Monday, 29 August 2016 10:51

የእግር ኳስ ዳኝነት ሚስጥር በካፍ ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(27 votes)

 ክፍል  2
8 ዓመታት ባስቆጠረው የመሰለ መንግስቱ ‹‹እግር ኳስን በራድዮ ተመልከቱ›› ቀጥታ ስርጭት ላይ የካፍ ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ ቋሚ ተሰላፊ ናቸው፡፡ በተለያዩ የብሮድካስት ሚዲያዎች፤ የውይይት መድረኮች በእግር ኳስና ዳኝነቱ ዙርያ በሚሰጧቸው አስተያየቶች ከበሬታን ያተረፉ ናቸው፡፡ በእግር ኳስ ዳኝነት ሙያቸው ከ46 ዓመታት በላይ ልምድ አካብተዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከስፖርት አድማስ ጋር ካደረጉት ሰፊ ቃለምልልስ የመጀመርያውን ክፍል ማቅረባችን የሚታወስ ነው፡፡ ይህ የቃለምልልሱ የመጀመርያ ክፍል በአጠቃላይ የህይወት ታሪካቸው፤ የሙያ ተመክሮ እና የስራ ልምዳቸው ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
ኢንስትራክተር ሽፈራው የኢትዮጵያ እግር ኳስ የዳኝነት ሙያን በየጊዜው በሚያሳድጉ ተግባራት ንቁ ተሳታፊ ናቸው፡፡ በዳኝነቱ የህግ ትርጓሜዎች፤ ስልጠናዎች እንዲሁም ሙያዊ አስተያየቶች በእግር ኳሱ ዙርያ ለሚገኙት ባለድርሻ አካላት ብዙ እውቀት አስጨብጠዋል፡፡ ለአመታት በዳኝነት ሙያ ውስጥ በማለፍ ለሙያው ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማድረጋቸውም በላይ ለእግር ኳስ ተጫዋቾች፣ ለአሰልጣኞች ፣ ለእግር ኳስ አመራሮች፣ ዳኞች እና ለስፖርት ቤተሰቡ የቅርብ አጋር ሆነው በመስራት ይታወቃሉ፡፡  ባለፈው ሳምንት የዘመናት ጥንስሳቸው የሆነውን “የእግር ኳስ ዳኝነት ሚስጥር“ በሚል ርዕስ ያዘጋጁትን መጽሃፍ በኢንተር ኮንቲኔታል ሆቴል በርካታ የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አስመርቀዋል፡፡ ኢንስትራክተሩ መፅሃፋቸው በመማርያእና በማስተማሪያ ሰነድነት የሚያገለግል፤ በእግር ኳስ ሜዳ ላይ የሚታዩት አለመግባባቶችን የሚቀንስ፤ የእግር ኳስ ዳኞች የህግ እውቀታቸውን በማስተካከል የዳኝነት ቴክኒካቸውን እንዲያሳድጉ የሚያደርግ፤ ጨዋታው በህግ እንዲመራ ብቻ ሳይሆን በህግ ለመከታተል የሚያግዝ መሆኑን ያስገነዝባሉ። በምረቃው ስነስርዓት ላይ የተገኙት የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ለመፅሃፉ ሙሉ ለሙሉ እውቅና መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡ መጽሃፉ ለዳኞች ከፍተኛ ምሳሌ የሚሆንና ሞራላቸውን የሚገነባ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለአገራችን