Monday, 15 August 2016 09:55

ከ“ሆረር” ደራሲው ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(7 votes)

ጋዜጠኛ፡- እስቲ ለተመልካቾቻችን ስምህንና የሰራኻቸውን የድርሰት ስራዎች በማስተዋወቅ እንጀምር ….
ደራሲው፡- ለቴሌቪዥን ነው እንዴ ኢንተርቪው የምታደርገኝ? … ቃለ መጠይቁ በሬዲዮ የሚተላለፍ መስሎኝ እኮ ነው ቤቴ እንድትመጣ የፈቀድኩልህ፡፡ አስቀድመህ ብትግረኝ ትንሽ መኝታ ክፍሌን አስተካክል አልነበር እንዴ… ለማንኛውም እኔ ራሴን ማስተዋወቅም ሆነ መቆለል አልፈልግም። አግባብ ያለው ጥያቄ መጠየቅ ያንተ ስራ ነው፤ የሚመለከተኝ ከሆነ ለመመለስ እኔ እተባበራለሁ፡፡
ጋዜጠኛው፡- … እሺ እንደገና እንጀምር … ተመልካቾቻችን ዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው በድርሰት ዓለም ብዙ ዓመት ከመቆየቱና ካበረከታቸው ጥበባዊ ትሩፋቶች አንፃር በጥቂት አንባቢያን ዘንድ እንጂ ለሰፊው ታዳሚ ባይተዋር የነበረውን ደራሲ ኤልያስ ጭረቱን ነው። ኤልያስ በድርሰት ዓለም ኤስ እየተባለ በቅፅል ስም ከመጠራቱ ውጭ ስለ ማንነቱ ብዙም ይፋ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ለመሆኑ ኤስ ማነው? የሰራቸው ድርሰቶችስ የትኞቹ ናቸው?  
ደራሲው፡- የካሜራውን መብራት ትንሽ ልትቀንሰው ትችላለህ ማነህ … አባ ኪያ! … አይኔን እያስለቀሰኝ ነው፡፡ በኋላ ተመልካች እንዳይደነግጥ፡፡ ወይንም የተቸገርኩ መስሏቸው ብር እንዳያሰባስቡልኝ ..፡፡ ለማንኛውም ኤስ ማነው? ላልከው ጥያቄ መልሱን አላውቀውም፡፡ አንተ የሆነ ነገር ብታውቅ ነው ልትጠይቀኝ የመጣኸው ብዬ ነው ቃለ መጠይቅ ላድርግህ ስትለኝ የተስማማሁት፡፡ … ድርሰቶችህ ስንት ናቸው ካልከኝ “ብዙ ናቸው” …
ጋዜጠኛው፡- … ግዴለም … ነፃ ሆነህ ተናገር፡፡ እኔ ለቃለ-መጠይቁ አግባብ ያልሆኑትን ኤዲት አድርጌ ሁለታችንም የተስማማንበትን ብቻ አስተላልፈዋለሁ፡፡ ስንት መፅሐፍት አሳትመሀል?
ደራሲው፡- ኤስ በሚለው ስም ሁለት መፅሐፍ አሳትሜአለሁ፡፡ የዛሬ አስር አመት ገደማ፡፡ ሁለቱም መፅሐፍት ገበያ ላይ ገዥ አላገኙም። አለመፈለጋቸው ሲያበሳጨኝ ሰብስቤ ቤቴ ከመርኳቸው፡፡ … አሁን እዛ ጥግ ላይ የምታየው ሶፋ፣ መፅሐፍቱን በኮላ አጠባብቄ የሰራሁት ነው፡፡ ይሄ እኔ የተቀመጥኩበት ደግሞ ከሶስተኛው መፅሐፌ ያነፅኩት ነው፡፡
ጋዜጠኛው፡- በጣም ያሳዝናል … ለምን አንባቢ ሳታገኝ ቀረህ? ማስታወቂያ አላሰራህም? ወይንስ የንባብ ማህበረሰቡ ያንተን ድርሰት ለመቀበል ዝግጁ አልነበረም?
ደራሲው፡- ለዚህ ጥያቄ መልስ የለኝም፡፡ ማህበረሰቡም መልስ የሚሰጥህ አይመስለኝም … ማህበረሰቡ ለአንድ ጥያቄ አንድ መልስ የሚሰጥበት፣ አንድ አፍም ሆነ ጆሮ የለውም።
ጋዜጠኛው፡- የመፅሐፍቱ አርዕስት ምን የሚል ነበር?
