Monday, 15 August 2016 09:05

አገራዊ ችግሩን ወደ እርቅ መድረክ እናምጣው!!

Written by  አብዱራህማን አህመዲን (የቀድሞ የፓርላማ አባል) ahayder2000@gmail.com
Rate this item
(3 votes)

ለሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ፣
 እ.ኤ.አ ከ1998 እስከ 2002 ድረስ የነበረውን የፓርላማ የሥራ ዘመኔን በሰኔ ወር 2002 እንደጨረስኩ፣ ከነበርኩበት ፓርቲ (ከኢዴፓ) በራሴ ፍላጎት ለቀቅኩ፡፡ ከዚያ ወዲህ የየትኛውም ፓርቲ አባልም ደጋፊም አይደለሁም፡፡ አገር ውስጥ በሚገኝ አንድ የግል ኩባንያ እየሰራሁ የግል ህይወቴን እየኖርኩ ነው፡፡
ከግንባር መስመር ፖለቲካ (Front Line Politics) ራሴን ባገልም እንደማንኛውም ዜጋ የሀገሬ ጉዳይ ያሳስበኛል፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜአት ወዲህ እየሆነ ያለው ሁኔታ ሰላም አልሰጠኝም፡፡ ምን ማድረግ አለብኝ? እያልኩ ሳሰላስል አንድ ሃሳብ መጣልኝ - ብሔራዊ እርቅ፡፡
በአገር ውስጥ በጉዳዩ ላይ አንዳንድ ሰዎችን እያነጋገርኩ ነው፡፡ የዲያስፖራውን ማህበረሰብ በወሬ ከሚናፈሰው ውጪ ቀርቤ በጥልቀት አላውቀውም። በስም በርቀት የማውቃቸው ጥቂት ሰዎች አሉ። እነሱንም ለማነጋገር እጥራለሁ፡፡ ከዚያ በተረፈ ይህንን ጽሁፍ ያነበበ ሁሉ በአድራሻዬ ሊያነጋግረኝ ይችል ዘንድ ለዚህ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ላኩት፡፡
ነገሩ ሁሉ ተበለሻሽቶ ሀገር ከመፍረሱ በፊት በጋራ የምንሰራው ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ በበኩሌ፤ በተለይም ከተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የለቀቅን ሰዎች፣ ሌሎችንም ወንድሞችና እህቶች (ከአገር ቤትም ከውጪም) ጨምረን በመነጋገር፣በጋራ የምንሰራቸው ነገሮች ያሉ ይመስለኛል፡፡
አሁን ያለው ሁኔታ አያምርም፡፡ የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ትኩረት አድርጎ የመዝመት አዝማሚያ መኖሩን ነው እየሰማሁ ያለሁት፡፡ የዚህ ዘመቻ ውጤት ደግሞ መንግስት በመለወጥ የሚቆም አይመስለኝም፡፡ 25 ዓመታት የተቋሰለና በድህነት ውስጥ ያለ ሕዝብ ሰበብ ካገኘ ይተላለቃል፡፡ ጂኒው ከጠርሙሱ ከወጣ በኋላ እመልሳለሁ ማለት ዘበት ነው፡፡ አገሪቱ ትበተናለች ወይም ወታደሩ እንደ ደርግ ስልጣን ላይ ይወጣና ሌላ የደርግ ዘመን ይመጣል የሚል ስጋት አለኝ፡፡
እናም ሀገራችንን ማዳን አለብን፡፡ ችግሩን ወደ እርቅ መድረክ እናምጣው፡፡ አሁን ያለውን መንግስታዊ ስርዓት ከመለወጥ በመለስ ውጤት የሚኖረው፣ ብሔራዊ የእርቅና የመግባባት መድረክ በመፍጠር ለሀገሪቱ ህልውና ወሳኝ በሆኑ ዋና ዋና ሀገራዊ ችግሮች ዙሪያ እንምከር፡፡ መንግስት ለማንኛውም ዜጋ ምህረትና ይቅርታ እንዲያደርግና ለእርቅ እንዲዘጋጅ እንግፋው፡፡ በዲያስፖራም በአገር ቤትም ያሉ ፖለቲከኞችም እንዲሁ ወደ እርቅ ይገፉ፡፡ የእርቁ ውጤት ወደ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲያመራ አቅጣጫ እናሳይ፡፡
በበኩሌ በሽምግልናው ሂደት ከማንኛውም ሀገር ወዳድ ጋር አብሬ ለመስራት ፈቃደኛ ነኝ።   የምንሰራው ነገር የለም” ከተባለም ቢያንስ መልእክቴን ለሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በማድረሴ ከሞራል አኳያ የድርሻዬን ተወጥቻለሁና የሚጸጽተኝ ነገር አይኖርም፡፡ ለማንኛውም ለመነሻ ይሆን ዘንድ የኔን ሃሳብ የያዘ 3 ገጽ፣የብሔራዊ እርቅ የመነሻ ሃሳብ አቅርቤአለሁ፡፡
የብሔራዊ እርቅ መነሻ ሃሳብ
1. መግቢያ
