Sunday, 04 September 2016 00:00

ፖለቲካዊ ግጭቶችን እርቅ በመፍጠር መፍታት ይቻላል?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

· ለአገር ሲባል ከእልህ መውጣት አለብን
· ከእርቅ በፊት ደም መፋሰሱን ማቆም አለብን
· ማንም ኢትዮጵያዊ መሞት የለበትም
· ምሁራን አማራጮችን ማሳየት አለባቸው

የአለም እርቅና ሰላም ግብረ ሰናይ ድርጅት እንዴት ተመሰረተ?
ከተመሰረተ ረጅም ጊዜ ሆኖታል፡፡ የዛሬ 17 ዓመት ነው ድርጅቱ የተመሰረተው፡፡ ከመስራቾቹ ብዙዎቹ ዛሬ በህይወት የሉም፡፡ በወቅቱ የሃይማኖቶች ግጭት እየተከሰተ ስለነበረ፣ ይሄ ጉዳይ በጊዜ መፍትሄ ካላገኘ አደገኛ ነው በሚል አንድ ጉባኤ ለማካሄድ ታቅዶ ነበር፡፡ በወቅቱ እኔ የጥናት ፅሁፍ እንዳቀርብ ነበር የተነገረኝ፡፡ ከ2 ሺህ ሰው በላይ ይገኛል ተብሎ ነበር የታሰበው ፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ችግሮች አጋጠሙና ያ ጉባኤ ሳይካሄድ ቀረ፡፡ በኋላም ለምን ሰፋ አድርገን አናየውም ተብሎ የእርቅ ሃሳብ መጣ፡፡ ከኤችአይቪ ጋር ተያይዞም ሰፊ እንቅስቃሴ ይደረግ ነበር፡፡ በዚህ ሂደት የተፈጠረው ግንኙነት፣ የዓለም እርቅና ሰላም ተቋምን እንዲፈጠር አደረገ፡፡ ድርጅቱም ህጋዊ እውቅና አገኘ፡፡
ለምንድን ነው ተቋሙን አለም አቀፍ ያደረጋችሁት?
ሰላም የአለም ነው፡፡ ዓለም ሰላም ካልሆነች የአካባቢ ሰላም አይገኝም፡፡ እነዚህ ሁለቱ ጠርዞች የተያያዙ ናቸው፡፡ በአላማ ደረጃም ስናየው፣ ከአለም ጋር የሚያገናኘን እትብቶቹ እየሰፉ ነው የመጡት። ለምሳሌ ኤችአይቪ/ኤድስ የቤታችን ብቻ ሳይሆን የአለም ችግር ነው፡፡ ሰላምም እንዲሁ ነው፡፡ በእሳቤ ደረጃ አለማቀፍ መሆኑ የሚከብድ አይደለም። አተገባበር ላይ ከግለሰብ ወደ ቤተሰብ፣ አካባቢ፣ ሀገር፣ አህጉር፣ አለም አቀፍ … እያለ ነው የሚሄደው፤ የሰላም ጉዳይ፡፡
የተቋሙ መስራቾች እነማን ናቸው?
እነ ዶ/ር ዘውዴ፣ ፕ/ር ጀማል አብዱልቃድር፣ ፊታውራሪ አመዴ ለማ፣ ፕ/ር ስዩም … የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እኔ መስራች አይደለሁም፡፡ በህይወት ያሉት መስራች ዶ/ር ያዕቆብ በቀለ ናቸው፡፡ ግለሰቦቹ በግል ተነሳሽነት ጀመሩት፡፡ ከዚያም የሃይማኖቱ ግጭት መጣ፤የፖለቲካ ቀውስ ተከለተለ፡፡ በምርጫ 97 ጉልህ ስራ አከናውነዋል፡፡  
በሃይማኖት ግጭቶች ላይ ምን ያህል ጣልቃ ገብታችሁ እርቅ አውርዳችኋል?
