Sunday, 21 August 2016 00:00

እባካችሁ፤ አዳም እምብርት ይኑረው

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(3 votes)

አዳም ተፈጠረ እንጂ አልተወለደም ብላችሁ የምታምኑ ሁላችሁ እንደምን ናችሁ፡፡ እኔ ደህና ነኝ … ካለናንተ ሀሳብና ናፍቆት በስተቀር እንዳልላችሁ …  እኔ እናንተን አላውቃችሁም፡፡
“አዳም ተፈጠረ እንጂ አልተወለደም” …የሚለው ሀሳባችሁ በጥቅል ይገልፃችኋል ብዬ ልገምትና በዚህ እምነታችሁ መሰረት፣ ትውውቃችንን ላፋፍመው፡፡ ያልተፈተነ ትውውቅ በኋላ ያካክዳል፡፡ ስለዚህ እምነታችሁን ልፈትን፡፡
ፊሊፕ ጎስ የሚባል በቪክቶሪያ ዘመን የነበረ ደራሲ “ኦማፓሎስ” (Omphalos) የሚባል መፅሐፍ ደርሶ ነበር፡፡ “ኦማፓሎስ” በግሪክ ቋንቋ “እንብርት” የሚል ነው ትርጉሙ፡፡ ደራሲው በመፅሐፉ አዳም ያልተወለደ ቢሆንም እንብርት ግን ነበረው እያለ ይወዛገባል፡፡
እናንተ አንባቢዎችስ ምን ታስባላችሁ፤ እንብርት ነበረው ወይንስ አልነበረውም? … እንብርት የሌለው ሰው ሲበላ ቢውል አይጠግብም ብለን እናስብ ነበር ልጅ ሳለን። እንግዲህ አዳም የተፈጠረ እንጂ ያልተወለደ ከሆነ ዘረ - መል (gene) የለውም ማለት ነው፡፡ ዘረ - መል ከሌለው ብቻ ነው የእድገት ሂደቱን ጨርሶ፣ ከጭቃ ተጠፍጥፎ ሊፈጠር የሚችለው። ልክ እንደ ሐውልት፡፡
እንብርት የሚያመለክተው፤ተወላጁ በእናቱ ማህፀን ውስጥ ያሳለፈውን ቆይታ ነው፡፡ ከመሐፀን ያልወጣ እንብርት አያስፈልገውም። በአዳም ዘመን የ“ክሎኒንግ” ቴክኖሎጂ ነበር ማለት ነው፡፡ “ክሎን” ያደረገው ፈጣሪ ነው እንበል፡፡ እንበል ካልን ፈጣሪ አምላክነትና ሳይንቲስትነትን አጣምሮ የሚያከናውን ነው ማለት ይሆን?
ግን ጥያቄው ወዲህ ነው፡፡ የሰው ተፈጥሮ እንደ አዳም አፈጣጠር ቀላል አይደለም፡፡ አልቆ አልተፈጠረም፡፡ ህፃን ሆኖ ይወለድና ወደ ጎረምሳ ይለወጣል፡፡ ጎርምሶም አይቀርም፤ ይጎለምሳል፡፡ ጎልምሶም አይቀርም ያረጃል። ይሞታል፡፡ በውልደትና ሞት መሀል ደግሞ ልጅ ወልዶ ራሱን ይተካል፡፡ አዳም ግን እንደ ሀውልት ነው፡፡ ከጭቃ መሰራቱም ሀውልትነቱን የሚያመለክት ነው፡፡ ግን የሚንቀሳቀስ ሀውልት ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ሚስት አግብቶ ልጅ ወልዷል፡፡ ዘረ - መልን ለተተኪ የማስተላለፍ ሂደት ነው ልጅ መውለድ፡፡ ስለዚህ አዳም እንብርት ባይኖረውም ዘረ - መል ግን ነበረው ማለት ነው፡፡ ዘረ - መሉ መውለድ ያስችለዋል። ዘረ መሉን በዓለም ላይ ላሉ የሰው ልጆች አካፍሏል፡፡ እንብርትን አውርሶናል፡፡
ከታች ወደ ላይ
