Monday, 15 August 2016 09:09

ለአዲስ አበባ የብስክሌት ትራንስፖርት ያዛልቃት ይሆን?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

3 ማህበሮች፣ በ210 ቢስክሌቶች ሥራ ጀምረዋል

የአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ፤ በቅርቡ የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት  በመዲናዋ ሶስት ቦታዎች ላይ አስጀምሯል፡፡ ለብስክሌቶቹ በ22 ሚሊዮን ብር መንገድ ተገንብቶላቸዋል - በከተማዋ ሦስት የተለያዩ ቦታዎች፡፡ መንግስት እስካሁን 210 ያህል ብስክሌቶችን ከቻይና በመግዛት፣አስር አስር ሆነው በአነስተኛና ጥቃቅን ለተደራጁ ሶስት ማህበራት 70 ሳይክሎችን አስረክቧል - ለእያንዳንዳቸው 70 ሳይክሎች፡፡
ለቢስክሌቶቹ ታስበው የተገነቡት የአስፋልት መንገዶቹ፤ ባለፈው ሀምሌ አጋማሽ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት ተመርቀው ሥራ ጀምረዋል፡፡ ይሁን እንጂ መንገዶቹን ከእነሱ ይልቅ እግረኞች በደንብና በብዛት እየጠቀሙበት ስለሆነ ሥራችን ላይ ፈተና ጋርጠውብናል - ይላሉ፤ የቢስክሌት ማህበራቱ ሃላፊዎች፡፡
ከሶስቱ የብስክሌት ትራንስፖርት ቦታዎች፣አንዱ ከሰሚት ለስላሳ ፋብሪካ ፊት ለፊት ተነስቶ ሲኤምሲ አደባባይ የሚደርስ ሲሆን ‹‹በቃሉ ሳሙኤልና ጓደኞቻቸው የሳይክል ትራንስፖርት ህብረት ስራ ማህበር›› ተብሎ ይጠራል፡፡ የማህበሩ ም/ስራ አስኪያጅ ወጣት ሳሙኤል አስረስ፤  የቢስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ገና ወር ባይሞላቸውም ብዙ ፈተናዎች እንደተጋረጠባቸው ይናገራል፡፡ ከሁሉም ትልቁ ፈተና 22 ሚ. ብር ወጥቶበት የተሰራው የብስክሌቱ መንገድ፤ለእግረኛ መጠቀሚያ መዋሉ ነው፤ ይላል ወጣቱ። “ምንም እንኳን መንግስት ለእኛ መልካም የስራ አጋጣሚ ቢፈጥርልንም፣ህብረተሰቡ ስለ ብስክሌት መንገዱ ግንዛቤ ስላልተሰጠው በአግባቡ መስራት አልቻልንም›› ያለው ሳሙኤል፤ ብስክሌቶቹ በእግረኛ መንገድ ላይ ለመሄድ በመገደዳቸው ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ሲሆን ለጊዜና ለገንዘብ ኪሳራም ተጋልጠናል ሲል ያስረዳል፡፡
ከሰሚት ሲኤምሲ አደባባይ በብስክሌት ደርሶ መልስ 10 ደቂቃ ብቻ እንደሚወስድ የገለጸው ሥራ አስኪያጁ፤ እግረኛው መንገዱን ሞልቶ ስለሚይዘው ብስክሌት ተከራዮች ደርሶ መልስ 40 እና 50 ደቂቃ እንደሚፈጅባቸው ጠቁሞ በዚህም የተነሳ በ50 ደቂቃ ልናገኝ የሚገባንን ጥቅም ያሳጣናል ብሏል። ሳይክሎቹ በጣም ውድ ነው የተገዙት፤ ለአዋቂ የሚሆነው ሳይክል 42ሺህ ብር፣የህፃናቱ ደግሞ እያንዳንዳቸው 29 ሺህ ብር የፈጁ የቻይና ስሪቶች ናቸው ብሏል፡፡  
እስካሁን ለብስክሌቶቹ ታሪፍ ባይወጣላቸውም በ10 ደቂቃ ደርሶ ለመመለስ 10 ብር እንደሚያስከፍሉ የገለፀው ሳሙኤል፤ እግረኞች በፈጠሩት የመንገድ ችግር በ50 ደቂቃ 50 ብር ማግኘት ሲገባቸው፣10 ብር ብቻ እያገኙ መሆኑን ይናገራል፡፡ ‹‹መንገዱ የተሰራው ለብስክሌት ነው፤ በእግረኛ መንገድ ተጠቀሙ ብለን ስንናገር ከስድብ እስከ መደባደብ የሚጋበዘው ሰው ብዙ ነው›› ሲል ችግሩን አስረድቷል፡፡ መንግስት መፍትሄ ካላበጀላቸው እንዲህ ለመቀጠል እንደሚቸገሩም ሥራ አስኪያጁ አስረድቷል። 70ዎቹ ብስክሌቶች በጠቅላላ በ2 ሚ.375 ሺህ ብር የተገዙ ሲሆኑ መንግስት ለወጣቶቹ ሰርተው እንዲከፍሉ ነው የሰጣቸው፤ነገር ግን በዚህ አይነት ፈተና ውስጥ ሆነው የመንግስትን እዳ ለመክፈል እንደሚከብዳቸው ወጣቶቹ  ተናግረዋል፡፡
