Monday, 15 August 2016 08:53

ለፖለቲካዊ ችግሮቻችን ፖለቲካዊ ውይይት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

መንግስት፤ የኃይል እርምጃውን አቁሞ ህዝቡን ማወያየት አለበት
ኢህአዴግ የሚነሱ ቅራኔዎችን የመፍታት አቅሙ ተዳክሟል
በግርግር የሚቀየር መንግስት ለዚህች አገር አይበጅም
አመራር ደናሽ ሳይሆን ሁሉንም አስደናሽ ነው መሆን ያለበት

በአገራችን የተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት እንጂ እየተሻሻለ አልመጣም፡፡ ውጥረቱ እያየለ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት አርብ በጎንደር፣ ቅዳሜ በከፊል በአዲስ አበባና በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች፣ እሁድ ደግሞ በባህር ዳር ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ የተደረገ ሲሆን ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭት በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል። ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎችም ቆስለዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና ነዋሪዎችን ጠቅሶ ባወጣው መግለጫ፤ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በሁለቱ ቀናት ብቻ ወደ 100 የሚደርሱ ዜጎች ሞተዋል፡፡ በርካቶችም ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ይሄ አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡
ህዝብ መብቱን ለመጠየቅ አደባባይ መውጣቱ ህገ-መንግስታዊ መብቱ መሆኑን አስረግጠው የሚናገሩ አንዳንድ ፖለቲከኞችና ምሁራን፤ መንግስት በሰልፈኞች ላይ መሳሪያ መተኮሱንና የበርካቶች ህይወት መጥፋቱን አጥብቀው እንደሚቃወሙ ገልጸዋል፡፡ ህዝቡም ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ፍጥጫ ውስጥ ሳይገባ የመብት ጥያቄዎቹን ማቅረብ እንዳለበት መክረዋል። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ሰሞኑን ያነጋገራቸው ፖለቲከኞችና ምሁራን፤ ህዝቡን ለተቃውሞ ያስነሳው ምንድነው? ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ከመንግስት ምን ይጠበቃል? የአገሪቱ ምሁራን ሚና ምን መሆን አለበት? በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት እንደገለጽነው፤ የዚህ ውይይት ዓላማ፣ በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮች ዙሪያ ሃሳቦችን በማንሸራሸር መፍትሄ ማፈላለግና መጠቆም ነው፡፡ በአገራችን ለተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ መፍትሄ የሚሆን ሃሳብ ወይም አስተያየት ላላቸው ወገኖች ሁሉ  መድረኩ ክፍት ነው፡፡

