Sunday, 21 August 2016 00:00

ንጉሥ የማይደፍረው!!

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

‹‹የእንግሊዝ  መኖሪያ  ቤት  በሩ ፤
ጠንካራ  የዴሞክራሲ   ጋሻ  ነው ››
ይህ ክቡር የምስክርነት ህያው ቃል ከዋና አርእስቱ በላይ የሰፈረበት ጽሑፍ፤ ከ70 አመታት በፊት በኒውዮርክ ሄራልድ ትሪቢዩን የታተመና በድጋሚ በሪደርስ ዳይጀስት ገጽ ለንባብ የበቃ፤ የአንዲት ሩሲያዊት ልዕልት ድንገተኛ የእኩለ ሌሊት ገጠመኝና ዘመን ተሻጋሪ ፍሬ ሀሳብን ያዘለ የእውነተኛ ታሪክ ማስታወሻ ነው፡፡ጽሑፉ የተገኘበት የ1943 እ.ኤ.አ ሪደርስ ዳይጀስት እትሞች ባንድ የተደጎሱበት ወፍራም ጥራዝ፤ በሽፋኑ የውስጠኛ ገጽ ላይ፤ ከንጉሠ ነገሥቱ የዘውድ አርማ ስር በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተጽፎ የተለጠፈው ማስታወሻ እንዲህ ይላል.፡-ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መስራች፤ ዕውቀት ፈላጊዎችና ተመራማሪዎች  ከመጻሕፍት የሚያገኙትን ጥቅም በመገንዘብ፤ ዩኒቨርሲቲው በተመረቀበት በታኅሣሥ 9 ቀን !954 ዓ.ም. ለዩኒቬርሲቲው ቤተ መጻሕፍት መቋቋም
ይረዳ ዘንድ፤ መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ ይህንን መጽሐፍ ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቬርሲቲ ቤተ
መጻሕፍት ሰጡ፡፡(እርግጥ ነው እኔ አግኝቼ ያነበብኩት ከአንድ አሮጌ መጽሐፍት አዟሪ ወጣት እጅ ላይ ነበር፡፡ ጊዜው በግምት 20 አመታት፤ ቦታው ሾለ ያ ነጭ ጠላ - ቀጨኔ፡፡)
እነሆ የልዕልቲቱ አንደበት . . .
*   *   *
ከብዙ አመታት በፊት፤ ሎንዶን አቅራቢያ በሚገኝ ከጡብ በተሰራ አነስተኛ ቪላ ውስጥ ሰከን ብለን እንኖር ነበር፡፡ ቤተሰቦቼ ስለዚህ ሀገሪቱ ለእኛ ስላደረገችው ውለታ ምስጋና መቸር እንደሚገባኝ በቅጡ ስረድተውኛል፡፡ ምክንያቱም፤ አባቴ ከሩሲያ የተሰደደ ግዞተኛ ነበረና፤ በሩሲያ የደህንነት ተቋም ምስጢራዊ ፖሊሶች የስለላ ክትትል ስር ሆኖ መኖር ያመጣብን ጦስ እምን ድረስ እንደሆነም በደንብ እናውቀዋለንና ነው፡፡ አንድ ምሽት፤ ፖለቲካዊ ክርክር ወደሚደረግበት ስፍራ ሄድን፡፡ ስብሰባው ሲጠናቀቅ እኩለ ሌሊት ተቃርቦ ነበር፡፡ መኖሪያ ቤታችን ስንደርስ፤ ግቢያችን በር ላይ ሰላም አስከባሪ ቆሟል፡፡ክው! ብዬ ደነገጥኩ፡፡ በዚህች ዴሞክራሲያዊት ምድር፣ የአባቴ ነፃነት በማንም ሊገሰስ አይችልም የሚል ጽኑ እምነት ነበረኝ። ኮንስታብሉን እንዳየሁት ግን፤ ያ ሸሽተነው የመጣነው ጭቆና፤ እዚህም ድረስ ዳናችንን አነፍንፎ መጥቶ፤ ዳግመኛ አሳድዶ እንዳነቀን እርግጠኛ ሆንኩ፡፡በኋላ ግን ስለ ሀገረ እንግሊዝ ዴሞክራሲ ላቅ ያለ መረዳትን ያገኘሁበት አጋጣሚ ሆነ፡፡ ቦቢ (ፖሊሱ) እንዲህ ሲል ሰማሁት፤‹‹በዚህ አካባቢ እየተዘዋወርን ነበር፡፡ እናም የግቢያችሁ የፊት ለፊት በር ክፍት ሆኖ አየነው ጌታዬ፡፡ የመጥሪያ ደወሉን ደወልን፡፡ ምላሽ ስናጣ በቤቱ ሰው ባይኖር ይሆናል አልን፡፡ እናም ምናልባት አንድ ግቢውን የተዳፈረ ክስተት ተፈጥሮ ይሆንም ብለን ጠረጠርን፡፡››
