Sunday, 21 August 2016 00:00

ሰው ቢለብስ እንዳየሩ፤ ወፍ ቢጮህ እንዳገሩ

Written by 
Rate this item
(14 votes)

    ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጌታውን ወደ ጦር ሜዳ የሚወስድ ፈረስ ነበረ፡፡ ከጊዜ በኋላ ፈረሱ ማርጀቱ እየተሰማው መጣ፡፡ ፈረሱ በራሱ ጊዜ ለጌታው ማገልገሉን ትቶ የወፍጮ ቤት አገልጋይ ብሆን፤ ምናለበት ብሎ አሰበና ወደ ወፍጮ ቤት ለመቀጠር ሄደ፡፡ ባለወፍጮ ቤቶቹ፤ ‹‹ወደዚህ ለምን መጣህ?›› ሲሉ ጠየቁት፡፡ ፈረሱም፤ ‹‹እድሜዬ አረጀ፤ ቀጣዩን ዕድሜዬን የአሁኑን ማንነቴን ማረጋገጫ ማድረግ አለብኝ፤ ራሴን፣ የትላንት ማንነቴን ማረጋገጥ ማለትም፤ ይሄ ነው፡፡ ለፈረሱ፤ የወፍጮ ቤቱ ሕይወት እምብዛም ማራኪ አልሆነለትም፡፡ እንደ ከበሮው ምቱን ማጣጣም አልቻለም፡፡ ይልቁንም እያንዳንዷን እህል ለማድቀቅ፣ የእሱ የባርነት ጉልበት አስፈላጊ ሆነ፡፡ ኩራት ቀረ፡፡ ያም ሆኖ የዚህን ሥራውን ክብደት መሠረት አድርጎ፣ የበቆሎ መፍጨት ሥራውን መቀጠል ግድ ሆነበት፡፡ ‹‹ያገለገለ ፈረስ ሁሉ ወፍጮ ቤት እንዲሄድ አይመከርም!›› ይላሉ አዋቂዎች፡፡ ፈረሱ ግን ይሄ ፍልስፍና አልተዋጠለትም፡፡ ይህን ከባድ ሥራ ብሎ በወጉ ያስተዋለው ይህ ጉልበተኛ ፈረስ፤ ‹‹ጌታዬ! ከዕለታት አንድ ቀን፤ እኔ በጦርነት ቦታ ስመ ጥር አርበኛ ነበርኩ፡፡ ሴት ወንዱ እኔን ለማየት ከየቤቱ ወጥቶ አድናቆቱን ሲገልጥልኝ ከርሟል፡፡ የዛሬው የእኔ ቅርፅና መልክ ከዱሮው
በጣም የተለየ ሆኗል! ጦር ሜዳውን ትቼ ወደ ወፍጮ ቤት መምጣቴ ዛሬ በጣም ፀፅቶኛል፡፡አለው፡፡ባለ ወፍጮ ቤቱም እንዲህ አለው፤ ‹‹ስለትላንት መፀፀት ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ ንብረትና ባለፀግነት፤ አያሌ ላይና ታች፣ ክፉ የጥረት ውጣ-ወረድ፣ በእጅህ ሊኖር ግድ ነው! መጠንቀቅ የራሳችን ዋና ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር እንዳመጣጡ እንቀበለው፡፡ አንድ ወቅት ፈረሰኛ ነበርክ፤ አሁን ወፍጮ አስፈጪ ሆነሃል፡፡ ነገ ምን እንደምትሆን አይታወቅም፡፡ ሆኖም ነገንም በሰላም ለመቀበል ዝግጁ ሁን›› አለው፡፡

