Monday, 15 August 2016 09:40

የአበረ አያሌው ‹‹ፍርድ እና እርድ›› ግጥሞች

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

ሽርክት- ግጥሞች ዓመቱን ሙሉ ያበሽቁን የነበረበት ጊዜ -እያበቃ፣ በአዲስ ዘመን ጨረሮች ውስጥ በውበት የተጠቀለሉ በከፍታ የሃሳብ ሰረገላ-ደመና የሚቧጥጡ ገጣሚያንን ማየት ጀምረናል፡፡ ቆሽት የሚያሣርሩ ብቻ ሳይሆን አንጀት የሚያርሱ ገጣሚያን አደባባዮቻችን ምንጣፍ ላይ መራመድ ጀምረዋል፡፡ የከያኒያን እሸት ልቦች በጥበብ ችቦ እየደመቁ፤ ተደራሲያንን ቀልብ መግዛት አልቻሉም ብሎ መካድ፣ ከራስና ከውበት ጋር መጣላት ነው። ምናልባትም አንዳንዶቻችን በድሮ ቀረ አባዜ ተለክፈንበት፣ ያንኑ አሮጌ ታንቡር እየደበደብን ከሆነ አዲሱን መዝሙርና ቅኝት ሊሠማ የሚገባው ጆሮዋችን በጠጠር ተደፍኗል፤ ፈውሥ ያሥፈልገዋል። ሌላው ቀርቶ በወረቀት ላይ ግጥሞች በዘለለ፤ አደባባይ ላይ በመነበብ ላይ ያሉት ግጥሞች ማሥደመም ጀምረዋል፡፡ የአንዳንዶቹ ሃሳቦች በእጅጉ የተለቁና ጥልቅ አተያይና ፍልስፍና የተመሉ ናቸው፡፡ በተለይ ሁለንተናዊ ውበትን ቢጎዳኙና ቀዳዳዎቻቸውን በሥነ- ግጥም ሣጋዎች ቢሸጡት ኖሮ ተዐምር የምናደምጥበት ዘመን ነበር፡፡… ብቻ ዘመኑ ለግጥም መጥፎ አይደለም!... በተለይ አንዳንዶቹ…
የዘመኑን ጥቅል ሃሳብ የነካካሁት -ከዘመኑ መካከል አንድ ችቦ ያቀጣጠለውን የገጣሚ አበረ አያሌው- ግጥሞች (በተለይ ሃሳባቸውን) ለመዳሰስ ስለፈለግሁ ነው፡፡ የአበረ ግጥሞች ባብዛኛው ማሕበረሰባዊ ልማዶችን፣ የእምነት ተቋማትና መሪዎችን፤ አለው አልፎ የፖለቲካ መልኮችን ይዳሥሣሉ የሚወደዱም ናቸው፡፡ እኔ በበኩሌ ግን እምነት ነክ በሆኑትና የፍልስፍና ጥያቄዎቹ ይበልጥ አንዳንዴ ኤፍሬም ሥዩም በቁጥጥር 1 ሲደዊ በእንደቶኔ ዘይቤ ዳንዳ ላይ ሆኖ ፈጣሪን የሚያወራው ወሬ አይነት… ለምሳሌ፡-
ምን ትላለህ አንተ?
ሀይማኖት ሲዋለድ ፍቅር እንዴት ሞተ?
ከቀዳሾችህ ልብ የድሆችን ለቅሶ ማነው የጎተተ?