ነገሩ ውስብስብ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ፎቅ መስራት የፈለገ ባለ ሀብት ፎቁን የሚቀልስለት ኢንጂነር ይቀጥራል፡፡ ፎቁ ንድፍ (blue print) ያስፈልገዋል፡፡ ከላይ ወደ ታች የሚሰራ ነው ፎቁ፡፡ መጀመሪያ ንድፍ የሚያበጅ አለ፡፡ ንድፉን ወደ ተግባር የሚቀይሩ ሰራተኞች ይኖራሉ። ሰራተኞቹ ተግባራቸውን የሚያከናውኑት በንድፉ መሰረት ነው፡፡ በንድፉ መሰረት የፎቁ ስራ ከየት እንደሚጀምር፣ ከጀመረ በኋላ በቅደም ተከተል የትኛው ስራ እንደሚከናወን ሰራተኞቹ ያውቃሉ፡፡ የተለያዩ ባለሙያዎችን እንደ ቅደም ተከተላቸው አስተባብሮ ስራው እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚያስተሳስር የስራ ሂደት (እቺን ሐረግ አልወዳትም!) ኃላፊ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እንደ ኮንትራክተር ሊቆጠር ይችላል - የዚህ የኃላፊነቱ ተጠሪ፡፡
ፎቅ ለመቀለስ ይህ ነው የስራ ቅደም ተከተል ተዋረዱ፡፡ የሰው ልጅ ግን ሲፈጠር እንደ ፎቁ ነው? ከባዱ ጥያቄ ይሄ ነው፡፡ ምን ይከብዳል?! … ሰውም የተሰራበት ንድፍ (blue print) አለው! ብላችሁ ልትቆጡኝ ትችላላችሁ፡፡ ቆይ አትቆጡኝ! … በቁጣ መች ይሆናል ብላችሁ ነው! … ፎቶ ሲሰራ አንድ ንድፍ ነው ያለው፡፡ ፎቁ አንዴ ይሰራል … በጊዜ ሂደት ቁመትም ሆነ ቅርፅ አይቀይርም፡፡ ሐውልት ነገር ነው፡፡
የሰው ልጅ ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ መጀመሪያ ህፃን ሆኖ ይወለዳል፡፡ ይሄንን አንድ ንድፍ በሉት፡፡ በመሀፀን ውስጥ ልክ እንደ ፎቁ፣ በተለያዩ የተፈጥሮ ኃይሎች ርብርብ… ዘጠኝ ወር ፈጅቶ ፎቁ ይወለዳል፡፡ ግን ፎቁ (ህፃኑ) በዚያው አንድ ንድፍ አይቆይም፡፡ ከህፃን ወደ አዋቂ ደረጃ እያደገ እስኪደርስ ብዙ ንድፎች ያስፈልጉታል። የሚገርመው ግን ንድፉን የሚያበጀው ራሱ ንድፉ መሆኑ ነው፡፡ ንድፉ በህፃኑ ዘረ - መል ውስጥ ያለ ነው፡፡ ዘረ - መሉ ራሱ ንድፉ ሆኖ ሳለ ንድፉን የሚሰራውም ራሱ ነው፡፡ ልክ ራሱን እንደሚሰራ መኪና አድርጋችሁ እዩት፡፡ ራሱን የሚሰራው ግን አንድ ደረጃ እስኪደርስ ነው፡፡ አንድ ርቀት ሲደርስ ስራውን በራሱ ያቋርጣል። ይሄንን ራሱ የሚያቆምበትን ቦታ “ሞት” ብለን የምንጠራው ነው፡፡
ራሱን በራሱ እንዲያሻሽል (እንዲለውጥ) እና በተወሰነ ቦታ ላይ እንዲገታ የሚያደርግ ንድፍ ምን አይነት ነው? ህያው ስጋ (አካል) እንዴት እንዲሰራ … እንዲያድግና እንዲሞት የሚያደርገውን ህግ ለመገንዘብ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ አስቸጋሪ ያደረገው ውስብስብነቱ ነው፡፡
“epigenesis” የሚለውን ቃል የፈጠሩት ይሄንን አስቸጋሪ ፅንሰ ሀሳብ መግለፅ እንዲችሉ መሆን አለበት፡፡ ኢፒጄነሲስ ማለት፡- የአንድ ህይወት የመፈጠር፣ የማደግ፣ የመለወጥ ንድፍ ቢሆንም መፈጠር፣ መወለድ፣ ማደግን የሚያዘው ውስጠኛው ህግ ግን ባለበት ፀንቶ፣ ሳይለወጥ  የሚያከናው ሂደት እንደ ማለት ነው። … የሚለውን ህግ የሚዘውር የማይለወጥ ጠቅላይ ህግ እንደ ማለት ነው፡፡ (A theory of the development of an organism by progressive differentiation of an initially undifferentiated whole)