 የቀን ገቢያቸው እስከ 300 ብር የሚደርስ ሲሆን እሁድ እሁድ እስከ 700 ብር እንደሚያገኙ የጠቆመው ሳሙኤል፤ እሁድ ገቢው ከፍ የሚለው የብስክሌት መንገዶቹ በተወሰነ መልኩ ከእግረኛ ነፃ ስለሚሆኑ ነው ብሏል፡፡  
ብስክሌት የሚያከራዩት የቀበሌ መታወቂያ በመያዝ ሲሆን በተወሰነ ርቀት ላይ የማህበሩ ሰራተኞች እንደሚጠብቁና በከፍተኛ ቁጥጥር እንደሚሰሩ ሳሙኤል አስረድቷል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን ሶስት ተከራዮች ሶስት ብስክሌቶችን ይዘው የተሰወሩ ሲሆን ሁለቱ አሁንም ድረስ አልተገኙም። ሶስተኛውን ብስክሌት ይዞ የተሰወረው ግን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ አሁን  ማረሚያ ቤት እንደሚገኝና ጥቅምት 7 ቀን 2009 ዓ.ም ፍ/ቤት እንደሚቀርብ ተናግሯል፡፡
ሌላው የብስክሌቶቹ ችግር በአገር ውስጥ መለዋወጫ የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ እንኳን ሌላ መለዋወጫ ይቅርና የተገጠመላቸው ከለመነዳሪ ራሱ በጣም ስስና ጠባብ በመሆኑ ትንሽ እንደሰሩ ስለሚበላሹ፣ ከአገር ውስጥ ገበያ እያንዳንዱን በ120 ብር እየገዙ የሚቀይሩ ሲሆን  እስካሁን የ40ዎቹን ከለመነዳሪ እንደቀየሩ ወጣቶቹ ተናግረዋል። ‹‹አንዳንድ ተጠቃሚዎች እንችላለን እያሉ ቢስክሌት ይወስዱና እያጋጩ ይመልሳሉ›› ያሉት የማህበሩ ወጣቶች፤ በአነስተኛና ጥቃቅን የተደራጁ በመሆኑ ትርፍ ገንዘብ እንደሌላቸው ይገልጻሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ለመለዋወጫና ሌሎች ወጪዎች ገንዘብ ያጥረናል ብለዋል፡፡
ወደ ስራው ከመግባታቸው በፊት የተነገራቸውና ስራው ውስጥ ከበጉ በኋላ እየገጠማቸው ያለው ፈተና ከጠበቁት ውጭ እንደሆነባቸው የጠቆሙት ወጣቶቹ፤ መንግስት ለመንገዶቹም ሆነ ለብስክሌቶቹ ይህንን ያህል ብር ማውጣቱ ካልቀረ፣ብስክሌቹም ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ የገጠሙንን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ይፍታልን ሲሉ ተማፅነዋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ይህንን ዘገባ ለማጠናቀር በስፍራው በተገኘንበት ወቅት አራት ብስክሌት ነጂዎች ዋናው አስፋልት ላይ ሲነዱ በፖሊስ ተይዘው፣ ወደ ጣቢያ ሲወሰዱ ተመልክተናል፡፡ የብስክሌት መንገዶቹ መግቢያና መውጫው አካባቢ ብቻ መጠነኛ ምልክቶች ያላቸው ሲሆን የተወሰኑት ምልክቶችም መጥፋታቸውን ታዝበናል፡፡ መንገዱ ምንም አይነት መብራት ስለሌለው ብስክሌት አከራዮቹ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ስራ እንደሚያቆሙ ገልፀውልናል፡፡ ትንሽ መሸት ካለ ይዘው ለመሰወር የሚሞክሩ ግለሰቦች አሉ፤በቀንም አምነን መስጠት አልቻልንም ብለዋል ወጣቶች፡፡  