እግር ኳስ ዳኞች ጥራት እገዛ የሚያደርግ፤ ሁሉም የእግር ኳስ ባለሙያ እና ቤተሰብ ዘንድ ሰርፆ በመግባት የእግር ኳስ ጨዋታ ህግ ግንዛቤያቸውን የሚያሳድግ መሆኑን ፌደሬሽኑ እንዳመነበት የገለፁት ፕሬዝዳንቱ፤ በስሩ ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት በማሰራጨት እንደሚሰራበት በመጠቆም ለኢንስትራክተሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በሌላ በኩል በመፅሃፉ ምረቃ ወቅት በተዘጋጀው  አጭር የውይይት መድረክ የእግር ኳስ ጋዜጠኛ የሆነውና በብስራት ኤፍኤም 101.1 ላይ ብስራት ስፖርት በተባለ የራድዮ ፕሮግራሙ የሚሰራው መንሱር አብዱልቀኒ መፅሃፉ በእግር ኳስ ስፖርት ዙርያ ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት እንደማጣቃሻ ሆኖ በአማርኛ በተፃፈ ማብራርያ የቀረበ፤ ስለጨዋታው ህግ የሚያስተምር እና የሚያስተዋውቅ፤  ለስፖርት ሚዲያውና በአጠቃላይ በእግር ኳስ ላይ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ልዩ አቅም የሚፈጥር መሆኑን በመግለፅ አስተያየት ሰጥቷል። በብስራት ኤፍኤም 101.1 ላይ ‹‹ብስራት ሃይላይት›› ፕሮግራም አቅራቢ የሆነው ወጣቱ አሰልጣኝ እና ሚሊዮን ጉጉሳ በበበኩሉ የጨዋታው ህጎችን በዝርዝር ማወቅ በአሰልጣኝነት ሙያ ለሚሰሩ ብዙ ጥቅም እንዳለው አብራርቶ፤ በተለይ አሰልጣኞች በዳኝነቱ እና በጨዋታው ህጎች ዙርያ ግንዛቤ ማግኘታቸው የስፖርቱን መድረክ ሰላማዊ ያደርገዋል ብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢንተርናሽናል ዳኛ የሆነችው ሊዲያ ታፈሰ በበኩሏ የኢንስትራክተር ሽፈራው የዳኝነት ትምህርቶች እና ስልጠናዎች ከጅምሩ መከታተሏን መስክራ፤ ኢንስትራክተሩ በሚሰጧት ሞራል እና ምክር ጠንክራ በመስራቷ እስከ የሴቶች እግር ኳስ ዓለም ዋንጫ መድረሷን በመግለፅ ምስጋናዋን አቅርባለች፡፡ የዳኞች ማህበርን የወከሉት ኢንተርናሽናል ዳኛ ሚካኤል አርዓያ በበኩላቸው በስፖርቱ ዙርያ ያሉ ባለድርሻ አካላት በዳኝነት ሙያ ያሉ ሁኔታዎችን ከመፅሃፉ አንብበው በመረዳት ስፖርቱን መከታተላቸው በሙያው ላይ የሚንፀባረቁ የውዝግብ አጀንዳዎችን ቀስ በቀስ እያጠፋ እንደሚሄድ እና እግር ኳስ ሜዳን ሰላማዊ መድረክ ያደርገዋል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ባቀረብነው የመጀመርያ ክፍል ቃለምልልሳችን በአዲሱ  መፅሃፍዎ ይዘት ላይ በጀመርነው ውይይት   ነበር፡፡ በመፅሃፉ 4 ምእራፎች መኖራቸን ገልፀው፤ በተለይ በመጀመርያው ምእራፍ በአጠቃላይ የህይወት ታሪክዎ የሙያ ተመክሮ እና የስራ ልምድዎ ዙርያ በስፋት ማብራርያ ሰጥተውን ነበር።  የዛሬውን ቃለምልልስ በቀሪዎቹ የመፅሃፉ  ምዕራፎች ዙርያ ብንቀጥልስ…
