Monday, 29 August 2016 10:25

“መንግስት የሚቀርብለትን ሃሳቦች ማዳመጥ አለበት” አቶ ግርማ ሠይፉ (የቀድሞ የፓርላማ አባል)

Written by 
Rate this item
(2 votes)

    በ97 ምርጫ ማግስት መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ ከመጠን በላይ ኃይል መጠቀሙን በተመለከተ ያቀረበው ምክንያት ዘመናዊ የአድማ መበተኛ መሳሪያዎች የሉኝም የሚል ነበር፡፡ ዛሬም በዘመናዊ መንገድ አድማ መበተን አልቻለም። ለነገሩ በመጀመሪያ ደረጃ መበተንስ ያስፈልጋል ወይ? የሚለው መታየት አለበት፡፡ በእኔ እምነት ተቃውሞዎቹን እየበተነ ያለው የፖሊስ ሰራዊት አይመስለኝም፡፡ ወታደር ሲሰለጥን ግደል ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ ፖሊስ ግን ሲሰለጥን ወንጀለኛን መግደል የወንጀሉን ምንጭ ለማጣራት ስለማይጠቅም ግደል አይባልም፡፡ ወንጀለኛ ከተገደለ ወንጀሉ አይታወቅም፡፡ ረበሹ የተባሉ ሰዎችን ከነሙሉ አካላቸው ይዞ ነው፣ ለምን ይህን አደረጋችሁ? በሚል የሚያጣራው፡፡ አሁን ግን ግንባርና ደረት እየመቱ ነው የሚገድሉት፡፡ ይሄ በምንም አይነት ሁኔታ ተቀባይነት የለውም፡፡
ሰዎች ረብሸው ጎማ አቃጥለው፣ ቤት ሰብረው ቢሄዱ በካሜራ አጣርቶ፣ እንደዚህ ሲያደርጉ ተይዘዋል ተብሎ ፍ/ቤት አቅርቦ ማስወሰን የሚቻል ነው፡፡ አሁን ግን ሽብር በመንዛትና በማስፈራራት አፈና እየተካሄደ ነው ያለው፡፡ ወላጆች፤ ልጆቻቸው መብታቸውን እንዳይጠይቁ፣ ቤታችሁ እሰሯቸውና ቀልቧቸው ነው እየተባለ ያለው፡፡ በአጠቃላይ እየተደረገ ያለውን ተቃውሞ መንግስት የሚያስተናግድበት መንገድ የመንግስት አይመስልም፡፡ ልጅ ቢያጠፋ ዝም ብሎ አይደበደብም፤ምንድን ነው ተብሎ ተጠይቆ ይመከራል፡፡ መንግስት ግን በዚህ መንገድ አይደለም ህዝብን እየያዘ ያለው፡፡
እንደኔ ሰላማዊ ተቃውሞዎቹ በኦሮሚያና በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በብዙ የሀገሪቱ ክልሎች አሉ፡፡ ትግራይ ውስጥ ከምንግዜውም በላይ ሰው ተረብሾ ያለበትና በትክክለኛ መንገድ መተዳደር ያልቻሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በደቡብም ተመሳሳይ ነው። ግን ጎልተው እየወጡ ያሉት የኦሮሚያና የአማራ ክልል ናቸው፡፡ ከምንም በላይ የአማራ ብሄርተኝነት የሚባለው ነገር ነፍስ ዘርቶ፣ እግርና እጅ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው ያለው። ይሄን እንግዲህ ኢህአዴግ የኔ ፍሬ ነው ሊል ይችል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የአማራ ብሄርተኝነት እፈልጋለሁ ሲል ነበር ተፈጠረለት። የአማራ ብሄርተኝነት ሲፈጠር ደግሞ የአማራ የሚባሉ ጥያቄዎችን ያመጣል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ አለበት ማለት ነው። የፈጠረው የአማራ ብሄርተኝነት የሚያመጣውን ጥያቄ መመለስ አለበት። እነዚህ ጥያቄዎች ደግሞ ዝም ብሎ ከዚህም ከዚያም የሚነሱ አይደሉም፡፡ እነሱ እንደሚሉት፤ ሰው መሬት አስተዳደር ሄዶ ካርታ ስለተከለከለ፣ የኑሮ ውድነት ስላሰቃየው ወዘተ----የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ብቻ አይደለም፡፡ የነፃነት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ዙሪያ ማስተር ፕላን፣ ወለጋ ላለ ወጣት ይሄን ያህል ስሜት የሚሰጠው አይሆንም፡፡ አባይ አጠገብ ላለ የጎጃም ሰውም ጠረፍ ላይ ያለ መሬት ብዙም ሊያሳስበው አይችልም ነበር፤ ግን እነዚህ መነሻ ሰበቦች ናቸው፡፡
