Monday, 29 August 2016 10:26

እውነቱን ተናግረን ሰይጣንን እናሳፍረው

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(5 votes)

መንግሥት መድኃኒት በሚሆን መጠን ተቃውሞውን ይፈልገው ነበር
                
                   መግቢያ
ምናልባት ታስታውሱ ይሆናል፡፡ በወዲያኛው ሣምንት የአዲስ አድማስ እትም፤ ‹‹ፖለቲካዊ ትራጀዲ›› በሚል ርዕስ ባቀረብኩት አንድ ጽሑፍ ‹‹ኢህአዴግ ከዚህ ሁከት ምን ተማረ?›› የሚል ጥያቄ እንደ ዘበት አንስቼ ነበር፡፡ ጥያቄውን አነሳሁት እንጂ መልስ የሚሆን ነገር አልነበረኝም፡፡ አሁንም ኢህአዴግ ምን እንደ ተማረ አላውቅም፡፡ ሆኖም ታሪክ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡
ከታሪክ ለሚቀርብልን ጥያቄ መልስ ቢኖረንም ባይኖረንም ታሪክ ሂደቱን ይቀጥላል፡፡ አያቆምም። ታሪክ ለእኛ መልስ ደንታ የለውም፡፡ ንቁ የታሪክ ጉዳይ አስፈጻሚ (Conscious agent of history) ብንሆንም - ባንሆንም፤ እርሱ በግራ መጋባታችን ላይ እየተረማመደ ጉዞውን ይቀጥላል እንጂ፤ ‹‹ግራ የተጋባ ተሳፋሪ አለ›› ብሎ ለአፍታ እንኳን ከጉዞው አይቆምም፡፡ ታዲያ እኛ ሰዎች እንዲህ ያለውን የታሪክ ደንታቢስነት ለማሸነፍ የምንችለው ወይም ‹‹ንቁ የታሪክ ጉዳይ አስፈጻሚ›› ለመሆን የምንበቃው ወይም ‹‹ተደራጊ›› ብቻ ሳይሆን ‹‹አድራጊ›› የታሪክ ሂደት ተሳፋሪዎች የመሆን ማዕረግ ማግኘት የምንችለው፤ በመጠየቅ እና በመመርመር ነው፡፡ በመወያየት ነው፡፡
ስለዚህ አሁንም እጠይቃለሁ፡፡ ነገር ግን ዛሬ ‹‹ኢህአዴግ ከዚህ ሁከት ምን ተማረ?›› አልልም፡፡ ይልቅስ ጥያቄውን ወደ ራሴ እመልሳለሁ፡፡ መልሼም ‹‹እኔ ሆይ ምን ተማርክ?›› ብዬ ራሴን አስደነገጥኩት። ‹‹ኃላፊነት እንደሚሰማው አንድ ዜጋ አንተ ምን ተማርክ?›› ብዬ ራሴን ጠየቅኩት፡፡
አዎ፤ አንድ የተማርኩት ነገር መኖሩ ይሰማኛል። ግን ሐሳቤን የተደራጀ ስላልመሰለኝ ጽሑፉን ልተወው ሳስብ፤ ፍላጻ ከደጋን ሆነው የተቀባበሉት ሐሳቤ (ስሜቴ) እና ብዕሬ ከእኔ ፈቃድ ውጪ በሆነ ግፊት ተተኮሱ፡፡ ፍላጻው ደጋኑን ለቅቆ ሄደ፡፡ ተከተልኩት፡፡ የተደራጀ ሐሳብ የያዝኩ ሳይመሰለኝ መጻፌን ቀጠልኩ፡፡ ስለዚህ ‹‹በምዕራፍ ሁለት›› የምታነቡት ጽሑፍ ‹‹በቃ አለቀ›› ተብሎ የተጠናቀቀ ሐሳብ ሳይሆን፤ ሐሳቤን ለማደራጀት ባደረግኩት ጥረት የተፈጠረውን ጽሑፍ ነው፡፡ በአደባባይ እያሰብኩ ስጽፍ ታዩኛላችሁ ማለት ነው፡፡ ‹‹እኔ ሆይ ምን ተማርክ?›› ለሚለው ጥያቄ መልስ ስፈልግ ትመለከታላችሁ፡፡ ሐሳቤ በመደራጀት ሂደት ሲያልፍ ታዛቢ ትሆናላችሁ፡፡ ነገሩ፤ ገና ያልተወለደ ህጻንን በቴክኖሎጂ ዕርዳታ በማህፀን ሆኖ እንደማየት ሊታሰብ ይችላል፡፡
በምዕራፍ አንድ
