Monday, 15 August 2016 09:14

የወልቃይት ጠገዴ ነገር

Written by  ዳንኤል ሺበሺ
Rate this item
(15 votes)

ይህ ጽሑፍ የ‹‹አረናው” አብርሃ ደስታ÷ በተከታታይ በማህበራዊ ድረ,ገፅ ላይ ላሰፈረው ሃሳብ የተሰጠ የግል አስተያየትና የሃሳብ ሙግት ነው፡፡
እኔና አብርሃ ደስታ÷ የህወሓት መንግስት በካቴና ሳያወዳጀን በፊት ትውውቃችን በሩቁ ነበር፡፡ ህወሓት ኢህአዴግ ሊያፈርስ አስቦ ሲገፋን ግን በወህኒ ቤት መካከል ሰራንና የልብ ወዳጅ ለመሆን በቃን፡፡ ‹‹ሊያፈርስ አስቦ የወጠነውን…›› እንዲል ዘፋኙ፣ በርግጥም በሃሳብ ልዩነት የምናምን፣ ሊያፈርሱን ሲያስቡ የተሰራን ሆነን ይኸው በሃሳብ ለመሟገት በቃን፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የገዘፈው የወልቃይት የማንነት ጥያቄ  ደግሞ የሃሳብ ሙግታችን ማዕከል ነው፡፡ እንግዳ ደራሽ ያልሆነውና ከህወሓት የፌደራሊዝም ምስረታ ማግስት ጀምሮ የወልቃይት ህዝብ በግፉዓንነት ስሜት 25 አመታት የዘለቀበትን የቅሬታ ልክ በጎንደር ሰማይ ስር እያየሁ በመኖሬ  ከፍ ላለው የአማራና የትግራይ ቁርሾ እና መሳሳብ እንግዳ አይደለሁም፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ዓላማ  የአብርሃ ደስታን የግል ሰብዕና፣ የፖለቲካ አመለካከትና አቋም መመርመር ወይም መተቸት ሳይሆን በወልቃይት ጉዳይ በፌስቡክ ገጹ ያስነበበንን ሃሳብ ማጥራትና መሞገትን ያለመ ነው፡፡ ሃሳቡን ስሞግት ቃላቶቼ የሃሳቡ ባለቤት ላይ ያነጣጠሩ ቢመስሉ እንኳ ነገሩ ግላዊ (Personal) ተደርጎ ግንዛቤ እንዳይወሰድ አደራ ሳልተው አልሻገርም፡፡
አብርሃ በቀዳሚነት ‹‹አማራና ትግራይ›› በሚል ርዕስ ባዘጋጀው ጽሑፍ፤ ‹‹ ወልቃይት የአማራ ወይም የትግራይ ነው በል እያሉኝ ነው፡፡ እኔ ግን የአማራ ወይም የትግራይ ነው አልልም›› በማለት ለምን ለማለት እንዳልፈለገ ጭምር ምክንያቶች አስቀምጧል፡፡ አንዱና መሰረታዊው፤ ‹‹የወልቃይት ጥያቄ የተፈጠረው በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እጦት ነው፣ የሚፈታውም ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር በመፍጠር እንጂ በመሬት አከላለል ወይም በአስተዳደራዊ ክልል ማሻሻል አይደለም የሚል ሲሆን፤ሁለተኛው ወልቃይት የራሱ የወልቃይት ህዝብ እንጂ የአማራ ወይም የትግራይ አይደለም፡፡ ማንኛውም መብት የወልቃይት እንጂ የአማራ ወይም የትግራይ ሊሆን አይገባም የሚል ነው፡፡›› አብርሃ ይሄንን ግንዛቤ የመያዝም ሆነ የማራመድ ህጋዊም ሞራላዊም የአመለካከትና ሃሳብን ያለማንም ጣልቃ-ገብነት በነጻነት የመያዝም ሆነ የመግለጽ መብት አለው የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡  ስለዚህ በያዘው ወይም ባራመደው ሃሳብ ምክንያት ሊሰደብና ሊወገዝ አይገባም፣ በሌላ በኩል ግን ያራመደው የመሟገቻ ሃሳብ ቀሊል ወይም {Ordinary argument} ነው የሚል እምነት ስላለኝ፣ ሃሳቡን እንደ ገና በመፈተሽ እንዲያቀናው አለያም ግልፅ አቋሙን የበለጠ እንዲያብራራው የኔን ሃሳብ ላዋጣ ወደድኩ፡፡