አፄ ኃይለሥላሴ በመጨረሻው ሰዓታቸው ላይ ጥያቄው የደሞዝ ይመስላቸውና ለወታደሩ ደሞዝ ይጨምራሉ፤እንደገና የነዳጅ ዋጋ ጥያቄ ይመስላቸውና የነዳጅ ዋጋ ያስተካክላሉ ግን በወቅቱ የነበሩት ጥያቄዎች እሳቸው ያሰቧቸው አልነበሩም፡፡ የነፃነትና መሰረታዊ የሆኑ የስርአት ለውጥ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ አሁንም ዋና ዋና የሚባሉትን ጥያቄዎች ከዚህ አንፃር መመልከት ያስፈልጋል እንጂ ዝም ብሎ በግምት መልስ በመስጠት ብቻ የሚገላገሉት አይደለም፡፡
ስልጣኑን የያዙት ሰዎች በባህሪያቸው የሚሰጣቸውን ምክረ ሀሳብ የሚቀበሉ አይደሉም፡፡ አይሰሙም አያነቡም፤ ቢሰሙም ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ነው። እሱንም የሚሰሙት ያስተላለፉት መልዕክት በትክክል መነገሩን ለማጣራት ነው እንጂ ለማወቅ አይደለም፤ስለዚህ የመማር እድላቸው ሰፊ አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች እነሱ መስማት የሚፈልጉትን ብቻ ሳይሆን መስማት የማይፈልጉትንም ማድመጥ ይኖርባቸዋል፡፡ መፍትሄውን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ እየተናገርን ነው፡፡ አዳምጠው ራሳቸውን ለለውጥ ዝግጁ የማያደርጉ ከሆነ፣ ሁኔታው ወደ አልሆነ አቅጣጫ ሊጓዝ ይችላል፡፡  እነሱም ክብር በሌለው ሁኔታ የሰሩት አንድም ሁለትም የሆነ ጥሩ ነገር ካለ ጠፍቶ ለውጥ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ሁኔታው ወደዚያ እንዳያመራ ስርአት ያለው ሽግግር የሚፈጠርበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለባቸው፡፡
በእጅጉ መማር ያለባቸው እነሱ ያላቸውን እውቀትና ኃይል ተጠቅመው፣ ጥሩ ነገር እንሰራለን ብለው የፈጠሩትን ስህተት፣ አሁን እነሱ ባላቸው የእውቀት ደረጃ ሊፈቱት አይችሉም፡፡ ስለዚህ ተጨማሪ እውቀትና አስተሳሰብ ማዳበር አለባቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች አዲስ አስተሳሰብና እውቀት ለመያዝ ዝግጁ እንዳልሆኑ የሰሞኑ መግለጫቸው ያመላክታል፡፡ መግለጫቸውን የሰማ ሰው፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መሞታቸውን እርግጠኛ ይሆናል፡፡ አንድም እንኳ አዲስ መልዕክት የለውም፡፡ ከዚያ ሁሉ ገፅ መግለጫ አንድም የተጨበጠ መልዕክት አላገኘሁበትም፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው፣ ይህን አይነቱን ውስብስብ ችግር ሊፈቱ አይችሉም። ስለዚህ ህዝቡ አመኔታ ሊጥልበት የሚችልበትን የመፍትሄ አቅጣጫ መከተል አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምሁራን የሚሰነዝሩትን የመፍትሄ ሃሳቦች በሚገባ ማዳመጥ አለባቸው፡፡  

Read 4631 times