Monday, 15 August 2016 09:53

የሰዓሊው እረፍት

Written by  ድርሰት - ማርክ ትዌይን ትርጉም - ፈለቀ አበበ
Rate this item
(0 votes)

በ1892 መጋቢት ወር ላይ፤ በሜዴትራኒያን ባህር ዳርቻ ስር ባለች አዘወትሬ የምጎበኛት ከተማ መሀል በሚገኝ በአንድ ሆቴል ውስጥ አርፌ ነበር፡፡ ሜንቶኒ ሁሉም ነገር አላት፡፡ ብሩህ የጸሐይ ብርሀን፣ ነጭ የባህር ዳርቻ፣ ንጹህ ሰማያዊ ውኃ፡፡ በጣም ሀብታም የሆኑቱ ሰዎች ወደ ሜንቶኒ እምብዛም አይመጡም። ከሌሎቹ ሚሊየነሮች ጋር ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ስለሚመቻቸው ሞንቴ ካርሎን ማጨናነቅ ነው የሚመርጡት፡፡ አልፎ አልፎም ቢሆን ከባለጸጎቹም አንዳንዶቹ ብቅ ይላሉ። ከእነርሱም መካከል አንዱንና አሁን ባለሁበት ዴስ አንግሌስ ሆቴል ያረፈውን ዲታ አግኝቼዋለሁ፡፡
አንድ ቀን ጠዋት ቁርስ እየበላን ሳለ፤ ሚስተር ስሚዝ ብዬ የምጠራው አዲሱ ባልንጀራዬ፤ በጥድፊያ ወደ መውጫ በሩ እየጠቆመኝ፤
‹‹እየው! እየው!›› አለኝ ‹‹ከምግብ ቤቱ እየወጣ ያለውን ያንን ሰው እየው፡፡ በደንብ አየኸው ማን እንደሆነ ታውቃለህ››
‹‹አዎና!›› አልኩት ‹‹ ይኼማ ሽማግሌው ከበርቴ ቴኦፊል ማግናን አይደለም እንዴ! ላለፉት ሁለት ሳምንታትም እዚሁ ነው ያለው፡፡ ሥራ ከማቆሙ በፊት ላዮን ውስጥ የሚገኙትን አብዛኞቹን የልብስ ፋብሪካዎች ጠቅልሎ ገዝቷቸው ነበር፡፡ ሰዎች እንዲያ ብለው ነው የሚያወሩት፡፡ እሱ ግን ከማንም ጋር አይነጋገርም፡፡››
ከአንድ ወይም የሁለት ደቂቃዎች ፋታ በኋላ ሚስተር ስሚዝ፣ ‹‹የሀንስ አንደርሰንን ድርሰቶች ታውቃቸው ይሆን በጣም የማደንቀው ደራሲ ነው›› አለኝ፡፡
‹‹እንዴታ! በሚገባ ነዋ›› አልኩት፡፡ ‹‹ስለየትኛው ድርሰቱ ማንሳት ፈልገህ ነው››
‹‹ደስ የምትል ወፍ ስለነበረችው ትንሽ ልጅ፡፡ ወፊቱን በጣም ይወዳታል፤ ግን ከመመገብ ተዘናጋ። ቀስ በቀስ ወፊቱ እየደከመች ሄደችና መዘመሯን አቆመች፡፡ አንድ ቀን ማለዳም ወለል ላይ ፍንችር ብላ አገኛት፡፡ ልቡ ተሰበረ፡፡ እንባውን እያዘራና አሳዛኝ ዝማሬ እያንጎራጎረ በትንሽ ሳጥን ውስጥ ከትቶ ጉርጓድ ቆፍሮ ቀበራት፡፡››
‹‹ልክ እንደዚሁ ሁሉ እኛም ታላላቅ አርቲስቶቻችን በህይወት ሳሉ እንዘነጋቸዋለን። የሚተነፍሱትን አየር እየተመገቡ የሚኖሩ አድርገን እንቆጥራቸዋለን፡፡ ሲሞቱ ግን ለቀብር ስነ ስርአታቸው ይህ ነው የማይባል ወጪን እናወጣለን። ለምንድነው በህይወት እያሉ የማንረዳቸው››
በዚያው ቀን ምሽት እንደገና ከሚስተር ስሚዝ ጋር ተገናኘንና ማውጋት ቀጠልን፡፡ እናም ቀጣዩን ታሪክ አጫወተኝ . . .