አብርሃ፤‹‹ወልቃይት የወልቃይት ነው›› ማለቱ በጥሬው ትክክል ነው፡፡ ይኸውም አድዋ የአድዋ ነው ወይም ጎንድር የጎንደር ነው እንደ ማለት እንደ ሆነ ግልፅ ነው፡፡ አድዋ የአድዋ ነው ከሚለው ቀጥሎ አድዋ የትግራይ ነው ወይም ጎንደር የጎንደር ነው ከሚለው ቀጥሎ ጎንደር አማራ ነው እንደሚባል ሁሉ፣ ወልቃይት የወልቃይት ነው ካለ በኋላ ወልቃይት-------ነው ከተባለ፣በክፍት ቦታው የሚቀረው መመለስ ያለበት የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ነው። ወልቃይት አማራ ነው ወይስ ትግሬ? አብርሃ ለዚህ መልስ አልሰጠህም፡፡ ለዚህ የምሰጠው መልስ ወደ ህወሓት ደረጃ ያወርደኛል የሚል አመክንዬ እንዳለህ የጠቆምክ ቢሆንም፣ ሃሳብህ ትልቁን የማንነት ጥያቄ ሳይመልስ እንዲሻገር መግፍኤ ስለሆነ መሟገቻህን ደካማ አድርጎታል፣ {Ordinary argument idea} ያልኩትም ለዚሁ ነው፡፡ በዚህ ከተስማማንና  አብርሃ ደፍረህ ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ከሰጠህ፣ ሌሎች አስተዳደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ታሪካዊ ዳራዎች… በቀላሉ መቋጫ ያገኛሉ ማለት ነው፡፡
ሌላው የወልቃይት ጥያቄ የሚመለሰው በዴሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን እንጂ በአስተዳደር አከላለል ይህም ማለት፡- የአማራ ነው ወይም የትግራይ ነው በማለት አይደለም የሚል ሃሳብ አለ። ይህም በጥሬው ትክክል ነው፡፡ የህዝብ ጥቅም የሚከበረው በሚፈረጅበት (በሚመደብበት) የክልል መሬት ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ነው የሚለው ሃሳብህም ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ለማምጣት መጀመሪያ ‹‹እኔ አማራ ነኝ›› የሚል ጥያቄ ይዞ መሬት አንቀጥቅጥ ተቃውሞ እያሰማ ያለው ህዝብ፣ ‹‹የታገልነው ደርግን ለመጣል እንጂ ትግሬ ለመሆን አይደለም›› የሚለው የእነ ኮለኔል ደመቀ ሃሳብ መልስ ሳያገኝ፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት አንድን ዘሎ ሁለት ማለት፣እንዴት አዋጪ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አኳያ የአብርሃ ሃሳብ ጎዶሎ ነው ብሎ መከራከር ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ሌላው በዚህ ፅሁፍ የተጠቀሰው፣ ዜጎች ወይም ነዋሪዎች የሰፈሩበት ወይም የሚኖሩበት አካባቢ ሁልጊዜም ቢሆን ማንነታቸውን ይወክላል ወይ? የሚል ጥያቄ የሚያጭር ሃሳብ ተስተውሏል፡፡ ለምሳሌ እንግሊዞች ወይም ህንዶች፤ በደቡብ አፍሪካ ስለ ሰፈሩ ወይም ስለ ኖሩ አፍሪካዊ ማንነት በግድ ይጫንባቸዋል ወይ? ብንል፣ በፍፁም!! ... የሚል መልስ እናገኛለን፡፡ ማንነት ለመጤው ሰፋሪ፣በቦታ ሲለካ የምርጫ ጉዳይ እንጂ ግዴታ እንደማይሆን ሁሉ የነባሩን ማንነት ቀይሮ በኔ ይጠራልኝ፣ በመረጥኩት ይከለልልኝ ማለት ደግሞ ፈጽሞ መልስ ወይም ፍትሃዊነት ሊሆን አይችልም፡፡  ለምሳሌ የ 1977 ቱን ድርቅ ተከትሎ ከወሎ እና ከትግራይ የተነሱ በደቡብና በኦሮሚያ የሃገራችን ክፍሎች በተለያዩ አካባቢዎች የስፈሩ ወሎዬዎችና ትግሬዎች አሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በሰፈራ መልክ ባይሆንም ለስራ ፍለጋ በሄዱበት አካባቢ ተላምደው፣ ባጠቃላይ ኑሮው ስለተመቻቸው በየክልሉ በቋሚነት ኑሮ መስርተው የቀሩም ብዙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በጋብቻ ተሳስረው ተዋልደው የሚኖሩ በመሆኑ ለመለየት (እነሱ ወይም አኛ ብለን) አስቸጋሪ እስኪሆን ደርሷአል፡፡ የተቀሩት የጎንደሬዎች፣ የወሎዬዎች ሰፈር ተብሎ በዛው በሚኖሩበት ሰፈር ከብረው ተዋልደው እስከ ዛሬ አሉ፡፡ ይህ ማለት ግን ግዛቱም ወይም አስተዳደሩም ወይም ብሄራቸው ወይም ሰው መሆናቸውን አይጋፋም ወይም አይቀይርም፡፡ ዴሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብታቸውን በአስተዳደር ችግር  ወይም በአምባገነንነት ካልሆነ በስተቀር የሚነጥቃቸው የለም፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንኳን የግል ይዞታ፣ንብረት ሀብት አፍርተዋል። የጋራ የሆኑ ነገሮችም አሉአቸው፤ነገር ግን መሬቱ ክልሉ የወላይታዎች፣ የሲዳማዎች፣ የጋሞዎች፣ የከንባታዎች፣የጂንካዎች እንጂ ብዙ አማራዎች መጥተው ስለ ሰፈሩ፣ ቁጥራቸው ከነባሩ ቢልቅ እንኳ እኛ ስለበዛን ወላይታ ወይም ሲዳማ - አማራ ክልል ይባልልን” የሚል የመብት ጫፍ ሊኖራቸው አይችልም፡፡ እንግሊዛውያን እና ህንዳውያን ከ400 ዓመታት በላይ የኖሩበትን ደቡብ አፍሪካን፣ እንግሊዝ ወይም ህንድ ይባልልን እንዳላሉ ሁሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ግን ወደ ቅኝ ግዛት ጥግ ካልሄደ እንደ ሆነ ግልፅ ነው፡፡
ወደ ተነሳነው ነጥብ ስንመለስ፤ህወሓት ለትውልድ የሚተላለፍ ፈንጅ መቅበሩን ሳንዘነጋ ግን በቂ ምላሽ የሚሹ ነገሮች መኖራቸውን መካድ የለብንም፡፡ እንደው ዝም ተብሎ በኢትዮጵያዊነት፣ በሀገር አንድነት ስም ሸፋፍነን ማለፍ አለብን ብዬ አላምንም፡፡  ስለዚህ ቀጥሎ ያሉትን ጥያቄዎች አብርሃ መመለስ ይጠበቅበታል፡፡
1ኛ. ወልቃይት ጠገዴ እና አሁን ጭቅጭቅ ያለባቸው ሌሎች ይዞታዎች ከታሪክ እና ከሃቅ አንፃር መሬቱ የጎንደር ነው ወይስ የትግራይ? የጎንደሬዎች ነው ወይስ የትግሬዎች? ከህወሓት ኢህአዴግ አስተዳደር በፊት ማለቴ ነው፡፡ ለምንድነው ይሄን ያልኩት፣ ኢህአዴግ ላለፉት ሃያ አምስት አመታት በግድ ሲገዛን ካከወናቸው ክንውኖች ውስጥ ብዙዎችን ያለመቀበላችን ምክንያት እኔና አንተን ለትግል አደባባይ ያስወጡ፣ የኢትዮጵያን ህዝብን ለምሬት ያበቁ በርካታ የማንቀበላቸው በታኝ እና ጨፍላቂ አጀንዳዎች እንዳሉት ግልፅ ነው፡፡
ለምሳሌ፡-
ህወሓት የሸለመንን ባንዲራ፣
በሀገሪቱ ካርታና ወሰን ወይም ድንበር አከላለል፤
የህዝብ ቁጥርን በመረጠው መንገድ ከፍ ዝቅ ማድረጉ፤
በብሔር ስያሜ እና ትርጉም  ላይ የህወሓትን ፍላጎት ብቻ በግድ መጫኑ፣
ኢትዮጵያን ያለ ባህር በር ማስቀረቱ፣
ባህልና ቋንቋን ከማንነት ጋር ያያዘበት ሁኔታ ለህወሓት የፖለቲካ ጥቅም ያለመ ብቻ መሆኑ፤
ፍትህ፣ ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብትን ማዳፈኑ፣ ባጠቃላይ ህወሓት በፌደራሊዝም ስም ከፋፍሎ እየገዛና የአንድ መንደር ልጆች ጥቅም ለማስከበር እየተጋ ያለ ጨቋኝ ቡድን መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ቀጥሎ ለተዘረዘሩትን ጥያቄዎች ምላሽ ብትሰጥባቸው መልካም እንደ ሆነ ይሰማኛል፡፡  
1ኛ. የህወሓት አገዛዝ የሚመቸውን አይነት የቋንቋ ፌደራሊዝም በግድ ከመጫኑ በፊት ወልቃይት ከጎንደር ግዛት ውጪ በሌላ የተዳደረበት የታሪክ ማስረጃ ካለ ቢቀርብ/?
