Monday, 15 August 2016 09:03

መስተዋት የምትነግርህን የእናትህ ልጅ አትነግርህም

Written by 
Rate this item
(15 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ንሥር ጎጆ ቤቷን ትልቅ ዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ትሠራለች፡፡
አንዲት ድመት ደግሞ ከነልጆቿ የዛፍ ግንድ መካከል የተቦረቦረ ሥፍራ ትኖራለች፡፡
አንዲት የዱር አሣማ ደግሞ ከዛፉ ግርጌ በተቦረቦረው ግንድ ውስጥ ከነልጇቿ ትኖራለች፡፡
እነዚህ ሶስት እንስሳት እንደ ጎረቤታሞች ሁሉ በፍቅር ተሳስበው፣ በአንዱ ግንድ ላይ ሲኖሩ ያስቀኑ ነበር፡፡ በኋላ ግን ተንኮለኛዋ ድመት ያንን የመሰለ የፍቅር ህይወታቸውን ልታደፈርስ ተነሳች፡፡
ወደ ንስሩ ጎጆ ወጣች-ድመቲት፡፡
 እንዲምህ አለቻት፡-
‹‹እኔና አንቺ ከባድ አደጋ እያንዣበብን ነው››
‹‹እንዴት?›› አለች ንሥር››
‹‹አሣም ተንኮለኛ ናት፡፡ የእኛን ህይወት ለማበላሸት ሌት ተቀን ከመጣጣር አልታቀበችም››
ንሥርም፤
‹‹እኛ የምንኖረው የራሳችንን ኑሮ፡፡ አሣማም ልጇም የሚኖሩት የራሳቸውን ኑሮ፡፡ ለምን እንደራረሳለን?›› አለችና ጠየቀች፤ በሙሉ የዋህነት፡፡
ድመትም፤
‹‹አሣማ እንደኛ ቀና ብትሆን ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ልቧ ክፉ ነው፡፡ ስለሆነም የሁላችንም የጋራ መኖሪያ የሆነውን ግንድ ከሥሩ እየገዘገዘች ልትጥለው ነው፡፡ ከእንግዲህ መኖሪያ አይኖረንም። የአንቺም የእኔም ልጆች የእሷ ምግብ መሆናቸው ነው›› አለች፡፡ ንሥር በጣም ተረበሸች፡፡ ተሸበረች፡፡ ድመት ሆዬ፣ ከንሥር ጎጆ ወደዛፉ ግርጌ ወረደች፤ አሣማዋ ዘንድ መጣችና፤
‹‹እመት አሣማ፤ የእኔና አንቺ  ሕይወት አደጋ ላይ መሆኑን ታውቂያለሽ?›› ስትል አሣማን ጠየቀቻት፡፡
አሣማም፤
‹‹ለምን? እንዴት? እኔ ምንም የማውቀው ነገር የለም››፤ አለቻት፡፡
ድመትም፤
‹‹እዚያ፤ ዛፉ አናት ላይ ካለችው ንሥር መጠንቀቅ አለብሽ፡፡ አንድ ቀን ስትዘናጊላት ወደ ታች ወርዳ ግልገልሽን ይዛብሽ ትሄዳለች፡፡ ጊዜ እየጠበቀች ነው፡፡ ያንቺ ልጆች የንሥር ልጆች ቀለብ እንዳይሆኑ ብታስቢበት ይሻላል›› አለች፡፡
ልክ እንደ ንሥሩ ሁሉ አሣማም በጣም ደነገጠች፡፡ በጣም ተሸበረች፡፡ ድመት ሁለቱን ጎረቤቶቿን እጅግ አድርጋ ካስፈራራች በኋላ ወደ መኖሪዋ ተመለሰች፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላ የፈራች ለማስመሰል ድመት ቀን ቀን መውጣቷን ተወች፡፡ ለልጆቿ ምግብ ለመፈለግ ማታ ማታ ብቻ ሆነ የምትወጣው፡፡
ንሥር ከጎጆዋ መውጣት ፈራችና ራሷን ዘግታ ቁጭ አለች፡፡
አሣማም ከፍርሃቷ የተነሳ ከዛፉ ግርጌ ካለው ሥር ንቅንቅ አልልም ብላ ከመኖሪያዋ ሳትወጣ ልጆቿን መጠበቅ ሆነ ሥራዋ፡፡ ቀን እየገፋ ሲመጣ የንሥርና የአሳማ ቤቴሰቦች በረሀብ አለቁ፡፡ ድመትም ለራሷና ለልጆቿ የሚሆን የተትረፈረፈ ምግብ አገኘች፡፡
የጋራ ቤታቸውን አስከብረው፣ በፍቅር እየተሰባሰቡ የሚኖሩ የታደሉ ናቸው፡፡ በተንኮል የሌሎችን ህይወት የሚያደፈርሱ እኩያን፤ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ዋጋ መክፈላቸው አይቀሬ ነው፡፡ ለሁሉም በሚበቃ አገር፤ የሌላውን ህልውና በሚያጨልም መልኩ ግፍ መፈፀም የማታ ማታ ማስጠየቁ ሳታውቅ በስህተት፣ አውቀህ በድፍረት ባደረግኸው መጠየቅ አለና፤ የምታደርገውን በቅጡና በጥንቃቄ አድርግ! የሀገራችን ሰላም ማጣት ለማንም የሚበጅ አይደለም፡፡ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንጂ በኋይል ለመፍታት መሞክር ጊዜያዊ መፍትሔ እንጂ ዘላቂ መላ አይሆንም፡፡ መንግሥት በየጊዜው የሚወስዳቸው አርምጃዎች እንድም ሶስትም ናቸው ከሚባሉት ከመልካም አስተዳደር፣ ከፍትሕና ከሙስና ችግሮ አኳያ፣ ያላንዳች ማንገራገር ራሱን ካልመረመረ ወደ ካንሰርነት በመለወጥ ላይ ያለ በሽታ ይዞ እንደመክረም መሆኑ አይካድም፡፡