እኔ ራሴን ለሐገሩ ቀና እንደሚያስብ ዜጋ እቆጥራለሁ፡፡ አሁን አሳሳቢ ሆኖ የሚታየንን ወቅታዊ የሐገራችንን ሁኔታ በኃላፊነት ስሜት ለመረዳት ብዙ ጥረት አድርጊያለሁ፡፡ በየአካባቢው የተካሄዱት ሰልፎች በጣም ግራ አጋብተውኛል፡፡ ሰልፎቹ፣ የተቃውሞ እና የአመጽ መልክ ነበራቸው። ሰዎችን የማጥቃትና ንብረት የማውደም ተግባር የታየባቸው አንዳንድ ሰልፎችም ነበሩ፡፡ በእነዚህ ሰልፎች የተመለከትናቸው አንዳንድ መልዕክቶች፤ የቁጣ እንጂ የማስተዋል ባህርይ የሚንጸባረቅባቸው አልነበሩም፡፡ ይልቅስ ድንጋጤ የሚፈጥሩ እና የስጋት ድባብ የሚጥሉ ነበሩ፡፡ እንዲያውም አንደኛው ሰልፍ፤ ጠብመንጃ ያነገቱ ሰዎች የተሳተፉበት ሆኖ ሲያበቃ፤ ሰላማዊና የረጋ ባህርይ ይዞ የተጠናቀቀ ነበር። በጥቅሉ፤ ያየናቸው አንዳንድ ሰልፎች ‹‹ህገ ወጥ -ሰላማዊ›› ሰልፎች ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡
በርግጥ ከሰላማዊ ሰልፍ አካሄድ ጋር የተያያዘና ብዙ ጊዜ የሚሰማ አንድ አወዛጋቢ ጭብጥ መኖሩን አውቃለሁ፡፡ በዚህ ረገድ ሰፊ ውይይት ሊደረግ እና የጋራ ግንዛቤ ሊፈጠር ይገባል፡፡ ታዲያ የዚህ ውይይት ደመራ ወደ ግራም ወደቀ ወደ ቀኝ በደምደሚያችን ድምዳሜአችን፤ ‹‹ጠብመንጃ ይዞ ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ትዕይንተ ህዝብ ማካሄድ ተገቢ አይደለም›› እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ ምናልባት፤ ‹‹ማህበራዊ ዓውዱን በደንብ ለምናውቅ ሰዎች፤ በሰላማዊ ሰልፍ ጠብመንጃ ይዞ መታየት የሚያስተላልፈው መልዕክትና ድንጋጤ ለዓውዱ ባዕድ ለሆኑ ተመልካቾች ከሚሰጠው ትርጉም እና ከሚፈጥረው ድንጋጤ ይላያል›› የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል። እኔም እንዲህ ያለ ልዩነት መኖሩን እረዳለሁ፡፡ ሆኖም እንኳን ተራ ዜጎች፤ ፖሊሶችም መሣሪያ ይዘው በጎዳና  መታየታቸው ችግር ለሚፈጥርባቸው የውጭ ሐገር ሰዎች፤ ጠብመንጃ ይዞ ‹‹ሰላማዊ ሰልፍ›› ከእኛ በበለጠ ግራ እንደሚያጋባቸው አልጠራጠርም፡፡
ሐገር አቀፍ ምርጫ በሚካሄድበት ጊዜ ወደ ክልል ወጣ ያሉ የውጭ ሐገር ሰዎች፤ በምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ ጠብመንጃ የያዙ ሰዎች በተመለከቱ ጊዜ፤ ‹‹ምርጫው ነጻ እና ፍትሐዊ አልነበረም›› ከሚል ድምዳሜ ያደርሳቸው ይሆናል፡፡ በአዲስ አበባም ተመሳሳይ ስሜት ሊፈጥር ይችላል፡፡ ሆኖም በአንዳንድ ክልሎች ያለውን ማህበራዊ አውድ በደንብ የሚያውቅ ሰው እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊኖረው አይችልም፡፡ መሣሪያ ይዞ መታየት፤ መፋቂያ ይዞ ከመታየት የተለየ ስሜት የማይታይባቸው የሐገራችንን አካባቢዎች ብዙ ናቸው፡፡ ይሁንና ህግ የሚከለክለው ድርጊት ከሆነ፤ በባህልም ሆነ በሌላ የተለየ ምክንያት ጠብመንጃ ይዞ በሰላማዊ ሰልፎች መሳተፍ ተገቢ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡ ከመንግስት አካል ፈቃድ ሳያገኙ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድ በህግ የተከለከለ ከሆነ ህጉን ማክበር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በቅርቡ በተለያዩ ከተሞች የታዩት ሰልፎች፤ ሰላማዊ ሆነው ቢጠናቀቁ እንኳን፤ ‹‹ህገ-ወጥ ሰልፎች›› ከመባል ሊድኑ አይችሉም፡፡
