Monday, 29 August 2016 10:30

‹‹አመጹ መሪ ካላገኘ ወደ ከፋ ግጭት ሊያመራ ይችላል›› አብርሃ ደስታ (የአረና አመራር)

Written by 
Rate this item
(4 votes)

   በኦሮሚያና በአማራ ክልል እየተካሄዱ ያሉ ተቃውሞዎች፣የተጠራቀመ የህዝብ ብሶት ፈንድቶ የታየባቸው ናቸው፡፡ አመፁ የህዝብ ብሶት የወለደው ምሬት ነው፡፡ የኢህአዴግ ሰርአት አንገሽግሾት የወጣ ነው፡፡ ለብዙ ጊዜ የነበረ በደልና ጭቆና፣ ትንሽ ወቅታዊ ምክንያት በመፈለግ ሲፈነዳ የታየበት ነው። ለምሳሌ በኦሮሚያ ማስተር ፕላኑ መነሻ ምክንያት ነው፡፡ መሠረታዊ መነሻ አይደለም፡፡ በአማራ ክልልም መሠረታዊ መነሻው የወልቃይት ጉዳይ አይደለም፡፡ እሱ መነሻ ምክንያት ነው እንጂ ዋና ምክንያቱ ጭቆና ነው፡፡ የተደራጀ አመራር ወይም ሃይል የሌለውም በዚህ የተነሣ ነው፡፡ ህዝብ ያለ መሪ ስሜቱን የገለፀበት አመፅ ነው፡፡
 ይሄን አመፅ የሚመራው ድርጅት ከሌለና ካልተደራጀ ዝም ብሎ ንብረት መውደምና የሠው ህይወት መጥፋት ብቻ ነው የሚያስከትለው፡፡ ምክንያቱም ከኢህአዴግ ተፈጥሮ አንፃር ስናየው፤ ለህዝብ ጥያቄ መልስ ከመስጠት ይልቅ የሃይል እርምጃ መውሰድ ነው የሚቀናው፡፡ ህዝቡ ደግሞ እየተነቃቃ ለውጥ እየፈለገ ሲሄድ፣ ዝም ብሎ ንብረት መውደምና ህይወት መጥፋት ይሆናል። መጨረሻም ለውጥ ላይኖረው ይችላል፡፡ ለውጥ የሚኖረው የተደራጀና መሪ ሲኖረው ብቻ ነው፡፡ ህዝብ የሚተማመንበት ሃገራዊ የፖለቲካ ድርጅት ሲኖር ነው መነሳሳቱ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ፓርቲዎች በተለያየ አቅጣጫ ተደራጅተው፣ እርስ በእርስ ከመናቆር በመላቀቅ፣ ለሃገሪቱ መድህን መሆን አለባቸው። የህዝብ ችግር የኛ ችግር ነው ብለው ህዝቡን ለመምራት አንድነት ፈጥረው፣ሃገሪቷን ከአደጋ ለመጠበቅ መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ ይህን ካደረጉ ህዝቡን ይዘው ከኢሕአዴግ ጋር የመደራደር አቅም ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ ኢህአዴግ ወደ ድርድርና የፖለቲካ ውይይት እንዲገባ የማስገደድ ዕድል ያገኛሉ፡፡ ኢህአዴግም ከህዝቡ የተነሳው ተቃውሞ ሰፊ መሠረት ያለው መሆኑን አውቆ፣ ለድርድር ራሱን ሊያዘጋጅ ይችላል፡፡
ያለበለዚያ ኢህአዴግም እርምጃ እየወሰደ መቀጠሉ ስለማይቀር፣ዝም ብሎ መጠፋፋት ነው የሚሆነወ፡፡ ወደ እርስ በእርስ ግጭት ነው ሊያመራ የሚችለው፡፡፡ የህዝቡ የለውጥ ፍላጎት በሚገባ ካልተደራጀ፣ መጨረሻ ላይ ደግሞ እየተዳከመ ይሄዳል፡፡ ኢህአዴግ የህዝብን ሃሳብና ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ በህዝብ ላይ የሃይል እርምጃ መውሰድ መፍትሄ መሆን እንደማይችል መገንዘብ ይኖርበታል። ሃገሪቷንና ህዝቡን ከአደጋ የማዳን ሁኔታ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስራ ነው የሚሆነው። አሁን ህዝቡን መምራት መቻል አለባቸው። የመደራደር አቅማቸውን ማሳደግ ይገባቸዋል፡፡ እነሱም አንድ ሆነው፣ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት እንዲቆም ማድረግ አለባቸው፡፡

Read 8061 times