Monday, 08 August 2016 09:19

ዛሬ ወደ ጠፈር ጉዞ

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(7 votes)

    ጠፈርተኞች፤ መኖሪያ ፕላኔታቸውን ‹‹ጠፈር ጣቢያ መሬት›› (Spaceship Earth) ይሏታል፡፡ ጠፈርተኞች የጠፈር ህይወት ስንት አደጋ እንዳለው ያውቃሉ፡፡ ከአደጋው የኮስሚክ ጨረራ ጠብቃ፤ አቅፋ ደግፋ ይዛ ለምታኖራቸው መንኮራኩር ከሚገመተው የበዛ ጊዜ እንክብካቤ ያደርጋሉ፡፡ ብልሽት እንዳያጋጥማት አስቀድሞ የመከላከል፣ የጥንቃቄ እና የጥገና ሥራ ይሰራሉ፡፡ አንዳንዶች፤ ‹‹እኛ ለዚህ የጠፈር ጣቢያችን ከምናደርገው እንክብካቤ እና ጥገና የሩቡን ያህል፤ ለዚች የሁላችን መኖሪያ ለሆነችው ለትልቋ የጠፈር ጣቢያችን (መሬት) አይደረግላትም›› ብለው ያዝናሉ። ሰው ሐገሩን ለቅቆ ሲሄድ የሐገር ትርጉሙ እንደሚሰማው መሰለኝ፤ የእነሱም ስሜት፡፡ ይህች ልዩ መኖሪያችን ከጠፈር ሆነው ሲያይዋት እጅግ ውብ እና የምታሳሳ ሆና ስለምትታይ ብቻ ሳይሆን፤ ልጆችዋን ከአደገኛ የህዋ ክስተት (ለምሳሌ፣ የኮስሚክ ጨረር) የሚከላከል ጋሻ ይዛ ዘወትር ለምትጠብቀን መሬት መሳሳት ተገቢ ነው። ዶሮ ጫጩቶቿን ከተናጣቂ አሞራ ለመጠበቅ በጉያዋ አድርጋ፤ በክንፏ እንደምትሰውር፤ መሬትም እኛን ሳይንቲስቶች ኦዞን በሚሉት የአትሞስፌር ንብብር ጋርዳ ጠብቃ ታኖረናለች፡፡ ይህች በቀላሉ ልትጎዳ የምትችል ሰማያዊ ፕላኔት፣ ብቸኛ
መጠለያ ቤታችን ከተጎዳች ወዴት እንገባለን የሚል ጭንቀት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ሁኔታ
ውስጥ ናቸው፡፡ ስለዚህ መጨነቅ ይገባቸዋል፡፡ ዛሬም በዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ነን፡፡ ዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ከመሬት 402 ኪሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የ17 ዓመታት ዕድሜ ያለው ጣቢያ ነው፡፡ የአሜሪካ እና የሶቪየት ሳይንቲስቶችን አንድ (ሰው) ያደረገ  የፍቅር ጣቢያ ነው፡፡ ባለፈው ግንቦት ወር ለአንድ መቶ ሺህ ጊዜ መሬትን መዞሩ ተነግሮ ነበር። እስካሁን 222 ሰዎች ጎብኝተውታል፡፡ በዚህ ጣቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመኖር የገቡት አሜሪካዊ አስትሮናውት ቢል ሽፐርድ (Bill Shepherd)፣ ሩሲያውያን ኮስሞናውቶቹ ሰርጌ