የአገራችንን ጠቅላይ ስዕል (bigger picture) ማየት ተገቢ ነው፡፡ ገዢ የሚባሉትን ትላልቅ ችግሮች እንጂ እንደ ቀዶ ጥገና ሀኪም የተወሰኑ ብልቶን ብቻ ለይቶ ለማከም መጣር የተነካኩትን አካላት እንደ መዘንጋት ስለሚሆን አጠቃላይ ጤና ከመታወክ አይድንም፡፡ “የአብዬን እከክ ወደ ምዬ ልክክም” (Blame - Shifting) አያዋጣም፡፡ ነገ ተነገ - ወዲያ እናስተካክለዋለን ማለትም (procrastination) ችግሮችን ከማባባስና ቀንን ከማቅረብ በስተቀር የሚፈይደው ነገር አይኖርም። አድሮ ቅርንጫፍ አብቅሎ አፍጦ ይመጣብናልና፡፡
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን በ“ሐምሌት” ትርጉሙ እንዲህ ይለናል፡-
“ዛሬ ለወግ ያደረግሺው፣ ወይ ለነገ ይለምድብሻል፤ ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው፣ ወይ ይጠፋል ወይ ያጠፋል፡፡ ከርሞም የሰለጠነ እንደሁ፣ ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል”
እንጠንቀቅ፡፡ ራሳችንን እንመርምር፡፡ የችግሮቻችንን አጠቃላይ ስዕል እንቃኝ፡፡ ነጋ - ጠባ እያወራናቸው ያልፈታናቸው ችግሮች የትየለሌ ናቸው! በግልፅ ችግሮቻችንን እንወያይባቸው፡፡ ልዩ ልዩ ታርጋ እሰጠን አንሽሻቸው፡፡ ፈረንጆች Denial የሚሉት ዓይነት፤ ያለውን ነገር እንደሌለ አድርገን መካድና መካካድ፤ የትም አያደርሰንም፡፡ መረጃ ባለመስጠት፣ አገር አናድንም፡፡ ጥቃቅኑን ነገር እየመነዘርን ፀጉር ስንጠቃም ያው ከቁንጫ መላላጫ ማውጣት ነውና ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡ አንድም ደግሞ ከግጭት አዙሪት እንዴት እንውጣ ብሎ ራስን መጠየቅ አስፈላጊ ነው። እንደ ሰሞኑ የውሃ ዋና ጭቅጭቅ አፍጥጠው ሚመጡ አያሌ ጅላጅል ሀሳቦች፣ የማመን ያለማን ግልፅነት የጎደለው ስፖርት፣ የዓለም መሳቂያ እንዳያደርጉን አሁንም ዐይናችንን መክፈት ተገቢ ነው፡፡ ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎችን ከልብ እንፈትሽ፡፡
“የግጭት ቀለበለት ካሰርን ቆይተናል ሰርጉ ገና አልተደገሰም” እየተባለ ሲሾፍ፤ ውስጡ መራራ ዕውነት እንዳለ አለማስተዋል የዋህነት ነው፡፡ በበርካታ ስራ አጥ ወጣት የተወጠረች አገር ምንም አይነት ተንኮል ቢሸረብባት አይገርምም!! an idle mind is the devil’s workshop ይሏልና!! (ሥራ የፈታ አዕምሮ የሰይጣን ስራ - ቤት ይሆናል፤ እንደማለት ነው) እለት ሰርክ በተግባር የምናውን ነገር ስንክድ መፍትሄ መፈለግ ያባት ነው፡፡ ተግባር መስተውት ነው፡፡ ከተግባር ወዲ የምንቆጥረውም ስክር አይኖርም፡፡ “መስተዋት የምትነግርህን፣ የእናትህ ልጅ አትነግርህም” የሚባለው ተረትና ምሳሌ፣ በሀገራችን ያለውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ሁኔታ መቃወስ በቅጢ እንድንፈትሽ፣ መስተዋቱን በጥንቃቄ እንድናይ፤ አመላካች ነው፡፡

Read 7225 times