እግዜር ሆይ አደራ
አንተም እንደ ነሱ -ጥያቄ ለማምለጥ ሰይጣንን አትጥራ
‹‹ለሰበብ አስባቡ- መልስ ነኝ…›› እያለ እሱም እንዳይኮራ፡፡
‹‹ግብረ ይሁድ›› ከሚለው ግጥሙ መሀል ነው  እነዚህን ስንኞች የተዋስኩት፡፡ ሃይማኖት ቁጥሩ በዛ፤ ፍቅር ከሰው ልብ ሞተ፣ ቀዳሾችህ ወይም የሃይማኖ መሪነን የሚሉት ሰራተኞች፤ ልባቸው ውስጥ የድሀ ልቅሶ ደርቆ ጠጠር ሆኗል፡፡ ደጁንም አይረግጥም፤ በሌላ ትርጓሜ፤ የሀብታሞች ዕብሪት የቅንጦተኞች ሙዚቃና ዳንስ ተሞልቷል፤ በቪላ ሥዕሎች ተገጥሟል፤ እንባ የሚሰማ ልብ የላቸውም። የሀብታም ሣቅ የገደል ማሚቱ ናቸው የሚል ይመሥላል፡፡ እና ይህንን ምን አመጣው?... እያለ እግዜርን ጠይቆ መልሱ የእነርሱን መስሎ ‹‹ሰይጣን አሣሥቷቸው ነው›› በማለት ያንገሸገሸውን መልስ እንዳይመልስለት ይንገፈገፋል፡፡… ተደጋጋሚ ነገር ያቆሠለው ይመሥላል ገፀባህሪውን!
እነዚህ ዓይነት ግጥሞች ጥቂት አይደሉም። አሁንም ጥቂት ስንኞች መዋሴ አይቀርም፡፡ ስንኞቹ ክፍት ሥንኝ የሚባሉ ዓይነት ስለሆኑ ቢያስቸግሩም ነጠል አድርጌ ‹‹ቶሎና! ሣይሆን ቤትህ ኦና››ከሚለው ርዕስ ልዋስ፡፡
ካላየ ነው ሰፈር ካልሰማነው መንደር -ፈጠው እየመጡ
አገልጋይ በሚል ስም አገልግል ሊያበስ ካናት እየወጡ
‹‹ና ልን…›› ለሚል ህዝቡ…›› ልኮናል…›› እያሉ በሚያስጎበድዱ
ማሰገድ ሲያንሳቸው ለራሳቸው ምሥል ወድቀው በሚሰግዱ
ባለቃ ስም መጥተው- አለቃ በሆኑ… የሞላው መንገዱ..
አቀበት ጉድጓዱ …
‹‹… እግዜር ሆይ
አንተን አንተን ስንል- ካንተ እያጠፋን በስምህ የመጣ ‹‹ያገልጋይ›› አይና ውጣ
ቀስ በቀስ አልቁናል ከቤትህ ሸሽተናል ምን ቀርቶናል ብለህ ለማነው ምትመጣ?
ግጥሙ አሁንም እግዜር ጋ ነው፡፡ አገልጋይ ነን ያሉን ሰዎች ራሳችን ላይ ወጥተው አገልግል እያበሠሉ ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹እነሆ በቶሎ እመጣለሁ!›› ያልከው ጌታችን ካመጣህ ቤትህ ኦና ይሆናል፡፡ አገልጋዮችህ በጎችህን ውጠው ወፍረው ብቻቸውን ታገኛቸዋለህ ነው የሚለው!
‹‹እግዜር ተፀፀተ? በሚለው ግርጌ ስር ያለው ግጥም፤ በእጅጉ መሥጦኛል፤ ይህ ጥያቄ የአዳም ዘር ጥያቄ ነው፤ ገጣሚው ግን ቀለም ነክሮ፣ በፍቅር አጎንብሶ አደባባይ ላይ አምጥቶታል፤ እንዲህ እያለ፡፡
‹‹… እግዜር ሸክላ ሰሪ- ሁለት ጎራ ስራ
አንዱን ጎራ ሊሾም አንዱን ለመከራ…
ከነዚህ ስንኞች ወደ ታች ብዙ ስንኞችን ዘልሎ ደሞ እንዲህ ይላል
‹‹ታዲያ ለሸክሎቹ ለምን ሸክላ ሆነ?...›› የጠየኩትን ያደመጡ ሁሉ
‹‹ለድስቱም ለጌጡም እኩል የሚጨነቅ ፍቅር ነው…›› ይላሉ፤
-ይሁን-
ያልገባት ለነፍሴ- ሁሉ እየመረረ
መጀመሪያውኑ እግዜር በሸክላ ውስጥ ክብር አስስትንፋሱን እንዴት አምኖ አኖረ?