ክሪካሌቭ (Sergei Krikalev) እና ዩሪ ጊድዜንኮ (Yuri Gidzenko) በጠፈር ጣቢያው ለመኖር
የመጡት በ2000 ዓ.ም (እኤአ) ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ ጣቢያው ሰው አጥቶ አያውቅም፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያ በመጀመሪያ ሁለት ‹‹ሞጁሎች›› ብቻ ነበሩት፡፡ ‹‹ሞጁል›› (module) ጠፈርተኞቹ የሚሰሩባቸው ወይም የሚኖሩባቸው ቤቶች ሲሆኑ፤ እያንዳንዱ ‹‹ሞጁል›› ተለይቶ ለብቻ መሆን የሚችል አካል ነው፡፡ አሁን ‹‹ሞጁሎቹ›› 15 ደርሰዋል፡፡ በየጊዜው የሚላኩት ሞጁሎች ከነበረው አካል ጋር በመግጠም ጣቢያው እየሰፋ መጥቶ፤ አንድ የእግር ኳስ ሜዳ አክሏል፡፡ ጣቢያውም እስካሁን መቶ ቢሊየን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ሁለት ሞጁሎች የነበሩት የመጀመሪያው የጠፈር የጣቢያ ‹‹ዛርያ›› ይባል ነበር፡፡ በሩሲያ ቋንቋ ‹‹ወጋገን›› ማለት ነው፡፡ ‹‹ዛርያ›› ወደ ህዋ የተተኮሰው የዛሬ 17 ዓመት ኖቬምበር 20 1998 (እኤአ) ነበር፡፡ ይህ ጣቢያ ለ17 ዓመታት መቆየቱ፤ የሰው ልጅ በምህዋር ለመኖር የሚያስችል ጥበብ እንዳለው አረጋግጧል፡፡   
በጠፈር አዲስ ደራሽ እንግዳ ሰው በሙቀትና በቅዝቃዜ ሳቢያ ጣቢያው ቃቃ ሲል ሲሰማ፤ ልቡ ድው ድው ይልበታል፡፡ ጠፈርተኞቹ በገመድ ታስረው ያን አስጨናቂ የሚመስል የጠፈርተኛ ልብስ ለብሰው በመውጣት ጥገና ያደርጋሉ፡፡ ጠፈርተኞች በአብዛኛው ቀኑን ሙሉ እየሰሩ ይውላሉ፡፡ ሆኖም በአመሻሽ ወደ ቡና ቤት ጎራ ልበል ብዬ ልዝናና ማለት ባይችሉም፤ ሁሉም እንደየ ብጤቱ የሚወደውንና የሚያዝናናውን ነገር ያደርጋል፡፡ አመሻሽ አካባቢ፣ እንዲሁም ቅዳሜ እና እሁድ ይዝናናሉ፡፡ አንዳንዱ መጽሐፍ ያነባል ወይም ሙዚቃ ይጫወታል ወይም ፕራንክ ይሰራል፡፡ ቃቃ የሚል ድምጽ ሲሰሙ የሚደነግጡት እንግዶቹ ናቸው፡፡ አንዳንድ ፕራንኮች ግን ዓመት ለቆየው ጠፈርተኛም አስደንጋጭ ናቸው፡፡
በጠፈር ፕራንክ መስራት የተለመደም ነው፡፡ የጠፈርን ዝቅተኛ የስበት ሁኔታ (microgravity) በመጠቀም ፕራንክ መስራት ቀላል ነው፡፡  በጠፈር ጣቢያ አልጋ ወይም ወንበር የሚያስብል ኑሮ
