦ ቢጤ ነበር፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ነው፡፡ አቶ ተካ ኢገኖ የሚባሉ ባለሀብት ነበሩ፤በጅማ መስመር ያለው የሜታ ቢራ አከፋፋይ እርሳቸው ስለነበሩ፣ አንድ ቀን መኪናቸው ጭኖ ወደ ጅማ ሲጓዝ፣ የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ሠራተኛ የሆነ፣ ሾፌሩን ከስፖንዳ በላይ ጭነሀል በማለት ወደ ከተማው ከመግባቱ በፊት መኪናውን ያስቆመዋል፡፡ ጊዜውም ጀምበር ያቆለቆለችበት ስለነበር መኪናው መንገድ ያድራል፡፡ በነገታው ባለሀብቱ ባመለከቱት መሠረት፤ የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ጉዳዩን ለማጣራት ይመጣሉ፡፡ መኪናውን ሲያዩት ከስፖንዳ በላይ አለመጫኑ ይታወቃል፡፡ የዚህን ጊዜ መኪናውን ያስቆመው ሠራተኛ ፣ ወደ ሦስት ኬሻ ከላዩ ላይ አስነስቷል፤ይኸንን ሲያደርግ ያዩ ሰዎች አሉ ይላል፡፡ በዚሁ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ስለተመራ፣ ምስክሮች እንዲሰሙ ዳኛው ያዛል፡፡ ሆኖም ግን ምስክሮቹ ለቀረበላቸው የመስቀለኛ ጥያቄ፣ አንዱ አውራጆቹ የለበሱት ልብስ ይህን ይመስላል ፣ ባርኔጣም አድርገው ነበር ሲል፤ሌላው ደግሞ ልብሳቸው ይህን ይመስል ነበር ፣ ፎጣም እራሳቸው ላይ ጠምጥመው ነበር እያሉ ስለወሻከቱ፣ ዳኛው ምስክሮችን በእስር ይቀጣና፣ የባለሥልጣኑን መሥሪያ
ቤት ሠራተኛ ደግሞ ያለአግባብ በማስቆምህ ኪሣራ ትከፍላለህ ይለዋል፡፡ ዞር ብሎ የከባድ መኪናውን ሾፌር ደግሞ አንተም ከስፖንዳ በላይ በመጫንህ ጥፋተኛ ነህ ብሎ ይወስንበታል፡፡ አሁንም ታዲያ አቶ አሰፋ ጫቦ፤ በ60ዎቹ ፖለቲከኞች ላይ ተመሳሳይ ውሳኔ ነው የሠጡት፡፡ ሠላም
ሁኑልኝ!!

Read 4234 times