ደራሲው፡- ማን ያስታውሳል ብለህ ነው … ለማንኛውም አራተኛ መፅሐፌን ያሳተምኩት ኤስ በሚለው ስሜ ሳይሆን “ኤጭ” በሚል ነው፡፡ የአክስቴ ልጆች የእኔን አይነት ሶፋ እንድሰራላቸው ስለጠየቁኝ ነው አራተኛውን ያሳተምኩት፡፡ ወደ ገበያም ሳላሰራጨው ገና ከማተሚያ ቤት ሲወጣ ወደ ሶፋ ቀየርኩት። እዛ ከካሜራማኑ ጀርባ የሶፋው ፎቶ ተለጥፏል … ማየት ትችላለህ፡፡
ጋዜጠኛው፡- ከዛስ?
ደራሲው፡- ከዛማ ይኸው አለና!
ጋዜጠኛው፡- ማለቴ … ሶፋው በስዊትዘርላንድ የሞደርን አርት ኤግዚቢሽን ውስጥ እንዴት ተካተተ?
ደራሲው፡- እኔንጃ … ብቻ … ጥልቅ ትርጉም ያለው የጥበብ ስራ ነው … ሶፋ እና ሀውልትን አጣምሮ የተሰራ ፈጠራ ---- ምናምን ብለው .. አሞካሹት … ብዙ ዩሮ ከፍለው እንግዛህ አሉኝ ሸጥኩት፡፡
ጋዜጠኛው፡- (ከት ከት ብሎ እየሳቀ) በአቋራጭ መፅሐፍህን ሸጥከው ማለት ነው፡፡ አማርኛ ቋንቋን አለማቀፋዊ ለማድረግ አስበህ ይሆን መጀመሪያውኑ መፅሐፍህን ወደ ቁሳቁስ የለወጥከው?
ደራሲው፡- አይደለም፡፡ ግን ከአእምሮ ይበልጥ መቀመጫ … አለማቀፋዊ ወንድማማችነት አለው፡፡ የምታነበውን ትመርጣለህ … መቀመጫ ግን አትመርጥም፡፡ ሳታነብ መኖር ትችላለህ … ሳትቀመጥ ግን ኑሮን መግፋት አይታሰብም፡፡
ጋዜጠኛው፡- ስለዚህ አንተ ደራሲ ነህ ወይንስ የእንጨት አናጢ…?
ደራሲው፡- አንተ ልትጠይቀኝ ስትመጣ ምንድን ነው ብለህ አስበህ ነው?
ጋዜጠኛው፡- … እኔ ልጠይቅህ የመጣሁት ዝናህን ሰምቼ ነው፡፡ የዝናህን ምንጭ የምታውቀው አንተ ነህ፡፡
ደራሲው፡- … እኔ ስለማውቀው ነገር እንድነግርህ አንድ ጊዜ ካሜራውን አጥፋ፡፡
ጋዜጠኛው፡- የአንተን እውቀት ለተመልካች ብናካፍል አይሻልም? ካሜራው ከጠፋ ሰዎች ስለ አንተ ማወቅ የሚፈልጉትን መረጃ ማግኘት አይችሉም፡፡
ደራሲው፡- እኔ ጉዳዬ አይደለም … ካሜራው ቢበራ፡፡ እኔ የማውቀው የሆረር ድርሰት ፀሐፊ መሆኔን ነው፡፡ … ሆረር ማለት አንድ ጭራቅ ጥርሱን አሹሎ ሰው ሲቆረጥም የሚተርክ ዘውግ አይደለም፡፡ ወይንም የፃዕረ-ሞት መንፈስ አጋናንት ተመስሎ ከጓዳ በጭለማ ብቅ ሲል አይደለም የእኔ ድርሰት የሚተርከው፡፡ ሆረር ማለት ለኔ … ያልጠበቅኸው ነገር ማለት ነው ትርጉሙ፡፡ በውንም በህልምም ያላሰብከው ነገር ሁሉ ሆረር ነው፡፡
ጋዜጠኛው፡- ምሳሌ ስጠኝ …
ደራሲው፡- ለምሳሌ እኔ ድንገት አሁን በጥፊ ባጮልህ ያላሰብከው ነገር ነው … ግን የማይታሰብ አጋጣሚ አይደለም፡፡ በጥፊ ያጮልኩህ በምን ምክኒያት እንደሆነ ሲገባህ ወይ ትስቃለህ ካለዚያ መልሰህ ቡጢ ታቀምሰኛለህ፡፡ … በጥፊ የተመታኸው ማንም ሰው በሌለበት ባዶ ክፍል ከሆነ፣ ሆረሩ ይጀምራል፡፡ አጋንንት ነው ልትል ትችላለህ፡፡ ወይ አብጄ ይሆናል ብለህ ትደነግጣለህ፡፡ ፀበል መሄድ ልትወስን ትችላለህ፡፡ የገጠመህ ያልጠበቅከው ነገር ቢሆንም ለገጠመህ ነገር ምክኒያታዊ መንስኤ ትፈልግለታለህ፡፡ ወደ ሳይንስም ሆነ ወደ ሀይማኖት ልትገባ ትችላለህ… ግን እኔ የማወራው ሆረር ይሄ አይደለም ..፡፡  
ጋዜጠኛው፡- ገብቶኛል ማለት አልችልም .. አንተ የምትፅፈው የሆረር ታሪክ በምን አይነት ጭብጥ ላይ የሚያጠነጥን ነው?
