Monday, 29 August 2016 10:18

ትላንት በጎጃም ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(61 votes)

በጎንደር ለ2ኛ ጊዜ ከቤት ያለመውጣት አድማ እየተካሄደ ነው
     ተቃውሞውን ለማስቆም እርምጃ እወስዳለሁ”- የክልሉ መንግስት
        ትላንት በባህር ዳር አንዳንድ የንግድ ተቋማት ታሸጉ
                 
   ትናንት በተለያዩ የጎጃም ከተማዎች የተቃውሞ ሠልፍ የተደረገ ሲሆን በጎንደርና አካባቢው ባሉ ከተሞች ባለፈው ረቡዕ ለ2ኛ ጊዜ የተጀመረው የቤት ውስጥ መቀመጥ አድማ እንደቀጠለ ነው ተብሏል። በምዕራብ ጎጃም ዳሞት ወረዳ ቡሬ ከተማ ላይ በትናንትናው ዕለት ህዝቡ የአደባባይ ተቃውሞ ማድረጉን የጠቆሙት የመኢአድ ዋና ፀሐፊ አቶ አዳነ ጥላሁን፤ በተቃዋሚዎችና በፀጥታ ሃይሎች መካከል ግጭት መፈጠሩንና የተኩስ ድምፅም ሲሰማ እንደነበር ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ በቡሬ በተካሄደው ተቃውሞና ግጭት በሰዎች ህይወት ላይ ጉዳት ስለመድረሱ ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ሠዓት ድረስ ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
በሰሜን ጎንደርና በጎጃም ባህርዳርና ፍኖተ ሰላም ከተሞች ሰሞኑን  አድማዎችና የአደባባይ ተቃውሞዎች የተደረጉ ሲሆን በጎንደር ከተማና በተለያዩ ወረዳዎች ለሁለተኛ ጊዜ ከቤት  ያለመውጣት አድማ እየተካሄደ ነው፡፡ የክልሉ መንግስት፤ ከዚህ በላይ እንደማይታገስ ጠቁሞ፣ ተቃውሞውን ለማስቆም እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል።  በባህር ዳር ከተማ ደግሞ ከእሁድ ነሐሴ 14 እስከ ማክሰኞ ነሐሴ 16 የቆየ ከቤት ያለመውጣት አድማ የተደረገ ሲሆን የከተማው ንግድ ኢንዱስትሪ ቢሮ፤ የንግድ ተቋማት ድርጅታቸውን ከፍተው እንዲሰሩ፣ ካልሆነ ግን የንግድ ፍቃዳቸው እንደሚነጠቅ አሳስቦ እንደነበር የጠቆሙ ምንጮች፤ በትላንትናው ዕለት አንዳንድ የንግድ ተቋማት መታሸጋቸውን ገልፀዋል። ከቤት ያለመውጣት አድማው እስከ ረቡዕ ድረስ በከፊል መቀጠሉን የገለጹልን ነዋሪዎች፤ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ መደበኛ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ የባህር ዳር ኮሙኒኬሽን ቢሮ በበኩሉ፤በከተማዋ የተደረገ የህዝብ አድማ የለም ባይ ነው፡፡  
የጎንደር ከተማን ጨምሮ በአብዛኞቹ የሰሜን ጎንደር ዞን ወረዳዎች፡- በደምቢያ፣ ደባርቅ፣ ከሊፋ ጣቁሳ፣ ጫሂትና ሌሎች ከረቡዕ ጀምሮ ለሁለተኛ ጊዜ የቤት ውስጥ መዋል አድማ እያደረጉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። በጎንደር ከተማ በተመሳሳይ ቀን የተቃውሞ መነሻ የሆኑት የወልቃይት የማንነት ኮሚቴ መሪው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ፣ ታስረውበታል በተባለ ማረሚያ ቤት አካባቢ ከፍተኛ ውጥረት ተፈጥሮ እንደነበር ያስታወሱት ምንጮች፤ ኮሎኔሉ በፀጥታ ኃይሎች ሊወሰዱ ነው በሚል የከተማዋ ወጣቶች በቡድን ተደራጅተው በማረሚያ ቤቱ አካባቢ ተሰብስበው ማደራቸውንና የተኩስ ልውውጦችም መሰማታቸው ጠቁመዋል፡፡  
ረቡዕ በጎንደር በተጀመረው ቤት ውስጥ የመዋል አድማ ክሊኒኮች፣ ዳቦ ቤቶችና መድኃኒት ቤቶች እንዲሰሩ ተፈቅዶላቸዋል ያሉት ምንጮች፤ ሌሎች የንግድ ተቋማትም ሆኑ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ግን እየሰሩ አይደለም ብለዋል፡፡ አድማው ለ5 ቀናት እንደሚቆይ በግልፅ ተነግሯል ያሉት ምንጮች፤ እስከ ትናንት አመሻሽ ድረስ ወደ ከተማዋ የሚገባና የሚወጣ ተሽከርካሪ እንዳልነበረ ጠቁመው፤ በከተማዋ ዳቦ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች ግን እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡  