እንግዲህ ሁለተኛው ምእራፍ ለሁሉም የስፖርት ቤተሰብና ባለድርሻ አካላት በቂ እውቀት በግልፅ እንዲያስጨብጥ የተዘጋጀ ነው፡፡ በተለይ በእግር ኳስ ጨዋታ ህግ አመጣጥ እና የዳኝነት ታሪክ ዙርያ ያጠነጥናል፡፡ በእግር ኳስ ዳኝነት ለብዙ ዘመናት ምስጥር ሆነው የተቀመጡ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ በዳኝነቱ ዙርያ ያሉ እነዚህ መሰረታዊ እውቀቶች በጥቂት ሰዎች ግንዛቤ ብቻ ተወስነው ከእነሱ በሚገኝ አስተያየት ብቻ ለመገንዘብ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ የሚገርምህ ዳኛ ሆኜ ከማጫውትበት ጊዜ አንስቶ ይህን አካሄድ ስቃወመው ነበር፡፡ የእግር ኳስ ዳኝነት ሙያው ውስጥ ባሉ ሰዎች ተወስኖ መቀመጥ የለበትም ነው የምለው፡፡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ህጎቹን  ሊያውቋቸው ያስፈልጋል የሚል አቋም ነበረኝ፡፡ መፅሃፉን ለማዘጋጀት የወሰንኩበት ዋና መነሻዬም ይሄው ነው፡፡ እስከመቼ ድረስ የእግር ኳስ ዳኝነቱ በጥቂት ሰዎች ጭንቅላት ተወስኖ ይቀራል፤ የስፖርት ቤተሰቡ በዳኝነቱ እውቀት ሊኖረው የሚችለው እንዴት ነው የሚል ጥያቄ በማንሳት፤ የበኩሌን አስተዋፅኦ ለማድረግ ነው መፅሃፉን ያዘጋጀሁበት ዓላማ፡፡  ይህን በተመለከተም የእግር ኳስ ጨዋታ ህጎች አመጣጥና እድገት በማለት በመፅሃፉ ሁለተኛ ምዕራፍ 17ቱን መደበኛ የእግር ኳስ ህጎች በመዘርዘር ግንዛቤ ለመስጠት ሞክርያለሁ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እግር ኳስ በጨዋታ ህግ መዳኘት ከመጀመሩና ህጎች ከመውጣታቸው በፊት እንዴት ነበር የሚዳኘው፤ ጨዋታዎችን በዳኝነት ህጎች መምራት የት ነው የተጀመረው፤ በምን አይነት ሂደት እና እንቅስቃሴ ዳኝነቱ ያለንበት ዘመን ላይ ደረሰ፤ ህጎች በየጊዜው ተቀርፀው እና ተሰባስበው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰራባቸው ህጎች የሆኑት እንዴት እና መቼ ነው፤ ህግ ከመሆናቸው በፊት እየተንጠባጠቡ የመጡ ህጎች የትኞቹ ናቸው፤ በየዓመቱ እየተሻሻሉ የመጡት ህጎችስ ምን ምን ናቸው፤ ሁሉም ህጎች በየጊዜው በተለያየ ሂደት እና ሁኔታዎች እየታደሱ እየተሻሻሉ የመጡበት አቅጣጫ፤ አንዳንድ ህጎች ስንት ዓመት ተሰርቶባቸው እንዴት ተሻሻሉ በየትኞቹ ህጎች ተቀየሩ የሚሉትን ሁሉ በመፅሃፌ ሁለተኛ ምዕራፍ ደረጃ በደረጃ ለማብራራት ጥረት አድርጊያለሁ፡፡
ይቅርታ ኢንስትራክተር በምዕራፍ ሁለት እንግዲህ የተነሱ ነጥቦችን ሲጠቃቅሱ ለምሳሌ የሚሆን ነገር ቢያነሱልን?
