Sunday, 21 August 2016 00:00

“ሞጋች እውነቶች” ገበያ ላይ ዋለ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  የቀድሞው የ“አውራምባ ታይምስ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረውና በሽብርተኝነት ወንጀል 14 ዓመት እስር ተፈርዶበት ዝዋይ ማረሚያ ቤት የሚገኘው የጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፤“ሞጋች እውነቶች” የተሰኘ መፅሀፍ ሰሞኑን ገበያ ላይ ዋለ፡፡ መፅሀፉ ስለ አገራችን ወቅታዊ ሁኔታ፣ “ጉዋንታናሞ ቃ” ስለተባለው እስር ቤት፣ ስለ ዝዋይ ማረሚያ ቤት፣እድሜ ልክ ስለተፈረደባቸው ሰዎች ታሪክና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚዳስስ ነው፡፡
በ216 ገጾች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ71 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ደራሲው የመፅሀፉን መታሰቢያነት ለዲሞክራሲ፣ ለነፃነትና ለፍትህ ልዕልና አክብሮት ላላቸው፣አጋርነታቸውን ለሚያሳዩና ለሚታገሉ የሰው ዘሮች ይሁንልኝ ብሏል፡፡
ጋዜጠኛ ውብሸት፤ከዚህ ቀደም በእስር ላይ እያለ “የነጻነት ድምፆች” የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ ያበቃ ሲሆን የ2012 የሂውማን ራይትስ ዎች ሄልማን ሃሜት እና የ2013 የሲኤንኤን አፍሪካን ጆርናሊስት አዋርድ አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል፡፡
 በሌላ በኩል በአንተነህ አየለ የተፃፈውና በተለያዩ ሱሶች ምክንያት ከመስመር ስለወጡ ወጣቶች፣ ስለ ሱስ አጀማመር፣ ስለ ሱስ ማዘውተሪያ አካባቢዎችና ሱስን ተከትለው ስለሚመጡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ-ልቦናዊ ቀውሶች የሚያስቃኘው “ጃጃ ሲቲ” የተሰኘው መፅሐፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡ ፀሐፊው ስለ ሱስና መዘዞቹ ለመፃፍ የተነሳሳው ቾምቤ የተባለ ጓደኛው በሱስ ምክንያት ጓደኞቹ ከዩኒቨርሲቲ ሲመረቁ እሱ ሳይመረቅ በመቅረቱ የተሰማውን ቁጭትና ለቅሶ በማየት እንደሆነ በመግቢያው ላይ ገልጿል፡፡ በ216 ገጾች የቀረበው መፅሐፉ፤አገር ውስጥ በ76 ብር ከ90 ሳንቲም፣በውጭ አገራት በ20 ዶላር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

Read 2823 times