ምሳሌ ልስጥ፡- … የወጥ አሰራር ዘዴ (የንድፍ ህግ ማለት ይከብዳል) ወጥ የመወጥወጫ ቅደም ተከተል እንበለው፡፡ ፈረንጆቹ “recipe” ብለው ነው የሚጠሩት፡፡ ለእነሱ ሾርባ፣ ለእኛ ወጥ በምንቀምምበት ጊዜ፤ ከሽንኩርቱ ቀጥሎ ምን ወደ ቁሌቱ እንደገባ … ጨው መቼ እንደተጨመረ … ወዘተ … ወጡ ተቁላልቶ ለመብል ሲቀርብ ተመጋቢው ማወቅ አይችልም፡፡ አወሳሰብኩት መሰለኝ! … ግልፅ ላድርገው፡፡ የወጡን ጣዕም ተሰርቶ ካለቀ በኋላ በመቅመስ፣ የአሰራሩን ቅደም ተከተል ማወቅ አንችልም፡፡ በወጡ ውስጥ የተካተቱትን ቅመማ ቅመምና ሌላ ግብአቶች በማጣጣም ልንለያቸው ብንችል እንኳን … በቅደም ተከተል መጀመሪያ ምን ተጨምሮ ምን እንደተከተለ ተመጋቢው አጣጥሞ ንድፉን ሊደርስበት አይችልም፡፡
የኬክ መስሪያ “ሬስፒን” ተከትለን ኬክ መስራት ላይ ልንደርስ እንችላለን እንጂ ከኬክ ተነስተን “ሬስፒው”ን አናውቅም እንደማለት ነው፡፡ ሬስፒ ከፎቅ ስራ የሚለየው እዚህ ላይ ነው፡፡ ተሰርቶ ያለቀ ፎቅን ይዘን፣ ፎቁን ለመስራት ያገለገለውን “blue print” መልሰን መንደፍ እንችላለን፡፡ ልክ እንደዚሁ … ሰውን ከልጅነት እስከ እስከ እውቀት … ከዚያም እስከ ሞቱ ያሳለፈውን በመመርመር ሰውን ለመስራት ያገለገለውን ዘረ-መል ንድፍ ወደ ኋላ መፃፍ አይቻልም፡፡ ልክ የምግብን ሬስፒ እንደማግኘት ከባድ ነው፡፡ ዘረ - መልን መስራት በዚህ ምክኒያት አይቻልም፡፡
ስለዚህ፤ አዳም እንብርት አለው ወይንም የለውም ሳይሆን አስቸጋሪው ጥያቄ አዳም የተሰራበትን ዘረ-መልን … ንድፍ ማወቁ ነው ራስ ምታቱ፡፡ አዳምን የሰራው ፈጣሪ … ኋላ ቀር እንዳይባልብን፣በጭቃ ጠፍጥፎ ነው የሰራው የሚለውን ትረካ ቀስ እያልን መተው ሳንገደድ አይቀርም፡፡ ሰውን ከጭቃ ጠፍጥፎ … ትንፋሽ እፍ ማለት ፈጣሪን ከቀራፂ (Artist) የበለጠ ረቂቅ አያደርገውም፡፡
አዴች (አዳም) እንብርት ቢኖረው ግን ይረቅቃል፡፡ ምክኒያቱም፤ በእንብርት በስተጀርባ የመረገዝና የመወለድ ሂደት አለ፡፡ የመወለድ ሂደት ውስጥ ደግሞ ውስብስብ የሆነው ዘረ - መል (gene) እንቆቅልሽ አለ፡፡ የተፈጥሮ ደራሲ (እግዜር) ርቀቱና ጥልቀቱ የሚገባን በዚህኛው አቅጣጫ ከተመለከትን ነው፡፡ … ለፈጣሪ ጥልቀት መስጠት ብንፈልግም ባንፈልግም የተፈጥሮ ምስጢር ጥልቅ ነው፡፡ አዳምም ሆነ ጥቅሉ የተፈጥሮ አሻራ በዚህ የጥልቀት ንድፍ (እስትንፋስ) መዳሰሱ ግልፅ ይሆንልናል፡፡ ግልፅ ሆኖ ሳለ የፍጥረትን ታሪክ ወደ ሀውልት አቀራረፅ ታሪክ ላለማሳነስ ሲባል … እባካችሁ አዳም እንብርት ይኑረው፡፡  

Read 4805 times