Saturday, 20 August 2016 12:46

ቶታል ኢትዮጵያ አዲስ አፕሊኬሽን አስመረቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ቶታል ኢትዮጵያ ከኤም ብር ጋር በመተባበር አዲስ የተቀላጠፈ የሞባይል ክፍያ አሰራር መተግበር የጀመረ ሲሆን ደንበኞች ካሉበት ሆነው የድርጅቱን አጠቃላይ አገልግሎቶች በተመለከተ የተሟላ መረጃ የሚያገኙበት “ቶታል ሰርቪስስ” የተባለ አዲስ የሞባይል ስልክ አፕሊኬሽንም አስመርቋል፡፡
የቶታል ኢትዮጵያ የሽያጭና የማርኬቲንግ ስራ አስኪያጅ ክሪስቶፊ ፌራንድ ባለፈው ረቡዕ በተከናወነው የምረቃ ስነስርዓት ላይ እንዳሉት፣የሞባይል ክፍያ አሰራሩ የኩባንያው ደንበኞች በማንኛውም ጊዜ የተለያዩ ክፍያዎችን መፈጸም፣ ገንዘብ መላክ፣ የሞባይል ካርድ መግዛት፣ ገንዘብ ማስቀመጥ ወይም ማውጣትና መገበያየት የሚችሉበት ነው፡፡
የኩባንያው ደንበኞች በተመረጡ የቶታል ማደያዎች ይህን አስተማማኝ፣ ጊዜ ቆጣቢና ቀልጣፋ የሞባይል ክፍያ ዘዴ በመጠቀም ነዳጅ መግዛት፣ መኪና ማሳጠብ፣ የመኪና ዘይት መግዛት፣ የሱፐር ማርኬትና የካፌ አገልግሎቶችን መጠቀም ወዘተ ይችላሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፤በቅርቡም ይህን አገልግሎት በሁሉም የቶታል ማደያዎች ለማስጀመር እየተሰራ እንደሚገን አስታውቀዋል። ቶታል ኢትዮጵያ ከዚህ በተጨማሪም ለደንበኞቹ ያለውን ተደራሽነት ለማስፋት በማሰብ፣ ደንበኞች ካሉበት ሆነው የሞባይል ስልኮቻቸውን በመጠቀም የድርጅቱን አገልግሎቶች በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎችን ማግኘት የሚችሉበትን ቶታል ሰርቪስስ የተባለ አዲስ የሞባይል ስልክ አፕሊኬሽን አስመርቋል፡፡  
አዲሱ የሞባይል አፕሊኬሽን፣ የቶታል ኢትዮጵያ ደንበኞች ባሉበት ሆነው በስልኮቻቸው አማካይነት ያለ ውጣ ውረድ በአቅራቢያቸው  የሚገኘውን የቶታል ማደያ ለማወቅና የሚሰጡ አገልግሎቶችን የተመለከቱ መረጃዎችን ለማግኘት የሚችሉበት ነው፡፡ ደንበኞች አዲሱን የቶታል ሰርቪስስ የሞባይል አፕሊኬሽን፣ ከጎግል ስቶር ላይ ማውረድ እንደሚችሉ በመጠቆም፣ ቶታል ኢትዩጵያ ለደንበኞቹ ያለውን ተደራሽነት ለማሳደግ ትኩረት በመስጠት በፀሐይ ብርሀን የሚሠሩ መብራቶች በማደያው እንዲሁም በህዳሴ ሱቆች ላይ ማቅረቡንም አስታውሰዋል፡፡
ኤምብር በአገሪቱ የሚገኙ አምስት ታላላቅ የብድርና ቁጠባ ተቋማትን በማቀፍ የጀመረውን ዘርፈ ብዙ የሞባይል የፋይናንስ አገልግሎት በማስፋፋትና የደንበኞቹን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ፣ የተቀላጠፈ አገልግሎቱን በስፋት እየሰጠ እንደሚገኝም በምረቃ ስነስርአቱ ላይ ተገልጧል፡፡

Read 2134 times