“የህዝቡ ነፃነት መከበር አለበት”
ወገናዊና የዝምድና አሰራር መስፈኑ የችግሮች ሁሉ መነሻ ነው

ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ
(አንጋፋ ታጋይና የአረና አመራር)
የሀገሪቱ ሁኔታ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ህዝብ ተቃውሞ፣ ግፊትና የተለያዩ ጥያቄዎችን እያቀረበ ነው፡፡ በእርግጥ እንቅስቃሴው ከዚህ በፊት ተደጋግመው ሲነገሩ ከነበሩ ችግሮች ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ፍትህ ማጣት፣ የዲሞክራሲ አለመኖር፣ የነፃነት እጦት፣ የመናገር ነፃነት መጥፋት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር ወዘተ --- ከመሻሻል ይልቅ መባባሱ፤ እንዲሁም ሙስና እየሰፋ መምጣቱ፣ ወገናዊና የዝምድና አሰራር መስፈኑ የችግሮች ሁሉ መነሻ ነው፡፡ ሰው መናገር አይችልም፤ አፈና አለ፡፡
ኢህአዴግ ራሱ በጉባኤው ላይ እነዚህን ችግሮች በማንሳት፣ እንደሚፈታቸው ቃል ገብቶ ነበር፤  በተግባር ግን አልታየም፡፡ ህዝቡ ችግሩ ሲብስበት ነው ብሶቱን ሊያወጣ የተገደደው፡፡ በየ5 ዓመቱ የሚደረገው ምርጫ ራሱ የተጭበረበረ ነው። በመንግስት ሚዲያ፤ ልማት፣ ዲሞክራሲ--- ይዘመራሉ፤ በተግባር ግን የሉም፡፡ ይሄ የህዝብ እሮሮ የፈጠረውን እንቅስቃሴ ነው አሁን ሀገሪቱ በማስተናገድ ላይ ያለችው፡፡ ይሄን ችግር የበለጠ ለማባባስና በአጋጣሚው የራሱን አላማ ሊያራምድ የሚፈልግም ኃይል ሊኖር ይችላል፡፡ ግን ተጠያቂው ያ ኃይል ሳይሆን፣ የችግሮቹ ሁሉ መነሻ የሆነው መንግስት ነው፡፡ ኢህአዴግ ለዚህ ተጠያቂ ነው። የተከሰተውን ችግር  እንዴት ነው እየፈታሁ ያለሁት?” ብሎ ራሱን መፈተሽና መጠየቅ ይገባዋል፡፡
 የህዝቡ ነፃነት መከበር አለበት፡፡ ህገ መንግስቱም እየተጣሰ ነው ያለው፡፡ እነዚህ ሁሉ ካልቆሙ ሀገሪቱ ወዳልሆነ አቅጣጫ ነው የምትጓዘው፡፡ ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀስ፣ ያለ ሁከት መብቱን እንዲጠይቅ ማድረግ ይገባል፡፡ ለሰላማዊ ሰልፍ ሲወጣ፣ ጥይትና ወታደር የሚላክበት ከሆነ ግን በእሳት ላይ ቤንዚን እንደማርከፍከፍ ነው፡፡ ይሄ ትክክለኛ አካሄድ አይደለም፡፡
የሰላማዊ ሰልፍ ፍቃድ የሚባለው፣ ሌላው ብዥታን የፈጠረ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ በህገ መንግስቱ የማውቀው፤ “ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማሳወቅ በቂ ነው” የሚለውን ነው፡፡ ከመንግስት መልስም መጠበቅ አያስፈልግም፡፡ መንግስት ግን ማሳወቅ የሚለውን በሌላ ተርጉሞ፣ “ፍቃድ ካልተሰጣችሁ መውጣት አትችሉም” እያለ ነው፡፡
ሁለተኛ ደግሞ ህዝቡ፤ ማሳወቅ በቂ ነው፣ በህገ መንግስቱ የተከበረ መብት አለን ብሎ ሰልፍ ሲወጣ፣ “ህጋዊ ሰልፍ አይደለም” በሚል የሚተኮስበት ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ መንግስት ይሄን ማቆም አለበት፤ ህዝቡም ከወታደር ጋር መጋፋጥ የለበትም፡፡ የኃይል እርምጃውን አቁሞ፣ ህዝቡን ማወያየት የመንግስት ሃላፊነት ነው፡፡  አሁን ለሚታዩት ችግሮች የመጀመሪያው መፍትሄ፣ ለህዝቡ ነፃነቱን መስጠት ነው፡፡ ይመለከታቸዋል የሚባሉ ኃይሎች በሙሉ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው የሀገሪቱን ሁኔታ መገምገም አለባቸው፡፡ ይሄ ከተደረገ በኋላ መፍትሄው ላይ የኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን  የሚመለከታቸው ኃይሎችም የመፍትሄ ሀሳብ ተቀባይነት ማግኘት አለበት፡፡
ዘላቂ መፍትሄ የሚገኘው በሽግግር መንግስት ነው ወይስ በሌላ አግባብ? የሚለውም በዚሁ ውይይት ላይ  ውሳኔ ሊያገኝ ይችላል፡፡ አሁን ግን መቅደም ያለበት ውይይት ነው፡፡ በሀገሪቱ የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ላይ ሁሉም ወገን ያገባዋልና መንግስት ይሄን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ውይይት ለማካሄድ ዝግጁ መሆን አለበት፡፡
በሌላ በኩል በተቃውሞ መሃል የሚታዩት የዘረኝነት እንቅስቃሴዎች በጣም አደገኛ ናቸው። መንግስትም በዚህ ረገድ ተጠያቂ ነው፡፡ ሀገሪቱ በዘረኝነት ስሜት ከተተራመሰች፣ በጣም የከፋ  ሁኔታ ውስጥ ነው የምትገባው፡፡ ሁላችንም ዘረኝነትን አጥብቀን መዋጋት አለብን፡፡ መንግስት የህዝብን የመብት  ጥያቄ የጥቂቶች ማድረጉም ትክክል አይደለም፤ የብዙኃን ጥያቄ ነው፡፡
====================================
‹‹ሠልፍ ድንጋይም ማስወርወር፤ ጥይትም ማስተኮስ የለበትም››

አንዱ ለመኖር አንዱ መጥፋት አለበት የሚለው አመለካከት ለምን ተፈጠረ?

ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሠ

ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሠ
በአጠቃላይ ተደማምጦ ተነጋግሮ፣ ችግሮችን የመፍታት ባህላችን ለምን አልዳበረም? በእኔ እድሜ እንኳ ሠልፍ ሁሌም የውዝግብ መነሻ ሲሆን ነው የማውቀው፡፡
ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ እስካሁን ሠልፍ ለዚህች ሃገር ትልቅ አወዛጋቢ ጉዳይ ነው። ይህ ለምን ይሆናል? እንደ እኔ እምነት፤ አንዳችን ለአንዳችን መስተዋት መሆን ይገባናል፡፡ አሁን ግን ያንን ማምጣት አልቻልንም፡፡
አንዱ ለመኖር አንዱ መጥፋት አለበት የሚለው አመለካከት ለምን ተፈጠረ? ፖለቲካን ተቻችለን ለመከወን መቸገራችን በጣም ያሳስበኛል፡፡ ከድሮው አዙሪት አሁንም አልወጣንም፡፡ በንጉሱ ዘመን፤ “ሰልፍ ውጣ አልወጣም” ነበረ፡፡ ዛሬም ያው ነው፡፡
ተጨዋቹ ቢቀየርም ጨዋታው አልተቀየረም፡፡ ሠልፍ በባህሪው ድንጋይም ማስወርወር፤ጥይትም ማስተኮስ የለበትም፡፡ ወደ መንግስት ስንመጣ ደግሞ የማድመጥ ባህል አለመኖር አንዱ ችግር ነው፡፡ የማድመጥ ብቻ ሳይሆን ሰው መደመጡን እንዲያውቅ አለማድረግም ሌላው ችግር ነው፡፡
ህዝብ እንደተደመጠ ማወቅ አለበት፤ አመራር ማድመጥን ይጠይቃል፡፡ የተደመጠ ሁሉ ተቀባይነት አለው ባይባልም፣ ሰው እንደተደመጠ ማወቅ አለበት፡፡ በሣል አመራር ማለት ይሄ ነው። ለኔ አመራርነት ጥሩ መደነስ አይደለም፤ ሁሉም ህዝብ እንዲደንስ ጥሩ ሙዚቃ ማጫወት ነው። አመራር ደናሽ ሳይሆን ሁሉንም አስደናሽ ነው መሆን ያለበት፡፡


===================================
“ጥይት የምንም ነገር መፍትሄ ሆኖ አያውቅም”