የለም። መቆም ወይም መቀመጥ የሚባልም ነገር የለም። ስለዚህ ጠፈርተኞች በየትኛውም ሥፍራ በቀላሉ እንቅልፍ ሊወስዳቸው ይችላል፡፡ ታዲያ አንዱ ጠፈርተኛ በአንዱ ሞጁል ተኝቶ እንቅልፍ ከወሰደው በኋላ ጓደኞቹ መጥተው ወደ ሌላ ሞጁል እየገፉ ይወስዱታል፡፡ ከተኛበት ክፍል ወደ ሌላ መወሰዱን የማያውቀው ጠፈርተኛም ሲነቃ ይደናገጣል፡፡ እዚህ እንዴት መጣሁ በማለት ለተወሰነ ደቂቃ ግራ ይጋባል። እንዲህ ያሉ ፕራንኮችን ያደርጋሉ፡፡ እንዲህ ያሉት ፕራንኮች ገራገር ናቸው፡፡ ሌሎች እጅግ በጣም አስደንጋጭ ፕራንኮችም ይሰራሉ። በአንድ ወቅት ወደ ጠፈር የተላከ ጎሪላ ነበር። ይህን ጎሪላ በካርቶን ነገር ውስጥ አስተኙት፡፡ አንዱ ጠፈርተኛ በካርቶኑ ውስጥ ያስቀመጠው ነገር ወጥቶ ጎሪላው ገብቶ እንዲተኛ መደረጉን ሳያውቅ፤ ወደ አንድ የዕቃ ግምጃ ቤት የመሰለ ክፍል ውስጥ አስገብቶ፤ ከአንድ ቋሚ ብረት ጋር አስሮ፤
ዕቃው ተመልሶ መግባቱን የሚያረጋግጥ ምልክት በሰነድ ላይ አድርጎ ከሞጁሉ ሊወጣ ሲል፤ በዚያ
እንዲተኛ ያደረጉት ጎሪላ፤ ካርቶን መሳይ ነገሩን ብርግድ አድርጎ ወጥቶ አሳደደው፡፡ እንደ ውሃ ዋና
ባለ ስልት አባራሪ እና ተባራሪ ሆኑ፡፡ ጠፈርተኛው በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ እየሾለከ ነፍሱን ለማትረፍ
ተሯሯጠ፡፡ ተሯሯጠ ሳይሆን ተሳሳበ ማለት ይሻላል፡፡ ጠፈርተኛው አሳዘነኝ፡፡ በድንጋጤ ተርበደበደ፡፡
ጠፈርተኞች በጠፈር ጣቢያው ሲኖሩ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ሲፈልጉ፤ ቋሚ ነገሮችን ገፋ እያደረጉ
ነው፡፡ ታዲያ አንዳንድ ጊዜ የሚገፉት ነገር ሲያጡ ከአንድ ቦታ ድርቅ ብለው ለአምስት ወይም
አስር ደቂቃ  ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ አዲስ የመጣ ሞጁል ከጠፈር ጣቢያው ጋር በጥንቃቄ ከተያያዘ በኋላ ወደ ሞጁሉ ዕቃ እስከሚገባ ድረስ ባዶ ይሆናል፡፡ እንዲህ ያለ ባዶ ሞጁል ውስጥ የሚገባ ጠፈርተኛ ከአንድ ቦታ ድርቅ ብሎ የመቆም ወይም መንቀሳቀስ ያለመቻል ችግር ሊገጥመው ይችላል። ምክንያቱም ሞጁሉ ያለው ስፋት እጅ ወደ ጎን ተዘርግቶ ግድግዳ ለመንካት የሚያስችል
አይሆንም። በዚህ ጊዜ የሚገፉት ነገር ስለሚያጡ ለመንቀሳቀስ ይቸገራሉ፡፡ የአየር ሞገድ ተንቀሳቅሶ
በመጠኑ ገፋ እስኪያደርጋቸው ድረስ መንቀሳቀስ ይቸግራቸዋል። በተረፈ በዚያ ሲኖሩ ጫማ
አያስፈልጋቸውም፡፡ በዚያ ለሚኖር ሰው ምቹ የሆነው አለባበስ፤ ወፍራም ካልሲ፣ ቲሸርት እና ብዙ
ኪስ ወይም ለማሰሪያ የሚያገለግል ጥብጣብ የበዛበት ሱሪ መልበስ ነው፡፡ ጥብጣቡ ከአንድ ቦታ