የሰው ልጅ ውስጣዊ ትርታዎች ናቸው። ያላመነ ሰው አይደለም፤ ያመነ ሰው በውስጡ የሚያመላልሳቸው ማሥቲካ ሃሳብ፡፡
አበረ አያሌው ሙሉ መጽሐፉን በንዑስ ርዕሦች ሥር፡- እውነትና እምነት፣ እግዜር፣ የሸንቁር እይታ፤ ፍቅር፣ ብትንትን፣ ሀገር፣ ፍርድና እርድ ብሎ ነው በቅደም ተከተል በጭብጥ የደረደራቸው፡፡
ከላይ የጠቀስኳቸው ግጥሞች፤ ‹‹እግዜር›› በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር የታቀፉ ናቸው፤ አሁን ደግሞ ‹‹ፍቅር›› ከተሠኘው ጠቅላይ ርዕስ ‹‹ትመጫሽ?›› ከሚለው አዋሳለሁ፡-
‹‹በቃ የኛ ሃገር›› -ብለሽኝ ስትጂ በቀን አላዩሽም
ብራኔ አድርጌሽ -ርቀሽ ስትሄጄ እኔ ላይ ቢመሽም!
ፀሀይም በርታለች- ጨረቃም እዛው ናት
ያቺ ቤታችንም- ያኔ እንዳቆምናት!
ንፋስም አልቆመ- ዝናብም ዘንቧል
እኛን እያየን’ኳ- ሰው ለጉድ ይጋባል!
አብረን እየነበርን -ከመቀመጫሽ ላይ አፍጥጠው የሚያልፉ
የሰፈር ጎረምሶች- እንደ ድሮው አሉ ሌላ እየለከፉ!
እዚህ ጋ ገፀባህሪው ፍቅረኛው የኛ ነገር በቃ!›› ስትለው፤ ሁሉም ነገር የሚያበቃ መሥሎታል፡፡ ፀሀይ የምትወጣ ጨረቃም ምድርን የምታረሠርሥ  መሆኑ ጠፍቶታል፡፡ የፍቅሩ ጥልቀት፤ ፍጥረት ሁሉ ከፍቅራቸው ጋር እንዲያያዝ ካፈቀሩ አይቀር እንዲህ ዕ-ብብ-ድ! ማለት ነው የሚያሰኝ አይነት እንደ ሆነ እያንዳንዱ ስንኝ ያወራል፡፡ ሌላው ቀርቶ የሰፈራቸው ጎረምሶች፤ እርሷ ከሄደች በኋላ ሴት ይለክፋሉ ብሎም አላሰበ! … በምን አንጀቱ! ዓለም ሁሉ በእርሱ አንጀት የታሰረ መስሎታል፡፡ ፍቅር - ትልቁን ሰው ህፃን ሲያደርግ እንዲህ ነው! …. ገጣሚ ደግሞ ያንን ኮልታፋ የልጅ ልቡን ሀሳብ ሀሳቡን በርቱዕ ብዕር ለአንባቢ ያቀብላል፡-
“ሀገር” በሚለው ንዑስ ርዕስ ስር “ዘርሽና ዘሬ ኑሮ ትዳራችን አይደለም የዛሬ!” የሚለው ረዘም ያለና ደም የሚያንፎለፎልበት ያገር ልብ ትርታ ነው፣ ሁሉ ቦታ የሚያጠቅስ፣ የዘነጋውን የሚያስታውስና በስንኝ ቀለም ሰቅሎ የሚያውለበልብ፤ ሲጀምር እንዲህ ነው፡-
“… እኔ ለዚች ሀገር
‹ሰው የላትም› ቢሉ - እልፍ ልጅ ወልጄ
“ብስል ጠፋ ሲሉ
ትኩስ ጫንቃዬ ላይ - ጥሬ ዕቃ ጥጄ
ልጆቹ እያደጉ - አለቃው አይበስል
እንደው ልፊ ብሎ እረግሞኝ ነው መሠል …
እኔ ለዚች ሀገር
ቀናተኛው እግዜር
የጠላቱን ወዳጅ ላንድም ቀን ባይወድም
መፍትሄ ነው ሲሉኝ
ለሆዱ ያደረ - ዲያቆን፣ ቄስ ስካድም
              …
እኔ ለዚች ሀገር - ህዝብ መሀል በቅሎ
ህዝብን ለሚወጋ - ለባዕድ ወታደር
ደም ከሆነ ወዜ - ራሴን ነፍጌ ቀለቤን ስሰፍር
በህዝብ እምባ ታጥቦ, ቆዳውን ላነፃ - ደሀ በል ነጋዴ
ሀገር የሚያለማ - አድባር መስሎኝ እንጂ ማጎብደዴ ….