ደራሲው፡- እኔ የማወራው ምንም ትርጉም የሌላቸው ነገሮች ሲጠባበቁ የሚመጣ፣ ትልቅ ትርጉም የለሽ ነገር የሚፈጥረውን ሆረር ነው፡፡ … ለምሳሌ እኔ አብረው የማይገጥሙ ቃላት ዝም ብዬ እየደረደርኩ፣ አንድ ገፅ ከዛሬ አስር አመት በፊት ፃፍኩኝ፡፡ አንዱን ገፅ ከሌላ ብዙ መቶ ተመሳሳይ ገፆች ጋር አበዛሁትና ጠረዝኩት፡፡ ጠርዤ መፅሐፍ ብዬ ጠራሁት። አተምኩት። ለመፅሐፉ የሰጠሁትን አርዕስት ቅድም ስትጠይቀኝ መዘንጋቴን ስነግርህ ጉራ ነበር የመሰለህ። መፅሀፉ ውስጥ ምን እንደተፃፈም ሆነ አርዕስቱ ከተፃፈው ጋር ስላለው ዝምድና ምንም የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ መፅሐፉ አለመሸጡ አይገርመኝም። እዚህ ሀገር እኔ እንደፃፍኩት አይነት እብደት የሚቀበል ማህበረሰብ አይደለም ያለው፡፡ መፅሐፌ እብደት እንጂ ሆረር መሆኑ አንባቢው አልገባውም፡፡
ጋዜጠኛው፡- መፅሀፉን አለመግዛቱ ትክክል ነበር ማለት ነው … በጊዜው?
ደራሲው፡- ትክክል ብቻ ሳይሆን ጤናማም ነበር፡፡ … ስለዚህ የሆረር ሙከራ ማካሄድ ጀመርኩኝ። ያልተሸጠውን መፅሐፍ ልክ እንደ ኮምፐርሳቶ እየገጣጠምኩ … እየቆራረጥኩና በሚስማር እየመታሁ .. የመቀመጫ ሶፋ ወንበር አበጀሁ፡፡
ጋዜጠኛው፡- አበጀሁ ሳይሆን አጠፋሁ ብትል ይቀላል? (ሳቅ)
ደራሲው፡- ከማያገለግል እብደት ውስጥ ለአገልግሎት የሚሆን ነገር ሰራሁ ብዬ ስለማስብ ነው፤ አበጀሁ ያልኩት፡፡
ጋዜጠኛው፡- … እሺ አበጀህ … ቀጥል
ደራሲው፡- አሁን ስዊትዘርላንድ ውስጥ ለአክስቴ ልጆች ከመፅሐፍ ሰርቼ በብዙ ወጪ ባህር ማዶ በመርከብ የተላከላቸው ሶፋ … ድንገት በሆነ ምትሀት የጥበብ ቁንጮ ተብሎ የዓለም እውቅናን አገኘ፡፡ … እንግዲህ ልብ በል .. እዚህ ጋ … ፡፡ ሆረር ማለት ይሄ ነው፡፡ ሶፋው አድናቆትና የጥበብ ቁንጮ የሚል ማዕረጉን ያገኘው በሶፋነቱ ቢሆን ይሄ አንድ ነገር ነው። ሶፋው በሌላ የሶፋ መለኪያ ከተመዘነ ያላዋቂ የተሰራና ለአገልግሎት እንዲውል ቢደረግ እንደ እርጥብ እንጀራ ፍትፍት ሆኖ የሚፈራርስ ነው፡፡ ለመቀመጫነት ሳይሆን ለሌላ አስተሳሰብ ማራመጃነት ነው የተፈለገው፡፡ ከመፅሐፍ የተሰራ ሶፋ መሆኑ ነው ለዘመናዊው የጥበብ መለኪያ ብቁ ያደረገው፡፡ መፅሐፍ እንደ መፅሐፍ መልዕክት የሚያስተላልፍ፣ ውበትን የሚገልፅ ቢሆን አይፈለግም፡፡ ምንም ውበት የሌለው፣ መልዕክት የማያስተላልፍ፣ ትርጉም የለሽ እብደት ከሆነ መፅሐፍ የተሰራ ቅርፅ መሆኑ ነው ሶፋውን ውድ ያደረገው፡፡
