Monday, 15 August 2016 09:59

ጭሮ አዳሪ (ወግ)

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(4 votes)

    የጭርቁንሳዊያን መናኸሪያ መንደር ናት። በጠባብ ደረቷ ላይ እንደ ብጉር የበቀለው ጉብታ ከሁሉ ገኖ ከዓይን ይገባል፡፡ ጉብታዋን የተወዳጀው  ወፈፌ ዶሮ ሳይጮህ ንጋቱን ለመንደርተኛው ከማብሰር ሰልሶ አያውቅም፡፡ መንደርተኛውም ቢሆን የወፈፌውን እንጉርጉሮ ቆዳው ተላምዶታል። ገና ወፈፌው አንደበቱን ማላወስ ሲጀምር ጆሮውን አንቅቶ ከወደቀበት ቀና ቀና ይላል፡፡ መኝታዋን ፊት በመንሳት ነዋሪውን ከኋላ የምታሰልፈው አንድ ዓይነዋ ነዳይ ነች፡፡ የደኮነችውን ክርታስ ገሸሽ ታደርግና ወፈፌውን በስድብ ታጥረገርገዋለች። ወፈፌውም ይህንን ባስተዋለ ጊዜ በስለታም ፊቱ እያደፋፋት በሰዶ ማሳደድ ግብር ልቧን ያጠፋዋል። የመንደሯ የሰርክ ወግ ከእዚህ ፈቀቅ ያለ ቁምነገርን አያንጸባርቅም፡፡
የእኔዋ ዞሮ መግቢያ በአንድ ዓይነዋ የከርታስ መጠለያና በወፈፌው መሰየሚያ ጉብታ መሃል  ላይ ነው የከተመችው፡፡ ዘወትር ከግራ ቀኝ የሚወረወረውን ሙግት አድምጬ ከመወዲቂያዬ ጋር እለያያለሁ፡፡ ዛሬ ያለ ልማዱ እንቅልፍ ከዓይኔ የበረረው ከወፈፌው ንጋት ማብሰሪያ ቀድሞ ነው። ተስፈንጥሬ ወጣሁ፡፡ ሕዝብ አዳም ተከናንቦ አሸልቧል፡፡ ወትሮም ከሀገሬው ቀድሜ  እንደ ወፍ የምበረው እኔ ነኝ፡፡ ዶሮ ሳይሰፍር እሰበሰባለሁ፤ ዶሮ ሳይጮህ የዕለት ጉርሴን ለማሳደድ ከመኝታዬ እላቀቃለሁ፡፡ የጭሮ አዳሪ ነገር…..፡፡ የክልፍልፈነቴን ያህል ከአንጀት የሚጠጋ ንዋይ አልቋጠርኩም፡፡ በኩርማን ዳረጎት ላይ ታች እየባተልኩ ከወር አፋፍ  እንደ ምንም ተፍገምግሜ እዳረሳለሁ፡፡
ገና ከመንደሯ እቅፍ ስላቀቅ ደርሶ እንደ ሎጥ የሚያበረኝ አባዜ ይጠናወተኛል፡፡ በአርበ ሰፊው ጎዳና ላይ ያለ ልክ ጥድፍ ጥድፍ እያልኩ፣ ከአዘቦት መተከዣዬ ሥፍራ ተቃረብኩ፡፡
 ጭሮ አዳሪው ማልዶ ገስግሶ  ችምችም ያለ ሽንጣም ሠልፍ ቀልሶ ጠበቀኝ፡፡ የሚሰቀልባትን ሚኒባስ አንደ ተስፋይቱ ቀን እየተጠባበቀ ነው። የሽንጣሙን ሠልፍ ጭራ ፈልጌ ተደመርኩ፡፡ በሠልፈኛው ገጽታ ላይ ያረበበው ጭንቀት እንደ ተስቦ ይጋባል፡፡
“ይህ ሞልቶ የማይሞላ ጎተራ” ድንገቴ  ብሶት አንደበቴን በጉልበት ፈልቅቆ ተስፈነጠረ፡፡ ጥሞና የሰጠኝ ግን የለም፡፡
 “እንዲህ ተኩኖ እስከመቼ” ሌላ ምሬት አስወነጨፍኩ፡፡  
“የዕለት ጉርሱ … ነው … ጭንቁ …… ለትራንስቦርቱማ ... ይህቺ ዘመን አመጣሿ … ባለፉርጎ አውቶቢስ አለች፡፡ የደሃ ባቡር እኮ ናት። ዛሬ ሳንገጣጠም ቀርተን ነው፡፡” ምስቅልቅል ገጽታ የወረሳቸው አረጋዊ፣ ዕድሜና ኑሮ  ተጋግዘው ያጎበጠውን ትከሻቸውን እየሰበቁ ቀንዴን አሉኝ፡፡