*  *  *
ይኼ ያልተለመደ አይነት ታሪክ ነው፤ ግን ደግሞ እውነተኛ ታሪክ፡፡ ለብዙ አመታት በኔና በሦስት ጓደኞቼ መሀል ምስጢር ሆኖ የኖረ ነው፡፡
ከረዥም ጊዜ በፊት፤ ገና አፍላ ወጣት አርቲስት ሳለሁ፤ ፈረንሳይ ውስጥ ካንዱ ከተማ ወደ ሌላው እጓዝ ነበር፡፡ በዙሪያዬ የማያቸውን የመልከአ ምድር ውበቶችንም እስላለሁ፡፡ በኋላም ክሎድ ፊርሳና ካርል ካላንዲ ከሚባሉ ሁለት ወጣት ሰዓሊያን ጋር ተቀራረብን፡፡ ሁላችንም ለሞያችን ላቅ ያለ ፍቅር ነበረን፤ እናም አብረን መኖር ስንጀምር በጣም ደስተኞች ሆንን፡፡
ምስኪን ድሆች ነበርን፡፡ አንድ ቀን በሰሜን ፈረንሳይ ከምትገኝ ትንሽ ከተማ ስንደርስ የምንበላው ምናምኒት ስንቅም ሆነ እምንገዛበት ቤሳቢስቲን ገንዘብ አልነበረንም፡፡ ነፍሳችንን ያተረፈልንን ሌላ ወጣት አርቲስት ጣለልን፡፡ ፍራንሷ ሚሌት ይባላል። በእርግጥ ያን ያህል ዝነኛ ሰዓሊ አልነበረም፡፡ ያው ልክ እንደኛው ነው፡፡ እሱም በአራተኛነት ቡድናችንን ተቀላቀለ፡፡ በቃ በጋራ እንቦርቃለን፤ እንዘፍናለን፡፡ እናም በጣም ብዙ የስዕል ስራዎችን አጠራቀምን፡፡ለሁለት አመታት ያህል እየቆነጠርን የምንቀቅላትን አትክልት እየተቋደስን ቆየን። ግን ደስተኞች ነበርን፡፡
በኋላ አንድ ቀን ክሎድ ሀሳብ አመጣ፤ ‹‹ስሙኝማ ልጆች፤ እያለቀልንኮ ነው፡፡ ዱዲ ፍራንክ የለንም፡፡ የምንቀቅለው አትክልትም አልቋል፡፡ ስዕሎቻችንንም የሚገዛን ሰው የለም፡፡ የሆነ መላ ካልፈጠርን በቀር የሚጠብቀን በነዚህ ሁሉ ውብ ስዕሎቻችን እንደተከበብን እዚሁ መሞት ብቻ ነው፡፡››
‹‹ባክህ አታሟርት!›› አለው ካርል፤ ‹‹ስዕሎቻችን ምርጥ ምርጥ ናቸው፡፡ ሁሉም ባይሆኑምንኳ...ለምሳሌ የሚሌት የሊቀ መልአኩን ስዕል ተአምረኛ ስራ ነው፤ ችግሩ ስዕሎቻችንን የሚገዛ ደንበኛ ማጣችን እንጂ፡፡››
‹‹የኔን የሊቀ መልዐኩን ስዕል ሸጣችሁ፣ ዳቦና አይብ መግዛት ትችላላችሁ›› አለ ፍሯንሷ ሚሌት፡፡
‹‹ቆይ ከዚያ ይልቅ ግን...›› ካርል ቀጠለ፤ ‹‹እኔ ሀብታም የምንሆንበትን አንድ የሆነ መላ አስቤያለሁ››
‹‹ጀመረህ ደሞ አንተ እብድ ልጅ!›› አለ ክሎድ፤ ‹‹ቅዠትህ እስኪለቅህ ትንሽ በጀርባህ ጋደም በል!››
‹‹ውይ ዝም በሉ!›› አለ ሚሌት፤ ‹‹የካርልን ሀሳብ እንስማው››
‹‹ጥሩ፤ እስቲ በዱሮ ጊዜ ስለኖሩ ታላላቅ አርቲስቶች አስታውሱ፡፡ መቼ ነው ዝነኛ የሆኑት በህይወት እያሉ ወይስ ከሞቱ በኋላ››
‹‹ብዙውን ጊዜ፤ ሁሉም ማለት ይቻላል ከሞቱ በኋላ ነው›› ምላሽ ሰጠ ሚሌት፡፡
‹‹ስለዚህ ከመካከላችን አንዳችን መሞት አለብን።›› ካርል ይህን ሀሳብ ያቀረበበት የመረጋጋት ሁናቴ ከተቀመጥንበት ዘልለን ከመነሳት ገታን፡፡ ወዲያው ግን ወደ መሬት ጎትተን አንደባለልነው፡፡
‹‹ስሙኛ!›› እያለ ጮኸ ‹‹የሚሞተው ሰውኮ ዝነኛ ይሆናል፡፡ እናም ከዚያ በኋላ አራታችንም የሀብታም ሰዎችን ህይወት መኖር እንጀምራለን››
