Sunday, 21 August 2016 00:00

ዛይ ራይድ ሜትር ታክሲ ሥራ ጀመረ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(19 votes)

የአዲስ አበባ ከተማን የታክሲ ችግር ይቀርፋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ዛይ ራይድ ሜትር ታክሲ ባለፈው ማክሰኞ ሥራ መጀመሩን አስታወቀ፡፡ የዛይ ራይድ ሜትር ታክሲ መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ ወጣት ሀብታሙ ታደሰ በሳምንቱ መጀመሪያ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤ መንግሥት ያዘዛቸው 750 ዘመናዊ ታክሲዎች ከጅቡቲ ገብተው ታርጋ እስከሚወጣላቸው ድረስ በከተማዋ ባሉ ላዳ ታክሲዎች ስራ መጀመሩን ጠቁሟል፡፡
እስከ ማክሰኞ ጧት ድረስ በታክሲው አገልግሎት ለመጠቀም 10,000 ሰዎች በፌስቡክ መመዝገባቸውን ጠቅሶ የጠቀሰው ወጣት ሀብታሙ የዋጋ ተመን እስከሚያወጣ ድረስ በ10 በመቶ ቅናሽ እንደሚሰሩ፣ በፌስቡክ ለመመዝገብ የደንበኛው ሙሉ ስም፣ ስልክ ቁጥርና ፎቶግራፍ እንደሚያስፈልግ ገልጿል፡፡
አገልግሎት ፈላጊው በሞባይሉ ጎግል ስቶር ወይም አፕስቶር አፕሊኬሽን አውርዶ ስሙን፣ ስልክ ቁጥሩንና ፎቶግራፉን አስገብቶ ይመዘገባል። አገልግሎት ሰጪው (የላዳው ሾፌር) ደግሞ ወደ ድርጅቱ ሄዶ ስሙንና ስልክ ቁጥሩን ነግሮ፣ ፎቶግራፉን ሰጥቶ ይመዘገባል፡፡ ደንበኛ አፕሊኬሽን አውርዶ አገልግሎት እንደሚፈልግ ሲገልጽ መልዕክቱ ድርጅቱ ጋ ይመጣል፡፡ ድርጅቱም አገልግሎት ፈላጊው ወዳለበት አካባቢ ያለ ሾፌር ጋ ደውሎ የደንበኛውን (የአገልግሎት ፈላጊውን) አድራሻ ይሰጠዋል፡፡ የሾፌሩ ስምና ስልክ ቁጥር ለአገልግሎት ፈላጊው ይላካል፡፡ ሾፌሩ አገልግሎቱ የተፈለገበትን ቦታ የሚያውቅ ከሆነ ይሄዳል፤ የማያውቅ ከሆነም በጂፒኤስ እየተመራ ይደርሳል፡፡ ከዚያም የአገልግሎት ፈላጊው ስልክ ስላለው “ደርሻለሁ” ብሎ ይደውልለታል፤ በዚህ ዓይነት ይገናኛሉ ብሏል፡፡
በተለመደው አሰራር አገልግሎት ፈላጊው መንገድ ላይ ቆሞ ወይም አስፋት ላይ ተሰልፎ ታክሲ ይጠብቃል፡፡ በእኛ አሰራር ግን ታክሲው አገልግሎት ወደፈለገው ሰው ዘንድ ይሄዳል ያለው ሀብታሙ፤ አገልግሎት ፈላጊው ቤት፣ ቢሮ ወይም ገበያ ቦታ ሆኖ ሊጠራ ይችላል፡፡ ታክሲው እዚያ ድረስ ይሄድለታል። ይህ አሰራር በተለይ ለአካል ጉዳተኞች በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ አገልግሎት ፈላጊው፣ ሾፌሩ ጥቃት (ጉዳት) ሊያደርስብኝ ይችላል ብሎ ከተጠራጠረ ለጓደኛው ወይም ለቤተሰቡ ደውሎ ያለበትን ቦታ መንገር ይችላል፡፡ እንደፈራው ሾፌሩ ያልታወቀ ቦታ ቢወስደው፣ በጂፒኤሱ ተከታትሎ ጉዳት ሳይደርስበት ማዳን ይቻላል ሲል አስረድቷል።
የአገልግሎት ክፍያውን በተመለከተ በተመኑ መሰረት በጥሬ ገንዘብ ወይም ታክሲው ላይ በሚለጠፍ ኤም ካሽ የገንዘብ ክፍያ ኮድ መክፈል ይቻላል ያለው ሀብታሙ፣ ደንበኛው፣ ሾፌሩ ተንከባክቦት ወይም አጎሳቅሎት ከሆነ ሲጋራ፣ አጫሽ፣ ጫት ቃሚ፣ መጠጥ ጠጪ፣ … መሆኑን በሚያሰፍርልን ማስታወሻ የሾፌሩን ሪከርድ ይዘን እንሸልመዋለን ወይም እናባርረዋለን ብሏል፡፡ በዚህ ዓይነት አሰራር የኬንያ ባለታክሲዎች ገቢያቸው በሦስት እጥፍ ማደጉንም ሀብታሙ ታደሰ ገልጿል፡፡

Read 9066 times