አቶ ሙሼ ሰሙ

“በሀገሪቱ የሚታየው ችግር መነሻ ምንድን ነው?” የሚለውን ከማየታችን በፊት አንድ ሀገር እንደ ሀገር፣ ሞትና እልቂት ሲደግስና አገር ወደ መፍረስ እየተገፋ መሆኑ ሲታይ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ በቅጡ ቁጭ ብሎ አለማሰብ በጣም አስደንጋጭ ነገር ነው፡፡ ከተሞች አካባቢ የሚታየው ዝምተኛነቱና ቸልተኛነቱ አሳሳቢ ነው፡፡ ይሄ ነገር ቀጥሎ የት ሊደርስ እንደሚችል  ማንም አዕምሮ ያለው ሰው መገመት አያቅተውም፡፡  
እነዚህ ግጭቶችና ተቃውሞዎች በኦሮሚያም በአማራም ክልሎች ሲቀሰቀሱ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል አመላካችና ጠቋሚ ነገሮች ያሳዩ ነበር። ማንኛውም ህዝባዊ ቁጣና አመፅ አመጣጡ የራሱ ዳራ አለው፡፡ መጀመሪያ ቁጣዎች ይረገዛሉ፣ ቀጥሎ ይወለዳሉ፣ ከዚያ ያድጋሉ፤ በመጨረሻ ይዳፈናሉ፤ እንደገናም ያገረሻሉ፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነገር ስንመለከተው፤ የወልቃይት ወይም የአንድ ቀበሌ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ለዘመናት ሲከማች የመጣ ችግር ውጤት ነው። ኢህአዴግ ሀገሪቱን  ሲረከብ ብዙ ተስፋ ሰጥቶ ነበር፡፡ ህይወታችን ይሻሻላል፣ ይለወጣል፣ ሀገሪቱም ወደተሻለ  ሰላም ትመጣለች ብለው ያሰቡ ነበሩ። በሌላ በኩል፤ ይሄንን ጉዳይ ከመጀመሪያውኑ ያልተቀበሉ ኃይሎችም ነበሩ፡፡ ይሄን የህዝቡን ተስፋ እውን ለማድረግ ጅምሩ ዲሞክራሲ የበለጠ እየሰፋ መምጣት ሲገባው፣ ህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩ አንቀፆች በመመሪያና በደንብ እንዲሁም በፖሊሲ እየተቆራረጡ፣ አሁን ላይ ፈፅሞ የማያፈናፍን ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ሃብቶች፣ የንብረት ባለቤትነትን  ማረጋገጥ ሳይቻል መብቶቹ በሙሉ እየተሸረሸሩ መጥተው፣ አሁን ፈፅሞ አሉ ለማለት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡
የማህበረሰቡ እስትንፋስ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሙያ ማህበሮች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሚዲያዎች በሙሉ አሉ በማይባልበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ ሀገሪቱ በየ10 ዓመቱ የሚያጋጥማት አዲስ ትውልድ አለ፡፡ ይህ ትውልድ ስራ ፈላጊ ሆኖ ነው የሚመጣው፡፡ እነዚህ ስራ ፈላጊ ወጣቶች ደግሞ ከት/ቤት እንደወጡ የመጀመሪያውን አመት ስራ ባያገኙም በትዕግስት ሊያልፉ ይችላሉ፤ ነገር ግን ከዚያ በላይ ሊታገሱ አይችሉም፡፡ በየ10  ዓመቱ በብዙ ቁጥር ወደ ስራ ፈላጊነት የሚመጣው ኃይል በቂ እድል ተፈጥሮለት ህይወቱን በቅጡ መምራት የማይችል ከሆነ፣ የቁጣው ባለቤት የሚሆነው እሱ ነው፡፡ አሁን ያለው እንቅስቃሴ በአብዛኛው በወጣቱና በወጣቱ ዙሪያ የተሰባሰበ መሆኑ ለዚህ አስረጅ ነው፡፡
ይሄ ኢኮኖሚያዊ ችግር ሌላም ጣጣ አለው። ተመጣጣኝ የሆነ የሀብት ክፍፍል አለመፈጠሩ ሌላው ጥያቄ ነው፡፡ መንግስት ይህን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ፍላጎት አሳይቶ አያውቅም፡፡ ጥቂቶች በሚሊዮን ብሮች የሚቆጠሩ ሀብቶችን በድንገት ሲያፈሩ ይታያል፡፡ በተቃራኒው የሚላስ የሚቀመስ አጥተው፣ ከህይወት ጋር ግብ ግብ የሚገጥሙ አሉ። ይሄም በማህበረሰቡ ውስጥ የራሱን ቁጣና ንዴት ፈጥሯል፡፡ በሀገሪቱ የሚፈጠረው ከፍተኛ የሆነ ሀብትም ዝቅተኛ የሆነው ማህበረሰብ ሊጠቀምበት የሚችልበት ሁኔታ አልተመቻቸም፤አየር ላይ ተንጠልጥሎ የቀረ ሀብት ነው፡፡ ይሄን ሀብት መጠቀም ያልቻለ ማህበረሰብ ጥያቄ ቢያነሳ የሚደንቅ አይደለም፡፡