2ኛ ህዝቡ (ወልቃይቶች) እያነሱት ካሉት ጥያቄዎች ውስጥ ዋነኛው የኛ ማንነት ጎንደሬነት (አማራነት) ነው የሚል ሆኖ ሳለ፣ ጥያቄያቸው የሚፈታው በአስተዳደራዊ መንገድ ነው ሊባል ይችላል?፡
3ኛ በህገ መንግስት የሰፈረ ቢሆን እንኳ ህዝብ በማንኛውም ጊዜ ጥያቄ ካነሳ ጥያቄውን ከመመለስ በቀር መንግስት ህግ አይፈቅድም በማለት የህዝብን መብት ማፈን እንደሌለበት ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ህወሓት ስልጣን በያዘ ማግስት ወደ ትግራይ ግዛት የከለለው የወልቃይት መሬት የትግራይ ነው ተብሎ በህግ ተጽፏል በማለት ክልከላ ማድረግ እና የህዝብን ጥያቄ ማፈንን እንዴት ታየዋለህ?
4ኛ ‹‹የወልቃይት ጥያቄ የማንነት ወይስ የአስተዳደራዊ ጥያቄ›› በሚል ርዕስ ስር ባሰፈርከው ክፍል ላይም የህዝቡን ጥያቄ በመብት፤ በዴሞክራሲና በማንነት ጥያቄ ዙርያ መሆኑን አምነህ ስታበቃ ግን የወልቃይት ጥያቄ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሊፈታ እንደሚችል አስምረሃል። ያልመለስከው ባድመን፤ አሰብ… ወ,ዘ,ተ የኢትዮጵያ እንደ ሆነ ሁሉ ወልቃይትም የኢትዮጵያ መሆኑን አልዘነጋሁም፡፡ ይህም ማለት አንተም እንዳልከው፤ ወልቃይት የኔም (ዳንኤል ሺበሺ ) ነው፡፡ የኢትዮጵያ መሆኑን ከተቀበልን ደግሞ እንደ አሁኑ አገዛዝ፣ በቋንቋ ሳንታጠር በአካባቢው መኖር እንደሚቻል ይገባኛል፡፡ ነገር ግን አሁን ከህዝብ እየተነሳ ካለው ጥያቄ አን|ፃር ወልቃይት የማን ይዞታ ነበር ለሚለው ግልፅ ምላሽ ብትሰጥበት ?