ህጎች የብዙሃኑ ህዝብ ፍላጎት መገለጫ ሰነዶች ናቸው፡፡ በህግ ሰነድ የሰፈሩ ድንጋጌዎች በተለየ ፍላጎት ወይም ባህል መነሻ ከሚፈጸም ማናቸውም ዓይነት ድርጊት የላቀ የገዢነትና የአስገዳጅነት ኃይል ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ፈረንሳዊው ፈላስፋ ሩሶ፤ አንድ ሰው የአስገዳጅነት ባህርይ ላለው አንድ ህግ ተገዢ እንዲሆን ሲገደድ፤ ያ ዜጋ ‹‹ነጻነት እንዲያገኝ እየተገደደ ነው›› የሚል ክርክር ነበረው፡፡ ይህ የሩሶ ሐሳብ ዘመናዊውን የፖለቲካ አስተሳሰብ በመቅረጽ ረገድ ወሳኝ ሚና የተጫወተ ሐሳብ መሆኑም ይነገራል፡፡ ይህ ነገር ‹‹የዴሞክራሲ አያዎ›› (paradox of democracy) የሚሉትን ጉዳይ በደንብ የሚያሳይ ነው፡፡ ዜጎች ወደው ፈቅደው አንድን ስርዓት መርጠው ካጸኑ በኋላ፤ በፈቃዳቸው ያጸኑት ያው ስርዓት ምርጫቸውን የሚገራ ልጓም ወይም ቅይድ ይሆንባቸዋል፡፡ በሌላ አገላለጽ፤ ሰዎች ነጻ ለመሆን ሲሉ በፈቃዳቸው የፈጠሩት አንድ ስርዓት ‹‹ባርያ›› ይሆናሉ፡፡ ‹‹ባርያ›› ሳይሆኑ ነጸነት የለም ማለት ነው። ነጻነት ለህግ ስርዓት ባርያ በመሆን የሚገኝ ፀጋ ነው። አንዳንዶች፤ ‹‹የዴሞክራሲ አያዎ›› ሲሉ የሚገልፁት ይህንኑ ነገር ነው፡፡
ታዲያ እነዚህ ሰልፎች ህገ-ወጥ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በጎ ገጽታም ነበራቸው ለማለት ይቻላል፡፡ እነዚህ ህገ ወጥ ሰልፎች፤ ዘረኝነትን የታከከ አቋምና አንዳንድ ዜጎችን ለጥቃት የዳረገ ችግር ባይታይባቸው ኖሮ፤ በበኩሌ ያን ያህል አሳሳቢ ነገር አድርጌ አልወስዳቸውም ነበር፡፡ ራሱ ኢህአዴግ ተቃውሞው በአሁን በታየው ደረጃ ከረር ያለ ባህርይ ይይዛል የሚል ግምት ባይኖረው እንኳን፤ ‹‹እንዲህ ያለ የህዝብ ተቃውሞ ሊፈጠር አይችልም›› የሚል ግምት እንዳልነበረው፤ ሰልፎቹ ከመካሄዳቸው በፊት አንዳንድ ነባርና ከፍተኛ የድርጅቱ አመራሮች ይናገሩት ከነበረው ነገር ለመገመት ይቻላል፡፡
ከወራት በፊት በመገናኛ ብዙሃን ቀርበው በመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ ከጋዜጠኛ ጋር ሲወያዩ የነበሩ አንድ የድርጅቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን፤ ‹‹ይህ ህዝብ ለአመጽ አለመነሳቱ የሚገርም ነው›› ሲሉ መናገራቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ከፍተኛ የመንግስትና የፓርቲ ባለስልጣናት በተሰባሰቡበት አንድ መድረክ ደግሞ፤ ‹‹ህዝቡ ሰላማዊ እና ህጋዊ በሆነ መንገድ በመንግስት ላይ ጫና በማድረግ የሚታዩት ችግሮች እንዲስተካከሉ ጥረት ሊያደርግ ይገባል›› እያሉ ይናገሩ ነበር፡፡ እንዲሁ በአስረኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ማጠቃለያ፤ አንድ የመንግስት ባለስልጣን፤ ‹‹ከድርጅታችን ውጭ ያሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በድርጅቱ ውስጥ ትግል በመለኮስ እገዛ እንዲያደርጉልን እንፈልጋለን›› ሲሉ መናገራቸውንም አስታውሳለሁ፡፡