በሌላ በኩል ከህዝብ ጥያቄ ሲነሳ ከመንግስት በኩል የሚቀርቡ መልሶች፣ የስልጣን ባለቤት ማን ነው? የሚል ጥያቄን የሚያጭሩ ናቸው፡፡ የስልጣን ባለቤት ህዝብ መሆኑ እየታወቀ፣ “ታግሰናል፣ ዝም ብለናል፣ ችለናችኋል” የሚሉ መልሶች ናቸው ከመንግስት የሚሰጡት፡፡ ይሄ የስልጣን ባለቤቱ ማን ነው? የሚለውን ጥያቄ ለማስነሳት በቂ ነው። ሰው ጥያቄ ሲያነሳ ተገቢውን መልስ ማግኘት አለበት። ጠብቅ ወይም ታገስ የሚል መልስ መሰጠት የለበትም፡፡
ሰው እየጠየቀ ያለው መሰረታዊ የህይወት ጥያቄ እንጂ ተጨማሪ ነገር አይደለም፡፡ ልጆቹን የማስተማር፣ የመመገብ ጥያቄ ሲያነሳ ታገስ መባል የለበትም፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ነው ዛሬ ላይ ጥያቄ ሆነው የቀረቡት፡፡
አንድ ህዝባዊ ቁጣና አመፅ በሂደት የራሱን የተለያዩ ተደማሪ ውጤቶች ይዞ ነው የሚመጣው።  አሁን እየተፈጠረ ያለው ቁጣ፣ በአንድ የወልቃይት ወይም የኦሮሚያ መሬት ጉዳይ ነው ማለት አልችልም። በመታመቅ፣ በመጨፍለቅ የመጣ ነው ጥያቄው፡፡ በባህርዳር ለተካሄደው ተቃውሞ የወልቃይት ጉዳይ መነሻ ይሁን እንጂ ጥያቄው የዘመናት ብሶቶች የተንፀባረቁበት ነው፡፡
አሁን ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስራ አጥ ወጣት መብቱን ለማስከበር ጥያቄ እያነሳ ነው፡፡ ሁለተኛ ቀላል የማይባል ህብረተሰብ ለዘመናት ሲያነሳቸው የነበሩ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች መልስ አላገኙም። እነዚህ ተደማምረው ነው ማህበረሰባዊ ቀውስ እየፈጠሩ ያሉት፡፡
ወጣቱ በዱቤ ተምሮ፣ እዳ በአናቱ ተሸክሞ ስራ የለውም፡፡ ግጭቶቹ የተፈጠሩባቸው ሁለቱ አካባቢዎች፣ ከሀገሪቱ ከፍተኛውን የማህበረሰብ ቁጥር የሚይዙ ናቸው፡፡ በዚያው ልክ ነው የስራ አጥ ቁጥራቸውም፡፡ በቱኒዚያ አመፅ የለኮሰው የቡአዚዝ መቃጠል ሆነ እንጂ ዋና ጥያቄው የሱ መሞት አልነበረም፤ከጀርባ ብዙ ጥያቄ ነበረ፡፡
ህዝብ መብቱን ለመጠየቅ አደባባይ ሲወጣ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችና ውጤታቸውን በተመለከተ አንደኛ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማስፈቀድ የሚባል ነገር ከ1980ዎቹ ጀምሮ ሲያወዛግብ የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ህዝብ መብቱን ለማስከበርና ጥያቄ ለማቅረብ ፍቃድ አያስፈልገውም፡፡  ማሳወቅ ነው ያለበት፡፡ እሱም ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጣው ህብረተሰብ ጉዳት እንዳይደርስበት የመንግስት ጥበቃ ለማግኘት ነው፡፡
መብቴ ተነክቷል ያለ ህዝብ፣ ፍቃድ እንዴት ይጠይቃል? ለህዝብ ፍቃድ ሰጪ ማን ነው? አሁን እኮ ሰላማዊ ሰልፍ እየወጡ ያሉት ቡድኖች  አይደሉም፤ ህዝብ ነው፡፡ ቡድን ቢሆን የፍቃድ ጥያቄ ሊመጣ ይችላል፡፡
የስልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ ግን እንዴት ፍቃድ አልጠየክም ሊባል ይችላል? ሌላው “ጥቂት” እየተባለ የሚገለፀው ጉዳይ ግራ አጋቢ ነው፡፡ ጥቂት ሲባል ስንት ነው? 500 ሺህ ህዝብ ጥቂት ነው? 100 ሺህ ህዝብ ጥቂት ነው? ስንት ሲሆን ነው ለኢህአዴግ ብዙ የሚሆንለት? እኛ እያየናቸው ያሉት ሰልፎች በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች የሚካሄዱ ናቸው።  ያውም ሰላማዊ ሰልፉ እውቅና የለውም ስለተባለ፣ ፈርቶ የቀረ፣ በልቡ ግን ሰልፉ ጋ ያለ ህዝብ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ጥቂት ማለት 1,2,3 ተብሎ የሚቆጠር ነው፤ እያየን ያለነው ሰልፍ እኮ ለቁጥር በሚታክት ህዝብ የሚካሄድ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ መሬት ላይ ያለውን እውነታ መካድ ነው። ደርግ መፈንቅለ መንግስቱ ሲሞከርበት፤ “ጥቂት ጀነራሎች” ነበር ያለው፡፡  ኢህአዴግ “ጥቂት” ይባል ነበር፤ ሻዕቢያ “ጥቂት” ይባል ነበር፡፡ ደርግ እነዚህን ሁሉ፣ እድሜ ልኩን “ጥቂት” እንዳለ ከስልጣን ተዋርዶ ወርዷል፡፡ ይሄ አሁንም እየተደገመ ነው፡፡
ኢህአዴግ ድርጅታዊ ስፋቱ ቢጨምርም ከጊዜ ወደ ጊዜ በሀገሪቱ የሚነሱ ቅራኔዎችን የመፍታት አቅሙ ተዳክሟል፡፡ እንዴት ነው ህዝብ ላይ ለመተኮስ በማለም፣ “እስከ ዛሬ ታግሻለሁ” የሚባለው? ጥይት የምንም ነገር መፍትሄ ሆኖ አያውቅም፡፡ የችግሮች ሁሉ መፍትሄ ውይይት ነው፡፡ ኢህአዴግ ቅራኔዎችን የመፍታት አቅሙ ስለተሸረሸረ ነው  የመጨረሻ አማራጭ እየወሰደ ያለው፡፡ ሆኖም ቅራኔዎችን በዚህ መንገድ መፍታት አይቻልም፡፡
መፍትሄ የሚመስለኝ ጥያቄዎችን ለመፍታት የሚያስችሉ መድረኮችን በብዛት ማዘጋጀት ነው። ጥያቄዎቹ ከስልጣን እስከ ማውረድና ምርጫ በድጋሚ እስከመጠየቅ ሊገፉ እንደሚችሉ በማሰብ፣ መንግስት የአዕምሮ ዝግጅት በማድረግ ወደ ውይይት ለመግባት መወሰን አለበት፡፡ ጥቂት የኢህአዴግ አባላትንና የስርአቱ ተጠቃሚዎችን ብቻ በአንድ አዳራሽ ውስጥ ሰብስቦ፣ አጨብጭቦና አውግዞ መለያየት፣ መሬት ላይ ያለውን ችግር አይፈታውም። ኢህአዴግ ለጊዜው ስልጣኑን ማሠብ አቁሞ፣ እንደ ማንኛውም ፓርቲ ሆኖ ነው ለውይይት መቀመጥ ያለበት፡፡
የራሱ አባላትና ደጋፊዎች ራሣቸው ጠያቂ፣ አውጋዥና ፈራጅ ሆነው የሚለያዩበት ስብሰባ፣ የበለጠ ችግሮቹን ያባብሳል እንጂ መፍትሄ አይሆንም። ሊፈጠሩ የሚገባቸው የውይይት መድረኮች ጥናት ተደርጎባቸውና እስከ ምን ድረስ ሊሄዱ እንደሚችሉ ታስቦባቸው መዘጋጀት አለባቸው፡፡ መድረኮቹ በውጭም ሆነ በሃገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችን በሙሉ ማሳተፍ ይኖርበታል፡፡   
ከዚህ መፍትሄ በመለስ ሚዲያዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መያዶች፣ ማህበራትና ተቋማት-- ነፃነታቸው በማያሻማ ሁኔታ ግልፅ ሆኖ መቀመጥ አለበት፡፡ ይሄ ወደሚቀጥለው የምርጫ ትግል ወስዶን፣ በትክክለኛ ምርጫ ያሸነፈ ሃገር ይመራል። ኢህአዴግ እንደ ወትሮው “መንገድ ሰርቻለሁ፣ አባይን ገድቤያለሁ፣ ስለዚህ ጥያቄ ሊነሣ አይችልም” ከሚለው ስሜቱ መውጣት አለበት። አሁን እየተጠየቀ ያለው፣ “አልሰራህም” ሳይሆን “ሁላችንንም ተጠቃሚ አላደረክም” ነው። ስለዚህ፤ “እስኪ ሁላችንም ከዚህች ሃገር ተጠቃሚ እንሁን” ነው፤ ጥያቄው፡፡
በመጨረሻም በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልል በተከሰቱ ግጭቶች የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ በዚህ ሁላችንም አዝነናል፡፡ ፈጽሞ መሆን የሌለበት ነው፡፡