የደርግ መንግስት ተወግዶ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ባሉት 25 ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተለያየ መጠንና ስፋት ያላቸው ችግሮች ተከስተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በርካታዎች ቆስለዋል፤ ታስረዋል፣ ተሰደዋል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዋጋ ያለው ንብረት ወድሟል፡፡ ጊዜ ባክኗል፡፡ ይህ ሁሉ መስዋእትነት ተከፍሎም ችግሩ እልባት አላገኘም። ችግሩ መላ ሀገሪቱን ከጠረፍ እስከ ጠረፍ እየናጠ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ጭራሽ ሊቀለበስ ወደማይችል አቅጣጫ እያመራ መሆኑ ይታያል፡፡ እናም፤ ይህንን ችግር እንዴት እንፍታው? የሚለው ጥያቄ የሁሉም አገር ወዳድ ጥያቄ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡
2. ዓላማ
ከጊዜ ወደ ጊዜ ባልተቋረጠ ሁኔታ እየተባባሰ የመጣውን ይህንን ችግር እንዴት እንፍታው? ለሚለው ጥያቄ የበኩሌን ሃሳብ ለማቅረብ ነው ይህቺን ማስታወሻ ያዘጋጀሁት፡፡ የዚህ ማስታወሻ ሁለተኛ ዓላማ የሀገሪቱ ሁኔታ ያሳሰባቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣… በተበታተነ መልኩ በተናጠል በመገናኛ ብዙሃን አማካይነት እየሰጡት ያለውን ስጋትና ጭንቀት የወለደው የመፍትሄ ሃሳብ ተቋማዊ ገጽታ፣ ቅርፅና ይዘት ባለው መልኩ እንዲያራምዱት ለመገፋፋት ነው፡፡
3. ችግሮቹ
በእኔ እይታ፤ የሀገራችንን ወቅታዊ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች በአጭሩ በሚከተለው መልኩ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡
ፖለቲካዊ
የፖለቲካ አጀንዳ ሆነው ፓርቲዎች ለምርጫ ውድድር ሊያቀርቧቸው በማይገቡ መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች (ሕገ-መንግስት፣ የፌዴራል ስርዓት አደረጃጀት፣…) በመሳሰሉ ጉዳዮች ዙሪያ ሀቀኛ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር አለመቻል፣
ከደርግ ውድቀት በኋላ የሽግግር ስርዓቱን የመሰረቱና ከዚያም በኋላ የተፈጠሩ የፖለቲካ ኃይሎች የፖለቲካ ምህዳሩ በመጥበቡ ምክንያት ከሠላማዊ የፖለቲካ ትግሉ እንዲሸሹ በመደረጋቸው ወደ ሌላ አማራጭ መገፋት፣ የአንድን ፓርቲ ልዕልና በማጠናከር የተጀመረውን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መሸርሸር፣
እንደ ምርጫ ቦርድ፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የፍትህ ተቋማት፣… የመሳሰሉ የዴሞክራሲ ስርዓት መገንቢያ ተቋማት፤የሕዝብና የፖለቲካ ኃይሎችን አመኔታ እንዲያጡ መደረግ፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና ህብረተሰቡን በሚያማርር ቢሮክራሲ መተብተብ፣
ጨቋኝ ሕጎችን በማውጣት፤ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ባለሃብቶችን፣… በየሰበብ አስባቡ ማሰር፣ ማንገላታት፣ እንዲሰደዱ ማድረግ፣ ሕዝብ ብሶቱንና አሉኝ የሚላቸውን ጥያቄዎች አደባባይ ወጥቶ እንዳይገልጽ መታፈኑ፣
ኢኮኖሚያዊ
ለስርዓቱ አገልጋይ የሆነ ጥገኛ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዳይኖር ማድረግ፣ በህብረተሰቡ መካከል ያለውን የሀብት ልዩነት ይበልጥ የሚያሰፋ የአሰራር ስርዓት መከተል፣ የእኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት መጓደል፣ በዚህም ምክንያት ጤናማ ኢኮኖሚ እንዳይፈጠር በማድረግ, ጥላቻና የበቀል ስሜት እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታ መፈጠር፣…