እኛ እንግዲህ ሽማግሌዎች ነን፡፡ በኛ አቅም ተው ማለት ነው ድርሻችን፡፡ ቦታው ላይ እንደ ተወርዋሪ ደርሰን ለማስታረቅ አቅሙ የለንም፡፡ በግለሰብ ደረጃ ነው የምንንቀሳቀሰው፡፡ የቢሮም ሰራተኛ የለንም። በአቅማችን ልክ እናስታርቃለን፡፡ ብዙ ስብሰባዎች አካሂደናል፤ ስለ እርቅና ሰላም፡፡ የኛ ስራ አሁን ግንዛቤ ማስጨበጥና ውይይት ማድረግ ነው፡፡ የሽማግሌዎች መረብ በመላ ሀገሪቱ ለመዘርጋት ሁሌም ይታሰባል። የተወሰኑ ሙከራዎችን አድርገናል፡፡
ከአባ ገዳዎችና ከአዛውንቶች ጋር ውይይትም አካሂደናል፡፡ ውጤታማ ሆነናል አልሆንንም በሚለው ላይ ራሱን የቻለ ግምገማ ያስፈልገዋል፡፡ ግን የገንዘብ አቅም ስለሌለን የነደፍናቸውን ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ጉድለት አለብን፡፡ ከየስብሰባው የምናገኘው ግብረ መልስም፤ “በጣም ዘገያችሁ፤ መስራት የሚገባችሁን ያህል አልሰራችሁም” የሚል ወቀሳ ነው፡፡
የ97 ምርጫን ተከትሎ በሀገሪቱ ግጭትና ቀውስ ከተፈጠረ በኋላ … የእናንተ ሚና ምን ነበር?
ብዙ ባለድርሻዎች ነበሩ፡፡ ሁሉም በየፊናው ችግሩን ለማቃለል ይሯሯጥ ነበር፡፡ የኛዎቹም ሽማግሌዎች የተለያዩ በሮችን እያንኳኩ ነበር። ብዙ እንግልትም ደርሶባቸዋል፡፡ በመንግስትም በፓርቲዎችም ብዙ ተንገላተዋል፡፡ ለረዥም ጊዜ አንኳክተው ነው በሮቹ የተከፈቱት፡፡ በወቅቱ ከየቦታው የተወከሉ ሽማግሌዎች አንድ ራሱን የቻለ አካል አቋቋሙ፡፡ የኛ ሽማግሌዎችም በዚህ አካል ውስጥ ነበሩበት፡፡ ከሌሎች ጋር አብረው ሆነው እርቁንና ይቅርታውን ማረሚያ ቤትና መንግስት ጋ በመመላለስ ስኬታማ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ እኔ ደስ የሚለኝ የውጭ ኃይል ሳያስታርቀን እኛው በእኛው መታረቃችን ነው፤ በእውነቱ ትልቅ ድል ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች እንቅልፋቸውን አጥተው ነበር ያን ሁሉ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበረው፡፡
በወቅቱ በመንግስትና በተቃዋሚዎች መሃል እርቅ እልወረደም፤ መንግስት በገደብ ይቅርታ አደረገ እንጂ የሚሉ ወገኖች አሉ … በሁለቱ አካላት መሃል የተፈጠረው እርቅ ምን አይነት ነበር?
የሽምግልና ሚና ጫና ማሳደር ነው፡፡ ሁለት ተሸማጋዮች ቁጭ ብለው እንዲወያዩ ሁኔታዎችን ማመቻችት ነው፡፡ የዳኝነት ውሳኔ ጉዳይ አይደለም። የመንግስትን አካል ተክቶ የሚሰራበት ፍልስፍናም የለም፤ ድርሻው ጫና ማሳደር ነው። ጣልቃ ገብቶ አንዱን መኮነን፣ አንዱን ንፁህ ነህ ማለት አይችልም፡፡ ችግሩን በመተንተንም ለውሳኔ አያቀርብም፤ሽማግሌ። ምናልባት ሞራላዊ ጫና ለማሳደር መገሰፅ ይችል ይሆናል፡፡ ሽምግልና ዳኝነት አይደለም፡፡ በወቅቱ ሲደረግ የነበረውም በዚህ መልኩ ነው፡፡
እንደ አሁኑ ያለ የፖለቲካ ቀውስ ሲከሰት፣በሁሉም ዘንድ ተሰሚነት ያላቸውና የሚከበሩ ሰዎች (ሽማግሌዎች) አለመኖራቸው ጎድቶናል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ሀሳብ ላይ ምን ይላሉ?
