Monday, 29 August 2016 10:33

‘ወንበር’ እና ሰው…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ይህ የሆነ ‘የዘመኑ ሰው ምኞት’ በራሱ አንደበት ሲነገር ነው፡፡
‘ወንበር’ አማረኝ… ወንበር አግኝቼ ማስተካከል ያሉብኝ ነገሮች አሉ፡፡ የባንክ ደብተሬ መወፈር አለበት፡፡ የጀመርኩት ቪላ ቤት ወደ ‘ጂ ፕላስ ስሪ’ ማደግ አለበት፡፡ የሚስቴ መሰንበት ጉዳይም ቢሆን አያሳስብም አይባልም፡፡ በቃ ሚስቴ ሳይሆን ትልቋ አክስቴ እየመሰለችኝ ነዋ!  ቂ…ቂ..ቂ… የሳቅሁት እሷ እንደማታየኝ እርግጠኛ ሆኜ ነው፡፡ ሰሞኑን ትንሽ መቀማማስ ሳይሆን በደንብ ጨልጬ ሳልነግራት የማልቀረው ታሪክ አለ…
ባልና ሚስት ወደ መኝታ ለመሄድ እየተዘጋጁ ነበር፡፡ ራሷን እንደ ቆንጆ የምትቆጥር ሚስት መስታወት ፊት ቆማ ራሷን ለረጅም ደቂቃዎች ስታይ ቆየችና ወደ ባሏ ዘወር አለች፡- “ታውቃለህ ውዴ፣ መስታወት ውስጥ ራሴን ሳይ የምትታየኝ ፊቷ የተጨማደደ፣ ሆዷ የተንጠለጠለ፣ ጭኖቿ የወፈሩና ክንዶቿ የተልፈሰፈሱ አሮጊት ሴትዮ ነች፡፡ እባክህ ስለ ራሴ መልካም እንዲሰማኝ አንድ ጥሩ ነገር ንገረኝ…” አለችው፡፡ ባሏም ምን አላት አሉ…
“የማረጋግጥልሽ ቢኖር የማየት ችሎታሽ አስደናቂ መሆኑን ነው፣” ብሏት አረፈ፡፡
እኔም ሚስቴን እንደዛ ለማለት እንዲያስችለኝ ወንበር ያስፈልገኛል፡ ዘንድሮ ከወንበር ጋር አብሮ የሚለወጠው የባንክ ደብተር ብቻ ሳይሆን ሚስትም ነዋ!  
እናማ… የዕቁብም ጸሀፊነትም ይሁን… የአብሮ አደግ ሰብሳቢነትም ይሁን…የቤተሰብ ጉባኤ አደራጅነት ይሁን ወንበር ያስፈልገኛል፡ ልክ ነዋ…ወንበር ላይ ፈልሰስ ብሎ የተቀመጠው ሁሉ እንዲህ ‘እንደ ልቡ’ ሲያደርገው የፈለገው ቢጠፋ ‘የኬኩን ሸራፊ’ የማልቀምስሳ!
እናማ ወንበሩ ላይ ከተቀመጥኩ በኋላ የማደርገውን አውቃለሁ፡፡ ማለት…ሌሎቹ እንደሚያደርጉት አደርጋለኋ! እናላችሁ ወንበሩ ላይ ያስቀመጡኝ ወይም አስቀመጡኝ ያልኳቸውን ሰዎች ብሶት ለመስማት ስባ እጠራለሁ፡፡
ታዲያላችሁ… በጭብጨባ ታጅቤ መድረክ ላይ እወጣለሁ፡፡ ለነገሩ…ጭብጨባው እኮ በአብዛኛው “ካሜራ ስላለ እንዳትበላ አጨብጭብ…” እየተባለ የተደረገ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ለማጨብጨብ ‘የአእምሮ ብቃት’ ምናምን አያስፈልገው! እኔ የምፈልገው እጃቸውን እንጂ አእምሯቸውን አይደል! አንድ ታሪክ አለ…የአሜሪካኖቹ ታሪክ ነው፡፡ ሰውየው የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊ ነው፡፡ አያቱ ይታመሙና ወደ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ይወሰዳሉ፡፡ ከአንድ ሰዓት በኋላ ዶክተሩ ከድንገተኛው ክፍል ይወጣል። ሰውየውም፣
“ዶክተር አያቴ እንዴት ነው?”
“አዝናለሁ፣ መልካም ዜና የለኝም፡፡ አያትህ የህይወት ማቆያ መሳሪያ ተገጥሞላቸዋል፡፡ ልባቸው አሁንም ይመታል፡፡ ሆኖም አእምሯቸው በድን ሆኗል…” ይለዋል፡፡ ሰውየው ምን ይላል አሉ…
“በዘራችን ውስጥ የዴሞክራት ፓርቲ ደጋፊ ያለ አይመስለኝም ነበር፡፡”   
እነሂላሪ አእምሯቸው በድን ነው ማለቱ ነው እንዴ!
