Monday, 15 August 2016 09:01

ፖለቲካዊ ትራጀዲ!

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(9 votes)

የመንግስት እና የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሁሉ ስለ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ትምክህትና ጠባብነት የስርዓቱ አደጋ መሆናቸውን ዘወትር አበክሮ ሲናገር ይሰማል፡፡ የመንግስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ነባር የፓርቲው አመራሮች፤ በተለያየ ጊዜ ይህን ችግር እያነሱ ይነግሩናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ገና ከማለዳው (በ1992 ዓ.ም) ጀምሮ ሲብሰከሰኩ ቆይተዋል፡፡
በ1992 ዓ.ም (?) መሰለኝ፡፡ የህወሓት የምሥረታ በዓል በመቐለ ይከበራል፡፡ ጋዜጠኛው ጓደኛዬ በስብሰባው ታድሞ ነበር፡፡ የጉባዔውን ድባብና ትኩሳት ነገረኝ፡፡ የቀረፀውን ‹‹ሪል ቴፕ›› ሰጠኝ፡፡ ያኔ እንዲህ ነበር፡፡ አሰፋ ጎሳዬ (ነፍሱን ይማረው) የሪል ቴፕ ማጫወቻ ነበረው፡፡ ይዞልኝ መጥቶ ሰማሁት፡፡ ጉባዔው ትኩሳት ነበረው፡፡ በዚያ ጉባዔ አቶ አባይ ፀሐይ የተናገሩትን ዛሬም አስታውሳለሁ፡፡ ለየት ያለ ድባብና ነፃ የውይይት መንፈስ የተንጸባረቀበት መድረክ ነበር፡፡ የተለያዩ ምሁራን ጥናት ለማቅረብ የተጋበዙበት መድረክ ነበር፡፡ በዚህ መድረክ ጉባዔ ሲመሩ የነበሩት አቶ አባይ ፀሐይ፤ እንግዳ ለሆነ ሰው በሚያስደነግጥ አኳኋን እና በጋለ ስሜት የተናገሩት ቃል እንዲህ የሚል ነበር፡፡ ዛሬም አስታውሰዋለሁ፡-
‹‹ያን ጊዜ [በትጥቅ ትግሉ ወቅት]፤ በየለቱ በእሣት ትፈተናለህ፡፡ በየዕለቱ በህዝብ ትፈተናለህ ….. ይህ የድርጅቱን መስመር ጠብቆ ለመጓዝ ያግዘን ነበር። አዲስ አበባ ከገባን በኋላ ግን ሁኔታው ተለወጠ፡፡ የታጋዮች ጽናትን የሚፈታተን ችግር ውስጥ ገባን፡፡ የትግል ጽናትን የሚሸረሽር ችግር ገጠመን›› በማለት በድል ማግስት፣ ኢህአዴግ ያልተጠበቀና ከባድ ችግር እንደ ገጠመው ተናግረው ነበር፡፡
ታዲያ ነገሩ አያዋዊ በሆነ መንገድ መጓዙ ቀጠለ።
ወደ ኋላ ችግሩ በአዲስ ቋንቋ ይገለጽ ጀመረ። ኪራይ ሰብሳቢነት ተባለ፡፡ መንግስት፤ ‹‹ችግሩ መዋቅራዊ ወይም ስርዓታዊ ለውጥ በመፍጠር እንጂ በዘመቻ ሥራ ሊወገድ አይችልም›› እያለ ቆይቶ፤ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካ-ኢኮኖሚ ምንጭ የሆኑትን ነገሮች ለማድረቅ እሰራለሁ ሲል ከርሞ፤ በቅርቡ ‹‹በዘመቻ ዘላቂ ለውጥ ባይመጣም፤ ስርዓቱን የመቀየር ጥረት ከዘመቻው ሥራ ጋር ተቀናጅቶ መሄድ ይኖርበታል›› ከሚል ድምዳሜ ደርሶ፣ ከህዝቡ ጋር ሥራ ለመስራት አውጆ ሥራ ሲጀምር ሁከት ተቀሰቀሰ፡፡ የፖለቲካዊ ትራጀዲ መድረኩ ተከፈተ፡፡  
የትራጀዲ ተውኔት ገፀ ባህርያት በብዙ ረገድ እንከን የለሽ ታላቅ ሰብዕና ያላቸው ናቸው፡፡ አስተዋይነት፣ ጀግንነትና ሁሉንም ሰው የሚያስቀና ባህርይ ያላቸው እነዚህ ገፀ ባህርያት፤ ከታላቅ ሰብዕናቸው ውስጥ የተወሸቀ አንድ የባህርይ እንከን ይኖራቸዋል፡፡ ይህም የባህርይ እንከን ወደ ውድቀት ይመራቸዋል፡፡