ጋዜጠኛው፡- ከማያገለግል መፅሐፍ የተሰራ የማያገለግል ሶፋ ነው እያልከኝ ነው? …
ደራሲው፡- … ከዚህ በላይ የሆረር ልብ ወለድ ተፅፎ አያውቅም እያልኩህ ነው!
ጋዜጠኛው፡- … ሁለት የማይጠቅሙ … ወይንም ቅድም እንዳልከው ትርጉምም ሆነ እሴት የሌላቸውን ሁለት ነገሮች አንድ ላይ ስላጣመረ ነው ሆረር የሆነው?
ደራሲው፡- … አይደለም … አሁን በቅርቡ በደረሰኝ መረጃ … ጥቅም ያላቸውን መፅሐፍት ከላይብረሪያቸው እያወጡ፣የመፅሐፍት ሶፋ እንዲሰራላቸው የሚያደርጉ ብዙ ሰዎች እየፈሉ መምጣታቸው ነው ሆረሩ! የሚገርምህ ሶፋው እንዲሰራላቸው የሚከፍሉት ብር … ምርጥ የእንጨት ሶፋ ከማሰሪያም ሆነ ሙሉ ላይብረሪ ቅርስ በሆኑ መፅሐፍት ለመሙላት ከሚከፈል ብር የላቀ መሆኑ ነው ሆረሩ!
ጋዜጠኛው፡- በጣም ትልቅ ንቅናቄ በዓለም ላይ በመፍጠርህ የሀገራችን እንቁ ጀግና ነህ። የሀገራችንን ስም በዓለም ላይ ከፍ ብሎ እንዲሰፍር በማድረግህ ከየትኛውም ጥበበኛ የላቀ ምስጋና ይገባሃል፡፡ … አበበ ቢቂላ፣ ኃይሌ ገ/ሥላሴ… በኦሎምፒኩ ሜዳ ባንዲራችን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያደረጉ ጀግኖች እንደሆኑት ሁሉ፣ በጥበቡ ደግሞ እንደ አንተ አይነት ትልቅ አሳቢዎች ማፍራት መቻላችን እጥፍ ድርብ ያኮራናል …
ደራሲው፡- ይሄ ነው ሆረሩ!
ጋዜጠኛው፡- ሆረር ለዘላለም ይከበር!
ደራሲው፡- ሌላ ሆረር ልጨምርልህ፡፡ …. ምንም እንኳን የሆረርን ትርጉም የመረዳት አቅም አለህ ብዬ ባላምንም … “just because you are a character it doesn’t mean you have one” እንዳለው ኩዊንቲን ታራንቲኖ በ pulp fiction ፊልሙ ላይ .. አንተም horrific ስለሆንክ ብቻ Horror ምን እንደሆነ ታውቃለህ ማለት አይደለም፡፡
ጋዜጠኛው፡- ይሁን … ብቻ ምንድነው የምትጨምርልኝ?