አሁን ለምሳሌ ህግ 1 ብለን ነው የምንጀምረው። የጨዋታውን ሜዳ የተመለከተ ነው፡፡ አሁን ዛሬ የምንጠቀመው የኳስ መጫወቻ ሜዳ ብዙ የለውጥ ሂደቶችን በማለፍ የመጣ ነው፡፡ የሜዳው ዲዛይንና መስመሮቹ የማዕዘን ምት የሚመታባቸው ስፍራዎች እና የሚቀመጡ ባንዲራዎች በየጊዜው የተሻሻሉ ናቸው። ኳስ ጨዋታ ሲጀመር ከጅምሩ የመጫወቻው ሜዳ እንዲሁ በደፈናው በገመድ ታጥሮ ነበር የሚካሄደው። እሱ ከቀረ በኋላ አራት ማዕዘኑ ሜዳ ዙርያው ተቆፍሮ የመጫወቻ ቦታና የተቃራኒ ቡድኖች ድንበር የሚለዩ መስመሮች፤ የኳስ በጎን እና በእጅ ውርወራ መስመር የሚወጣበትን ለመለየት በሚያስችሉ ምልክቶች እየተከለለ… ማለት ነው።  በመቀጠል በጨዋታው  ህግ ቁጥር 2 የምትጠቀሰው ኳሷም ብትሆን ያለፈችባቸውን ሂደቶች ይመለከታል፡፡ ድሮ ኳሶች ባለቀለም ሁሉ ነበሩ፡፡ በበረዶ ላይ ለመጫወት ነጥ አይሆንም ተብሎ መጫወቻዎቹ ቀይ ኳሶች ሁሉ ነበሩ፤ የኳሷ ክብደት ዙርያ ገቡ መቼ ተሻሻለ፤ መቼ ተወሰነ… ወቅቶቹ እየተጠቀሱ ማብራርያ እየተሰጠበት ይቀጥላል፡፡ በሌላ በኩል በ2016 /17 አዲስ የጨዋታ  ህግ 3 ለተጨዋቾች ብቻ በተናጠል የተጨመረው አንቀፅ ነው፡፡ ተጨዋች ተብሎ በፊት በነበረው ህግ የተጨዋቾች ብዛት ተብሎ ተገድቦ የተቀመጠ ህግ ነበር፡፡ በአንድ ቡድን ስንት ተጨዋቾች ሜዳ ገብተው መጫወት እንዳለባቸው፤ በአንድ ጨዋታ መሰለፍ ያለባቸው ተጨዋቾች የመጨረሻ ብዛት፤ የተጨዋቾች አቀያየር ስነስርዓት፤ የትጥቅ አለባበሳቸው፤ እነዚህን የሚያመለክቱ ህጎች አሁን በተሻለ መነግደግ  ህግ 3 ተጨዋቾች እንዲሁም ህግ 4 የተጨዋቾችትጥቅ በተሰኙ አንቀፆች ተከፋፍሎ በዝርዝር ሊቀርብ የቻለበት ነው፡፡
በእግር ኳስ ዳኝነትና የጨዋታ ህጎች አፈጣጠር እና ድንጋጌ የትኛው ዓለም አቀፍ ተቋም ወይም አገራት ናቸው ፈርቀዳጆቹ?  ብዙ ለውጦች እና መሻሻሎችን እነማን ያከናውኗቸዋል? ከየት በመነሳት ነው አሁን ያለበት ደረጃ የደረሰው? ….
የሁሉም መነሻ የህግ አውጭው አካል ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበራት ቦርድ International Football Association board አይኤፍኤቢ ነው፡፡ በሱም ዙርያ የመፅሃፉ ሁለተኛ ምዕራፍ ይዳስሳል፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ተቋም ምስረታው ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፊፋ ሁሉ የቀደመ ነው፡፡ እንዴት እንደተቋቋመ፤ መስራች አገራቱ እነማን ናቸው የሚል ማብራርያ አለ በምዕራፍ ሁለት፡፡ አይኤፍቢኤ ወይንም ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበራት ቦርድ የተመሰረተው በ1882 እና 83 አካባቢ ሲሆን በ1904 እኤአ ከተመሰረተው ፊፋ አስቀድሞ የነበረ ነው፡፡ ይህ የህግ አውጭ አካል አይኤፍኤቢ ማለት ነው፤ ከተመሰረተ በኋላ የመጀመርያውን ዓለም አቀፍ ስብሰባ እኤአ በ1886 ነበር ያደረገው፡፡ ከዚያ ቦርድ ስብሰባ በፊት በየአገሩ ቡድኖች ይጫወቱ የነበረው በየራሳቸው ይዘው በሚመጡት የመግባቢያ ደንቦች መሰረት ነበር፡፡ ውድድሩን የሚዳኙ ግለሰቦች ቢኖሩም ስያሜው ወጥቶ መሰራት የተጀመረው በ1891  እኤአ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ጨዋታውን የሚመሩ ዳኛ ከጨዋታው ሜዳ ውጭ ዳር ዳር ሆነው ለውሳኔ ሰብሰብ ብለው ነበር የሚሰሩት፡፡ እንግዲህ በ1891 እኤአ ላይ  አይኤፍኤቢ ባደረገው ስብሰባ ፈርቀዳጅ ከነበሩት አገራት ዋንኞቹ በታላቋ ብሪታኒያ ስር ተጠቃልለው የሚገኙት እንግሊዝ፤ አየርላንድ፤ ስኮትላንድና ዌልስ ሲሆኑ በዚሁ ስብሰባ ባወጧቸው ህጎች በመስራት  ፈርቀዳጆች ነበሩ፡፡ በ1904 እኤአ ላይ ፊፋን ያቋቋሙ ሰባት አገራት ቤልጅዬም፤ ፈረንሳይ፤ ስዊዘርላንድ፤ ሆላንድ፤ ዴንማርክ፤ ስፔንና ስዊድን ከአይፍኤፍኤቢ ውጭ የነበሩ ናቸው፡፡  እነዚህ በፊፋ መስራችነት የተሰባሰቡ አገራት መደበኛ ህጎችን በማውጣት ሲንቀሳቀሱ ቆይተው በህግ አውጭ አካልነት ከሚሰራው አይኤፍኤቢ  በጋራ ለመስራት የወሰኑት ከዚያ በኋላ ነው። ፊፋ ይህን የጋራ ስምምነት በመንተራስም አይኤፍኤቢ በየጊዜው አርቅቆ በሚያወጣቸው ህግ እግር ኳሱን የሚያስተዳድሩ  አገራትን መልምሎ እንዲያቀርብ እና የፊፋ አባል የሚሆኑበትን እውቅና እንዲሰጥ በማድረግ መሰራቱ ቀጠለ፡፡ ስለሆነም በፊፋ አባል የሆኑ መስራች አገራት እና በአይኤፍኤቢ ስር ያሉት የታላቋ ብሪታኒያ አገሮች ተዋህደው በህግ አውጭው አካል በጋራ መስራት የሚችሉበት ሂደት ተፈጥሯል፡፡ በአጠቃላይ የዓለም እግር ኳስ ዋና የህግ አውጭው አካል የሆነው IFAB ሲሆን ለፊፋ መቋቋም መሰረት የጣለ ተቋም ነበር፡፡ በዚህ መሰረት አይኤፍኤቢ የሚያወጣቸውን ህጎች ፊፋ ለአባል አገራቱ እያስተዋወቀ እና እያሰራጨ የሚሰራበትን ሁኔታ መፍጠር ተችሏል፡፡ ይህ ተቋም አሁንም ድረስ የእግር ኳስ ዋንኛው ህግ አውጭ አካል ሆኖ ሲሰራ በየዓመቱ ለፊፋ አባል አገራት የሚያዘጋጃቸው የጨዋታው ህጎች ሲሰራጩ የፊፋ የጨዋታ ህጎች የሚለው መሪ ርእስ ተቀይሮ አሁን ሙሉ ለሙሉ ዓለም አቀፋዊ የእግር ኳስ መጫወቻ ህጎች በIFAB  መዘጋጀቱ ተገልፆ መቅረብ ጀምሯል፡፡ አሁን የአይኤፍኤቢ የጨዋታው ህጎች በሚል አካሄድ እየተሰራበት ነው፡፡