ገዢው ፓርቲ እንከን የሌለው ድርጅት አይደለም፡፡ ሆኖም እንደ ትራጄዲያዊ ገፀ ባህርይ ለማየት የተለያዩ በጎ ጥረቶቹን መጥቀስ እንችላለን። ሌላው ቢቀር በዓለም ተጠቃሽ የሆነ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ልማት ዕድገት ማረጋገጥ ችሏል፡፡ ህዝቡን በህዳሴ ጎዳና ለመምራት እየሞከረም ነው። ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል በመፍጠር ረገድም በታሪክ የሚጠቀስ ሚና የሚኖረው ድርጅት ነው፡፡ ይሁንና አሳምሮ የሚያውቀውንና ለብዙ ዓመታት እንደ ክፉ አደጋ ሲመለከተው የቆየውን ችግር ተሸክሟል፡፡ ይህን ችግር በቶሎ መፍታት ተስኖት ስንመለከት አሁን ከፊቱ የተደቀነውን ተግዳሮት ስንመለከት፤ ፖለቲካዊ የትራጀዲ ተውኔት የምናይ ይመስላል፡፡ የነገሩን ትራጀዲያዊ ባህርይ ይበልጥ አጉልቶ ለማሳየት ያሰበ ማለፊያ ደራሲ የተለመው ታሪክ ይመስል፤ ችግሩን ለመፍታት ሲነሳ፤ አሁን ያየነው ዓይነት ሁከት ተከሰተ፡፡
አንድ ስሙን የዘነጋሁት የፖለቲካ ምሁር፤ ርዕሱን በማላስታውሰው የጥናት ሥራው፤ ‹‹ኢህአዴግ ፈጣን ተማሪ አይደለም፡፡ ሆኖም አዝግሞ በተማረው ነገር ሁለተኛ ሲሳሳት አይገኝም›› ማለቱን አስታውሳለሁ። አሁን በሚታየው ነገር ከፈረድነው፤ ኢህአዴግ አዝጋሚ ተማሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን አዝግሞ በተማረው ነገር ሁለተኛ የማይሳሳት ተማሪ መሆኑን ለመመስከር የሚቻል አልመሰለኝም። ለመሆኑ፤ ከሰሞኑ ሁከት ኢህአዴግ ምን ተማረ? እኔ አላውቅም፡፡ ግን ነገሩ ሁሉ የአንድ ንጉስን ታሪክ የሚያስታውስ ሆኖ ተሰማኝ፡፡
አንድ ንጉስ ነበር፡፡ በግዛቱ በመላ የሚገኙ የጥበብ መጻህፍት እንዲሰበሰቡለት፤ በየግዛቱ ሰዎችን ሰደደ። ለወራት የጥበብ መጻህፍትን ሲያድኑ የከረሙት ሎሌዎ፤ች አንድ ሺህ ገደማ መጻህፍት ሰብስበው አመጡለት፡፡ ንጉሱ መጻህፍቱ ተከምሮ ሲመለከት ልቡ ፈሰሰ፡፡ ‹‹አይ ይህን ሁሉ መጽሐፍ ለማንበብ አልችልም፡፡ አሳጥራችሁ አምጡልኝ›› አለ፡፡ የንጉስ ቃል ነው፡፡ ትዕዛዙ ይከበራል፡፡ ስለዚህ በአንድ ሺህ መጻሕፍት ውስጥ የገለጸው ጥብብ ወደ አምስት መቶ መጻሕፍት አጥሮ ቀረበለት፡፡ ሆኖም ይህ ሥራ ዓመታትን የጠየቀ ሥራ ነበር፡፡ ንጉሱ አምስት መቶ መጽሐፍ ለማንበብ ብርታት ያለው አልነበረም፡፡ ገና ሲያስበው ደከመው፡፡ አሳጥሩ አለ፡፡ በግማሽ ለማሳጠር ሌሎች ዓመታት አለፉ፡፡ አሁንም ሁለት መቶ ሐምሳ መጽሐፍ ለማንበብ አልፈለገም። አሳጥሩ አለ፡፡ ሌሎች ዓመታት ነጎዱ፡፡ አሳጥሩ አለ። እንዲህ እያለ፡፡ ከሦስት መጽሐፍ ደረሰ፡፡ እርሱ ግን አሁንም አሳጥሩ አለ፡፡ ግን ታመመ፡፡ ከአልጋ ዋለ፡፡ በመጨረሻም ሞተ፡፡ ህዝብን ለመምራት የሚያስችል ጥበብ ለማግኘት እንደተመኘ ያሰበውን ሳያሳካ ሞት ቀደመው፡፡   
ገዢው ፓርቲ አለብኝ የሚለውን ችግር ለመፍታት ጥበብ ሳይሆን ቁርጠኝነት የቸገረው ይመስለኛል፡፡ ነገሩን በጣም አቃልዬ አይቼው ይሆናል፡፡ ግን ዞሮ ተመልሶ ነገሩ ከቁርጠኝነት ማጣት መውደቁ አይቀርም እላለሁ፡፡ አሁን ችግሩ ለያዥ ለገራዥ የሚያስቸግርና እንቆቅልሽ መሆን ይዟል፡፡