ረግቶ ለመገኘት በፈለጉ ጊዜ አሰር ለማድረግ ይረዳቸዋል፡፡ ዛሬ እንኳን የለም፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ቅዳሜ ቅዳሜ በታላቅ ፊልም የቴሌቭዥን ዝግጅት እንዝናና ነበር፡፡ በጠፈር ጣቢያም ቅዳሜ ቅዳሜ ታላቅ ፊልም አለ፡፡ ታዲያ ጠፈርተኞች ፊልም ለማየትና ዘና ብሎ ለመቀመጥ ከወንበር መቀመጥ አያስፈልጋቸውም፡፡ እየተንሳፈፉ ፊልሙን መመልከት ይችላሉ፡፡ ግን ነገሩ በመሬት እንደለመዱት  እንዲሆንላቸው፤ ዘና ብሎ  መቀመጥ ወይም ጋደም እንዳሉ ማየት ሲያምራቸው፤ ከሱሪያቸው ባለው ጥብጣብ ራሳቸውን ከወለሉ ጋር ያስራሉ፡፡ ፊልሙን ጋደም ብለው ማየት ይችላሉ፡፡ ግን እዚህ እንደለመዱት ፖፕኮርን (popcorn ) መብላት
የለም፡፡ ፖፕኮርን በጠረፍ ጣቢያ አይፈቀድም፡፡ በእርግጥ እዛ ድረስ የሄዱ ጠፈርተኞች በሰማይ የሚመለከቱት ከዋክብት ብዛት እኛ በምድር ካለነው የበለጠ አይደለም፡፡ እዛም የሄደ ሰው በበለጠ ምቹ ሁኔታ ከዋክብትን ለማየት የሚችሉት seven- window cupola dome እያሉ ከሚጠሩት ክፍል ሲሆን ነው፡፡ ጨረቃ በማትታይበት ቀን፤ ፕላኔቶች፣ ከዋክብቱ፣ ውራውራው (aurora borealis) እንደ እንዝርት ይሾር በሚመስለው ፍኖተ ሐሊብ (Milky Way) ውስጥ ያሉ የከዋክብት ክምችቶች (galaxy) ከዋክብት በደንብ ይታያሉ፡፡
ሆኖም በአንዳንድ የምድር አካባቢዎች ካሉ ተራራዎች በመውጣት ከጠፈር ሆኖ ከሚመለከት
ጠፈርተኛ ጋር ተመሳሳይ የሆነ እይታ ማግኘት ይቻላል ይላሉ። ለእይታ እገዛ የሚያደርግ ምቹ አትሞስፌርን አናገኝም እንጂ በምድር ሆነንም በቁጥር ከእነሱ ያነሱ ከዋክብትን በመመልከት አንቆጭም፡፡
ብዙዎቻችን እንደምናስበው፤ ጠፈርተኛ መሆን ሁልጊዜ ወደ ጠፈር የመጓዝ ግዴታን አያመጣም፡፡ ጠፈርተኞች ወደ ህዋ የሚጓዙት በጣም አልፎ አልፎ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ለ15 ዓመታት
ጠፈርተኛ ሆኖ ቢሰራ ወደ ህዋ የሚጓዘው በአማካይ ሁለት ጊዜ ብቻ ይሆናል፡፡ጠፈርተኞች በጠፈር ሳሉ፤ ህልማቸው ምድራዊ ሊሆን ይችላል፡፡ ወደ መሬት ከተመለሱ በኋላም
የመሬት ስበት ኃይሉ እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ያልማሉ፡፡ በነገራችን ላይ በጠፈር
ጣቢያ ስበት የመሬት ስበት አለ፡፡  ነገር ግን የስበቱ ኃይል እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ በዩኒቨርሱ የሚኖር