‹‹ታዲያ ወደ ውስጥ ገብታችሁ አላረጋገጣችሁም ?››
‹‹ኦ!ኦ! አረ በፍጹም ጌታዬ!›› ፖሊሱ የአባቴ ጥያቄ አስደንግጦት ነበር፡፡ ‹‹ዋራንት የለንማ! ህጋዊ የብርበራ ወረቀት ሳንይዝ፣ወደ ዜጎች መኖሪያ ቤት ለመግባት አንችልም’ኮ፡፡ እንዲያ ለማድረግ መሞከርማ ሕጉን የሚፃረር ተግባር መፈጸም ነው ጌታዬ››‹‹ግንኮ በሩም አልተቆለፈም ነበር›› አለ አባቴ፡፡››እሱ ምን ለውጥ ያመጣል ብለው ነው?›› ሲል መለሰ ቦቢ-ፖሊሱ ‹‹ገና ለገና በሩ ክፍት ሆኖ አግኝተነዋል ብለንም ቢሆን፤ የአጥር ግቢያችሁን ወሰን አንዲት ጋትም አልፈን ወደ ውስጥ እንገባ ዘንድ ሕጉ አይፈቅድልንማ፡፡
የግቢያችሁን የጀርባ በር በአትክልት ስፍራችሁ ውስጥ ሆኖ እንዲጠብቅ አንድ ባልደረባችንን መድበናል፡፡ እኔና ይኸኛው ባልደረባዬ ደግሞ ከምሽቱ አንድ ሰአት ገደማ ጀምሮ ላለፉት አምስት ሰዓታት ያህል እዚሁ ቆመን እየጠበቅን ነው ያለነው፡፡ አሁን እንግዲህ ከመጣችሁ ወደ ውስጥ ዘልቀን ለመፈተሽ ዝግጁ ነን፡፡ ያንንም ቢሆን ታዲያ እናንተ እንድንገባ ፈቃደኛ ከሆናችሁ ብቻ ነው ጌታዬ››ከአስር ደቂቃ በኋላ ፍተሻው ተጠናቀቀ፡፡ ማንም ሰው ወደ ውስጥ ዘልቆ አለመግባቱም ተረጋገጠ፡፡ ሁለቱ መኮንኖች ሲሰናበቱን፤ አባቴ ያቀረበላቸውን የገንዘብ ጉርሻ ‹እምቢ! የማይሆነውን!!› አሉ፡፡ አንድ አንድ ብርጭቆ ቢራ ለመጋበዝ ፈቃደኛ ቢሆኑም፤ አፍታም ሳይቆዩ ለአባቴ ‹‹ስራችንን ማስተጓጎል ስለማይገባን በቶሎ መንቀሳቀስ አለብን›› አሉትና እየተጣደፉ ውልቅ ብለው ሄዱ፡፡ወደ ውጪ ወጥቼ የፊት ለፊቱን የግቢያችንን በር ትክ ብዬ አየሁት፡፡ በአጥራችን ዙሪያ ያለውን አፀድ በሶምሶማ እያቆራረጥኩ ሄጄም፣የጀርባውን የግቢ በራችንንም እንዲሁ በደንብ አብጠርጥሬ አስተዋልኩት። ሁለቱም ያን ያህል ጠንካራ የሚባሉ በሮች አልነበሩም። አሁን ግን ከወትሮው
በተለየ ሁኔታ ጥንካሬያቸው ገዝፎ እንዲታየኝ የሚያደርግ ግንዛቤ በውስጤ ተፈጠረ፡፡ የእንግሊዝ መኖሪያ በሮች ናቸዋ! ሕጉ ነው ቅጽሩን ‹የሚጸልለው›፤ ግዘፍ ነስቶ የሚያረብብበት፤ የቱንም ያህል ደሳሳ ይሁን እንጂ፤ መኖሪያ ቤት ተብሎ እስከተጠራ ድረስ፡፡ የህይወትና አካላዊ ደህንነት ጉዳይም አስተማማኝ ነው - ከእንግሊዝ በር ጀርባ፡፡ከአንድ መቶ ሀምሣ አመታት በፊት፤ ከክቡር እምክቡራኑ ወገን (Earl of Chatham) ሆኖም ሳለ፤ ይህን አንጸባራቂ ሀሳብ ያመነጨውና በአስደናቂ ሁኔታም ያቀረበው ዊልያም ፒት (William Pitt)
የተባለ ታላቅ ሰው ነበረ፡፡ እንዲህ ሲል፡-. . .
