Sunday, 21 August 2016 00:00

ያረጀ ቲቪ እና አገር፤ መንግስት እና ‘ሕዝብ’...

Written by 
Rate this item
(21 votes)

• ዘረኝነት፣ … ማብሪያና ማጥፊያ የለውም። ዛሬ ‘ኦን’፣ ነገ ‘ሳይለንት’ ማድረግ አይቻልም።
• በዘፈቀደ ማበላሸትና ማፍረስ እንጂ፣ በዘፈቀደ መገንባትና ማስተካከል አይቻልም።
 
ያረጀ ቴሌቪዥን፣ ብዥ ብዥ፣ እያለ ሲያስቸግር ምን እናደርጋለን? ‘ግራና ቀኝ’ ማንገራገጭ፣ መደለቅ!
ነቅነቅ ነቅነቅ ሲደረግ፣ ይስተካከል ይሆናል። መቼም፣ ምኞት አይከለከልም። ግን፣ ምኞት ብቻውን፣ አያዘልቅ። ያለ እውቀት፣ ያለ ሞያና ያለ ጥረት፣... ሌጣ ምኞት ብቻውን፣ እያሳሳቀና እያታለለ ገደል ይከታል። ግራ ቀኝ በማንገራገጭና በመነቅነቅ፣ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ማስተካከል ቢቻል ኖሮ፣... የተበላሹ ኮምፒዩተሮችና ቴሌቪዥኖች፣ መጋዘን ባላጣበቡ ነበር። ቴሌቪዥን መጠገኛ ቤት ሂዱ፣... ከወለል እስከ ጣሪያ ድረስ ተደራርበው አቧራ የለበሱ የቴሌቪዥን አይነቶችን ታያላችሁ።
ማንገራገጭና መነቅነቅ፣ አልፎ አልፎ ብልሽትን ያስተካክል ይሆናል። ግን ብልሽትንም ሊያባብስ ይችላል። ለዘለቄታው፣ የዘፈቀደ ንቅናቄ... መፍትሄ አይሆንም።
አሳዛኙ ነገር፣ አገራችን ኢትዮጵያ፣ እንደ ተበላሸ ቲቪ፣ ግራና ቀኝ የሚደልቅና የሚያንገራግጭ እንጂ፣ በእውቀት፣ በሙያና በጥረት፣ ላይ ተማምኖ፤ አሳምሮ የሚጠግንና የሚያስካክል ብልህ፣ ጥበበኛና ጀግና አላገኘችም። አንዱ፣ እንደመጣለት ሲደልቅ፣ ሌላኛው በተራው ለማንገራገጭ እየተነሳሳ፣ በዙር እየተቀባበሉ ያጦዙታል፡፡ በእርግጥ ይሄ፤ የኛን አገር ብቻ የሚመለከት ችግር አይደለም፡፡ ጦዘው ጦዘው መውጫ ወደታጣለት ትርምስ ውስጥ ገብተው የተዘፈቁ አገራት በየአቅጣጫው እያን ነው። እንዲያም ሆኖ፣ … ይሄን ሁሉ እያየንም፣ ትንሽ ቆም ብሎ ከምር የሚያስብ፣ እውነታን አገናዝቦ የጠራ የነጠረ ሀሳብ ለማበጀት የሚሞክር ሰው ብዙም የለም፡፡
በአንድ በኩል ነባሩን ፕሮፓጋንዳ እየዘረፉ፣ በሌላ በኩል በአፀፋ ምላሽ ነባር የአሉባልታ ባህልን እያቀጣጠለ አገሬውን ቀውጢ ያደርጉታል፡፡ በአንድ በኩል፣ መንግስት፣ ባለሀብቶች ላይ ጥርሱን እየነከሰና ሰዎችን ከመኖሪያቸው እያፈናቀለ፣ እንዳሻው በሰው ኑሮ ላይ አድራጊ ፈጣሪ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፤ የባለሀብቶችን ስም በማጥፋት ንብረት የሚያቃጥል “የነፃነት ታጋይ” ዙሩን ያጦዘዋል፡፡