እንቅስቃሴ ሁሉ ለስበት ኃይል የተገዛ ነው፡፡ እኛ መሬት ለቅቀን እንዳንሄድ ይዞ ከዚሁ ከምድር
የሚያቆየን ስበት ነው፡፡ ጨረቃ በመሬት፤ በመሬትም በፀሐይ ዙሪያ ምህዋራቸውን ጠብቀው
እንዲጓዙ ያደረጋቸው ስበት ነው፡፡ ሆኖም ብዙ ሰዎች በስህተት በህዋ ውስጥ ስበት የሌለ አድርገው
ያስባሉ፡፡ በህዋ ውስጥ ስበት አለ፡፡ ሰዎችን ይዘው ወደ ህዋ የሚሄዱ መንኮራኩሮች ከመሬት ከ193 ኪሜ እስከ 579 ኪሜ በሆነ ርቀት በመሆን፤ የራሳቸውን ምህዋር ይዘው ይሽከረከራሉ። በተጠቀሰው ርቀት የማይናቅ የስበት ኃይል አለ፡፡ ነገሩን በደንብ ካሰብነው፤ ይህ ርቀት በጨረቃ እና በመሬት መካከል ካለው ርቀት 1 ነጠብጥ 8 መቶኛ ርቀት ነው፡፡ ለምሣሌ፤ ከመሬት 402 ኪሜ ርቀት ላይ 88.8 መቶኛ የመሬት ስበት አለ፡፡
ስለዚህ ምህዋር ይዞ በመሬት ዙሪያ የሚሽከረከረው የጠፈር ጣቢያ ወይም መንኮራኩር፤ እንዲያ
መሽከርከር የቻለው የመሬት ስበት ስላለ ነው፡፡ የመሬት ስበት ባህርይ የታወቀው የዛሬ 300 ዓመት ገደማ ነው፡፡ የመሬት ስበት ነገርን የተረዳው ሰር አይዛክ ኒውተን ነው፡፡ ስበት (Gravity) በሁለት ግዝፈት ያላቸው ነገሮች መካከል ያለ የመሳሳብ ክስተት ነው፡፡ ሆኖም ይህ የመሳሳብ ነገር ለተመልካች ሊታይ የሚችለው በመሬት መጠን ግዙፍ የሆነ አካል ሲኖር ነው፡፡ መሬት ላይ ያለ ሰው ብርቱካን ከእጁ ቢሾልክ ወደ መሬት
ይወድቃል፡፡ በጠፈር ጣቢያ ያለ አንድ ጠፈርተኛም ከእጁ አንድ ሎሚ ቢሾልክ ይወድቃል። ግን
የሚወድቅ አይመስልም፡፡ የሚወድቅ የማይመስለው ሎሚውም፣ ጠፈርተኛውም፣ የጠፈር
ጣቢያውም አብረው ወደ መሬት እየወደቁ ስለሆነ ነው፡፡ ግን ወደ መሬት እየወደቁ ሳይሆን፤
በመሬት ዙሪያ እየወደቁ ነው፡፡ ሎሚውም፣ ጠፈርተኛውም፣ የጠፈር ጣቢያውም በተመሳሳይ
የፍጥነት መጠን አብረው እየወደቁ ስለሆነ፤ በጠፈር ጣቢያው ከጠፈርተኛው እጅ የሾለከው ሎሚ
‹‹ዜሮ ግራቪቲ›› እያልን በምንጠራው ሁኔታ እየተንሳፈፈ መስሎ ይታያል፡፡ በትክክል ለመናገር
‹‹በዜሮ ግራቪቲ›› ሳይሆን ‹‹በማይክሮ ግራቪቲ›› (1x10-6 g) መባል ያለበት፡፡  ‹‹በመሬት ዙሪያ እየወደቁ ነው ማለት ምን አማርኛ ነው?›› የሚል ነገረኛ ሰው ካለ፤ ኒውተን
