Monday, 15 August 2016 09:29

የኢትዮ-ትሬል 3ኛው የተራራ ላይ ሩጫ ሁለገብ ስኬት ነበረው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(5 votes)

     ባለፈው ሳምንት ከአዲስ አበባ 200 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በአርሲ ነገሌ በሚገኙት የአብያታና ሻላ ሀይቆች ዙሪያ ገብ በሚያካልለው ብሄራዊ ፓርክ በ12 ኪ.ሜ እና በ21 ኪ.ሜ የተካሄደው የተራራ ላይ ሩጫ ሁለገብ ስኬት ነበረው፡፡
የተራራ ላይ ሩጫውን ያዘጋጀው ሪያ ኢትዮጵያ ሲሆን ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፣ ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ከኢትዮጵያ የዱር ሀብት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ነው፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ዙሪያ የሚገኙ ኃይቆችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ በተያዘ መርህ ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ በሪያ ኢትዮጵያ አዘጋጅነት የተካሄደው የተራራ ላይ ሩጫው በከፍተኛ ደረጃ እድገት እያሳየ ይገኛል፡፡
ሪያ ኢትዮጵያ የተራራ ላይ ሩጫውን በ3 ዓይነት ርቀቶች በ12፣ በ21 እና በ42 ኪ.ሜ ያካሂዳል፡፡ ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ ሲካሄድ ግን ባለፉት 2 ዓመታት የተከናወነው የ42 ኪ.ሜ ውድድር አልተደረገም፡፡ ዋና ምክንያቱም በዕለቱ የነበረው የአየር ሁኔታ ምቹ ሆኖ ባለመገኘቱ ነው። ለ42 ኪ፣ሜ በተዘጋጀው የመሮጫ ጎዳና 10 ኪ.ሜ ያህሉ በዘነበው ዝናብ በጭቃ ተበላሽቶ ስለነበር ተሳታፊዎች ቢኖሩም አዘጋጆቹ ውድድሩን በመጨረሻው ሰዓት ለመሰረዝ ግድ እንደሆነባቸው ገልፀዋል፡፡  
የተራራ ላይ ሩጫው በአብያታ እና ሻላ ኃይቆች ዙሪያ ገብ በሚገኘው ብሄራዊ ፓርክ ሲካሄድ ዓለም አቀፍ ትኩረት አግኝቶ ነው፡፡
በመልክዐ ምድሮቿ ውበትፈ እና በታላላቅ ሯጮቻ የምትታወቀው ኢትዮጵያ ልታዘጋጀው የሚገባ ውድድር መሆኑን በውድድሩ ላይ የተሳተፉ የውጭ ዜጎች ገልፀዋል፡፡
ታላቁ የስምጥ ሸለቆ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ እስከ ታችኛዋ ማደጋስካር እስከ ሶርያ እንደሚዘልቅ የሚታወቅ ሲሆን፤ የተራራ ላይ ሩጫው የሚካሄድባቸው አብያታና ሻላ ሀይቆች ብቻ ቢሆኑም ላንጋኖ፣ ዝዋይ፣ ጫሞ፣ አባያ እና ሀዋሳ በስምጥ ሸለቆው ዙሪያ የሚገኙ ሌሎቹ ሃይቆች ናቸው፡፡
በአብያታና ሻላ ሀይቆች ዙሪያ ገብ የሚገኘው ብሄራዊ ፓርኩ 887 ስኩዌር ኪ.ሜ የሚሸፍን ሲሆን ኃይቆቹ ደግሞ 482 ኪ.ሜ ስፋት አላቸው፡፡ ከአፍሪካ ኃይቆች በጥልቀቱ የሚጠቀሰው ሻላ በ226 ሜትር ጥልቀት ያስመዘገበ ሲሆን የአብያታ ጥልቀት ደግሞ 14 ሜትር ነው፡፡
በብሄራዊ ፓርኩ የፔሊካንና የፍላሚንጎ አዕዋፋት ዝርያዎች በብዛት ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የአዕዋፍት ዝርያዎች ግማሽ ያህሉ ማለትም ከ400 በላይ የአዕዋፍት ዝርያዎች በሀይቆቹና ዙሪያ ገብ ብሄራዊ ፓርክ የሚገኙ ሲሆን ዝንጀሮ፣ አጋዘንና ሌሎች የዱር አራዊቶችም አሉ፡፡
በሁለቱ ኃይቆች መካከል ደግሞ ትልቁ ተራራ ፍቄ ይስተዋላል፡፡ በሪያ ኢትዮጵያ የሚዘጋጀው የተራራ ላይ ሩጫው በሁሉም ኃይቆች እና በዙሪያ ገቡ ብሄራዊ ፓርክ ያሉትን የዱር አራዊቶችና፣ የተፈጥሮ ሀብቶች ለመጠበቅ እና ለመንከባከብ የሚካሄድ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
በ12 ኪ.ሜ ሩጫው በመሳተፍ የተራራ ላይ ሩጫው በማራኪ የተፈጥሮ ድባብ፤ በሚያስደንቅ የአካባቢው ህዝብ ድጋፍ እና ተሳትፎ፣ በአስቸጋሪና ፈታኝ መልክዓ ምድር የሚካሄድ መሆኑን ለመገንዘብ ያስችላል፡፡