በአንድ በኩል፣ መንግስት በብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካዊ አማካኝነት፣ ሰዎችን በጅምላ የማቧደን ቁማር ይጫወታል፡፡ በሌላ በኩልስ? ያው፣ በተመሳሳይ ቁማር፣ አደጋውን የሚያጋግሉ “ተቃዋሚ ታጋዮች” ተጨምረውበት አገሪቱ ትቀወጣለች፡፡
ፕሮፓጋንዳን በአሉባልታ፣ ጉልበትን በስድብ
መንግስት፣ ከእውነታ የራቀ የፕሮፓጋንዳ አባዜ እንደጠናወተው ራሱም አይክደውም፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ የተነገረውን የሚደጋግም ተራ አዝማሪ እንዲሆን አድርገነዋል በማለት ባለስልጣናት ራሳቸውን ሲተቹ ሰምተናል፡፡ ከሌላ ሰው የሚመጣ ትችትንና አቤቱታን መስማት ግን አይፈልጉም፡፡ በጉልበት ማፈን፣ መፍትሄ ይመስላቸዋል፡፡
ትክክለኛው መፍትሄ ግን፣ እውነትን የሚያከብር ሃሳብና ውይይት ነው፡፡ አይደለም እንዴ? ነው እንጂ። ግን፣ ከበርካታ “ተቃዋሚ ታጋዮች” ብዙ ጊዜ የሚቀርበው መፍትሄ፣ ከመንግስት ፕሮፓጋንዳ ጋር የሚፎካከር አሉባልታ ነው፡፡
እንደ መንግስት ለጊዜው ጉልበት ባይኖራቸውም፣ ስልጣን እስኪይዙ ድረስ፣ የስድብ ዱላ ያዥጎደጉዱታል፡፡ የነሱ የአሉባልታና የስድብ ዘመቻ፣ ለመንግስት ጥሩ ሰበብ ይሆንለታል - ፕሮፓጋንዳና አፈና ለማስፋፋት። ፕሮፓጋንዳውና አፈናው ደግሞ በተራው፣ የአሉባልታና የስድብ አፀፋ ለማዝነብ ሰበብ እየሆነ፤ አገሬው የቅዠት አዙሪት ውስጥ ተዘፍቋል፡፡
“ችግሮችን በውይይት መፍታት ይቻላል” ብለው የሚያምኑ ሰዎች የሉም ማለቴ አይደለም። መኖርማ አሉ፡፡ ነገር ግን፣ ይህንን ምኞት እውን ለማድረግ፣ በቅድሚያ፣ “እውነትን የሚያከብር ስልጡን አስተሳሰብ” እንደሚያስፈልገን ይረሱታል። እውነትን ከምር የሚያከበር አስተሳሰብ ለመፍጠር ካልጣርን፣ “ውይይት … ውይይት” እያልን ብንውልና ብናድር ዋጋ የለውም፡፡ እውነት የማያከብር አገር ውስጥ፣ ፕሮፓጋንዳና አሉባልታ፣ አፈናና ስድብ እርስበርስ እየተቀባበሉ መንገሳቸው አይቀርም፡፡
የቅፅበት የቅፅበቷን፣ “ስዎች ኦን” “ስዎች ኦፍ”
በኑሮና በኢኮኖሚ ዙሪያ፣ ዋናዎቹ ጥያቄዎች “ሀብት ፈጠራ” እና “የንብረት ባለቤትነት መብት” ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ በእያንዳንዱ ሰው ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ… ወይም ደግሞ ጉልበተኛ እንዳሻው አዛዥ ናዛዥ የሚሆንበት “የእዝ ኢኮኖሚ” ናቸው አማራጮቹ፡፡