የሚለውን ልነግረው እችላለሁ፡፡ ኒውተን በአዕምሮ ላብራቶሪ (ሐሳባዊ በሆነ ማሳያ) ነገሩን ለማብራራት ሞክሯል፡፡ አንድ መድፍ ከተራራ አናት ወስዳችሁ አስቀምጡ፡፡ ከዚያም ተኩሱ፡፡ የተተኳሹ ጥይት አረር ከተተኮሰ በኋላ ሄዶ ሄዶ ወደ መሬት ይወድቃል፡፡  የመድፉ ጉልበት የቱንም ያህል ኃይለኛ ቢሆን፤ አረሩ የሚጓዘው ርቀት ይጨምር ይሆናል እንጂ ዞሮ ዞሮ መውደቁ አይቀርም ነው፡፡ ስለዚህ የመድፉ አረር ወደ ፊት እየተጓዘ ሳለ ወደ መሬት እየወደቀ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ሆኖም ይህ አረር በመሬት ዙሪያ እየወደቀ አይደለም፡፡ ግን ወደፊት እየተጓዘ ሳለ ቀስ በቀስ ወደ መሬት እየወደቀ ነበር፡፡ የኒውተን ነገር ይገርማል፡፡
ይህ አይዛክ ኒውተን የነገረን ነገር ሳይታወቅ፤ በመንኮራኩር መጓዝ አይቻልም፡፡ ታዲያ የመድፍ ጥይት ከፍተኛ የሆነ አስፈላጊ ኃይል አግኝቶ በተተኮሰ ጊዜ፤ የፊዚክስ ጠቢባን state of continuous free-fall ከሚሉት ሁኔታ ውስጥ ይገባል፡፡ ወደ መሬት እየወደቁ መዞር የሚመጣው አሁን ነው። ምህዋር ማለት በስበቱ ኃይል ወደ ያዘን ግዙፍ አካል እየወደቅን፤ በአንድ ጎዳና ያለማቋረጥ መጓዝ ነው። ስለዚህ በአንድ መንኮራኩር ያለ አንድ ዕቃ የሚንሳፈፍ ወይም የማይንቀሳቀስ መስሎ ቢታየንም ዕቃውን የያዘው መንኮራኩር በሰዓት ሃያ ስምንት ሺህ (28.000) ኪሜ  እየተጓዘ ነው፡፡ በአንድ ሰዓት ውስጥ ከአዲስ አበባ ሽራሮ 28 ጊዜ መመላለስ በሚያስችል ፍጥነት እየተጓዘ ነው፡፡ጠፈርተኞች ወደ ጠፈር ጣቢያ የሚሄዱት ለከንቱ ገድል አይደለም፡፡ በዚያ ሆነው የሚሰሩት ሥራ በመሬት ለሚኖሩ ሰዎች የማይጠቅም ነው፡፡ በጠፈር ጣቢያ የሚከናወን የምርምር ሥራ ሁሉንም የሳይንስ መስኮች የሚያግዝ ውጤት ይኖረዋል ይላሉ ጠፈርተኞቹ፡፡ በጠፈር ጣቢያ የምናደርገው ምርምር በመሬት የሚኖሩ ሰዎችን የተለያዩ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ዕውቀት የሚገኝበት ነው፡፡ ለምሣሌ፤ በጠፈር የሚኖሩ ተመራማሪዎች የአጥንት መሳሳት (bone loss) ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ ይህ ችግር በመሬት ያሉ አንዳንድ ሰዎች የሚገጥማቸው ችግር ነው፡፡ እናም በጠፈር ጣቢያ በአጥንት መሳሳት ችግር ዙሪያ የሚካሄደው ምርምር በዚህ ችግር ለተጠቁ ሰዎች ፈውስ የሚሰጥ ምርምር ነው፡፡ ታዲያ ጠፈርተኞች ከሚገጥማቸው የአጥንት መሳሳት ችግር ለመጠበቅ ከባድ የአካል እንቅስቃሴ ወይም ስፖርት ይሰራሉ፡፡ በጠፈር ጣቢያ የስፖርት መስሪያ ክፍሎች፤ 42 ኪሜ የሚሮጡ ጠፈርተኞች አለ፡፡

Read 4929 times