==============================

“ከህዝብ ጋር እውነተኛ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል”

ዶ/ር አለማየሁ አረዳ

  በመጀመሪያ እንደ አንድ ዜጋ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እየተከሰቱ ባሉ ነገሮች በጣም ነው የማዝነው፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች ለመቆጣጠር የሚረዳ ዘዴ ጠፍቶ ነው ወይ፣ የሰው ህይወት እስኪጠፋ የደረስነው የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ጉዳቱ ለደረሰባቸው በሙሉ ሃዘኔን እገልፃለሁ፤ በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡
ወደ ችግሮቹ ስንመጣ፣ በተለያዩ ወቅቶች መንግስት ራሱ የመልካም አስተዳደር ጉድለት አለብኝ እያለ በየሚዲያው ሲናገር ሰምተናል። በየስብሰባ አዳራሹ ይሄንኑ ደጋግሞ ይናገራል፡፡  የመጀመሪያው ችግር፤ ሁለትና ሶስት ሰዎች ሙስና ስለፈፀሙ መልካም አስተዳደር የሚጎድል፣ እነዚህ ሰዎች ሙስናን ከተዉ ደግሞ መልካም አስተዳደር የሚሰፍን ተደርጎ መወሰዱ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር በዲሞክራሲያዊ ስርአት ውስጥ ነው ሊፈጠር የሚችለው፡፡ ስለዚህ ስርአቱ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን እያስተናገደ ያለበት ሁኔታ ላይ ይመስለኛል ችግሩ ያለው፡፡ ህብረተሰቡ ከየአቅጣጫው የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ቁልጭ ብለው የተቀመጡ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በኦሮሚያ የተነሳው ጥያቄ፣ አዲስ አበባ ለኦሮሚያ የምትሰጠው ጥቅም በደንብ በህግ ተደንግጎ አለመውጣቱ የመሳሰሉት በውይይት መፈታት የነበረባቸው ናቸው። ግን የተያዘበት መንገድ ይመስለኛል የቅራኔው መነሻ፡፡ የህዝብ ጥያቄ ሁልጊዜ መነሻው የተቃዋሚ ፓርቲ ቅስቀሳ አይደለም፡፡ መነሻው ህዝቡ በስርአቱ ላይ ያለው እምነትና ተስፋ ነው። ይሄን ከማስተካከል ይልቅ ተቃዋሚና ሻዕቢያን ሰበብ ማድረግ የሚያዋጣ አይደለም፡፡ ህዝብ  በሰው ቅስቀሳ ህይወቱን አሳልፎ አይሰጥም፡፡
ሌላው ጥያቄዎች ሲፈጠሩና ሰዎች ወደ አደባባይ ሲወጡ፣ መደናገጥና ህይወትን የሚያጠፋ እርምጃ መውሰድ ተገቢ አይደለም፡፡
መንግስት፤ የቀድሞ ሥርዓቶች የፈጸሙትን ስህተቶች ላለመድገም መጣር አለበት፡፡ የህዝብ ስሜት በጥቂት ሰውም ሆነ በብዙ ሰው ሊገለፅ ይችላል፡፡
መንግስት ማተኮር ያለበት ምን መሰረታዊ እውነትነት አለው የሚለው ላይ ነው፡፡ ጥያቄው በኤርትራ ተላላኪም ሆነ በሌላው ይቀስቀስ የህዝብ እስከሆነ ድረስ መንግስት ጥያቄውን ፈትሾ፣ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ የተነሳውን ጥያቄ በአግባቡ ካላስተናገደ፣ የትኛውም ኃይል ክፍተቱን ሊጠቀምበት እንደሚችል መገንዘብ አለበት። ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት፤ “ጥቂት ወንበዴዎች”፣ “ሀገር በታኞች” ወዘተ---ሲባሉ የነበሩ ቡድኖች የፈጠሩት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ “ጥቂት” እያሉ ነገሮችን ማንኳሰስ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ የተነሳው ጥያቄ ላይ እንጂ ያነሳው ሰው ቁጥር ላይ ትኩረት ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡
ሰላማዊ ሰልፉን ደግሞ “ካልጠየከኝና ካልፈቀድኩልህ አትሰለፍም፤ ባልፈቀድኩልህ ሰልፍ ላይ ከወጣህ ለሚደርሰው ጥፋት ተጠያቂው አንተ ነህ” እንዴት ይባላል? ይሄ ከመንግስት የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ተጠይቀው እኮ አልፈቀዱም፡፡ ፍቃድ ተጠይቀው የማይሰጡ ከሆነ፣ ፍቃድ ሳይጠየቅ ሲወጣም ዋጋ የሚያስከፍል ከሆነ ግራ ያጋባል። ደርግን እኮ “ፈጣሪ ያንሳህ!” ብሎ ረግሞት የተቀመጠው፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ያቃተው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ ህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጣ ለመንግስት ትልቅ ምልክት ነው፡፡ የህዝብን ብሶትና ጥያቄ የሚሰማበት እድል ነው፡፡ በዚህ እድል ውስጥ ለምን የሰው ህይወት ይቀጠፋል? “ኃይል አለኝና እንዳመጣጥህ እመልስሃለሁ” የሚለው አካሄድ ለመንግስት ፈፅሞ አይሰራም፡፡ ራሱን ማረም አለበት፡፡
መንግስት በችግሩ ለደረሰው ጉዳት ሙሉ እውቅና መስጠት ይገባዋል፡፡ በመቀጠል ከህዝብ ጋር የሚነጋገርበትን ድልድዮች በአስቸኳይ መፍጠር አለበት፡፡ ዝም ብሎ ካድሬው ሳይሆን ሁነኛ   ሹማምንት የህዝቡን ብሶት ለማዳመጥ ጆሮአቸውን ክፍት ማድረግ አለባቸው፡፡
የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ጉዳይ በግልፅ መፍትሄ ማግኘት አለበት፡፡ ከህዝብ ጋር እውነተኛ ውይይት ማድረግ የግድ ነው፡፡ በህዝብ ላይ ለሚደርሱ ጉዳቶች መንግስት እውነተኛ ተቆርቋሪነቱን ማሳየት አለበት። ያለበለዚያ ዛሬ የበረደ እሳት፣ ነገ ጨምሮ ይመጣል፡፡ ትናንት ፌዴሬሽን ም/ቤት፣ መፍትሄ ይስጠን ያሉና መፍትሄ የተነፈጋቸው ናቸው ዛሬ የጉዳዩ ማዕከል የሆኑት፡፡
መንግስት ችግሮችን ወደ ውጭ ከመግፋት ይልቅ የራሱን ውስጥና ቀዳዳ መመልከት አለበት። የራሱን ጓዳ ማፅዳት አለበት፡፡ መንግስት ራሱ ቢቀየር ወግ ባለው ስርአታዊ መንገድ ሲቀየር ነው እንደ ሃገር ልንቀጥል የምንችለው፣በግርግር የሚቀየር መንግስት ለዚህች አገር አይበጅም፡፡ ሰላማዊ ሰልፎችን በአግባቡ ማስተናገድ ያስፈልጋል፡፡ የብዙ ሚሊዮን ህዝቦች ፍላጎትና ጥቅም የተመሰረተባት አገር ነች። ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ ከሆኑ ግን ወደ ከፋ ብጥብጥ ውስጥ ልንገባ እንችላለን፡፡ እንዳንገባ እፀልያለሁ፡፡
በቅርቡ “የሰጎን ፖለቲካ” በሚል ርዕስ በወጣው መፅሀፌ ላይ እንደገለጽኩት፤የኢትዮጵያ ምሁራን በተቻለ መጠን ህዝባዊ ውይይቶች ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል፡፡ ሀገር በተያዘው መንገድ ከሄደች ወዴት ልታመራ እንደምትችል ማሳየት አለባቸው። ምሁራን ከጉዳዩ የሸሹት ፈርተው አይመስለኝም፤ ሁነኛ መድረክ አጥተው ነው፡፡ እኔ ለምሳሌ ሀገሬ ከእንግዲህ በኋላ በትጥቅ የሚመጣ የመንግስት ለውጥ እንድታስተናግድ አልፈልግም፡፡ ይሄን አቋሜን የምናገርበት መድረክና እድል ሊኖረኝ ይገባል፡፡




Read 8328 times