ስለ እነ ሂላሪ እንኳን እኔ ልነገራችሁ አልችልም። “ምንስ አግብቶኝ በሰዎች ነገር፣ በሰዎች ሥራ…” ተብሎ የለ! ሆኖም ከደጋፊዎቼ ጥቂት የማይባሉት አእምሯቸው ‘ማልኖሪሽድ’ መሆኑን እንደማውቅ ግን ልክዳችሁ አልፈልግም፡፡
እናም ንግግሬን እጀምራለሁ፡፡ “የተከበራችሁ የስብሰባው ተካፋዮች አገራችን በልማት…“ ምናምን እያልኩ አንድ ሠላሳ ደቂቃ ‘እደሰኩራለሁ፡፡’ እናማ…‘አዳሜ’ ጸጥ ብሎ ሲያዳምጥ ሳይ ትከሻዬ ሰፍቶ ግድግዳውን የሚነካ ይመስለኛል፡፡ “አገርን ለማሳደግ ቀበቶአችንን አጥብቀን…” ምናምን እያልኩ ቀበቶ መግዛት አቅቶት ሱሪውን ሠላሳ ጊዜ ወደ ላይ ለሚጎተተው ተሰብሳቢ ‘የዜግነት ኃላፊነቱን’ እነግረዋለሁ፡፡ ከዚያም… “ውዳሴው ቢያልቅበት ቀረርቶ ጨመረበት…” ምናምን በሚለው መርህ መሰረት የፈረደባቸውን ያለፉትን ስርአቶች እቀጠቅጣቸዋለሁ፡፡
“ያለፉት ስርአቶች የህዝቡን ተጠቃሚነት በመርገጥ ራሳቸውን ሲያደልቡ…” ምናምን እያልኩ ታሪክ የሆኑት ስርአቶችን ልክ ልካቸውን አጠጣቸዋለሁ፡፡ ልክ ነዋ… ራሳቸውን ‘ሲያደልቡ’ ኖረው ዝም ልላቸው ነው!  ቂ…ቂ…ቂ… (ለአዲሱ ቤቴ ሳሎን ዕብነ በረድ ከማሌዥያ ለማምጣት የተስማማው ሰውዬ መርከብ ላይ ጭኖልኝ ይሆን እንዴ!)
ልክ ነዋ…መጀመሪያ የመቀመጫዬን ነዋ! በስንቱ ቀዳዳ ተሟሙቼ ያሠራሁትና ሲያልቅ ሰባና ሰማንያ ሺህ ብር አከራየዋለሁ ያልኩት ቤቴ ያሳስበኛላ! አንድ ታሪክ ቢጤ አለች…
ሰውየው አሮጌ ጎማውን ሊሸጥ ወደ ጓደኛው ጋራዥ ይሄዳል፡፡ ሊሸጥ ያሰበውም በሠላሳ ዶላር ነበር፡፡ በኋላ የስልክ ጥሪ ይደርሰውና ለጥቂት ጊዜ ሄድ ብሎ መመለስ ነበረበት፡፡ ባለጋራዡንም ጎማውን እንዲጠብቅለት ሲጠይቀው ሰውየው ይስማማል፡፡
“ግን የሆነ ሰው ከሠላሳ ዶላር በታች ልግዛው ካለ ምን ያህል ትወርዳለህ…” ሲል ባለ ጋራዡ ይጠይቃል፡፡
በተቻለ መጠን ከሠላሳ ዶላር በላይ ለመሸጥ ሞክር፡፡ ግን ካልሆነ አሥራ አምስት ዶላር ልትሸጠው ትችላለህ፣” ይለዋል፡፡ ሰውየው ጉዳዩን ጨርሶ ሲመለስ ጎማው ተሽጧል፡፡
“ስንት ሸጥከው?” አለው፡፡
“አሥራ አምስት ዶላር…”
“ማነው የገዛው?” ሲለው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“እኔ ራሴ…”
እኔም እንኳን ወንበር አግኝቼ ባላገኝም ኖሮ “እኔ ራሴ…” የሚለው መመሪያዬ መሆኑ ይታወቅማ! በጠንካራ ሰብእና የሚገኝ ቡራኬ እንጂ ፈራንካ አይደለማ!
እናላችሁ…ቀጥዬ ደግሞ…የመሥሪያ ቤት ሥራ አስኪያጅ አይደለሁ… (ለነገሩ ምንም ደረጃዬ ያን ያህል ባይወጣም ሲ.ኢ.ኦ. መባል ነው የምፈልገው። በእንግሊዝኛ ሲሆን ያምራላ! ቂ…ቂ…ቂ…) የመሥሪያ ቤቱን ዓመታዊ ‘ሪፖርት’ አቀርባለሁ…
ገለጻዬንም… “ድርጅታችን የምናምነኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን…” ምናምን እያልኩ ለመድረክ ንግግሮች ‘ኮምፐልሰሪ’ የሆኑ ቃላትን  በማዝነብ እጀምራለሁ፡፡ “ድርጅታችን በዘንድሮው የበጀት ዓመት….ያህል ምርት ለማምረት እቅድ ይዞ…አምርቷል፡፡ ይህም የእቅዱን 48% ማለት ነው፡፡ ይህ ስኬት የተገኘው…”  (አሀ…‘አፍህን ያዝ አያደርግህም ወይ…’ ብሎ ጥያቄ ምንድነው! ማን አፉን ያዝ እንዳደረገው እኔን ያደርገኛል! ለምን ብሎ፣ ምን ቆርጦት ነው አፌን ያዝ የሚያደርገኝ! የእኔ ዋናው ተግባር አፍ ማስያዝ እንጂ አፍ መያዝ አይደለማ!) ‘ስኬቱ’ የተገኘው ማኔጅመንቱና ሠራተኛው እጅና ጓንት ሆኖ በመሥራቱ መሆኑን አስረዳና… ይህም ‘ጠንካራ የሥራ መንፈስ ወደፊትም እንዲቀጥል አሳስቤ ታሪካዊው ንግግሬን አበቃለሁ፡፡ እስከ ጥግ ድረስም ይጨበጨብልኛል… ወደው ነው የሚያጨበጭቡት!
