Monday, 29 August 2016 10:53

ንግድ ባንክ የበጀት ዓመቱ ክንውን አመርቂ መሆኑን ገለጸ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2008 በጀት ዓመት ባደረገው እንቅስቃሴ 27.5 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ጠቅሶ፣ የባንኩ ያልተጣራ ትርፍ 13.9 ቢሊዮን ብር መሆኑንና የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 384.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታወቀ፡፡
ባንኩ፣ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው የ2008 ዓመታዊ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣ የበጀት ዓመቱን ክንውን ከሐምሌ 25-30 መገምገሙን ጠቅሶ የተገኘው ውጤት በአብላጫው አመርቂ መሆኑን አመልክቷል፡፡ የባንኩ የሁለተኛው አምስት ዓመት ስትራቴጂ ዕቅድ ተግበራ የመጀመሪያ ዓመት እንደመሆኑ ዕቅዶች ተለጥጠው የተቀመጡና አፈጻጸማቸውም ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ከመሆኑ አንፃር በሁሉም የሥራ ክፍሎች የተቀመጠው ግብ ለማሳካት የተደረገ ጥረት አበረታች መሆኑን ገልጿል።
ለ40 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የኮንትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ በመንግሥት ውሳኔ ከንግድ ባንክ ጋር መዋሃድ በአገራችን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ አዲስ ክስተት ነው ያለው መግጫው ውህደቱ በአጭር ጊዜ በስኬት መደምደሙን፣ 2000 ያህል የባንኩ ሠራተኞች ከንግድ ባንክ ጋር መቀላቀላቸውንና 88 የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ቅርንጫፎች አገልግሎት እንዲቀጥሉ መደረጋቸውን አመልክቷል።
በበጀት ዓመቱ ተቀማጭ ሂሳብ ለማሳደግ በተደረገው ጥረት 46.8 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገንዘብ መሰብሰቡን፣ ክንውኑም የባንኩን ጠቅላላ ተቀማጭ 288.5 ቢሊዮን ብር ማድረሱንና ባለፈው ዓመት ከነበረው 241.7 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር በከፍተኛ ደረጃ በ46.8 ቢሊዮን ብር ማደጉን ገልጿል፡፡
ባንኩ፣ በግልና በመንግሥት ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች 91.9 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር መስጠቱን፣ ቀደም ሲል ከተሰጡ ብድሮች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሠረት 47.8 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን፤ በበጀት ዓመቱ ከወጪ ንግድ ከውጭ ከሚላክ ገንዘብና ከሌሎች የተለያዩ ምንጮች 4.7 ቢሊዮን ዶላር መሰብሰቡንና ከውጭ ለሚገቡ የልማት ግብአቶች፣ ለነዳጅና ለሌሎች የውጭ ግዢዎች 6.8 ቢሊዮን ዶላር ክፍያ መፈፀሙን አስታውቋል፡፡
ተደራሽነቱ ለማስፋት ከፍተኛ እንቅስቃሴዎች እያደረገ መሆኑን ጠቅሶ፣ በበጀት ዓመቱ 84 አዳዲስ ቅንርጫፎች መክፈቱንና 88 የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ቅርንጫፎች አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ በመደረጉ የንግድ ባንክ ጠቅላላ ቅርንጫፎ 1,136 መድረሳቸውን፣ በዓመቱ 1.4 ሚሊዮን ካርዶችን ለተጠቃሚዎች ማድረሱንና ለደንበኞች የተሰራጩ ካርዶች ቁጥር 2.8 ሚሊዮን መድረሱን አመልክቷል፡፡
በዓመቱ 595,216 ደንበኞች ለሞባይል ባንኪንግ፣ እንዲሁም 24,054 ደንበኞች ለኢንተርኔት ባንኪንግ መመዝገባቸውን ጠቅሶ፣ የሞባይል ባንኪንግ ቋሚ ተጠቃሚዎች ቁጥር 716,454፣ የኢንተርኔት ባንኪንግ ቋሚ ተጠቃሚዎች ቁጥር 15,481 መድረሱን ገልጿል፡፡ በዚህ ዓመት 250 አዳዲ ኤቲ ኤሞችና 4,383 የፓስ መክፈያ ማሽኖችን ወደ አገልግሎት ማስገባቱን ጠቅሶ ኤቲ ኤሞችን ቁጥር 889፣ የፓስ መክፈያ ማሽኖችን ቁር 6,269 ማድረሱን፣ እነዚህን ክንውኖች ተከትሎ 2.6 ሚሊዮን አዳዲስ የደንበኞች ሂሳብ የተከፈቱ ሲሆን የባንኩ ጠቅላላ የደንበኞች ሂሳቦች ቁጥርም 13.3 ሚሊዮን መድረሱን ገልጿል፡፡
ባንኩ ዋነኛ ግቦቹን ለማሳካት ለሰው ኃይል ልማት ከፍተኛ ትረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሶ፣ በዓመቱ 4,202 አዳዲስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃን መቅጠሩንና ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ 966 ሰራተኞችን በመቀበል ጠቅላላው የባንኩ ሰራተኞ ቁጥር 28,467 መድረሱን፣ ሰራተኞቹ፣ ለደንበኞቻቸው አርኪና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ፣ ድግግሞሽን ጨምሮ ለ43,809 የባንኩ ሰራተኞች የክህሎት ማበልጸጊያና የመልካም ስነ ምግባር ስልጠናዎች መስጠታቸውን አስታውቋል፡፡
አዳዲስ የባንክ ቴክኖሎጂዎችና ተያያዥ አሰራሮን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ስራ ላይ የሚያውለው ባንኩ፣ በዚህ ዓመትም የፕሮጀክት ማኔጅመንት ቢሮ ከያዛቸው ፕሮጀክቶች መካከል የደንበኞች መረጃና 24 ሰዓት ነፃ አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከልን ጨምሮ ሌሎች የባንኩን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል፣ የኦዲት ስራዎችን በዘመናዊ መረጃዎች ለማከናወንና ሰራተኞች የእውቀት ልውውጥ የሚያደርጉበት 6 የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ስራ መጀመራቸውንና ሁለት ፕሮጀክቶች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን፣ የ30 ደቂቃ ሳምንታዊ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራም ስርጭት መጀመሩንና በተወሰኑ የውጭ አገራት ቅርንጫፎች ለመክፈት የአዋጪነት ጥናት መሰራታቸውን የባንኩ መግለጫ አመልክቷል፡  

Read 1956 times