የቅጽበቶች  መዳመጥን ተከተሎ ጥንድ ከርካሳ ግልገል አውቶቢሶች ለዓይናችን ተከሰቱ፡፡ እርስ በእርስ ተዛዝለን ተሞጀርንባቸው፡፡ የእኔዋ ከርካሳ ደርሶ ሆድ ይብሳታል፡፡ ከፊት ለፊቷ የሚፋለማት አቀበት ሲገጥማት የጣሯ አበዛዝ መንፈስን ያውካል።
ጊዜው አሻቅቧል፤ውኃ ቀጠነ ብሎ ለጠብ የሚጋበዘው ደመ-ሙቁ አለቃዬ ከፊት ለፊቴ ድቅን አለ፡፡ ስንቱን ታቦት ተማጽኜ የቀናኝን ጎተራ መሙያ እንደ ሰባ ሙክት  አጋድሜ ስባርከው በእዝነ ኅሊናዬ ወለል ብሎ ታየኝ፡፡ ገጽታዬን አኮማትሬ በሐሳብ ከከርካሳዋ ግልቢያ ጋር ግራ ቀኝ እየተላጋሁ ማዝገሜን ተያያዝኩት፡፡
የሐሳብ ግልቢያዬን የሚያስተጓጉል ግርዶሽ ከተሳፋሪው መሃል ድንገት ብቅ አለ፡፡ ሁዳድ መሬት በሚያህል መዳፉ ድሪቶ ወረቀቶችን ጨብጧል፡፡ ድሪቶው ላይ የተሞነጫጨረውን መልዕክት በሌባ ጣቱ እየጠቆመ እንደ ራሽን አከፋፈለን፡፡
“የፈንጂ አደጋ መስማዬን አዳፍኖታል፤ያላችሁን ተዘከሩኝ” ባልተንዘላዘለ መልዕክት ተማጽኖውን አቀረበ፡፡
ሰውዬው ፊት ላይ ነጥብ ጠባሳ አይታይም። ፈንጂው በምን ተአምር መስሚያውን ነጥሎ እንደ አዳፈነው ግራ ሆነብኝ፡፡
“እንዲህ ተራክሶ በእርጥባን ፈቃድ ከማረፋፈድ፣ ምነው ዛሬውኑ ክልትው ቢል” በውስጤ እርግማኔን አዘነብኩበት፡፡
እንደ አልባሌ ያንጠለጠልኩትን ድሪቶ ወረቀት ገጽታውን ከስክሶ ነጠቀኝ፡፡ እርጥባን ጠያቂው ተሳፋሪዎችን እንኳን በቅጡ  ሳያመሰግን ተክለፍልፎ ለመወረድ ሲጣደፍ፣ ተጎራባቼ ሴት ንዴት በቆራረጠው ድምጽ፣ በፀጉረ ልውጥ ቋንቋ እየቀበጣጠረች ጥድፊያውን ገታችው፡፡
“ሀገርኛው ቋንቋ ማንን ገደለ?” ሆን ብዬ ቆሰቆስኳት፡፡
 “ጠፍቶኝ መስሎህ? አውቆ አበድ ሆኜ እንጂ” ሽሙጥ አከናነበችኝ፡፡
ምራቋን ዋጥ ያደረገች ባልቴት ናት፡፡ ፀጉሯ እንደነገሩ ተሸክፏል፡፡ የፈረንጅ ባህል የነካካት ትመስላለች፡፡
“ማን ያውቃል፣ አንቺን ሰበብ አደርጎ ከእዚህ የጭሮ አዳሪ ሕይወት ቢገላግለኝ?” በውስጤ አጉተመተምኩ፡፡
“እረ እቴ.. የምን መወሻከት ነው፡፡ እዚህ ልሰብሰብ ብል እንኳን፣አድባሯም አትቀበለኝ” ከተነሳው ርዕስ ጋር የማይገጥም ንጭንጭ አሰማች፡፡
 “እረ ማን እንደ ሀገር አፈር” በታይታ መቆርቆር መንቁሬን አሾለኩ፡፡   በወረደው ተመጽዋች ምትክ ሌላ ተሳፋሪ  እላያችን ላይ ሲከመርብን ምልልሳችን ለጊዜውም ቢሆን ተገታ፡፡ የከርካሳዋ ጋላቢ ቦታ እንዳናባክን በኃይለ ቃል ባዘዘን መሠረት ችቦ ሰርተን ተዛዝለናል። ከፊት ለፊቴ የተከመረውን ተሳፋሪ አሳብሬ አንዲት ጥቅስ ላይ አነጣጠርኩ፡፡
“ኑሮ እና ታክሲ ሞልቶ ስለማይሞላ ተጠጋጉ” ይላል፡፡ በፈገግታ እየተደነቃቀፍኩ የተስፋይቱን ሴት ገርመም አደረኳት፡፡ አቀርቅራ ብጣሽ ወረቅት ላይ ትሞነጫጭራለች፡፡ ለአለባበሷ ግድ የላትም፡፡ የባዕድ ሀገር ኑሮ የፈጠረባት የባህል ሽግግር ሳይሆን አይቀርም፡፡ መዳረሻዋ እየተቃረበ እንደሆነ ምልክት መስጠት ጀመረች፡፡ ድንገት ወደ እኔ መለስ ብላ፣