ቢጫ እና ቀይ ካርድ እንዴት እንደመጣ፤ በፊት እንዴት የሚሰራበት እንደነበር ሁሉ በዚህ ምዕራፍ 2 ይብራራል። የሚገርምህ የቅጣት ካርዶች ባልነበሩበት ዘመን እዚህ አገር ውስጥ ዳኛ ሆኜ አጫውቼ ነበር፡፡ ቢጫ እና ቀይ ካርድ ህግ ሆኖ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የገባው በ1968 ዓም ነበር፡፡ እኛ ያለ ቢጫእና ቀይ ካርዶች ስናጫውት በሜዳ ላይ የነበሩትን ህጎች ይዘን  ስንገባ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የተጋጣሚ ቡድኖችን ተጫዋቾች በመልበሻ ቤት ሰብሰብ አድርገን ስለዲስፕሊኑ በቂ ማብራርያ ሰጥተን ጨዋታውን እናስጀምር ነበር፡፡ ዛሬ  የቡድን መሪዎች፤ አምበሎች፤ አሰልጣኞች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከጨዋታ በፊት የሚያደርጉትን ስብሰባ የመሰለ ነው፡፡  ምክሩ እና ማሳሰቢያው እንደጨዋታው ክብደት ጠንከር እና ቀለል ያለ ሊሆን ይችላል፡፡ ካርዶች ስላልነበሩ ለሚያጠፉ ተጨዋቾች በመጀመርያ በንግግር ማስጠንቀቂያ እሰጥ እና ሌላ ጥፋት ከደገመ ደግሞ በእጅ ምልክት ከሜዳ እንዲወጣ እናደርግ ነበር፡፡ ያንግዜ ዳኛ የነበረው አንድ ስልጣን ምንድነው፤ ከሜዳ የተባረረ ተጨዋች ሙሉለሙሉ ድንበሩን አልፎ ከመውጣቱ በፊት በፊሽካ ጠርቶ በርህራሄ ሊመልሰው ሁሉ ይችል ነበር፡፡ ድሮ ያለቢጫእና ቀይ ካርድ ሲያጫውቱ የዳኝነት ውሳኔዎች ተቀባይነት የሚያጡባቸው የሜዳ ላይ ክስሰቶች የትኞቹ ናቸው በውሳኔዎች ላይ  በተደጋጋሚ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎች በምናሳልፍባቸው ውሳኔዎች ተጨዋቾች ተበደልኩ አይነት ስሜት ውስጥ መግባታቸው ነው፡፡ ይህን ያደረግኩት በመጀመርያ የተፈፀመብኝን ስላላስተዋልክ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ውሳኔህ ተቃራኒን በመደገፍህ ነው ይባልም ነበር፡፡ ቢጫ እና ቀይ ካርድ ሲመጣ ግን ብዙ ለዳኞች እፎይታን የፈጠረ ነበር። የቢጫ ካርድ የሚያሰጡ፤ የቀይ ካርድ የሚያሰጡ ህጎች በዝርዝር መስፈራቸው ጨዋታዎችን በብቃት የመምራት እድል ሊፈጥር ችሏል፡፡ በነገራችን ላይ የቅጣት ካርዶችን በፈርቀዳጅነት ለማስተዋወቅ የተበቃው ከመነሻው  በታላቋ ብሪታኒያ ስር  ያሉ አገራት በ1976 እኤአ ላይ ተቀብለው መተግበር ከጀመሩ በኋላ በመላው ዓለም አሰራጭተውታል፡፡ ይህም የራሱ ታሪክ እና ሂደት ነበረው። የቀይ እና የቢጫ ካርዶች መሰረት የትራፊክ መብራቶች ሲሆኑ ኬን ሃስተን የተባለ እንግሊዛዊ ዳኛ የፈለሰፈው ነው፡፡ በመፅሃፌ ውስጥ ከስር መሰረቱ የተብራራ ነው፡፡ በአጠቃላይ የቀይ እና ቢጫ ካርድ በእግር ኳሱ መጠቀም ሲጀመር ሁሉንም የዓለም ክፍል የሚያግባባ ቋንቋ ሊሆን ችሏል፡፡
የእግር ኳስ ዳኝነት ሚስጥር ምእራፍ 3 እና ምዕራፍ 4 ይዘታቸው ምን ይመስላል?