ሳጠቃልለው፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ በባድመ፤ ፓላስታይን እና እስራኤል ስለ እየሩሳሌም እንደሚሻኮቱ እና ደም እንደሚቃቡ ሁሉ በወልቀይት ጉዳይ ሌላ ባድመ እንዳይፈጠር ስጋት አለኝ፡፡ በፍፁም ህወሓት በዘረጋው ፈንጂ ላይ መሮጥ የለብንም፤ስለዚህ መፍትሄው ሃቁን አምኖ መቀበል ነው፡፡ ሃቁን ከተቀበልን በኋላ እንዴት በዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ማስታረቅ ወይም ለአንድነታችን የሚበጀው እንዴት ብንጠቀምበት ነው በሚል ወደ ውይይት መግባት ይቻላል፡፡ በታሪክ እንደሚታወቀው፤ትግራይ በረጅም የታሪክ ዘመን ከሌላው የሀገራችን አካባቢዎች በሄዱ የፖለቲካ አመራሮች ተዳድራ አታውቅም፡፡ ዛሬም ቢሆን የህወሓት ልጆች ትግራይን ሙሉ ለሙሉ ይዘው ሲያበቁ፣ ለተጨማሪ መስፋፋት ወደ ሌላው ግዛት እጃቸውን እያስገቡ ሀገሪቷን ወዳልተገባ ቀውስ እየከተቱ መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡  ከዚህ በመነሳትና እውነተኛ የታሪክ መሰረቶችን በመቀበል ብቻ ህወሓት በወልቃይትም ጉዳይ የጉልበትና የሴራ ነገር መጠቀሙን በድፍረት መተቸት የሚቻል ይመስለኛል፡፡
እንደሚታወቀው ከደርግ ማግስት ጀምሮም የትግራይን ክልል የሚያስተዳድረው የሌላ አካባቢ ተወላጅ ሳይሆን የህወሓት ቡድን ነው፡፡ በተለይም የሌላው አካባቢ ተወላጅ ወደ ትግራይ አካባቢ ዝር ባላለበት ሁኔታ፣ የትግራይ ልሂቃን ወይም የህወሓት ወኪሎች መላውን የደቡብ  ግዛት፤ ኦሮሚያን፤ ጋንቤላን፤ አፋርን… ወ.ዘ.ተ  ያስተዳድሩ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን በቀጥታና በተዘዋዋሪ በማስተዳደር ላይ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም የፌደራል መዋቅሩም ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ፤ በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ኢትዮጵያ በምትወከልበት የኃላፊነት ቦታዎች፣ በኤምባሲዎች እና በዲፕሎማቲክ መደቦች፣ በትላልቅ የንግድ ተቋማት፣ ኩባንያዎች እና ኢምፓየሮች፤ በአስመጪነት እና በላኪነት፣ በግንባታ ኮንትራክተርነት፣ በማዕድን ኩባንያዎች፣ በመሬት ይዞታዎች… ወ.ዘ.ተ በትግራይ ግዛት ላይ ጨምረውና ደርበው እንደ ያዙ የታወቀ ነው፡፡  ይህ የሆነው ግን ከሌላው አካባቢ ሃገር መምራት የሚችል ብቁ እና ንቁ ዜጋ ስለታጣ ወይም ሌሎች  እንደ ህወሓት የቅንጦት ኑሮ ስለሚጠሉ አይደለም።  
ዋነኛ መንስዔው ህወሓቶች፡-ጠቅላይነት፣ ዘረኝነት፣ ጦረኝነት፣ ኢ,ፍትሃዊነት እና አምባገነንነት ስለተጠናወታቸውና ሌላውን በጠላትነት ፈርጀው በአንድ ቡድን ስለተቆጣጠሩት እንደ ሆነ ግልፅ ነው። በዚሁ መሰረት አብርሃ፤ይህንን እኩይ ተግባር ከዚህ ቀደም ፊት ለፊት ተጋፍጠህ ለእውነት በመቆም መከራ እንደ ተቀበልክ ሁሉ፣ በወልቃይት ጉዳይም ፊት ለፊት ልትጋፈጠው ይገባል የሚል እምነት ስላለኝ፣ ይህንን አስተያየት ፅፌያለሁ፡፡ በቀና እንደምታየው ፅኑ እምነት አለኝ፡፡
የታሪክ ደርሳናት፤ የመስኩ ምሁራን፣ በቀደሙት ስርዓት አካባቢውን ያስተዳድሩ የነበሩ ባለስልጣናት እና አዋቂ ሰዎች ስለ ወልቃይት ይዞታና ማንነት የሰጡትን ምስክርነት መመርመር ይገባል፡፡ ይህ ምስክርነት ወደ እውነት ይመራናል የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡  …. አብርሃ አንተም እንዳልከው በኢትዮጵያዊነቴ ወልቃይት የኔ ነው፤እኔም የወልቃይት ነኝ፡፡ ‹‹የአክሱም ሃውልት ለወላይታ ህዝብ ምኑ ነው›› እንደሚለው የመለስ አፍራሽነት ልገዛ አልችልም፤ የወልቃይትን ህዝብ ጥያቄና ትግል የማከብረውና ከጎናቸው ለመቆም የምፈልገው ለዚሁ ነው፡፡ ቸር ያሰማን…




Read 12136 times