    …
የአገራችን ሁኔታ ወደድንም፣ ጠላንም አሳሳቢ ነው! ነገ ምንም ይምጣ ምን ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለብን፡፡ ቀውጥ እና ነውጥ ነገ የዕለት ሁኔታ ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹ኃይል ሁልጊዜ አያበላም››፤ ይላሉ አበው፡፡ ምክንያቱም ውሎ አድሮ ኃይል የለሹ ኃይለኛ ሊሆን ይችላልና ነው፡፡ ሰላም ያለ ተግባር ግልፅ አይደለም - አይገባም፡፡ ሰላምን ለማምጣት ሰላም- ለሚያሳጡ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ግዴታ ነው፡፡ ጥንት የመንግሥት ለውጥ በተደረገ ማግሥት፤ አንድ መሰረታዊ ነገር በሃገሪቱ መሪ ተነግሮ ነበር፡፡ ‹‹ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር አንዲት ጥይት አትጮህም›› ተብሎ ነበር፡፡ ከዚያ ወዲያ የተከተለው ነገር ሁሉ ግን፤ ግምቱንና ትንበያውን ያስተባበለ ነው፡፡ በከፊል ከማህበረሰቡ፣ በከፊል ደግሞ ከመንግስት በመነጨ ግጭት፤ ‹‹የአንድ ጥይት- አይጮህም›› ፅንሰ- ሃሳብ እንደ ከሸፈ ጥይት መሆኑ በይፋ ታይቷል፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ፤ ሀሳብን መግለፅ መታቀቡ የልብን መናገር አለመቻሉ፤ ለአንድ ሀገር ፍፁም አደጋ ነው። ‹‹ተናግሮ የትም አይደርስም›› ከሚል አምባገነናዊ ዕብሪት፤ እስከ  ‹‹እኔ እያወኩለት ምን ነገር ያስባዝተዋል›› እስከሚል ክልከላ ድረስ፤ ኢ-ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ መንሰራፋቱ ስህተት ላይ እንዳይጥለን መጠንቀቅ፤ እጅግ በጣም ወሳኝ
ነው! ሥራ- እጥነት አፍጦብናል። የኑሮ ውድነት የጥንቆላ ሳይሆን ነባራዊ ዕውነታ ነው፡፡ የቸገረው ሰው ጥያቄ ሲያነሳ መልስ እንጂ የነገ-ያልፍልሃል ራዕይ አያፅናናውም! በኃይል ሊገደብ ሲሞከር ደግሞ የባሰ ጥፋት ነው! ለማናቸውም ጥያቄ ህጋዊ መልስ ያስፈልገዋል የሚል መንግሥት፤ ህጋዊ ተቃውሞን አይንቅም። ማናቸውንም መሬት የያዘ እንቅስቃሴም ‹‹ከጀርባው የውጪ ኃይል አለበት››፣ ‹‹የአመለካከት ህፀፅ ነው››፣ ‹‹እኛ ከተነሳንበት ሀገራዊ ዓላማ ተፃራሪ ነው››፣ ‹‹ባለቤት የለውም›› ወዘተ በማለት ችግሩን እንዳናይ ሊያውረን አይገባም!! እሳት እየተቀጣጠለ እያለ፤ ‹‹እሳት የለም›› ብሎ መካድ ሳይሆን፤ አንድም እሳቱን የሚያቀጣጥሉ ኃይሎችን ልብ ብሎ ለይቶ መጠበቅና ተገቢ እርምጃ መውሰድ፤ ሁለትም ነገሩ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን በወቅቱ የእሳት አደጋ ሰራተኛ
መመደብና ረጋ ብሎ ማሰብ፤ ያሻል፡፡
ከዚህ ሁሉ ባሻገር ደግሞ፤ “እኔ ብቻ ነኝ እሳቱን የማጠፋው” ብሎ ግትር ከማለት ይልቅ፤ ሌላም ለሀገር የሚቆረቆር ዜጋ አለ ብሎ ማመን ዋና ነገር ነው! የፀጥታ ኃይሎችን አቅም ከማባከን ህዝቡበሰላማዊ መንገድ አስቦ፣ ተሳስቦ፣ መፍትሔ እንዲፈልግ መላ መምታት የተሻለ ነው፡፡መስማት የሚፈለገውን ድምፅ ብቻ የሚናገሩ ማህበረሰቦችን መሰብሰብ በኃይለስላሴም፣ በደርግም፣ አሁንም አላዋጣም፤ አያዋጣምም! በመሠረቱ ሀገራችን መበታተን የለባትም የሚለው የሁላችንም መፈክር ነው፡፡ የሥልጣን ክፍፍል፣ የሀብት ክፍፍል ማመላከቻ መሆን የለበትም፡፡ ባለሙያን እናክብር! ከሥር ያመረቀዘው ቁስል እስኪፈነዳ ጊዜ በሰጠን ቁጥር የህላዌ ገመዳችን እየሰለሰለ እንደሚሄድ አንዘንጋ፡፡ አንድ በሳል ፀሐፊ ስለ ኢህአዴግ መንግሥት አተያይ ሲሰጥ፤ ‹‹እኛ ስፉ እንጂ ጥፉ አንልም›› ይላል፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል! ራስን አለማሞኘት የችግራችን ግማሽ መፍትሔ ነው፡፡ ፅንፈኝነትን ግን አውቆ፣ ነቅቶ፣ በቅቶ መከላከል፣ ግዴታ ነው፡፡ ሆኖም እክሉን ለማስወገድ ከራስ መጀመር አሌ የማይባል ጉዳይ ነው! የችግር ሁሉ አዋቂ እኔ፣ መፍትሔውም እኔ ማለት፤ L’etat, c’est moi›› (መንግስትማ እኔ ራሴ ነኝ እንደማለት) እንዳለው የፈረንሳይ መሪ፤ አባዜ ይፈጥራል፡፡ ደርግ የሰራው ስህተት ሳናውቀው
እንዳይበክለን ማስተዋል እጅግ ብልህ ያደርገናል! ገለልተኛ የፓለቲካ ሂደት እንዲፈጠር መጣጣር
ወሳኝ ነው፡፡ አንዘናጋ! መምከርና መመካከር ዛሬ የማይታለፍ እርምጃ ነው! ብልህነት ነው!
የማንነት ጥያቄ ክስተት ሳይሆን በማናቸውም ጊዜ ህዝብ ሊጠይቀው የሚችል የለውጥ ነፀብራቅ ነው፡፡ ትልቁ ቁም ነገር በኃይል ሳይሆን በአግባቡ ጉዳዩን ማጤን ነው፡፡ ለመወያየት ዝግጁ መሆን ነው! ሁኔታዎችን እንደ ህዝብ ስሜት መከተል፤ ትላንትም፣ ዛሬም፣ ነገም ያለና የሚቀጥል ዕውነታዊ
ግዴታ ነው፡፡ እንደ ህዝቡ ዋና ስሜት ለመጓዝ እናስብ፡፡ ‹‹ሰው ቢለብስ እንደ አየሩ፤ ወፍ ቢጮህ
እንዳገሩ›› የሚለውን ተረት መቼም አንርሳ!

Read 6881 times