እነዚህን አስተያየቶች መነሻ በማድረግ፤ መሠረታዊ ለውጥ ፈላጊ ለሆኑ የድርጅቱ አመራሮች፤ ሰልፎቹ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሄዱ ከመስጋት በቀር፤ መካሄዳቸው ያን ያህል የሚያስደነግጣቸው አይመስለኝም፡፡ ‹‹ህገ ወጥ›› ሊባሉ በሚችሉት ሰልፎች የተገለጸው ተቃውሞም የብራ መብራቅ አይሆንባቸውም ብዬ አስባለሁ፡፡ ያልገመቱትና ያልፈለጉት ነገር ገጠማቸው ለማለትም አቅማማለሁ። በሌላ አነጋገር፤ መድኃኒት በሚሆን መጠን የህዝቡን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ይፈልጉት ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ስለዚህ ሰልፎቹ ህጋ  ሰላማዊ በመሆን ሚዛን ጉድለት ቢኖራቸውም፤ ህዝቡ ቸል ሊባል የማይችል ግልጽ መልዕክት ለመንግስት ማስተላለፍ የመቻላቸው ነገር እንደ ትልቅ ፋይዳ ሊታይ ይገባዋል፡፡ ወደፊትም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይፈጠር በቁርጠኝነት ለመስራት የሚያነሳሳ አንቂ ደወል አድርጎ በመውሰድ መስራት ይገባል፡፡ በዚሁ ስሌትና ልክ ሰልፎቹን ጠቃሚ አድርገን መመልከት እንችላለን፡፡  
በበኩሌ፤ የተቃውሞ እንቅስቃሴው ጠቅላላ ስርዓቱን እንደ ጎርፍ ጠራርጎ በሚወስድ አኳኋን መገንፈሉ ወይም በህዝቦች መካከል መቃቃርና ግጭት ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮች በመታየታቸው ከመስጋት በቀር፤ ሌላው ነገር ያን ያህል አሳሳቢ ሆኖ አይታየኝም፡፡ የህግ የበላይነትን በማይጻረርና ከኃይል አማራጭ ውጪ በሆነ መንገድ የሚደረግን የህብረተሰብ የመብት ማስከበር ጥረት እደግፋለሁ። ሆኖም የሐገራችን ዴሞክራሲ ካለው መዋቅራዊ ችግሮች የተነሳ፤ የተለያዩ ቡድኖች የሚያደርጉት ፖለቲካዊ መሳሳብ፣ ከሰላማዊና ህጋዊ ማዕቀፍ የመውጣት ዕድል ያለው መሆኑን በማሰብ ከመጨነቅ በቀር፤ ህዝቡ ያሰማውን የተቃውሞ ድምጽ፤ ስርዓቱ ራሱን በራሱ ለማጽዳት ሲንቀሳቀስ የተፈጠረ ድምጽ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡
ውሻ በቀደደው ጅብ ገብቶ፤ የሐገራች መሻሻል የሚጎዳቸው የሚመስላቸው የውጭ ኃይሎች ጣልቃ በመግባት፤ ከመንገድ እንዳያስወጡን ከመጨነቅ በቀር፤ የተረፈውን ነገር ሁሉ ‹‹ዕዳው ገብስ ነው›› በሚል ስሜት ለማስተናገድም ዝግጁ ነኝ፡፡
በበኩሌ የተማርኩት አንዱ ነገር ከፍ ብሎ የገለጽኩት ነው፡፡ ለጋዜጣ ገጽ፤ ከመነሻ ብዙ ያወራሁለትን የጽሑፌን ሁለተኛ ምዕራፍ አሳደርኩት።

Read 2510 times