ማህበራዊ
የሃይማኖት ተቋማት፡- የየእምነቱን ሰዎች አስተባብረው ለስራ የሚተጋና መልካም ስነ-ምግባር ያለው ህብረተሰብ ለማፍራት የሚያስችላቸውን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ፋንታ የሃይማኖት መሪዎችን በማሰርና በማሳደድ,፣ ተቋማቱ ሀገራዊ አስተዋጽዖ እንዳይኖራቸው በማድረግ፣ የአክራሪ ኃይሎች አስተሳሰብ ልዕልና እንዲኖረው በር መክፈት፣
በብሔር/ብሔረሰብ እና በሃይማኖቶች መካከል ያሉ ልዩነቶች፣ የውበታችን መገለጫዎች መሆናቸው ስር እንዲሰድ ባለመደረጉ የነበሩ ልዩነቶች የበለጠ እንዲሰፉና የጥላቻና የጎሪጥ መተያየት እንዲጎለብት እድል መፍጠር፣
በአጠቃላይ፤ በሀገሪቱ ሕገ-መንግስት ላይ የሰፈሩት መሰረታዊ ጉዳዮች መሸርሸርና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ፈታኝ ሁኔታዎች እንዲጋረጡበት መደረጉ፣ የህዝቡ የአብሮነትና የመተሳሰብ ባህል በመላላቱ የሕዝብ መነሳሳትን ተከትሎ የቂም በቀል ስሜቶችና የተግባር እንቅስቃሴዎች ጎልተው መታየታቸው፣ ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣… ይህ ሁሉ ተደማምሮ የሀገሪቱን ህልውና በቀላሉ ሊቀለበስ ወደማይችል ችግር ውስጥ መግፋቱ የዚህ ወቅት የሀገሪቱ ዋነኛ ችግር ነው፡፡   
4. መፍትሄ
ከላይ የተጠቀሱትንና መሰል ችግሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስወገድ የሀገሪቱና የህዝቧ ሰላምና ደህንነት ተጠብቆ፣ በልዩነት ውስጥ አንድነትን እውን ለማድረግ የሚያስችል፣ አሁን ያለውን መንግስታዊ ስርዓት ከመለወጥ በመለስ ውጤት የሚኖረው፣ ብሔራዊ የእርቅና የመግባባት መድረክ በመፍጠር፣ ለሀገሪቱ ህልውና ወሳኝ በሆኑ ዋና ዋና ሀገራዊ ችግሮች ዙሪያ መምከር፡፡
5. የምክክሩ ተሳታፊዎች
የፖለቲካ ኃይሎች፣
የሃይማኖት ተቋማት፣
ምሁራን፣
የሀገር ሽማግሌዎች (ከየማህበረሰቡ)
ታዋቂ ግለሰቦች፣
ባለሃብቶች፣
መገናኛ ብዙሃን (ሂደቱን ተከታትለው ለመዘገብ)
6. ከመድረኩ የሚጠበቅ ውጤት
የእርቅ የቃልኪዳን ሰነድ፣
ሰነዱን የሚያስፈጽም ተቋም (ብሔራዊ የእርቅና የሕዳሴ ምክር ቤት - National Reconciliation and Renaissance Council)
7. የምክክሩ መድረክ አስፈጻሚ
ሃሳቡን የጠነሰሱ አስተባባሪዎች
8. ምክክሩ የሚካሄድበት ቦታና ጊዜ
አዲስ አበባ
በአጭር ጊዜ (ሃሳቡን በጠነሰሱና በተሳታፊዎች ስምምነት የሚወሰን)
9. የሚያጋጥሙ ችግሮች
ኢህአዴግ፤ ስልጣን አጣለሁ በሚል ስጋት ሂደቱን “ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በማፍረስ ስልጣንን በአቋራጭ ለመቀማት የሚደረግ ጥረት ነው” በሚል ሰበብ ሃሳቡን ውድቅ ሊያደርገው ይችላል፡፡
ተቃዋሚዎች፤ አሁን ያለውን የሕዝብ መነሳሳት በመመልከት “ይህ መንግስት አልቆለታል፣ አንድ ሀሙስ ነው የቀረው” በሚል ስሜት ሃሳቡን ላይቀበሉት ወይም ቅድመ ሁኔታዎችን ሊደረድሩ ይችላሉ፡፡
10. የመፍትሄ ሃሳብ
ሁለቱም ኃይሎች የሚሄዱበት መንገድ ውጤቱ “ስልጣን በማጣትና - ስልጣን በማግኘት” የሚቋጭ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱን የሚበታትን አደጋ የሚጋብዝ መሆኑን በተጨባጭ በማሳየት ሳይታክቱ ለማግባባት መጣር፡፡

11. በሃሳቡ ጠንሳሾች መከናወን የሚገባቸው ተግባራት
በጉዳዩ ላይ በስፋትና በጥልቀት በመወያየት የጋራ ግንዛቤ መያዝ፤
የጋራ ግንዛቤውን መሰረት አድርጎ ለሂደቱ የሚረዱ ሰነዶችን ማዘጋጀት፣
የምክክሩ ተሳታፊዎች እነማን መሆን እንደሚገባቸው መለየት፣ በተናጠል ማነጋገር፣ ማግባባት፣
በተናጠል የተደረጉትን ንግግሮች መሰረት ያደረገ የማስፈጸሚያ መርሐ-ግብር ማዘጋጀት፣ በጀት መመደብ፣ ማስፈጸም፣

Read 2666 times