‹‹ምንድነው የምትቀባጥረው›› ሲል ጠየቀ ክሎድ፡፡
‹‹አንደኛችን እዚሁ ቀርተን ስዕል መስራታችንን እንቀጥላለን›› ማስረዳቱን ቀጠለ ካርል ‹‹በጣም ብዙ ስዕሎች ነው የሚያስፈልጉን፡፡ ቀሪዎቹ ሦስታችን ደግሞ በመላው የፈረንሳይ ከተሞች እየተዟዟርን ስለ መናጢ ድሀውና በጠና ህመም ላይ ስላለው ወዳጃችን እንደሰኩራለን፡፡ እግረ መንገዳችንንም የዚሁኑ ወዳጃችንን ትንንሽ መጠን ያላቸውን ስዕሎቹንም እንሸጣለን፡፡ ሕዝቡ ሁሉ ስሙን በደንብ አወቀው ማለት አይደል፤ ያኔ ስለ እሱ በስፋት መወራት ይጀመራል፡፡ ከዚያ በኋላ ይሞታል፡፡ እኛም አስከሬኑን ተሸክምን ወደ ዘላለማዊ ማረፊያ ስፍራው እንወስድና ግብአተ መሬቱን እንፈጽምለታለን። ያለጥርጥር የህልፈቱ ዜና ከህይወት ታሪኩ ጋር ታትሞ በሁሉም ጋዜጦች ላይ ይወጣል፡፡ ከዚያማ ምኑ ቅጡ ይወራል፤ እያንዳንዱ ሰው የዚህን የሞተ አርቲስት የስዕል ስራዎች እያሳደደ መሻማት ይጀምራል፡፡ የስእሉ መሸጫ ዋጋም ሰማይ ይነካል። እኛም በቀሪው የህይወት ዘመናችን ባለጸጎች ሆንን ማለት ነው፡፡››
‹‹እሺ ከአራታችን ሦስታችን ባለጸጎች ሆንን እንበል። ግን ደግሞ ከአራታችን አንዳችን እንሞታለን!›› ሚሌት አምባረቀ፡፡
‹‹አይደለም! እንዴት ማሰብ ያቅታችኋል ሟቹኮ የእውነት አይሞትም፡፡ ስሙን ቀይሮ ይሰወራል፡፡ ባዶውን ሳጥን ነው ጉድጓዱ ውስጥ የምንቀብረው›› ሲል አብራራ ካርል፡፡
በዚያኑ ቀን በእቅዱ ዙሪያ ተመካከርን፤ የሚሞተውንም አርቲስት መረጥን፡፡ በማግስቱም ክሎድ፣ ካርልና እኔ የመላ ፈረንሳይ ዙሪያ ጉዟችንን ጀመርን፡፡ ፍራንሷ ሚሌት ደግሞ ለመሰወር መዘጋጀት ጀመረ፡፡
ሁለት ቀናት ሙሉ ተጉዤ፤ አቀበት ላይ አንድ ትልቅ የገጠር መኖሪያ ቤት ካለበት ሰፈር  ደረስኩ። በዚያም የቤቱን ገጽታ በመሳል ላይ ሳለሁ፤ የቤቱ አባወራ፤ የምሰራውን ስዕል ለማየት ወዳለሁበት መጣ፡፡ በአነስተኛ መጠን የሰራሁትን ስዕሌንም ወደደው፡፡ ከቦርሳዬ ውስጥ ከሚሌት ስዕሎች አንዱን መዝዤ አወጣሁ፡፡
‹‹በጣም ደግ መምህር ነበር ያስተማረኝ›› ገለፃዬን ጀመርኩ ‹‹የታላቁ ሰዓሊ የፍራንሷ ሚሌት ተማሪ ነኝ። ይህቺ ትንሽዬ ስዕልም የእሱ የጥበብ አሻራ ያረፈባት ነች። ይሄንን ከስዕሉ ስር ያሰፈረውን ፊርማውን በደንብ እንደሚያውቁት እርግጠኛ ነኝ። የእሱን የስዕል ስራ መሸጥ አልፈልግም ነበር። ግን ደግሞ እሱ ባልጋ ቁራኛ ተይዞ ነው ያለው፡፡ ከእንግዲህም ብዙም በህይወት መቆየቱንም እንጃ። ከሞተ በኋላ የስዕል ስራዎቹን ለመግዛት መሞከር መቸም የማይታለም ነው፡፡ ያፈለገውን ያህል ገንዘብ ከፍለውም ቢሆን አያገኙትም፡፡
