Monday, 15 August 2016 09:21

የብራዚሏ ፕሬዚዳንት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተወሰነባቸው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

     የብራዚል ምክር ቤት አባላት ባለፈው ረቡዕ ባደረጉት ስብሰባ፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዲልማ ሩሴፍ፤ከታክስና ህጋዊ ካልሆነ ወጪ ጋር በተያያዘ በቀረበባቸው ውንጀላ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ በአብላጫ ድምጽ መወሰናቸውን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንቷ ለፍርድ ይቅረቡ ወይስ አይቅረቡ የሚለውን ለመወሰን የምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ድምጽ፣ 59 ያህሉ ለፍርድ ይቅረቡ ሲሉ፣ 21 ያህሉ ደግሞ አይቅረቡ በሚል ድምጻቸውን መስጠታቸውን የጠቆመው ዘገባው፤  ጉዳዩ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ በፍርድ ቤት መታየት ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጧል፡፡
ሩሴፍ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እ.ኤ.አ ከ1930ዎቹ ወዲህ ወደ ከፋ ዝቅጠት እያመሩት ነው በሚል ሲወነጀሉ መቆየታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ፕሬዚዳንቷ የቀረቡባቸውን ክሶች በሙሉ ክደው በመከራከር ለፍርድ እንዲቀርቡ መወሰኑ እሳቸውን ከስልጣን ለማውረድ የሚፈልጉ ሃይሎች ሴራ ነው ማለታቸውን አስረድቷል፡፡ ፕሬዚዳንት ሩሴፍ በቀረቡባቸው ክሶች ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ሙሉ ለሙሉ ከስልጣናቸው ይነሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፤ተቀናቃኛቸው ፕሬዚዳንት ሚሼል ቴመር በጊዚያዊነት አገሪቱን መምራት ይቀጥላሉ መባሉን ገልጧል፡፡
የአሜሪካው ሴናተር በርኒ ሳንደርስ በበኩላቸው በድረገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ፕሬዚዳንቷ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መወሰኑን በመቃወም፣ጉዳዩ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡትን ፕሬዚዳንት ከስልጣን ለማስወገድ ታስቦ የተደረገ ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው ማለታቸውን ዘ ኢንኩዚተር ዘግቧል፡፡

Read 1174 times