እርግጥ ነው የተበላሸ፣ የጠፋ ነገር አለ። በፊት አንድ መንደር ውስጥ ተሰሚነት ያለው ሰው አይጠፋም ነበር፡፡ የሚያዳምጡት፤ ምክሩን የሚቀበሉት ሰው ይኖራል፡፡ ይህ ሰው እምነቱና ታማኝነቱ ታይቶ ነው ተሰሚነት የሚኖረው፡፡ ድሮ ባህታውያን ንጉሶችን ይመክሩ ነበር፡፡ ዛሬ የሚመክረን ኢንተርኔቱ፤ ቴክኖሎጂው ሆኗል፡፡ እነዚህ የመጡት ስለፈለግናቸው ወይም ስለጠላናቸው አይደለም፤ የሂደት ጉዳይ ነው፡፡ የህይወት ፍልስፍና ለውጥም ለዚህ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ዛሬ ትምህርት ቤት የሲቪክና ስነ ምግባር ትምህርት ይሰጣል፤ ጥሩ ነው ግን የህይወት ፍልስፍና የለውም፤ ትምህርቱ። ያ ከሌለው ደግሞ ዝም ብሎ መካኒካል ይሆናል። አዲሱ መብትና ባህላዊ መብት አሁን ላይ ተጋጭቷል፡፡ እርግጥ ነው መጋጨታቸው ጥሩ ነው፡፡ ትምህርት እናገኝባቸዋለን፡፡ ልጆቻችንም ፈሪ እንዲሆኑ አንፈልግም፤ ከጊዜው ጋር መሄድ አለባቸው። ግን ይሄ ሲሆን በምን አግባብ ነው? የትናንቱን በመጣል ነው? በዚህ ላይ ሰፊ ውይይት ያስፈልጋል። ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ተወያይተናል፡፡  የስነ ምግባር ትምህርት የመጣው በኛ ግፊት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ያለውን የለውጥ ሂደት መቀበል ያስፈልጋል፡፡
ሽማግሌም ተሰሚ ሰውም የጠፋው ለምንድን ነው የሚለውን፣ሁላችንም ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ያሉብን ግጭቶች ብዙ ናቸው፡፡ ግለሰብ ከፈጣሪ ጋር መታረቅ አለበት፡፡ ከዚያ ከራሱ ጋር ይታረቃል፡፡ በኋላ ነው ከዘመድ አዝማድ የሚታረቀው፡፡ እንቅስቃሴ የሚጀመረው ከግለሰብ ነው፡፡ ግለሰቦች ሰላማዊ ከሆኑ ሀገር ሰላም ይሆናል፡፡ አለም አሁን በጦነት ውስጥ ነው፡፡ ሰው ይሞታል፡፡ እኛም ጋ እየሞቱ ነው፡፡ ሰዎች ይሰደዳሉ፣ ይታሰራሉ፡፡ በአንደኛውም ሆነ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዲሁም ዛሬም የምናየው ተመሳሳይ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሰው ሲገደል ማየትም ሆነ መስማቱ ተለምዷል፡፡ መጥፎ ወሬ ለጆሮ መክበዱ እየቀረ ነው፡፡
የሃይማኖት አባቶች በህብረተሰቡ ዘንድ የነበራቸው ቅቡልነት በመቀነሱ ግጭቶችን ለማብረድ የሚሰጡት ማሳሰቢያ ሰሚ ማግኘት አልቻለም የሚሉ ትችቶች ይሰነዘራሉ፡፡ እርስዎ ይሀን አጢነውታል?
እንዳልኩት ብዙ የተበላሹ ነገሮች አሉ፡፡ ከሃይማት አባቶች ጋር ብዙ ስብሰባ አድርገናል፡፡ እኛን የት ነበራችሁ እስከ ዛሬ ይሉናል፡፡ በነገራችን ላይ እኛ ችግር ያሰባሰበን የሀገር ሽማግሌዎች እንጂ የሃይማኖት አባቶች አይደለንም፡፡ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንፈስ አባቶች ናቸው፡፡ ያንን የመንፈስ አባትነት የተሸከመ ግለሰብ፣ ልጆቹን ማስተናገድ አለበት፡፡ ብዙ ጊዜ ወጣቶች አይሰሙንም ይሉናል። የሃይማኖት አባትነት ለምድራዊ ህይወት ብቻ አይደለም፤ ለሚመጣው ህይወትም ኃላፊነት አለበት፡፡ ግን እነሱም ዘንድ ጥቅመኝነትና ሙስና ገብቷል፡፡ ታዲያ የተበላሸ ሰው እንዴት ይመክራል? የድሮ ክብራቸውንና ቦታቸውን ለማግኘት፣ እነሱም ከዚያ መውጣት አለባቸው። ያላስቀመጡትን ክብር ማግኘት አይቻልም፡፡ ግን ኢትዮጵያ የእምነት ሀገር ነችና ማንኳኳቱ ይቀጥላል፡፡ መንፈሳዊ አባቶችም እውነተኛ መንፈሳዊ አባት ሲሆኑ ተደማጭነታቸው ከፍ ይላል ማለት ነው፡፡
አሁን በሀገሪቱ በተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ላይ ምን እየሰራችሁ ነው?