በመኖሪያ ጎጆው ውስጥ ያለን አንድን ምስኪን ድሀ፤የዘውድ ስልጣን ከነሙሉ ኃይሉ አይገዳደረውም፡፡
ምሰሶው ዘምሞ የፈረሰ፤ ምርጊቱ ተነድሎ የተቆራረሰ፤ጣራው ዘብጦ የተበጣጠሰ፤ አውሎ ነፋስ የሚያፏጭበት፤
ወጀብ የሚፈነጭበት፤ ዶፍ ዝናብ የሚንዠቀዠቅበት ሊሆን ይችላል፤የእንግሊዝ ንጉሥ ግን መግባት አይችልም፡፡ከነሙሉ የዙፋን ስልጣኑና ኃይሉም ሁሉ ጋር፤ የዚያችን የተጎሳቆለችታዛ መግቢያዋን ተሻግሮ ለማለፍ ከቶም አይቃጣም፡፡ግቢያችን በር ላይ ቆሞ ባገኘሁት ኮንስታብል የተነሳ፤በዚህ በሰው ልጆች የግለሰብ ነጻነት እጹብ ድንቅ ቅርስ በእጅጉ ተደመምኩ፡፡ ታላቁ ሰው፤ የራሱን ስልጣን ሊያሳጣው እንደሚችል እያወቀም እንኳ፤ የእኛን የእያንዳንዳችንን ሰብዐዊ ነጻነት ለማስከበር ሲል፣ ይህን ክቡር ሀሳብ በድፍረት ማቅረቡ ይገርማል - ወኔው! (ሀሳቡ በጊዜው ከስንቱ ጋር አቆራርጦትስ ይሆን!)  ከዚያ በኋላ ታዲያ፤ አልፎ አልፎ ስለ እንግሊዝ ዴሞክራሲ አሉታዊ አመለካከቶች ሽው ሲሉ በሰማሁ ቁጥር  እሱን አስታውሰዋለሁ፡፡ በተለይም ዛሬ ላይ፤ በእነዚህ ጨፍጋጋ ቀናት ውስጥ ሆኜ፤ ሰላምን በመሻት
ስቃትት፤ ዘወትር ስለ እሱ አስባለሁ፤ ለተረጋጋች ዓለም የተስፋ ስንቅ!!
*   *   *
እኛም፤ ምንም እንኳ የሰው ዘር መገኛ ምድርና የቀደምት ስልጣኔ ባለታሪክ ህዝቦች ብንሆንም፤ ለዘርፈ ብዙ ችግሮቻችን በየጉዳዩ ዙሪያ  የተሻለ ተሞክሮ ያላቸውን ሀገራትና ሕዝቦች ታሪክ በማንጸሪያነት ማስተዋላችን ደግ ነው መቸም፡፡ ስለዬህ፤ በሰው ልጆች የሰብዐዊ መብት ክብር ዙሪያ ዛሬ ለተነሳው የዴሞክራሲ ርእስ ጉዳይም የእኛኑ ገጽ ገልጠን አየት አድርገን ብንሰነባበትስ . . .‹‹የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት - ምዕራፍ ሦስት - መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች - ክፍል አንድ - ሰብአዊ መብቶች - አንቀጽ !4 - የሕይወት፡ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት - ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፡ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት አለው፡፡ ››
እጹብ ድንቅ! ሸጋ፡፡ ይሁና . . .
ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያን ይባርክልን!!
አሜን!!
ምንጭ - Even The King May Not Enter.
by - Princess  Alexandra  Kropotkin

Read 1232 times