“ለማንኛውም ሌላ ቀን ከቀድምከኝ…” በጅምር በተንጠለጠለ ሐሳብ ውስጤን እየጠረቋቆሰችኝ፣ ብጫቂ ወረቀት በመዳፌ አስጨብጣኝ እብስ አለች፡፡
የብጫቂ ወረቀቷ እርቃን በሆሄሀትና በአሀዝ ተነቅሷል፡፡ ፊቴ እንደ ጠሐይ በራ፡፡ በመንታ ስሜት ተሰነግሁ፡፡ ባህር ተሻጋሪ ወሃ አጣጭዬን በመዳፌ መጨበጤ ከፊል ደስታ፣ከፊል ግራ መጋባት ፈጠረብኝ፡፡ በተሳሰረ አንደበት ወራጅነቴን አውጄ ወደ የዕለት ጉርስ ማብሰያዬ ተንደረደርኩ፡፡
በማግስቱ
ጊዜ የአእምሮ ባሪያ እንደሆነ የተረዳሁባት ታሪካዊ ሌሊት እንደምንም አከተመች፡፡ የወፈፌው የንጋት ማብሰሪያ ድምጽ እንኳን ሁለት ሌሊት ነው ያስከነዳብኝ፡፡ ለፍቅር ጨዋታ ተቻኩያለሁ፡፡ ወፍ ጭጭ ሲል ወደ ተስፋይቱ ሴት ፈጥኜ ስልክ መታሁ። ትንሽ ጠርቶ ተነሳ፡፡
“ሄሎ” የወንድ ይሁን የሴት የማይለይ ቃጭል ድምጽ ከወዲያኛው መስመር አስተጋባ፡፡
የተስፋይቱን ሴት ስም ጠቀስኩ፡፡ ቃጭል ሳቅ ተቀበለኝ፡፡
“ምነው፣ ተሳሳትኩ?”
“አይ …አይ …ወዲህ ነው?…. ለነገሩ.. የወል መጠሪያ ነው” ሳቁን ማባራት ተሳነው፡፡
“ታዲያ ይህ ምን ይደንቃል” አልኩኝ ጥሪቷ ሊያከትም ቤሳቤስቲን ሳንቲም የቀራት ስልኬ እያሳሳችኝ፡፡
“ይደንቃል እንጂ…አፈር ከለበሰ አሥር ዓመታትን የተሻገረ ሙትን እረፍት መንሳት……ለነገሩ ምን ታደርግ …ተይዛ ነው፡፡”
አፌን ደም ደም አለኝ፡፡
“ፍቅረኛዋ ክንዱን ሲንተራስ፣ እርሷ ጨርቋን ስትጥል አንድ ሆነ፡፡”
 “የምትለው አልገባኝም”
“ሴቲቱ ያስታቀፈችህ የሙት ፍቅረኛዋን መጠሪያ ነው፡፡ ይገባሃል?? ንክ መሆኗን ዘንግተኸው ነው?”
 ምድሪቷ እላዬ ላይ የተደፋች መሰለኝ፡፡
“ትናንት እንደውም ሕመሟ ተባብሶ አፋፍሰን ነው ማምሻውን አማኑኤል ያስገባናት……”
“የባህር ማዶው ጉዞሰ…..” ከጤንነቷ ይልቅ ባህር ተሻጋሪነቷ እያሳሳኝ በተሟጠጠ አቅም ጣር ያዘለ ድምጽ አወጣሁ፡፡
ቃጭሉ እንደገና እንደ ብርጭቆ በሚሰባበር ሳቁ የበለጠ አሳመመኝ፡፡ ስልኬ እንጥፍጣፊ ጥሪቷ ተሟጦ የቃጭሉን ልሳን ጠረቀመችው፡፡
እንደ ሎጥ በርሬ ከእቅፏ የምስፈነጠረው መንደሬን ባልተለመደ እርጋታ እንደ ኤሊ እየተጎተትኩ በፍቅር ዓይን ደባበስኳት፡፡ ወደ አዘቦት መተከዣዬ የሚያቀናውን ጎዳና አገባድጄ ከአፋፉ ላይ ብቅ አልኩ፡፡ ችምችም ያለ፣ ሥፍር ቁጥር የሌለው ሠልፈኛ የሚሰቀልባትን ሚኒባስ እንደ ተስፋይቱ ቀን ይጠባበቃል፡፡ የጭሮ አዳሪውን ሠልፈኛ በአንድ አሀዝ ለመጨመር ወደ እዚያው ጠደፍ ጠደፍ እያልኩ ማዝገሜን ተያያዝኩት፡፡ የጭሮ አዳሪ ሕይወት ይቀጥላል…



Read 1268 times