በ12 ኪ.ሜ የተራራ ላይ ሩጫው በሐይቆቹ ዙሪያ ያለው ማራኪ የተፈጥሮ ሀብትና መልክዐ ምድር፤ ንፁህ አየር፣ ጎንና ጎናቸው በበቆሎ ማሳዎች የተሸፈኑት የመሮጫ ጎዳናዎች፣ በየቦታው ቆመው በጭብጨባና በፉጨት ሯጮችን የሚያበረታቱ የአካባቢው ህዝቦች፤ አሸዋማው የመሮጫ ጎዳና የውድድሩ ገፅታና ድምቀት የፈጠሩ ናቸው፡፡ በየቦታው የሚሰማው የተለያዩ አዕዋፋትና ዝማሬ ለውድድሩ ማራኪ ድባብን አላብሶታል፡፡
በሪያ ኢትዮጵያ አዘጋጅነት በአብያታና ሻላ ሀይቆች ዙሪያ ገብ ብሔራዊ ፓርክ የተካሄደውን የተራራ ላይ ሩጫ ለመዘገብ ከ20 በላይ የመንግስትና የግል መገናኛ ብዙሀናት ጋዜጠኞች ነበርን፡፡
በ12 ኪ.ሜ ሩጫው የተወሰንን የስፖርት ጋዜጠኞችም ተሳትፈናል፡፡ የሰንደቅ ጋዜጣ ስፖርት አምድ አዘጋጅና በኤፍ ኤም 97.1 አዲስ ዜማ ሬዲዮ ፕሮግራም አቅራቢ የሆነችው ቆንጂት ተሾመ በተራራ ላይ ሩጫው እንድንሳተፍ ያስተባበረች እና ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ በመጨረስ ለመሸለም የበቃች ነበረች፡፡ በ12 ኪ.ሜ ሩጫው ከቆንጂት ተሾመ ጋር እኔን ጨምሮ፣ የስፖርት ዞን አዘጋጅ ሰይድ ኪያር፣ የሪፖርተር ስፖርት አምድ አዘጋጅ ደረጃ ጠገናው ተሳትፈናል፡፡ በሩጫው በመሳተፋችንም ለውድድሩ ያለን ግንዛቤ አሳድገናል፡፡
ከአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀናት ባሻገር ከ4 የተለያዩ አገራት የመጡ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው የሚዲያ ባለሙያዎችም ነበሩ፡፡ ከአሜሪካ ታዋቂው የአትሌቲክስ ዘጋቢ መፅሄት “ኮምፒውቴተርስ”፤ ከስፔን በተራራ ላይ ሩጫ ውድድሮች አተኩሮ በመስራት የሚታወቀው መፅሄት “ትሬይልድ ራን”፣ ከጀርመን ታዋቂው የአትሌቲክስ መፅሄት “ራኒንግ” እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካ በፍሪላንስ ጋዜጠኝነት ለበርካታ የስፖርት ሚዲያዎች የሚሰራ ባለሙያን ይገኙበታል፡፡
የተራራ ላይ ሩጫው አዘጋጆች ከባለ ድርሻ አባላት ጋር በመሆን በላንጋኖ ሀይቅ ዳርቻ በሚገኘው የሲንቦልኔ ሪዞርት በሰጡት መግለጫ ውድድሩ ሁለገብ ስኬት እንደነበረው የሚያረጋግጡ አስተያየቶች ሰጥተዋል፡፡
የክልሉ የባህልና ቱዝም ቢሮ ኃላፊ በመግለጫ እንደተናገሩት በክልሉ ያለውን ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብትና የባህል እሴቶች ለማስተዋወቅ የተራራ ላይ ሩጫው ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቅሰው ለቱሪዝም እንቅስቃሴው መጠናከር እና ለቱሪስቶች ብዛት መጨመር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውና ክልሉን በቱሪዝምና በባህል እሴቶች በማስተዋወቅ እና በማነቃቃት መጠነ ሰፊ እድሎችን መፍጠሩን አውስተዋል፡፡ በውድድሩ ላይ ላሸናፊዎች ሽልማት ሆነው የቀረቡ የተለያዩ ስጦታዎችን የክልሉን የቱሪዝም ሀብትና የባህል እሴቶችን የሚገልፁ መሆናቸውና የተሰሩትም በአካባቢው ወጣቶች መሆኑ እንደውጤት ይቆጠራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የዱር ሀብት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ከፍተኛ ኃላፊ በበኩላቸው የተራራ ላይ ሩጫው ከተጀመረ ገና 3ኛ ዓመት መያዙን አስታውሰው አዘጋጁ ሪያ ኢትዮጵያ ከባለድርሻ አባላቱ ጋር ተቀናጅቶ በመስራት በስኬታማ መንገድ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አድንቀዋል፡፡
