Monday, 15 August 2016 09:57

አቤል ተስፋዬ፤ በካናዳ የኢትዮጵያ ጥናት ለማስጀመር 1.2 ሚ ብር ሰጠ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ የግዕዝ ትምህርት ለመጀመር አስቧል
    ፎርብስ መጽሄት በቅርቡ ባወጣው የ2016 የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ዝነኞች ዝርዝር ውስጥ የተካተተውና የወቅቱ የአለማችን የሙዚቃ ኮከብ እንደሆነ የሚነገርለት ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቤል ተስፋዬ፣ በካናዳ በሚገኘው ቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ፕሮግራም ለማስጀመር የሚያግዝ 50 ሺህ ዶላር (1.2 ሚ ብር ገደማ) በስጦታ ማበርከቱ ተዘገበ፡፡
የግራሚ ተሸላሚው ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ፤ ቢቂላ አዋርድስ ከተባለ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ተቋም የቀረበለትን የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄ በመቀበል ስጦታውን ያበረከተ ሲሆን፣ ተቋሙ በድምጻዊው ፈጣን ምላሽ መደነቁንና የገንዘብ ድጋፉ ባህላችንን ለመጠበቅና ለተቀረው አለም ለማስተዋወቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲል ምስጋናውን ማቅረቡን ዘ ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል፡፡
“እጅግ ድንቁንና ጥንታዊውን የኢትዮጵያ ታሪክ ለተቀረው አለም ልናስተዋውቅ ነው፡፡ በካናዳ የኢትዮጵያ ጥናት ፕሮግራምን ለማስጀመር በሚደረገው ጥረት የበኩሌን ድጋፍ ለማድረግ በመቻሌ ኩራት ይሰማኛል” ሲል በትዊትር ገጹ ላይ የተናገረው አቤል ተስፋዬ፤ ሌሎችም ለዚህ ጅምር መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ፕሮግራም ለማስጀመር ታስቦ እየተካሄደ በሚገኘው የገንዘብ ማሰባሰብ እስካሁን ድረስ ከ170 ሺህ ዶላር በላይ  መገኘቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ ዩኒቨርሲቲው በዚህ አመት የግዕዝ ቋንቋ ጥናትን ለማስጀመር አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡
የቢቂላ አዋርድስ ፕሬዚዳንት አቶ ተሰማ ሙሉጌታ፣ በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ፕሮግራም መጀመሩ የአገሪቱን ጥንታዊ ስልጣኔዎች በመመርመር እንዲሁም ቱባ ባህላችንን፣ ታሪካችንንና ባህሎቻችንን ጠብቆ በማቆየት ረገድ ተጠቃሽ አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲሉ መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በኦሎምፒክ ጀግናው አበበ ቢቂላ ስም የተቋቋመው ቢቂላ አዋርድ፣ በኢትዮ-ካናዳውያን መካከል የአካዳሚክ፣ ሙያዊና የቢዝነስ ትብብር የመፍጠርና በጎ ፈቃደኝነትን የማጠናከር አላማ ይዞ እንደተመሰረተ የጠቆመው ዘገባው፣ ተቋሙ ከሁለት አመታት በፊትም ለድምጻዊ አቤል ተስፋዬ የሙያዊ ልቀት ሽልማት እንዳበረከተለት አስታውሷል፡፡
ለ117 አለማቀፍ የሙዚቃ ሽልማቶች በመታጨት፣ ሁለት የግራሚና ስምንት የቢልቦርድ ሽልማቶችን ጨምሮ 36 አለማቀፍና ክልላዊ የሙዚቃ ሽልማቶችን ያገኘውና በወቅቱ የአለማችን የሙዚቃ መድረክ አብሪ ኮከብ ሆኖ የወጣው የ25 አመቱ ድምጻዊ አቤል፤ፎርብስ መጽሄት በቅርቡ ይፋ ባደረገው የ2016 ከፍተኛ ተከፋይ 100 የዓለማችን ዝነኞች ዝርዝር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተካተቱት 15 ዝነኞች መካከል አንዱ እንደነበርና  ከእነዚህ ዝነኞች መካከልም ከፍተኛውን ገቢ ማግኘቱን፣ ባለፉት 12 ወራት ብቻ 55 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳገኘም መዘገባችን አይዘነጋም፡፡




Read 1266 times