ከዛማ ሠራተኛው ሀሳቡን እንዲሰጥ ‘ዕድል’ ይሰጠዋል፡፡ (እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… “ዕድል መስጠት…” ብሎ ነገር ምንድነው!  መብትን መጠቀምና ዕድልን ምን አንድ አደረጋቸው? ልክ እኮ ሀሳብ አቅራቢው በመብቱ የሚጠቀም ሳይሆን እርጥባን የተሰጠው ያስመስሉታል፡፡)
እናላችሁ…መጀመሪያ ያው እኔም የማውቃቸው፣ እነሱም ‘ራሳቸውን የሚያውቁ’ ሰዎች ስለ ድርጅቱ ጠንካራነት፡ ስለ እኔ አመራር ጥበብ ምናምን ተራ በተራ ይናገራሉ፡፡ ከዚያ መቼም ነገር ምንም ቢጠራ አደፍራሽ አይጠፋም አይደለ…አንዱ እጁን ያነሳና ዕድል ይሰጠዋል፡፡
“ይጠገናሉ ተብለው ከመሥሪያ ቤቱ ጀርባ አሥራ ስምንት መኪኖች ነበሩ፡፡ አሁን ግን አምስቱ በቦታው የሉም፡፡ የት እንደሄዱ ይነገረን…” ምናምን ይላል። (ይሄ የትራንስፖርት ክፍሉ ሰውዬ አረቄውን ግቶ ለፍልፎ ይሆናል! ደግሞስ ሀሳብ አቅራቢ ተብዬው ስለ መኪና ምን አገባው! ዝም ብሎ የፕሮጀክት ዝግጅት ሥራውን አይሠራም! ቆይ ማህደር ክፍል ወርውሬ ሳምባና ጉበቱን አቧራ፣ በአቧራ ባላደርገው እኔ ሰውዬው አይደለሁም!)
“በእርግጥ ስለ እነሱ መኪኖች ሙሉ ዘገባው ባይደርሰኝም በጥቂቱ ሰምቻለሁ፡፡ ጠፉ የተባሉት መኪኖች ለመጥፋታቸውና እውነት የጠፉ ከሆነም ምክንያቱን ለማወቅ ምክንያቱን ለማወቅ ጥናት ይካሄዳል፡፡ አስፈላጊ ከሆነም ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴ እናቋቁማለን፡፡ (እንደ ‘ባለ ወንበርነቴ’ ይቺ ኮሚቴ የሚሏትን ነገር ስወዳት!  ልክ ነዋ…‘ማንኛውም ሥራ በሚገባ እንዲሠራ ካልፈለግህ ወደ ኮሚቴ ላከው’ የሚሏት አባባል አለች፡፡ እኔም የመኪኖቹን ጉዳይ ወደ ኮሚቴው እልከዋለሁ፡፡ — ‘ፎርዊል ድራይቩ’ ያን ያህል ያረጀ አልመሰለኝም ነበር! — በወር ከአሥራ አምስት ቀኑ ኮሚቴው እርስ በእርሱ ይበጣበጥና ይፈርሳል፡፡ ሌላ ኮሚቴ ለማቋቋም ደግሞ ዓመትም ሊፈጅ ይችላል፡፡ ታዲያ ያን የመሰለ ‘ወንበር ላይ ተቀምጬ’ ኮሚቴ የማልወድሳ! ኮሚቴ የዘላለም ይኑር የሚለው መፈክር በልባችሁ ያለ ሌሎች የእኔ ቢጤ ‘ባለ ወንበሮች’… ኮሚቴ—ተኮር ፒ.ኤል.ሲ. ምናምን ነገር የማናቋቁምሳ!
ብቻ በዚህም በዛም ለወንበር አብቁኝና የማደርገውን አብረን እናያለን፡፡ ይቅርታ፣ ማስተካከያ… እንደዛ ሳይሆን እኔ የማደርገውን አደርጋለሁ፤ እናንተ ታያላችሁ፡፡ ስፍራችንን እንወቃ!  ቂ…ቂ…ቂ…
ወይ ‘ወንበር’ እና ሰው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4674 times