አድማው የተደረገው ማክሰኞ ማታ በተበተነ የጥሪ ወረቀት ምክንያት ነው ያሉት ምንጮች፤ የወልቃይት ጉዳይ እልባት ካላገኘ ተቃውሞውም ሆነ አድማው እንደሚቀጥል  መነገሩን ጠቁመዋል፡፡ የመጀመሪያው ተቃውሞ በጎንደር ከተማ ከተደረገ ወዲህ እስካሁን ድረስ ኢንተርኔት ፌስቡክና ማህበራዊ ሚዲያዎችን የመሳሰሉ አገልግሎቶች መቋረጣቸውን  ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡  
በተመሳሳይ ረቡዕ ዕለት በፍኖተ ሠላም ከተማ፣ ከ60 ሺህ ህዝብ በላይ የተሣተፈበት የአደባባይ ተቃውሞ ሲደረግ የዋለ ሲሆን በተቃውሞው ላይ የክልሉንና የፌደራል መንግስትን የሚያውግዙ መፈክሮች ተስተጋብተዋል ተብሏል፡፡ ህዝቡ ሁለት እጆቹን ወደ ላይ አንስቶ በማጣመርም ለኦሮሞ ተወላጆች ትግል ያለውን ድጋፍ አሳይቷል ያሉት ምንጮች፤ በሰልፉ ላይ አርማ የሌለው ሰንደቅ አላማ ሲውለበለብ መዋሉንም ተናግረዋል፡፡ ተቃውሞውን ተከትሎ  ከትናንት በስቲያ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን የክልሉ መንግስት አስታውቋል፡፡ ወደ ከተማዋ የሚያስገቡ ዋና ዋና ጎዳናዎችም ረቡዕ ዕለት በድንጋይ ተዘግተው መዋላቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡   
የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከትናንት በስቲያ ለአማራ ክልል መገናኛ ብዙኃን በሠጡት መግለጫ፤ በክልሉ ያለው ተቃውሞና ግጭት ከዚህ በላይ እንዲቀጥል መንግስት እንደማይፈቅድና ተቃውሞዎቹን ለማስቆም እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል፡፡  
‹‹እየተፈጠረ ያለው ግጭት ህብረተሰቡን ለፍርሃትና ለጭንቀት ዳርጓል” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይም ችግር አስከትሏል ብለዋል፡፡ ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ የበለጠ እየተወሳሰበ፣ የህብረተሰቡን ሰላም የሚያደፈርስና ማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ፣እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አቶ ገዱ ጠቁመዋል።
በክልሉ ከተወከሉ የተለያዩ ሽማግሌዎች፣ ወላጆች፣ የሃይማኖት አባቶችና ወጣቶች ጋር በህዝቡ ተቃውሞዎችና ጥያቄዎች ዙሪያ ውይይት መካሄዱን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ በውይይቱ የተነሱ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት በትጋት እንደሚሰራ ገልፀዋል። ባለፈው ረቡዕ በጎንደር ማረሚያ ቤት የሚገኙት ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ፣ ወደ ሌላ ቦታ ሊወሰዱ ነው በሚል በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት ነግሶ እንደነበር የጠቀሱት አቶ ገዱ፤ ግለሰቡ በወንጀል ተጠርጥሮ በህግ ቁጥጥር ስር የሚገኝ እንደመሆኑ መጠን፣ ሁሉም ነገር ህግ በሚፈቅደው አግባብ እንደሚፈጸም አስረድተዋል። “ተጠርጣሪውን ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር ቢፈለግ ኖሮ፣ በቁጥጥር ስር በዋለበት እለት ማዛወር ይቻል ነበር” ብለዋል - ፕሬዚዳንቱ፡፡

Read 13550 times