ሶስተኛ ምዕራፍ የጨዋታ ህጎች ትርጉም እና አፈፃፀም የቀረበበት ነው፡፡ የጨዋታ ህጎች ወጥተዋል፤ እንዴት ተግባራዊ ይሆናሉ በሚል ለእያንዳንዷ ምዕራፍ  እንግዲህ ለ21 ዓመታት ያል ለኢትዮጵያ እግር ኳስ የጨዋታ ህጎችን በመተርጎም ያካበትኩትን ልምድ ሁሉ የተንተራሰ ዝግጅት አድርጌበት ነው፡፡ በጨዋታ ህጎች ላይ በየዓመቱ የሚደረጉ ማሻሻያዎችን የሚያካትት ፤ የሚያስገነዝብ እና የሚተነትን ነው፡፡ ያሉትን አዳዲስ ህጎች ከመደበኛው ሰነድ ትርጓሜዎች በመነሳት ተጨማሪ ትንታኔ እና ትርጓሜ ለሚያስፈልጋቸው የህግ ትርጓሜዎች ምላሽ የተሰጠበት ነው፡፡ ዋናው የጨዋታ ህግ ሰነድ ላይ በቀጥታ ነው የሚተረጎመው፤ እኔ ባዘጋጀሁት መኝሃፍ ግን ተጨማሪ ማብራሪያዎች እና ትርጓሜዎች በመስጠት፤ በምሳሌ እና በስዕላዊ መረጃዎች በማስረዳ፤ በጥያቄ እና መልስ መልክ ግንዛቤ ለመስጠት እንዲሁም ቀጥታ የመማር እና የማስተማር መንገድን በመከተል ቀለል ብሎ የቀረበ ነው፡፡ በምዕራፍ 4 ደግሞ ለማቅረብ የተሞከረው ብቃት ያለው የእግር ኳስ ዳኛ ሆኖ ለመገኘት የሚረዱ ዓለም አቀፍ ሙያዊ ልምዶች እና ምክሮችን ነው፡፡ በ19 ክፍሎች የቀረበው ይህ ምእራፍ በ45 ዓታት የስራ ልምዴ የተገኘ እውቀትን በተለያዩ አቅጣጫዎች ያቀረብኩበት ነው፡፡
በመጨረሻም የመፅሃፉን ዋና ዋና ዓለማዎች ቢገልፁልን..
የእግር ኳስ ጨዋታ እና ዳኝነት ሳይንስ እየሆነ መጥቷል፡፡ ዘመኑ የመረጃ እንደመሆኑም የስፖርቱ ባለሙያዎች ብቃታቸውን እያሳደጉ ግልጋሎት እንዲሰጡ ማዘጋጀትም ያስፈልጋል፡፡ የጨዋታውን ህጎች በተግባር ከሚያስፈፅሟቸው ዳኞች ባሻገር በተለያየ ደረጃ ባሉ የስፖርት ቤተሰቦች ዘንድመታወቃቸው በየሜዳዎቹ የሚታዩትን አለመግባባቶች ይቀይራሉ፤ ይለውጣሉ። የስፖርቱ ተወዳጅነት ይጨምራል የእውቀት ሽግግር እንዲኖርም ያግዛል፡፡ በአጠቃላይ ይህ መፅሃፍ የተዘጋጀበት ዓለማ የእግር ኳስ ጨዋታ ዳኞችን በብቃት ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ ብቻ ሳይሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እና ሙያውን እንዲያፈቅሩ የሚያዘጋጅ ነው፡፡ መፅሃፉ የእግር ኳስአፍቃሪዎች በቀላሉ የጨዋታውን ህጎች መንፈስ እንዲገነዘቧቸው ያደርጋል፡፡ ዳኞች የሚያሳልፏቸውን ውሳኔዎች በፅሞና እንዲመረምሩ ያግዛቸዋል፡፡ የዳኞችን ወቅቱን የጠበቀ የህግ እውቀት እና የዳኝነት ቴክኒክ ያሳድጋል፡፡ በየደረጃው ያሉ የእግር ኳስ ጨዋታ ሃላፊዎች፤ አሰልጣኞች፤ ተጨዋቾች፤ የክለብ አመራሮች፤ የስፖት ሚዲያ ባለሙያዎች፤ የእግር ኳስ ጨዋታ ደጋፊዎች እና ታዳሚዎችን የመጠቀም ዓላማም ያለው ነው፡፡የሴት እግር ኳስ ዳኞች እና እግር ኳስ ተጨዋቾች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ ሆነው የሚያድጉበትን እድል ያነቃቃል፡፡…ወዘተ ተረፈ

Read 13276 times