ደራሲው፡- በቅድሙ መረጃ ላይ ሌላ ልጨምርልህ። ሶፋውን ለመስራት የተጠቀምኩባቸው ትርጉም አልባ መፅሐፍቶቼ ታትመው፣ በመላው ዓለም የምርጥ መፅሐፍ ሽያጭ ሰንጠረዥ ላይ በደረጃ አንደኛውን ስፍራ እየያዙ ነው፡፡ ትርጉም በሌለው የአማርኛ ፊደል ስብስብ ተፅፈው፣ የአማርኛ ተናጋሪ እብደት ናቸው ብሎ ችላ ያላቸው መፅሐፍት እንደነበሩ ቅድም ነግሬሀለሁ፡፡ እኒሁ መፅሐፍት ታዲያ ሶፋ የተሰራበት ንጥረ ነገር በመሆናቸው ብቻ የአማርኛ ፊደል ወደ ላይ ይዘቅዘቅ ወደ ታች በማያውቁ የባዕድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሀገር፣ በብዙ ሺ ኮፒ በአዲስ መልክ ታትሞ፣ ገበያውን እየተቆጣጠረ መሆኑ ሌላ የሆረር ምንጭ ነው፡፡ … ስለዚህ የሆረር ልብ ወለድ ፀሐፊ ነኝ ብዬ ቁጭ ብያለሁ፡፡
ጋዜጠኛው፡- ከሶፋው ሽያጭ ወይንም ከሶፋው ፓተንት ራይት ላይ ያገኘኸውን ብር .. ዮሮ … ዶላር… ወይንም ከመፅሐፍ ሽያጭ ከሚገኘው ንዋይ የምታፍሰውን በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት ምን ልታደርግበት አስበሃል? … ይህ የመጨረሻው ጥያቄዬ ነው!
ደራሲው፡- ሌላ የሆረር ፈጠራ ለመስራት እጠቀምበታለሁ፡፡
ጋዜጠኛው፡- ለመስራት ያሰብከው ቀጣይ የሆረር ፈጠራ ምን አይነት ቅርፅ ወይንም አላማ እንደሚኖረው ልትገልፅልን ትችላለህ?
ደራሲው፡- … አንተ የገለፅከው በሚሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ እጄ ሲገባ … ብሩን በኮላና ማስቲሽ እያያያዝኩ እንደ መፅሐፍ ጠርዤ ገበያ ላይ ላቀርበው አስቤአለሁ፡፡ መፅሐፍቱ በጣም ጥቂት ስለሚሆኑ በጨረታ አወዳድሬ ዝቅተኛ ዋጋ ለሚከፍል ባለ እድል ቤቱ ይዞ እንዲገባ ማድረግ ነው እቅዴ፡፡ ይህን ለማድረግ በነፃ እስፖንሰር የሚያደርጉኝን በጎ አድራጎት ድርጅቶች አሳትፋለሁኝ፡፡ ይህ ከተሳካልኝ ትልቁ የሆረር ፈጠራዬ ይሆናል። የሆረር ፈጠራዬ የመጨረሻው ነጥብ የሚሆነው ምንድነው አትለኝም?
ጋዜጠኛው፡- ልልህ ነበር .. ቀደምከኝ
ደራሲው፡- በዝቅተኛ ዋጋ አጫርቼ የሸጥኩት በመፅሐፍ መልክ የተጠረዘ የውጭ ምንዛሪ … የሚያስገባው መጠነኛ የኢትዮጵያ ብር ቢሆንም፣ ወላጅ አልባ ህፃናትንና ጧሪ የሌላቸው በአቅም የደከሙ አረጋውያንን፣ ለአንድ ቀን በትልቅ አዳራሽ ሰብስቤ የምሳ ግብዣ አደርግላቸዋለሁ፡፡ … እዚህ ላይ የሆረር ‘Performance Art’ ኤግዚቢሽን ይጠቃለላል፡፡  
ጋዜጠኛው፡- ከዚህ የጥበብ ፈጠራህ ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሚሆነው ማነው?
ደራሲው፡- ማንም አለመጠቀሙ ነው የሆረርን ጥበብ ልኬቱን የጠበቀ፣ ጥልቅና የተሳካ የሚያደርገው ….
ጋዜጠኛ፡- የተከበሩ ኤስ(ኤጭ) ለሰጡኝ ቃለ ምልልስ በተመልካቾችና በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡
ደራሲው፡- ሌላ የምትለው የለህም? … ሆረር ማለት ይሄ አይደል ታዲያ?!




Read 4964 times