በዚህ ዓመት መጀመሪያው ግድም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የህዝብ አመጽ ሲነሳ፤ ጠያቂ (ህዝቡ) እና ተጠያቂ (መንግስት) አንድ ዓይነት ቃል እየተናገሩ፤ ነገር ግን በመንገድ ተለያይተው ሲጋጩ አየን፡፡ ከሳሽና  ተከሳሽ አንድ ሆነው ግራ አጋቡን፡፡ ተከሳሹ በከሳሽ ላይ ያደረሰውን በደል፤ ከተበዳዩ በላይ አክርሮ ይናገራል፡፡ ‹‹አዎ ልክ ነህ ተበድለሃል›› ይላል፡፡ ይህን ነገር በዳኝነት የሚመለከት አንድ ፈራጅ ቢኖር፤ በሁለቱም ወገን የሚቀርበውን አስተያየት ሰምቶ፤ የክርክሩን ጭብጥ ለማውጣት ይቸገራል፡፡
ሙግት የጨረባ ድግስ እንዳይሆን፤ የክርክር ጭብጥ ነጥሮ መውጣት ይኖርበታል፡፡ ጭብጥ የሙግት እምብርት ነው፡፡ ጭብጥ ተለይቶ መውጣቱ፤ ለግራ - ቀኙ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ‹‹ሙግት ለማገዶ እንደሚሰበሰብ ፍልጥ ቢታሰብ፤ ጭብጥ እንደማሰሪያው ልጥ ነው፡፡›› ወትሮም፤ ‹‹ለሺህ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ›› ነው የተባለ፡፡ ማሰሪያ የሌለው ፍልጥ ተበታትኖ ለአያያዝ እንደሚያስቸግር፤ በጭብጥ ያልተያዘ ሙግትም ወደ ጭፍጫፊ ነጥቦች እየተሰነጣጠረና እየተሰበጣጠረ ስለሚሄድ መያዣ መጨበጫ የሌለው ይሆናል፡፡
ጭብጥ የሙግትን ዳር ድንበርና ይዘት ጭምር ይወስናል፡፡ ግራ - ቀኙ የተለያዩበትን ሥረ ነገር እና ህጋዊ መሠረቱን አጥርቶ ያመለክታል፡፡ ተከራካሪዎቹ ጭብጣቸውን እንዲያስረዱ፤ ደግሞም በጭብጣቸው እንዲረጉ፤ ፈራጅም በጭብጡ ተወስኖ የቀረበለትን ማስረጃ መዝኖ፤ ክርክሩን አዳምጦ፤ ሕጉን አገላብጦ፤ ሙግትን እንዲቆርጥ ውሳኔ እንዲሰጥ ያስችለዋል፡፡ አሁን በሚያነጋግረን የፖለቲካ ይዘት ባለው ውዝግብ ትልቁ ዳኛ ህዝብ ነው፡፡
ግን ትልቁ ዳኛ ህዝብ፤ የክርክሩ ጭብጥ ሳይመሰረት፤ ሾላ በድፍን የሆነ ሙግት ገጥሞት ተቸገረ፡፡ ሾላ በድፍን የሆነ ክርክር አስቸጋሪ ነው፡፡ ሾላ በድፍ የሆነ ሙግት የዕድሜ ልክ መንገድ ነው፡፡ መድረሻ የሌለው ጅረት ነው፡፡ መንግስት ጭብጦቹ ፈጥጠው እንዲወጡ ማድረግ የተሳነው ሆኖ ሲታይ፤ ክፉ የሚያስቡ ኃይሎች ተረባርበው ችግሩ እንዲድበሰበስ ለማድረግ ድንጋይ ፈነቀሉ፡፡ ፈራጁ ዳኛ የነገሩ ውል ጠፍቶበት ተደነባበረ፡፡ ይህም ለሁከት ምቹ ሁኔታን ፈጠረ፡፡ የዚህ ተደራቢ ሆኖ የጎንደሩ ችግር መጣ፡፡ ታዲያ ነገሩ እንዲህ ይቀጥላል ወይስ ኢህአዴግ ነገሩን መልክ አስይዞ፣ ፊቱን ወደ ልማት ብቻ ሳይሆን ወደ ዴሞክራሲና  መልካም አስተዳደር ያዞራል? የተውኔቱ መጋረጃ አልተዘጋም።
መጋረጃው ባይዘጋም፤ ለዚህ ጽሑፍ መዝጊያ የሚሆን አንድ ቃል መናገር እፈልጋለሁ፡፡ የተሳፈርንበት መኪና ጭቃ ውስጥ ከተዘፈቀ፤ የምንደርስበት ቦታ ሩቅ ወይም ቅርብ፤ አስደሳች ወይም መጥፎ መሆኑ ትርጉም የለሽ ነው፡፡ የሰሞኑ ድምጽ አስፈሪ ነው፡፡ ድምጻችን የእኛ አይመስልም፡፡ ይህ ድምጽ ቃናው ተለውጧል፡፡ አሁን የምንሰማው ድምጽ እየገነነ ሲሄድ አደጋ አለው፡፡ የጋጠ ወጥ ድምጽ ሲገንን፣ የአስተዋዮቹ ሰዎች ድምጽ እየተዳከመ ይመጣል፡፡ ሰብአዊነት መጠጊያ ያጣል። ይህ ድምጽ ሊያሸንፈን አይገባም፡፡ ምነው፤ ሰው መሆን ቸገረን?

Read 4113 times