Monday, 15 August 2016 09:23

የአሜሪካ ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣናት፤ ትራምፕ ለአገሪቱ ህልውና አደጋ ናቸው አሉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ለትራምፕ ድምጻቸውን ላለመስጠት ተፈራርመዋል
   50 የቀድሞ የአሜሪካ ከፍተኛ የብሄራዊ ደህንነት ባለስልጣናት፣ አነጋጋሪው የአሜሪካ ዕጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ በምርጫው በለስ ቀንቷቸው የሚመረጡ ከሆነ የአገሪቱን ብሄራዊ ደህንነትና ህልውና አደጋ ላይ ይጥላሉ ማለታቸውን ኒውዮርክ ታይምስ ዘገበ፡፡
የሪፐብሊካን አባላት የሆኑት እነዚሁ ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣናት ለኒውዮርክ ታይምስ በጻፉት ደብዳቤ፣ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን የባህሪ፣ የእውቀትና የልምድ እጥረት እንዳለባቸውና ብቁ እንዳልሆኑ ገልጸው፣ በምርጫ አሸንፈው ስልጣን የሚይዙ ከሆነ የአገሪቱን ብሄራዊ ደህንነት የከፋ ችግር ላይ ይጥላሉ ብለዋል፡፡
ትራምፕ በምርጫው የማሸነፍ ዕድል ካገኙ፣በአሜሪካ ታሪክ እጅግ ግድየለሹና እንዝህላሉ መሪ ይሆናሉ ያሉት የደህንነት ባለስልጣናቱ፤ ሰውዬው የአገሪቱን ህገ መንግስት በቅጡ ስለማወቃቸውና በህገ መንግስቱ ስለማመናቸው እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጉዳዮችን በቅጡ ስለመረዳታቸው እንጠራጠራለን ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል፡፡
እነዚሁ የቀድሞ የአሜሪካ ከፍተኛ የደህንነት ባለሙያዎች በምርጫው ድምጻቸውን ለትራምፕ ላለመስጠት መወሰናቸውን በደብዳቤያቸው ማስታወቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ከ100 በላይ የሪፐብሊካን የብሄራዊ ደህንነት ባለሙያዎች በተመሳሳይ መልኩ ትራምፕን በመቃወም የጋራ ደብዳቤ መጻፋቸውንም አስታውሷል፡፡

Read 4197 times