እያለ ይቀጥላል፡፡ (የስንኞቹን አደራደር ለገፅ ቁጠባ ለውጫቸዋለሁ፡፡ የስሜት ለውጥ እንጂ የሀሳብ ለውጥ አያመጡም ብዬ፡፡)
ጥሬ በዝቶ ይብሰል ተብሎ አናት ላይ ያፈናጠጡት ዶለዝ፤ በስሎ ይንተከተካል ሲባል ዕድሜውን ሙሉ ቃሪያ ሆኗዋል፤ ደሞዝ የተሰጠውም ወታደር ጠብ ያለ የደሃ አገልጋይ ነው ብሎ አስራት መባውን እየዛቀ፣ ለካስ ለሆዱ እንጂ ለእግዜር ያደረ አይደለም። በህዝብ እምባ የታጠበውን ነጋዴም ለሀገር የሚያለማ፣ አድባር ነው ተብሎ ጎንበስ ቀና ሲባልለት ለካስ፣ እንዲያው አድባር መሳይ ሸንበቆ ነበር፣ ንፋስ ብቻ እያለ ግጥሙ ያገር ነቀዞች ላይ ያላግጣል፣ የወገን ደመኞች ላይ በትካዜ ያፏጫል፡፡ ገጣሚው ያርገንና ያገር ሰውን ጉዳይ እንዲህ ነው ያየው፡፡
የአበረ አያሌው “ፍርድ እና እርድ” በሚል የተጠረዘው መጽሐፍ፤ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ቃኝቷል፡፡  ልዩ  ልዩና   ዥንጉር ጉር  ሀሳቦችና  ሰካራም  ልቦችም በየፊናቸው ታይተውበታል፡፡ ሁሉንም በየመልካቸው አስቀምጧቸዋል፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት፤ ሀሳቡ ላይ ትኩረቴን ባደርግም የአሰነኛኘት ውበቱም ሸጋ ነው፡፡ በየሰከንዱ ዜማ በመስበር አያበሳጨንም፡፡ ለግጥም ደግሞ ሙዚቃ ውበቱ ነው፡፡ በደካማ አናባቢዎችና በከፊል አናባቢዎች ጥምረት፣ ጥልዝ ምትና ድምፅ በሌላቸው ቀለማት በአንድ የቤት አመታት ስልት መከራ ያበሉን ገጣሚያን ቁጥር‘ኮ ቀላል አይደለም፡፡
ለሀገራችን ገጣሚያን ጥቂት ስነ - ልቦናዊ ፍንጭ ለማግኘትና በቀለም ቆጠራ ለመታገዝ የዶ/ር ጌታነህ አማረንና የፕሮፌሰር ባዬን - ቀላል የአማርኛ ሰዋሰው መጽሐፍት መጋበዝ ያሰኘኛል፡፡ ከልል ምት፣ በደረቱ ከሚሳብ ሙዚቃ ይታደገናልና!
አበረ አያሌው ግን “ፍርድ እና እርድ” በሚለው መጽሐፉ በጉልበት ዳዴ እያለ ሳይሆን በሁለት እግሮቹ ቆሟል፡፡ አበባውን ተቀብለን እናሽትተው! መዓዛው በአፍንጫችን ልክ ውስጣችን ይገኛል! ብዬ አምናለሁ!





Read 2159 times