Monday, 29 August 2016 10:17

አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ሜዳልያው ፀደቀለት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(48 votes)

በኢንተርኔት ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰባስቦለታል
           መንግስት የፖለቲካ አቋሙን እንደሚያከብርለት ገልጾ ነበር
                  
   አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በሪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ላይ ያሳየው የተቃውሞ ምልክት በውድድሩ 2ኛ በመውጣት ያገኘውን የብር ሜዳልያ እንዳያሰርዝበት ተፈርቶ ነበር፡፡ ከትናንት በስቲያ አለማቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ፤ አትሌት ፈይሣ በውድድር መጨረሻ ላይ የኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውን ትግል ለመደገፍ እጁን በማጣመር ላሳየው ምልክት እንደማይቀጣ መወሰኑን አስታውቋል፡፡  
የኢትዮጵያ መንግስት አትሌቱ ወደ ሀገሩ ቢመለስ የተለየ ችግር እንደማያጋጥመው ያስታወቀ ቢሆንም ወደ አገር ቤት ከመመለስ ይልቅ እዚያው ብራዚል ሪዮ ከተማ መቅረትን መርጧል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከአሜሪካ የሄዱ 3 ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጠበቆች የህግ ድጋፍ እያደረጉለት ነው ተብሏል፡፡ ቢቢሲና አልጀዚራን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አትሌቱ ባሳየው የተቃውሞ ምልክት በኢትዮጵያ በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልል ያለውን ተቃውሞና ግጭት ለዓለም አጋልጧል የሚሉ ዘገባዎችን ሲያቀርቡ ሰንብተዋል፡፡
ሮይተርስ ያነጋገራቸው የአትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ወላጅ እናት፤ ልጃቸው ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንደሌለበትና ባለበት እንዲቆይ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። ባለቤቱ በበኩሏ፤ ፈይሣ ይሄን ማድረጉ ብዙም እንዳላስደነቃትና ወትሮም ሰዎች በተቃውሞው ስለመገደላቸው ይጨነቅ እንደነበር ገልፃለች፡፡ ኬንያዊው አትሌት ኢማኑኤል ኢጉንዛ ስለ ፈይሳ ድርጊት ከቢቢሲ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ፤“ፈይሳ አስተዋይ የኦሎምፒክ ተወዳዳሪ መሆኑን ቢያስመሰክርም ድርጊቱ ህይወቱን በስደት እንዲመራ አድርጎታል” ብሏል፡፡  
አትሌቱ ጥገኝነት ለመጠየቅ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ተቀማጭነታቸውን አሜሪካ ካሊፎርኒያ ያደረጉ ኢትዮጵያዊያን 10 ሺህ ዶላር ለማሰባሰብ አቅደው በኢንተርኔት “go found me” የተሰኘ ድረ ገፅ በመክፈት እስከ ትናንት ድረስ ከ130 ሺህ ዶላር (3 ሚሊዮን ብር ገደማ) ማሰባሰባቸው ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል የማራቶን ውድድሩ በኢቢሲ ጣቢያ 3፣ በቀጥታ ሲተላለፍ እንደነበር የጠቆመው ቢቢሲ፤ የተቃውሞ ምልክቱ ከታየና ውድድሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ፈይሳ በሀገሪቱ ጣቢያ ዳግም ለህዝብ አልታየም ብሏል፡፡ አልጀዚራም ባጠናቀረው ተመሳሳይ ዘገባ፤  አትሌቱ የተቃውሞ ምልክቱን ካሳየ በኋላ፣ ኢቢሲ ምስሉን ለህዝብ አላሳየም ብሏል፡፡
የአትሌቱን የተቃውሞ ምልክት ማሳየት ተከትሎ፣ ቴሌግራፍ፣ ዴይሊሜል፣ ዘ ጋርዲያን፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ሮይተርስ፣ የአሜሪካ ድምፅ (የአማርኛና እንግሊዝኛ ጣቢያዎች) ኢቪኒንግ ስታንዳርድ፣ ዘ ትሬት ታይምስ፣ ሞስኮ ቪሌጀር፣ ቻይና ፖስትና ሌሎች በርካታ የተለያዩ ሀገራት ሚዲያዎች ዘገባውን እንደተቀባበሉት ታውቋል፡፡  
ይህ በዚህ እንዳለ መቀመጫውን በአሜሪካን ያደረገ ‹‹የኦሮሞ ጥናት ማህበር›› የተሠኘ ተቋም በኦሮሚያ ክልል ስላለው ተቃውሞ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ በፃፈው ደብዳቤ፤ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ የኦፌኮ ተ/ፕሬዚዳንት አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎች ፖለቲከኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ ጠቅሶ፣ የአሜሪካ መንግስት ከእስር እንዲፈቱ ግፊት ያድርግ ዘንድ ጠይቋል። የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በበኩሉ፤ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እንዳሳሰበው ጠቁሞ መንግስት ተቃውሞውን እያስተናገደ ያለበት አግባብ ለራሱም የሚበጀው አይሆንም ብሏል፡፡ እስከ መጪው የፈረንጆች ዓመት የካቲት ወር ድረስ (Feb 18,2017) የሚቆይ የጉዞ ማስጠንቀቂያም ለአሜሪካውያን ዜጎች አስተላልፏል፡፡ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ባወጣው የጉዞ ማስጠንቀቂያ፤‹‹በሃገሪቱ ያለው ተቃውሞ ቀጣይነት ያለው ይመስላል፤አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ሊስፋፋ ይችላል፡፡ የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት እየተቋረጠ በመሆኑም በኢትዮጵያ ያሉ አሜሪካውያን ከኤምባሲያቸው ጋር መገናኘት እየቻሉ አይደለም” ብሏል፡፡ አሜሪካውያን ስለ አካባቢያቸው በቅጡ ግንዛቤ እንዲጨብጡና ሁኔታዎችን እንዲመረምሩ ያሳሰበው የጉዞ ማስጠንቀቂያው፤ህዝባዊ ተቃውሞዎችና ሰልፎች ከሚካሄዱባቸው ሥፍራቸው እንዲርቁም በጥብቅ መክሯል፡፡

Read 7301 times