ያው፣ ብዙውን ጊዜ፣ ጉልበተኛው አዛዥ ናዛዥ፣ መንግስት ነው፡፡ አንዳንዴ፣ አልፎ አልፎ፣ “ተቃዋሚ ታጋዮች”፣ ከሰልፈኛ መሃል ገብተው፣ የሰውን ንብረት ያቃጥላሉ - ጉልበተኛ በሆኑበት ቅፅበት። ስልጣን ከያዙ ደግሞ፣. እንደዛሬው መንግስት፣ መደበኛ ጉልበተኛ ይሆናሉ፡፡ አዙሪት ነው፡፡
እንግዲህ አስቡት፡፡ መንግስት፣ ስለ “ንብረት ባለቤትነት መብት” በቁም ነገር ሲናገር ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? እንዲው፣ ለወግ ያህል ብቻ ስለ “ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ” ማውራት እንኳ ትቷል - ስንት አመቱ! ዛሬ የንብረት ባለቤትነት መብትን ሲያናንቅ፣ ነገ ንብረት ለሚያቃጥሉ ሰዎች አገሬውን እያመቻቸ መሆኑን ለማገናዘብ አይፈልግም፡፡ የዛሬ የዛሬዋን ብቻ ነው የሚያየው፡፡
እና፣ በዚህኛው ወር፣ በዚያኛው ከተማ፣ በተቃውሞ ሰልፍ መሃል፣ ጥቂት ነውጠኞች፣ የሰውን ንብረት ቢያቃጥሉ፣ … ምን ይገርማል? አብዛኛው ጨዋ ሰልፈኛ፣ ጥቂት ነውጠኞችን ለመከላከል የሚሳነው አለምክንያት አይደለም፡፡ ለሃብት ፈጠራና ለንብረት ባለቤትነት መብት ብዙም ክብር የለውም፡፡ ያኔ ጉልበተኞችና ነውጠኞች ይመቻቸዋል፡፡ በአንድ በኩል መደበኛው ጉልበተኛ መንግስት፣ በሌላ በኩል ነውጠኛ “ታጋዮች” እየተቀባበሉ፣ አገሬውን ያንገጫግጩታል፡፡
የብሄር ብሄረሰብና የሃይማኖት ፖለቲካ ቁማር
ሰዎችን በጭፍን ስሜትና በመንጋ ለማነሳሳት፣ የድጋፍ ሆይ ሆይታ ለመፍጠር፣ ተቀናቃኝን ለማጥፋት ነው፤ የቁማር ጨዋታውን የሚጀምሩት፡፡ ነገር ግን፤ ዛሬ የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካን እያራገበ፣ ቁማር የሚጫወት መንግስት፣ ነገ ሌሎች ተመሳሳይ ቁማርተኞች እንደሚመጡ ማወቅ የለበትም?
ዛሬ፣ ሃይማኖትን በመጠቀም፣ ጭፍን ስሜትን የሚያጋግል መንግስት፤ … ነገ፣ ከነገ ወዲያ በጭፍን የሚነሳሱ ብዙ መንጋዎችን እየፈለፈለ እንደሆነ መገንዘብ አይገባውም?
በዘር የማቧደን ዘመቻ የሚያካሂድ ተቃዋሚ፣ ለተመሳሳይ የዘረኝነት ቁስቁሾች አገሬውን እያመቻቸ እንደሆነ፣ አይታየውም?
አይታያቸውም የቅፅበት የቅፅበቷን በቁንፅል ለማየት ነው የሚፈልጉት፡፡ ነገር ግን ዘረኝነትና በጅምላ የመቧደን አስተሳሰብ፣ ጭፍን ስሜትና ጭፍን እምነት …  ስንፈልግ “ስዊች ኦን”፣ ስንፈልግ “ስዊች ኦፍ” ልናደርገው አንችልም፡፡
አገር ስንቀውጥበት ውለን፣ ማታ “ሳይለንት” አድርጎ መተኛት አንችልም፡፡







Read 6757 times