ሁሌም የምንጋብዘው ወደ እርቅ ነው፡፡ ሰው ከሞተ በኋላ አይመለስም፡፡ የሁሉም ሂሳብ ፈጣሪ ጋ ነው ያለው፡፡ ጥፋትን በዚህ ምድር የምናወራርደው ሂሳብ አይደለም፡፡ ትልቁ ጥረት መደረግ ያለበት ህይወት እንዳይጠፋ ነው፡፡ በቴሌቪዥን እንደምናየው አይነት አካሄድ ከሄድን ጉዳቱ የከፋ  ይሆናል፡፡ ከዚያ መራቅ ይኖርብናል። ሁሉም ወገን ከእልህ መውጣት አለበት። ነገሩን ማን ጀመረው የሚለውን ትተን፣ ጥፋቱ ይበቃናል ብሎ ከእልህ መውጣቱ ነው መድኃኒቱ። አይ እልሁን እንቀጥልበታልን ከተባለ፣ ያው ሰው ይሞታል፤ ንብረት ይጠፋል፤ሁሉ ነገር ምስቅልቅሉ ይወጣና ስደተኛ መሆን እንኳ የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ 100 ሚሊዮን ዜጎች ያላት ሀገር ከተበተነች የሚመጣውን ችግር መገመት ቀላል ነው። ፈረንጆቹም ሚዲያዎቹም ይሄን ተንትነው እየነገሩን ነው፡፡ ማስተዋል ያስፈልጋል። መንግስትም የፖለቲካ ኃይሎችም ትንሽ ጊዜ ሰጥተው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ መቆዘም አለባቸው፡፡ የጉልበት ነገር መጨረሻው ጥፋት ነው፡፡ በየጊዜው ደም መፍሰሱ ውጤቱ ለብዙዎች ይተርፋል፡፡ ሰልፍ አደረጉ ተብለው የሚያዙ ሰዎች ቶሎ ቢፈቱ ጥሩ ነው፤ በቆዩ ቁጥር ቤተሠብ ይቆስላል፡፡ ከቤተሠብ ጋር የተያያዙትን በሙሉ ያቆስላል፡፡ እነዚህን ነገሮች መንግስትም በቅጡ ማሠብ አለበት፡፡ ሰልፍ ከተወጣ በኋላ ወንጀል ማፈላለጉ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፤ ብዙ አይነት ሰው ስለሆነ የሚወጣው፡፡ ሆኖም ቶሎ ጉዳዩን አጣርቶ የሚፈታውን መፍታት ያስፈልጋል፡፡
ብዙ ህይወት ከጠፋና ግጭት ከተፈጠረ በኋላ እርቁ ምን ያህል የሠመረ ይሆናል ትላላችሁ?
ጉዳዩ ሰፋ ያለ መድረክ የሚያስፈልገው ሊሆን ይችላል፡፡ ሠላም በማስፈን ጉዳይ አሁን የምንጠይቀው ውይይት አንዲካሄድ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የህግ ታራሚዎች ጥያቄን እናነሣለን፡፡ ቶሎ ቶሎ ስርአት እንዲይዝ እንጠይቃለን፡፡ ይሄን እያደረግን ነው፤ በሂደት እነኝህን ግፊቶች እንቀጥላለን። ስብሰባዎችን ለማድረግ እያቀድን ነው፡፡ እሡ ከተሳካልን ብዙ አካላት ጋ እንደርሳለን ብዬ አስባለሁ።
እርቅ ለመፍጠር ያለው ሂደት ምን ይመስላል ?
