Monday, 29 August 2016 10:55

ሀበሻ ዊክሊ የአዲስ ዓመት ፕሮጀክቶቹን ይፋ አደረገ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 በናይጄሪያ ሌጎስ እህት ኩባንያ ከፍቷል
   ትልልቅ ኤክስፖዎችንና ሁነቶችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ሀበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን በመጪው አዲስ ዓመት የሚያከናውናቸውን አዳዲስ ፕሮጀክቶች አስተዋወቀ፡፡  
ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ ድርጅቱ በሳሮማሪያ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ከሚያከናውናቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች መካከል በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ “አፍሪካ ኢንተርናሽናል ማኑፋክቸሪንግ ኤክስፖና ኮንፍረንስ” ከጥር 15-17 በሚሊኒየም አዳራሽ ያካሂዳል፡፡ በዚህ ኤክስፖና ጉባኤ ላይ ከመላው ዓለም ተሳታፊዎች እንደሚካፈሉበት ጠቁሟል። ሌላው የአዲስ አመት ፕሮጀክቱ “ሀበሻ ዊክሊ ሚዲያ በ8 ማዕዘን” የተሰኘ ሲሆን በዚህ ፕሮጀክት ስምንት አይነት የሚዲያ ስራዎችን እንደሚያከናውን የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አዶኒክ ወርቁ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ይተላለፍ የነበረው የሀበሻ ዊክሊ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በልዩ ዝግጅትና በአዲስ መልኩ ተዘጋጅቶ “ሀበሻ ዊክሊ በስምንት ማዕዘን” በሚል መጠሪያ አዝናኝና ቁምነገር አዘል መረጃዎች እንደሚቀርብበት ተገልጿል፡፡ ሌላው የሀበሻ ዊክሊ የሬዲዮ ፕሮግራም ሲሆን በተለያዩ አገራዊና አለም አቀፋዊ መረጃዎች ዳብሮ በሳምንት ሁለት ቀን ለአድማጭ የሚበቃ ነው ተብሏል፡፡ ሀበሻ ዊክሊ ወርሀዊ መፅሄትም ከስምንቱ የሚዲያ ዘርፎች አንዱ እንደሚሆን ታውቋል፡፡ ሌላው የሚዲያ አካል www.habeshaweekly.com የተሰኘው የድርጅቱ ድረ ገፅ ሲሆን በአገር ውስጥና በመላው አለም ያሉ የመዝናኛ እንቅስቃሴዎችን በየፈርጁ እንደሚያቀርብ የሀበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ሃና ኢተቻ ገልፀዋል፡፡
ድርጅቱ በ2009 ከሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች ተጠቃሹ የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን ምክንያት በማድረግ በሀረሪ ክልል ሀረር ከተማ የሚያዘጋጀው የልማትና የንግድ ትርኢትና ባዛር ሲሆን ጨረታውን አሸንፎ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡   
ሃበሻ ዊክሊ በናይጄሪያ ሌጎስ እህት ኩባንያውን የከፈተ ሲሆን በፊልምና በመዝናኛው ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸውን ስራዎች ለመስራት የተቋቋመ ነው ተብሏል፡፡ 

Read 1576 times