እውነት ነው ሰውየው የፍራንሷ ሚሌትን ፊርማ አያውቁም፡፡ እንደው በድንገት ግን ደርሶ ፊርማውን የሚያውቁት ሆነው ተገኙና ፊርማውም የእሱ የራሱ መሆኑን አይተው አረጋገጡ፡፡ ከአፍታ ውይይት በኋላም የሚሌትን ስዕል በስምንት መቶ ብር ሸጥኩላቸው፡፡ ወቸ ጉድ! ጓደኛዬ ሚሌት፤ ‹‹ከመታተሙ በፊትም›› ቢሆን ከአምስት መቶ ብር በላይ ስዕል ሸጦ አያውቅም ነበርኮ። ሰውየው ከኔም ላይ እዚያው ቁጭ ብዬ የሳልኩትን የመኖሪያ ቤታቸውን ስዕል በመቶ ብር ገዙኝ፡፡ የታላቁን ሰዐሊ የሚሌት ተማሪን አንድ ስዕልም ማስቀረት ፈለጉአ። ስምንት መቶ ብሩን ለፍራንሷ ልኬለት፣ እኔ ወደ አጎራባቹ ከተማ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ በቀን አንድ ስዕል ብቻ ነው የምሸጠው፤ ሁለት ስዕሎችን ለመሸጥ ፈቃደኛ አልነበርኩም፡፡
ካርልና ክሎድም በሌላኛዎቹ የፈረንሳይ ከተሞች በተመሳሳይ መልኩ እቅዳችንን እያጧጧፉት ነበር፡፡ በየትኛውም ስፍራ ለምናገኛቸው የጋዜጣ ሪፖርተሮችም ሁሉ መግለጫ እንሰጣለን፡፡ በስድስት ወራት ውስጥም ሰማኒያ ስድስት አነስተኛ መጠን ያላቸውን ስዕሎች ሸጠን 69 ሺህ ብር ሰበሰብን፡፡ ካርል የመጨረሻውን ትልቅ ዋጋ ያወጣውን የሊቀ መልአኩን ምስል ስዕል በ2ሺህ 2 መቶ ብር ሸጠው። ያንኑ ስዕል ቀድሞ ከገዛው ሰውዬ ላይ ሌላ የናጠጠ ነጋዴ በ550 ሺህ ብር ገዛው፡፡ እንግዲህ የፍሯንሷ ሚሌት መሞቻ ቀኑም ደረሰ ማለት ነው ፡፡
አንተስ ራስህ ስለ ሚሌት የህልፈት ዜና አላነበብክም ነበር ስመ ጥር የሆኑ ሰዎች ከአለም ዙሪያ ሁሉ በቀብሩ ላይ ተገኝተው የክብር አሸኛኘት አድርገውለታል፡፡ እኛ አራታችንም  ተለያይተን እንደማናውቀው ሁሉ፤ በቀብሩም እለት አስከሬኑን በውብ የሬሳ ሳጥን ውስጥ አኑረን ተሸከምነው። ከአራታችን በቀርም ማንም የሳጥኑን ጫፍ ንክች ያደረጋት የለም፡፡ ያን ያህል እንደማይከብድ መቸም ግልፅ ነው፡፡ አራታችንም ፍሯንሷ ሚሌት በሳጥኑ ውስጥ እንደሌለም እናውቃለን። ሚሌትማ ከእኛው ጋር ሳጥኑን በመሸከም ተግባር ተጠምዷል፡፡ በእለቱ እርሱ የሟቹ የዝነኛው አርቲስት የአጎት ልጅ ነበር። እነሆ ዛሬ ሁላችንም ሚሊየኔር ሀብታሞች ነን፡፡ተጨማሪ ገንዘብ ባስፈለገን ጊዜም ሁሉ ስዕሎቻችንን እንሸጣለን፡፡ ታዲያ የሟቹ ሚሌት ስዕል ዛሬም ድረስ ዋጋው አይቀመስም፡፡
*  *  *
‹‹ይኼ በጣም የሚገርም ታሪክ ነው›› አልኩት፤ ሚስተር ስሚዝ ትረካውን ሲጨርስ ‹‹እና ግን የፍሯንሷ  ሚሌት ጉዳይስ መጨረሻው ምን ሆነ››
‹‹ጠዋት ከምግብ አዳራሹ ሲወጣ ያሳየሁህን ሰው ታስታውሰዋለህ ፍሯንሷ ሚሌት ማለት እርሱ ነው፡፡››
‹‹እኔ አ...››
‹‹...አላምንም ልትለኝ ነው አይደል አዎን፡፡ ግን ሁሉም በትክክል የተፈጸመ ገሀድ እውነት ነው፡፡አንድ ታላቅ አርቲስት በህይወት ዘመኑ ለስራዎቹ በቂ ክፍያ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ ስለምን ብሎ ይሳቀቃል! ልክ በሀንስ አንደርሰን ታሪክ ውስጥ እንዳለችው ትንሽዬዋ ወፍስ ለምን ይሰቃያል! እነሆ እኛ ይህን እውን አድርገነዋል፡፡››
ምንጭ - Is He Living or Is He Dead?
by - Mark Twain




Read 1013 times