መጀመሪያ ደም መፋሰሱን ማቆም ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ በውይይት የጉማ ሆነ ካሣ ጉዳዮች ይፈፀማሉ። ትልቁ ነገር ከእልህ መውጣት ነው፡፡ ለሃገር ብሎ ከእልህ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ፈጣሪ የፈጠረውን መግደል ሃጢያት ነው፡፡ የምህረት ሂደቱ ምን አይነት ይሆናል የሚለው መቼም … ይህቺ ሃገር የሃይማኖት ሃገር ነች፤ ሃይማኖቶች የሚያስቀምጡት የራሳቸው ነገር አላቸው፡፡ ስልጣንን በተመለከተ በአለም ታሪክ ብዙ አይተናል… ሄዶ..ሄዶ ገደብ አለው፡፡ እኛ በወሣኝነት  ከመንግስት አንፃር ሣይሆን ከግለሰቦች አንፃር ነው የምንሰራው፡፡ ግድያ ግድያን ነው የሚያመጣው፤ስለዚህ ከእልህ መውጣት አለብን፡፡ እሳቤያችንን ማስፋት ይገባናል፡፡
የአንድ መንግስት ዘመን ምን ያህል መሆን አለበት? የሚለው ልንወያይበት የሚገባ ጉዳይ ነው። በኛም ሆነ በአፍሪካ ያለው ትልቁ ችግር የስልጣን ገደብ ጉዳይ ነው፡፡ የግጭት አፈታት ጉዳይም ሌላው ችግር ነው፡፡ እኛ የምንችለውን የሞራል ጫና በሁሉም ላይ ለማሳረፍ እንሞክራለን፡፡ የታራሚዎች ጉዳይ የሞራል ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሞቱ ያሳስበናል፡፡ ማንም ይሁን ማንም ኢትዮጵያዊ መሞት የለበትም፡፡ ወደ መጠፋፋት መቅረብ የለብንም፤ እልሃችንን መግታት አለብን፡፡
ከመንግስት አካላት ጋር በዚህ በእርቅ ጉዳይ ላይ ተገናኝታችሁ  አውርታችሁ ታውቃላችሁ?
እንደ ሃገር ሽማግሌ ሁሌም እናነጋግራቸዋለን። ከአንድም ሶስት አራቴ አነጋግረናል፡፡ አሁን እነሱም “የውስጣችንን እናጥራ” እያሉ ነው ያሉት፡፡ ይሄን እስኪያደርጉ እየጠበቅን ነው፡፡ አንዳንዴ ግን ሂደቶቹ እየቀደሙን ነው እንጂ እስከ መስከረም 30 ብዙ ነገር ለማከናወን አቅደን ነበር፡፡
አሁን ለሚታየው የአገራችን ችግር መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?
በመጀመሪያ ከራሳችን ጋር ሱባኤ መግባት አለብን፡፡ አለም ያለችበትን ሁኔታ ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው እርቅ የመሳሠለው የሚመጣው፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ አናት በአናት ላይ የፈላ ይመስለኛል፡፡ የበለጠ የሚያሟሙቅ ሁኔታ ነው የማየው፡፡ እንዴት እናረግባዋለን ለሚለው፣ በሃይማኖት አባቶች በኩል ሱባኤ የምንገባበት ሁኔታ መፈጠር ያለበት ይመስለኛል፡፡ የእምነት ቦታ ከፍተኛ ድርሻ ሊኖረው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ከሃይማኖት ነፃ አይደለችም፤ ሃይማኖት አለን፡፡ የመንግስት አካላትም አሁን እንቅልፍ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ይወያያሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡ የተነሱትን ችግሮች በተረጋጋ ሁኔታ አማራጮችን በማየት ማስተካከል ይቻላል፡፡ ውጤቱ ማሸነፍ መሸነፍን የሚያስከትል ከሆነ፣ዛሬ የተሸነፈ ነገ ለማሸነፍ እልህ ይጋባል፤ ስለዚህ ከዚህ መንፈስ መውጣት አለብን፡፡ የውይይት መድረኮች መፍጠርና ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች በዚህ ረገድ ድርሻቸው የጎላ ነው፡፡
በዚህ ወቅት የምሁራን ሚና ምን መሆን አለበት?
ተጨባጭ ሁኔታዎችን አይተው አማራጭ ሃሳቦችን ማፍለቅ አለባቸው፡፡ ያንን እያደረጉ ያሉም አሉ፡፡ አንዳንዱም ጥግ ይዞ እያየ ነው፡፡ እርግጥ ነው የፖለቲካ ባህላችን መጥፎ ነው፤ ከመሞት መሰንበት በሚለው ነው የተቃኘው፡፡ ምሁሩ አማራጮችን የማሳየት ግዴታ አለበት፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ውስጥ ውስጡን መድረኮች እያዘጋጁ እየሠሩ ይመስለኛል፡፡  

Read 1580 times