Monday, 15 August 2016 09:38

ጊዜ (ASIKO 2016)

Written by 
Rate this item
(0 votes)

(ካለፈው የቀጠለ)

ባለፈው ሳምንት ASIKOን ለመዳሰስ መንደርደሪያዎችን በመዘርዘር በአሁኑ ወቅት፤ በተለይም በዘመነኛ የኢትዮጵያዊ ሥነ-ጥበብ አውድ መጠየቅ የሚችሉ፤ መጠየቅ ያለባቸውንና መልስ እንኳን መስጠት ባንችል፣ ለጥያቄዎቹ መልስ እንድናፈላልግ የሚያስችሉ ውይይቶችን መጀመር ያለብን ወሳኝ ጊዜ ላይ መሆናችንን በማተት ነበር ጽሑፌን ያቀረብኩት፡፡ በዛሬው ተከታይ ክፍል፤ ስለ ሥነ-ጥበብ ስንነጋገርና ጠቅለል ያሉ ነገር ግን ወደ እኛ ወደ ዘመነኛው የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ውይይት ስንገባ፣ልናነሳቸው ለሚገቡ ጥያቄዎች መልስ ለማፈላለግ መንገዶች ሆነው በASIKO የተካተቱ አቀራረቦችን በዝርዝር እያነሳን እንመለከታቸዋለን፡፡
Elevator Pitch:  (የሊፍት ውስጥ ፈጥ ያለ ንግግር)፡- ውድ ነገር ቢኖር ጊዜ ነው፡፡ ለመስራት በቂ ጊዜ ያለው ባለሙያ፤ስለ ስራው ጥናት ማድረግ፣ ማሳወቅና ማስተዋወቅ የሥራው አካል እንደሆነ ግልፅ በመሆኑ ጥናት የምናደርግበት፣ የምናሳውቅበትንና የምናስተዋውቅበትን መንገዶች የማወቅና በዝግጁነት መጠበቅ የአንድ ሰዓሊም ሆነ አጋፋሪ ሙያዊ ሃላፊነትም ጭምር ነው፡፡ በሥነ ጥበቡ ዓለምም ሆነ በሌሎች ዘርፎች በሙያው ላቅ ያለ ደረጃ ያላቸው ሰዎች በአንፃራዊነት ጊዜ የሚያጥራቸው ሰዎች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ሰዎች፤የመንግስት ባለስልጣናት፣ባለሀብቶች ወይንም በሀላፊነት ቦታ የተቀመጡ የምንፈልጋቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ለሙያችን መበልፀግ ወሳኝ የሆኑ ሰዎችን ለምሳሌ በሊፊት ውሰጥ ድንገት ብናገኛቸው ምን አይነት አቀራረብ ይዘን ነው  ልናናግራቸው የምንችለው/ እንዴትስ ነው ስለ ሥራችን Highlight ወይም ብልጭታ ልንሰጣቸውና የተሟላ የሥራ ዕቅድ ይዘን እንድንቀርብ የሚያስችል እድል መፍጠር የምንችለው? ይህን አይነት አጋጣሚዎች ከግንዛቤ አስገብቶ፣ ሙያዊ ዝግጅት ማድረግ፣ አንደኛው የASIKO አቀራረብ ሲሆን ተሳታፊያን፣ ይህንን ልምምድ እንዲያደርጉ እድል ይሰጣቸዋል፡፡
ይህንን አቀራረብ ወደ ሀገራችን አምጥተን ስናየው፣ በአንድ በኩል አስቂኝ በሌላም አሳዛኝ ሆኖ ይታየኛል፡፡ አስቂኙ፤ አብልጫው የሀገራችን ሰዓልያን ስለ ሥራቸውም ሆነ ስለ ሥነ-ጥበባዊ ማንነታቸው ለተገቢው አካል የተመጠነ Highlight ወይም ብልጭታ ከመስጠት የተቆጠቡ ናቸው፡፡ በዚህ የንግግር ባሕላችን አለመዳበር ምክንያት ለምንሰራው ስራ ተገቢውን አትኩሮት ላናገኝ እንችላለን፡፡ የሃገራችን የሥነ-ጥበብ ተመልካች፣ በቂ የሥነ-ጥበብ ግንዛቤ የሌለው በመሆኑም ይህ የንግግር ባሕል አስፈላጊ ነው፡፡ ሌላኛው የዚህ ስራን የማስተዋወቅ ነገር አስቂኝነት አሳዛኝ የሚሆነው በሀገራችን አውድ በተለይም ስለ ሥራቸው ያለማቋረጥ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሚናገሩ መኖራቸው ነው፡፡ ታዲያ አስቂኝነቱ ወደ አሳዛኝነት የሚቀየረው እንዲህ አይነቱ ተናጋሪዎች፣ ወደ ስራቸው ስንመጣ ያወሩት ሁሉ ሃሳብ ይሆናል፡፡ በስራው (በእይታ)) ሌላ ይሆንና ወሬው ብቻ ስራ ይሆናል፡፡ በዚህ መንገድ የመንግስት ባለስልጣናትን፣ ባለሃብቶችንም ሆነ ባለሙያዎችን በእንቧይ ካብ ‘ሞልተው’ ለሙያውም ሆነ ለሠዓልያን ተገቢውን ክብር እንዳይሰጥ ያደረጉ እጀ ሰባራዎች ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህም፣ እንደ የሥነ-ጥበብ ባለሙያ (ሠዓሊ፣አጋፋሪ፣ደጋፊ… ወዘተ) የሰዎችን ቀልብ ለመግዛት ብቻም ሳይሆን የተገዛውን ቀልብ ለማርካትና ተገቢውን ቦታ ለማስያዝ የሚያስችል ከASIKO አቀራረብ አንዱ የሆነው Elevator Pitch አይነተኛ መማሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ የትኛው ባለሥልጣንና ባለሃብት ነው እንኳን ሊፍት ውስጥ ይቅርና ቢሮው  ሃምሳ ጊዜ ተመላልሰህ ያገኘኸው እለት እንኳን ጆሮ የሚሰጥህ? የሚልም ይኖራል፡፡ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን ጆሮውን ዳባ ያለበሰ በሞላበት፣ ጆሮ መኮርኮሪያ ማዘጋጀት የኛ የባለሙያዎች ኃላፊነት ነው፡፡
Crit- (Criticism) ሂስ፡- ከአቻ የሙያ አጋሮች፣ ከቀደምት (Senior) ባለሙያዎችም ሆነ በሌሎች የሙያ ዘርፎች ከሚገኙ ባለሙያዎች ጋር ስለምንሰራቸው የሥነ-ጥበብ ውጤቶች አስተያየትና ሂስ ለመቀበል ዝግጁ መሆን ይጠበቅበናል፡፡ በሥነ-ጥበቡም ሆነ በሌሎች የሙያ ዘርፎች በምናገኛቸው አጋጣሚዎችም ሥነ-ጥበባዊ ማንነት ያለው አስተሳሰብና ሂስ መስጠትም ከአንድ ሠዓሊም ሆነ የሥነ-ጥበብ ባለሙያ የሚጠበቅ ነው፡፡ በASIKO ባህል ስራን አቅርቦ መተቸትና ሂስ መቀበል የተለመደ ነው፡፡ ሂስ ሲባል ደግሞ እንደተገኘ መውቀጥ ሳይሆን ምክንያት ደርድረው ማሳመን፣ ሰዓሊው የሰራውንም ሆነ የሥነ-ጥበብ አጋፋሪው(Curator) ያጋፈረው ሥራ ውስጥ በተመሳሳይ መልኩ የተሰሩ ሥራዎችን የመዳሰስና የማጥናት፤ ተመሳስሎዎችን የመንቀስና ተቃርኖዎችን የመለየት እንዲሁም የዚህ ሁሉ ትንተና ጠቀሜታን ከተሰራውና ከሚሰራው ስራ ጋር ማያያዝ የሂስ መሰረታውያን ናቸው፡፡ የASIKO ተሳታፊያን በዚህ የሂስ ባህል እጅግ ተጠቅመዋል፡፡ ሥራቸውን ለማሻሻልም ስንቃቸውን ይዘዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሥነ-ጥበብ ታሪክ ውስጥ ሊጠቀሱ ከሚችሉት ሃያሲያን መሃከል የ1970ዎቹና ለ1980ዎቹ የሥነ-ጥበብ ታሪክ ምሁሩና አጥኚው ሃያሲ ስዩም ወልዴ ራምሴ እና በ1960ዎቹ  ደግሞ ገጣሚ ሰለሞን ደሬሳ ሲሆኑ የኢትዮጵያ የሥነ-ጥበብ ላይ ሂስ በመስጠት ይታወቁ ነበር፡፡ ነበር፡፡ ነበር። ነበር፡፡ ነበርንም ማንሳት አንድ መጽናኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ እስከ አሁን ዘመን ድረስ የሥነ-ጥበብ ታሪካችን የሂስ ድርቅ የመታው፤ የግልፅ ውይይትና የትችት መጋኛ የቆለፈውና ዝምታው አላስችል ሲል ሹክሹክታና ሃሜት ያጀበው ታሪክ ነው ያስተናገድነው፤እያስተናገድንም የምንገኘው፡፡ የሥነ-ጥበብ እውቀት ያላቸውና ያከማቹ የሥነ-ጥበብ ማኅበረሰቡ አባላትም ሆነ ሰዓሊያን፤ ሂስ ለመሰጣጠት ተነሳሽነት ያጡበት ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡ ሆኖም ዝምታ መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ የአንድ ሀገር ሥነ-ጥበብ ስኬት ሊኖረው የሚችለው በመጀመሪያ ደረጃ የሥነ-ጥበብ ማኅበረሰቡ ራሱ የሂስና የትችን ባህል ሲኖረው ነው። የሚሰሩት የሥነ-ጥበብ ውጤቶች ላይ ምክንያታዊ ሆኖ መቅረብ ሲቻል፤ ከሥነ-ጥበብ ማህበረሰቡ በዘለለ አመለካከቱ የሰላ፣ አተያዩ የዳበረና ግንዛቤውን ሊያሰፋ የሚችል መዛኝ ማኅበረሰብ (Critical Mass) መፍጠር ይችላል፡፡
ንባብና ምርምር (Reading and Research):- ሥነ-ጥበብ እይታ ላይ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ የምንሰራውን ሥነ-ጥበብ ማጠናከርም ሆነ ሥነ-ጥበባዊ አድማሳችንን ለማስፋት ንባብ ወሳኝ ነው። የሥነ-ጥበብ ታሪክን ለማወቅ፣ የሠዓልያንን የተሰጥኦና የመነቃቂያ ርዕስ ጉዳይን ይበልጥ ለመረዳት፣ ርዕሰ ጉዳዩ ሊነካካ የሚችላቸው ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮችን፣ በሚሰራበት ርዕስ ጉዳይ ዙሪያ የሚሰሩ የሌሎች ሰዓሊያንን ሥራዎች ማጥናት ሁሉ ከአንድ ሠዓሊ፣ የሥነ-ጥበብ ባለሙያም ሆነ ሥነ-ጥበብን ለመረዳት ከሚፈልግ ማንኛውም ሰው የሚጠበቅ ስራ ነው፡፡ ASIKO የዚህን ጠቀሜታ ያሰመረ ልምድ ነበረ የተወልን፡፡
የASIKO ሲምፓዚየም፡- በመጨረሻው የASIKO ሳምንት የተካሄደው የሁለት ሰዓት ተኩል አጠር ያለ ሲምፖዚየም በአይን ገላጭነቱ አይነተኛ ነበር፡፡ የሲምፖዚየሙ ርዕስ ‘የሥነ-ጥበብና የሥነ-ጥበብ አጋፋሪነት ትምህርት ቀጣይ ጉዞ በአፍሪካ’ የተሰኘ ነበር፡፡
ሲምፖዚየሙ ከሀገራችን፣ ከአፍሪካና ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የታደሙ ባለሙያዎችን ያሳተፈ ነበር፡፡ ሲምፖዚየሙ በዋናነት የሚሞግተው፣ የሀገራችንም ሆነ የሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሥነ-ጥበብና የሥነ-ጥበብ አጋፋሪነት ትምህርት በምዕራባውያንና በአውሮፖውያን ሥርዓተ ትምህርት የተቃኘ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን እውነት ለመቀየር በሚደረግ ጥረት ስለ ሀገራችንም ሆነ ስለ አህጉራችን እውነታዎች ቦታ የሚሰጥ ሥርዓተ ትምህርት በመቅረፅ ሂደት ውስጥ ሊያጋጥሙን የሚችሉ ፈታናዎችን በመዳሰስ፤ ከመንግስት፣ ከሠዓሊያንና ከሥነ-ጥበብ ባለሙያዎች የሚጠበቁ ኃላፊነቶችን ያመላከተ ነበር፡፡ የASIKO ተሞክሮ በወሳኝነት የሥነ-ጥበብና የሥነ-ጥበብ አጋፋሪነት ትምህርትን ሥርዓተ ትምህርት ለመቅረፅ ሀገራዊም ሆነ አህጉራዊ አውዶችን ማካተት ያለው ፋይዳ ያትታል፡፡ በሲፖዚየሙ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል፡- በአፍሪካ ሀገራት እየተሰጠ ያለው የሥነ-ጥበብ ስርዓተ ትምህርት ምን ያህል የሠዓልያንን ፍላጎት የሚያሟላ ነው? ከ21ኛው ክፍለ ዘመን እውነታዎች ጋር ለመራመድ የሚያስችል የሥነ-ጥበብና የሥነ-ጥበብ አጋፋሪነት ትምህርት በአፍሪካ ለመቅረፅ ምን ዓይነት አማራጭ ሞዴሎችን መጠቀም ይቻላል? በአፍሪካ የሚኖሩና የሚሰሩ ሠዓሊያንም ሆኑ የሥነ-ጥበብ አጋፋሪዎች ለሚኖሩበት እውነታ ሂሳዊና ወሳኝ የሆነ ሥራ ለመስራት የሚያስችላቸው ሥርዓተ ትምህርት ምን ሊመስል ይችላል? የሚሉ ጥያቄዎች ይገኙበታል፡፡ አህጉራዊና ሀገራዊ አማራጮችን ማሰስና መጠቆም ላይ ያተኮረው ይህ ሲምፖዚየም፤ የሥነ ጥበብ አጋፋሪነት ትምህርትን በተመለከተ በተለይ ለሀገራችን አውድ አንገብጋቢ የሚሆነው የአጋፋሪነት ሙያን ሥራ ላይ ማዋል እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ ከአ.አ.ዩ አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት፣ የሥነ-ጥበብ ትምህርት ክፍል በሲፖዚየሙ የተጋበዙት ሠዓሊና መምህር ክብሮም ገ/መድህንና መምህር አበባው አያሌ ያሰመሩበትም፣ የሥነ-ጥበብ ትምህርትን ለማዳበር ርብርቦሽ  ማድረግ በሚያስፈልግበት በዚህ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ የትምህርት ክፍሉ እንዲዘጋ ከዩኒቨርሲቲው ትዕዛዝ በመምጣቱ ሳቢያ፣ የትምህርት ክፍሉን ከመዘጋት በመታደግ ሂደት ውስጥ አማራጭ የሥርዓተ-ትምህርት በመቅረፅ፣ ት/ክፍሉ ወደ ‘ሥነ-ጥበብ ታሪክ’ ትምህርት ክፍልነት ለመቀየር እየተደረገ ያለውን ጥረት አስገንዝበዋል፡፡ በተለይ አቶ አበባው አያሌው፤ በት/ቤቱ በተለያየ ዘመን የተካሄዱትን የሥርዓተ-ትምህርት ለውጦችን በማንሳት ከመደበኛ ሥርዓተ ትምህርት ውጪ ያሉትን አማራጮች መመልከት ጠቃሚ እንደሆነም አስገንዝቧል። ረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊና ቀራፂ በቀለ መኮንን በበኩሉ፤ በሃገራችንም ሆነ በአህጉራችን የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቅኝት ውስጥ ‘በአንድ ፈረስ ላይ ብቻ የመረባረብ’ ልምድ ያካበትን መሆኑን በመግለፅ፣ ሥርዓተ-ትምህርታችንን ለማሻሻል አማራጭ ፈረሶችን መግራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ የASIKOን ቅርፅ እንደ ማሳያ አመላክተዋል፡፡
አሁንና እዚህ (Here and Here): የአሲኮ ትርዒት፡- የASIKO መርሃ ግብር ማጠናቀቂያ የነበረው የሥነ-ጥበብ ትርዒት ነበር፡፡ ትርዒቱ በአስኒ ጋለሪ የተካሄደ ሲሆን ሦስት ክፍሎች ነበሩት፡፡ የመጀመሪያ ድንበርን የተመለከተ ሲሆን በአፍሪካ ውስጥ መዘዋወርና ድንበር መሻገር ያለውን ውጣ ውረድ የሚያስቃኝ ነበር፡፡ ተሳታፊያኑ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የቪዛ ችግር የገጠማቸው ከመሆኑም በላይ በየመንገዱ ‘አፍሪካ!’ እየተባሉ መጠራታቸው ስለ አፍሪካዊነት ከኢትዮጵያውያን ጋር በሚያደርጓቸው ውይይቶች፣ ኢትዮጵያውያን አፍሪካውያን ሳይሆኑ ኢትዮጵያውያን ብቻ እንደሆኑ የሚያስቡ መሆናቸው በተሳታፊያኑ ዘንድ ግርምት የፈጠረ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሃገራት አንዷ መሆን ብቻም ሳይሆን ለአፍሪካዊነት የተጫወተችው ሚና ጉልህ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ወደ ሕዝቡ ሲወርድ ቦታ የሌለው በመሆኑ ተሳታፊያኑ ስለ አፍሪካዊነት እንዲያስቡበት አድርጓቸዋል፡፡ በትርዒቱም፡- ማንነት፣ ድንበር፣ መሰናክልና ስደት በአህጉሪቱ ያላቸው ገፅታ ተንጸባርቋል፡፡ የትርዒቱ ሁለተኛ ክፍል በቅርቡ የተመረቀው የአፍሪካ ፓስፖርትን መሰረት ያደረገ ፓስፖርት ሠዓሊያኑ የሰሩበት ክፍል ሲሆን ይህን ፓስፖርት ያልያዘ ማንኛውም ጉብኚ ወደ መጀመሪያው የትርዒቱ ክፍል መግባት አይችልም ነበር፡፡ ይኸም ተመልካቹን አሳታፊ በማድረግ ስለ አፍሪካዊ ማንነት፣ ድንበርና ስደት- -- ጥያቄዎችን በማስነሳት ውይይት እንዲፈጠር አስችሏል፡፡ የትርዒቱ የመጨረሻ ክፍል ‘ጉርሻ’ ነበር። እንደ አንድ የኢትዮጵያ ባህል፡- ጉርሻ በተለምዶ ፍቅርና መተሳሰብን መግለጫ ነው፡፡ በዚህ ትርዒትም በጋቢ የተሸፈነና ሶስት ቀዳዳዎች ካሉት ሳጥን መሳይ መከለያ ውስጥ ብቅ የሚሉ እጆች፤ጉርሻ ይዘው ጎራሹን ይመግባሉ፡፡ የአጉራሾቹ እጆችና የያዙት ምግብ እንጂ ፊታቸውና ገፅታቸው አይታይም፡፡ አጉራሹ ጎራሹንም አያይም፡፡ ይህ መሆኑ ፍቅርም ሆነ አመኔታን ያለ ቅድመ ሁኔታ መስጠትና መቀበልን እንድናስብ የሚያደርግ ነበር፡፡ በትርዒቱ ሦስቱም ክፍሎች በሠዓልያኑ የተሳሉ ሥዕሎችን አናይም። ሀሳቦችን የሚወክሉ መስተጋብሮችን በኩልኮላ (Installation) እና ትግበራ (Performance) አማካኝነት ያነሳል፡፡ በዚህም አፍሪካን ዋነኛ ትኩረት በማድረግ የአፍሪካን ጊዜ ‘አሁን’ በማለትና አፍሪካን እንደ ቦታ በመውሰድ፣ ‘እዚህ’ በማለት፣ በዚህ ወሳኝ ጊዜ ሊነሱና ሊዳሰሱ የሚችሉት አህጉራዊ ጉዳዮችን ያነሳል፡፡
ማጠቃለያ፡- እንደ ታላቅ መድረክነቱ፤ ASIKO አያሌ ጉዳዮችን አስተማሪ ሆኖ አልፏል፡፡ ዋናው ቁም ነገር፤ ወደ እኛ ወደ ራሳችን ዓውድ ስንመለስ.፣ ልናበራይ የምንችለውን መንቀስና ተግቶ መስራት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ፤ ከአፍሪካ ሥነ-ጥበብ አንዱ የሚሆንበትን ብሎም በዓለም የሥነ-ጥበብ መድረክ መቀላቀል የሚያስችለንን የሥነ-ጥበብ ማንነት፤ በሀገር ደረጃ የመገንባት፣ የሥነ-ጥበብ ሥርዓተ-ትምህርታችንን በራሳችን ቅኝት ውስጥ ለመቃኘትና አደጋ ላይ ያለውን ወሳኝ የሆነው የሥነ-ጥበብ ትምህርትን አቅጣጫ መግራት፣ ግለሰብ ሰዓሊያንንና የሥነ-ጥበብ አጋፋሪዎችንን እንዲሁም የሥነ-ተመልካችና አድናቂውን ሳይቀር ያለበትን የቤት ስራ ለመስራት፣ ሂስ  ለመስጠት፣ ጥያቄዎችን ለመፍታትና ውይይቶችን ለመጀመር ይህ ወሳኝ ጊዜ - ASIKO አመልካች ነበር፡፡ ቸር እንሰንብት!

Read 1215 times