የተራራ ላይ ሩጫውን በአገሪቱ የሚገኙ ፓርኮችን በመጠበቅና የተፈጥሮ ሀብቶቻቸውን በመንከባከብ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው በመጥቀስም ከሪያ ኢትዮጵያ ጋር ለሚቀጥሉት 2 ዓመታት በመሥራት በባሌና ሰሜን ተራሮች ለሚኙ ብሄራዊ ፓርኮቹ ተመሳሳይ ውድድሮች ለማዘጋጀት እቅድ አለን ብለዋል፡፡
የተራራ ላይ ሩጫ በዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛ ግምት እየተሰጠው መምጣቱን ከትራክና የጎዳና ላይ ውድድሮች እኩል በአጭር ጊዜ ታዋቂነትና ተወዳጅነት ማትረፉን የጠቀሰው አትሌት ገ/እግዚአብሄር ገ/ማርያም በዓለም ሻምፒዮና ደረጃ መዘጋጀት በመጀመሩ ተስፋ ፈጠሮልናል የሞል አስተያየት ሰጥቷል፡፡
በኬንያ እና በደቡብ አፍሪካ የሚካሄዱትን መሰል ውድድሮች ተምሳሌት አድርገን ብንነሳም የተራራ ላይ ሩጫን በተሻለ ደረጃ በኢትዮጵያ ማዘጋጀት እንደሚቻል አምነንበታል ያለው አትሌት ገ/እግዚአብሔር፣ የተራራ ላይ ሩጫውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ባለፉት 3 ዓመታት የተከናወኑ ተግባራት ሰፊ እውቅና መፍጠራቸውን ገልጿል፡፡
የተራራ ላይ ሩጫ በዓለም ሻምፒዮና ደረጃ መዘጋጀቱ የሪያ ኢትዮጵያ ውድድርን ደረጃ በማሳደግና የተሳታፊ አትሌቶችን ብዛት በመጨመር ማደጉን ይቀጥላል ያለው አትሌቱ፤ የኢትዮጵያ አትሌቶች አትሌቶች በተራራ ላይ ሩጫ የዓለም ሻምፒዮና ውድድርም ስኬታማ የሚሆኑበትን  ዕድል ይፈጠራል ብሏል፡፡
የሪያ ኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ቃለአብ እንደሚናገሩት፤ የተራራ ላይ ሩጫውን ደረጃ ለማሳደግ ለሶስት ዓመታት በተካሄዱት ውድድሮች ከፍተኛ ልምድ የተገኘ ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከውጪ የውድድር ዝግጅት ባለሙያዎችን በማምጣት፣ በተራራ ላይ ሩጫ የተሳካላቸው ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው አትሌቶች ጋብዞ በማሳተፍ፣ የዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸውን ሚዲያዎች በአካል ተገኝተው ሽፋን እንዲሰጡ ሁኔታዎችን በማመቻቸት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተራራ ላይ ሩጫው አብይ ስፖንሰር በመሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከውጭ ለመጡ ተሳታፊዎች ነፃ የበረራ ትኬቶችን በማቅረብ፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ለውጭ ሚዲያዎች አስፈላጊውን የጉዞ ወጪ በመሸፈን ላደረጉት አስተዋፅኦ ምስጋና ያቀረቡት አቶ ቃለአብ፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተራራ ላይ ሩጫው በኢትዮጵያ ከፍተኛ አቅም መኖሩን በመገንዝብ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው አበረታቶናል ብለዋል፡፡
በ12 ኪ.ሜ ሩጫው የተሳተፉት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ታደሰ ኢትዮጵያ በሩጫ ቱሪዝም በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ እንደምትሆን በማመን (Land of origins) በሚል በጀመርነው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ስፖርቱን በአጋርነት በመያዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ሪያ ኢትዮጵያ በቀጣይ በላንጋኖ ሀይቅ ዙሪያ በብስክሌት፣ በውሃ ዋና እና በሩጫ ውድድሮች የሚታጀበውን ትራያትሎን ለሁለተኛ ጊዜ የሚያዘጋጁ ሲሆን የወንጪን ሀይቅ ለመታደግ ግንዛቤ በሚያስጨብጥ ውድድር ለመስራትም እቅድ አለው፡፡ በዚህ መሰረትም ከወራት በኋላ የ17 ኪ.ሜ የበጎ አድራጎት ሩጫ እና የርምጃ ውድድር እንደሚያካሂድ ለማወቅ ተችሏል፡፡


Read 2885 times