ከ49 ቁጥር ማዞሪያ እስከ ሀያት አደባባይ የሚዘልቀው የብስክሌት ትራንስፖርት፤ ‹‹ሙሉቀን ዘየደና ጓደኞቹ የብስክሌት ትራንስፖርት ህብረት ስራ ማህበር›› ይሰኛል፡፡ ከሰሚቱ ማህበር ጋር ተመሳሳይ ችግሮች ይጋራሉ፡፡ እግረኞች የብስክሌቱን መንገድ መጠቀማቸው፣ የብስክሌቶች ከለመነዳሪ የማይረባ መሆንና በወር ሁለት ጊዜ ቻርጅ መደረግ የሚፈልገው የብስክሌቶቹ ባትሪ ዋና ፈተና እንደሆነባቸው የተናረው የማህበሩ አባል ወጣት ዳግማዊ ታደሰ፤ ባትሪዎቹን ቻርጅ አድርገን ለመጠቀም መብራት ስላልሰጡን ተቸግረናል ብሏል፡፡ የብስክሌት መንገዱ ከመጥበቡ የተነሳ ሁለት ሳይክሎች ጎን ለጎን እንደ ልብ መሄድ እንደማይችሉ የገለፀው ዳግማዊ፤ የተወሰኑ ግጭቶች ተከስተው እንደሚያውቁ ተናግሯል፡፡ ብስክሌት ይዘው የሚሰወሩ ገጥሟቸው እንደሆነ ተጠይቆ ሲመልስ፤ ‹‹በየቅያሱ ቆመን በንቃት ስለምንጠብቅ እስካሁን ይዞ ለመጥፋት የሞከረ የለም›› ብሏል፡፡ የብስክሌቶቹ ከለመነዳሪ ስስነት እንደ ችግር ጠቅሶ፤  መንግስት ለችግሮቻቸው አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቋል፡፡
ሌላው የብስክሌት ማህበር ከቦሌ ጫፍ እስከ ኢምፔሪያል ሆቴል የሚሰራ ሲሆን የእነዚህ ወጣቶች ችግር ከሁሉም የከፋ ይመስላል፡፡ የመንገዱ አሰራር እንደ ሌሎቹ ራሱን የቻለ ሳይሆን ከዋናው አስፋልት በብሎኬት መሳይ ድንጋዮች የተከለለ ነው፡፡ መንገዱም ባለ አንድ መስመር  (One way) ነው፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ መከለያ ብሎኬቶቹ ተሰብስበው መንገድ ዳር ተከምረዋል፡፡ በብስክሌት መንገዶቹ ላይ መኪኖች ቆመው አይተናል፡፡ ባለፈው ረቡዕ የቢስክሌት ማህበሩ አገልግሎቱን አቋርጦ ነበር። የማህበሩን ተወካይ በስልክ አግኝተናት እንዲህ ብላናለች፤  “አንደኛ የብስክሌቶቹን ባትሪ ቻርጅ ለማድረግ መንግስት መብራት አልሰጠንም፡፡ አራት ሺህ ብር ተበድረን ከሰዎች መብራት ለመውሰድ ብንሞክምርም፣ ወረዳው የኤሌክትሪክ መስመር የለንም በሚል ሊተባበረን አልቻለም፡፡ በሌላ በኩል መንገዱ ለሁለተኛ ጊዜ ፈርሶ በመበላሸቱና ብስክሌት ነጂዎች አስፋልት ላይ ሲነዱ፣ አደጋ ቢደርስ ተጠያቂ እናንተ ናችሁ ስለተባልን፣ ፈርተን ስራውን ሙሉ በሙሉ አቁመናል፤ምክንያቱም ኢንሹራንስ የለንም። ቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 3 ችግራችንን እንዲፈታልን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም፣ ከላይ ጨርሳችሁ ስለመጣችሁ ስራችሁ ከወረዳችን ጋር አይገናኝም ብሎናል” ስትል ማህበሩ የገጠመውን አጠቃላይ ችግር አስረድታለች፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ለመጠየቅ ወደ አዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖት ቢሮ ብንሄድም፣“ኃላፊዎቹ ስብሰባ ላይ ናቸው” በመባሉ፣ ሀሳባቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡
የብስክሌት ትራንስፖርት ዋና አላማ፣የካርበን ልቀትን በመከላከል ለከተማዋ አማራጭ ትራንስፖርትን ማቅረብ ነው ተብሏል፡፡ እውነት ቢስክሌት ለሸገር፣ አማራጭ ትራንስፖርት ይሆናታል??    




Read 2360 times