Sunday, 04 September 2016 00:00

አፈ-ሙዝ የሚያስልስ ብሶት ከየት መጣ!?

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(4 votes)

“ነፃነት ብርቅ ነው፤ ዲሞክራሲ ሰማይ ነው”

  ዛሬ በምጥ ላይ ስለጣደን የጎሳ ፖለቲካ፤አያሌ ፀሐፍት ብዕር መዝዘዋል፡፡ ገጣሚያን ስንኝ አዋድደዋል፣ ዜመኞች አቀንቅነዋል፡፡ ሀገር አደጋ ላይ እንዳትወድቅ፣ ልዩነታችን አንድነታችንን እንዳይውጥ፣እኛም የዜግነታችንን እንዳቅሚቲ አበርክተናል፡፡ ግና ብዙ አልተደማመጥንም፡፡  በሀሳብ የማያምኑ ሁሉ፤ ድልን የሚለኩት በብረት ነውና አሳዛኝ ግብ ሊኖረው እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ጥላቻና መናናቅ መቸም ቢሆን ለየትኛውም ወገን አይጠቅምም፡፡
ቢሆን ብንከባበር፣ ብንረዳዳና በታሪካዊ ጠላቶቻችን ፊት ከፍ ብለን፣ ሞገስ አግኝተን፣ በአንድ ባንዲራ ስር ብንኖር ደግ ነበር፡፡ ያለፈ በደልና ቂማችንን ሰርዘን፣ የቀጣዩን ዘመን ችቦ በአንድ ደመራ ስር ለኩሰን፣አድማሶቻችን በብርሃን ፀዳል ቢነከሩ ለሁላችንም ጠቃሚ ነበር፡፡ ግና እንዲያ አልሆነም፣ ማማው ላይ ግዙፍ የሆነው መንግስታችን፤ ወደፊት እያየ ባህሩን ከማሻገር ይልቅ፣ “ደም ተቃብታችኋል፣ ደሙ መድረቅ የለበትም፤ ይህ ጎሳ ያንን አጥቅቷል” በሚል ሰበብ በትውልድ ሁሉ ፊት ምሬት የሚለኩሱ የበቀል ሀውልቶችን በየሰፈሩ መትከል ያዘ፡፡
ለመሆኑ የየት ሀገር መሪ ለህዝቡ ይህንን ተመኝቶ ያውቃል? … ከመቶ ሃምሳ ዓመታት በፊት የሞተው ሊንከን፤በጦርነቱ ማግስት የደቡቡን ፌደራሊስት ዓመፅ ያነሱትን ሰዎች ዕጣ በምን ዓይነት እንደሚበቀል ሲጠየቅ፤ “ያለፈው ይበቃናል፣ ከእንግዲህ በኋላ ደም ሊፈስስ አይገባም!” ነበር ያለው፡፡ አርቆ ማሰብ እንዲህ ነው - ለአገርና ለህዝብ!! አንዱን ከአንዱ እያናጩ ብዙ ርቀት መጓዝ አይቻልም፡፡ እጅግ ከማከብረው ከጋሽ አሰፋ ጫቦ፣ “የትዝታ ፈለግ” ጥቂት ሀሳብ ልውሰድ፡-
አብርሃም ሊንከን፤ “with malice toward none, with charity for all with firmness in the right as God gives us the right to see” (ፊታችን ያለ ቂም በቀል ወደ ሁሉም ብንመልስ፣ ሁሉንም እጅ ዘርግተን ብናቅፍ፣ በሀቁ ላይ ፅናት ቢኖረንም ይህን ሃቅ እንድናይ አምላክ አይናችንን ቢከፍተው ..)
የአሜሪካዊያን ትልቅነት በቅዠት የተወለደ፣በጠማማነት የተገነባ አይደለም … የሚያከብሯቸው አባቶቻቸው (founding fathers) ያኖሩላቸው ባህልና ዋጋ ነው፡፡ … ከእርስ በርሱ ጦርነት ማግስት፤ አማፂው ጀኔራል ሮበርት ሊ፤ መንገድ ላይ እንዲለምን አልተደረገም፡፡ ይልቁንም አገሪቱን የሚጠቅም ዕውቀት ስለነበረው፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆኖ ነው ያገለገለው፡፡ እኛ ግን በዚህ የድህነት ጭራ ስር ተወትፈን፣ እርስ በእርስ በመበላላት ደም ማፍሰስና በቂም ችክ ብሎ መኖርን ዕጣችን አድርገናል፡፡ ይቅርታ መጠየቅ ሞታችን ነው፤ በተለይ መንግስት! ሃያ አምስት ዓመታት ለሰራው በደል መች አንድ ቀን ይቅርታ ጠይቆ ያውቃል? ምናልባት አንዴ በመብራት ችግር ጉዳይ ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ሲጠይቁ ሰምተናል። ከዚያ ውጭ የለመድነው ማስፈራራትና ድንፋታ ብቻ ነው፡፡ የሰለጠነ ሰው፤ ከተማ ኖሮ ማህበራዊ ኑሮንና  ስነ ምግባርን የሚያውቅ የሰዎች ስብስብ፣ እንዲህ ችክ ሲል ለራሱም ለሌሎችም አደጋ ነው፡፡ ምናልባት የአፍሪካዊያኑ በሽታ ነው ይሆን? ገጣሚ በለው ገበየሁ፣ ስለ አፍሪካ እጅግ መሳጭና ውብ ግጥም አለው፡፡ ጥቂት ስንኞች ልውሰድ፡-
ጋንኤል ጽፎ ሳይባርክ በተቸረሽ የስም በረካ
እናት መባል ስምሽ ሆኗል ስራ በስም አይለካ
ክፉ መላክ እንደ ብፁዕ ስም ያወጣ ኑሯል ለካ!
ቅም … አልኩ እቴ … ባንደበቴ
ድንቄም እናት - አንቺ አፍሪካ
የገነት ሕልም አምሳል አለም
የምድር ሲዖል ላንቲክ፡፡
እንደ ግጥሙ ነው፤ የምድር ሲዖል ሆኖብናል፡፡ ነፃነት ብርቅ ነው፣ ዲሞክራሲ ሰማይ ነው፡፡ አንዱ ተነስቶ “ልሙትህ!” ይልና ሥልጣን ሲጨብጥ፣በል ተራህን ልግደልህ ይላል፡፡ ኢህአዴግም “ደሜን አፍስሻለሁ፣ አጥንቴን ከስክሻለሁ” እያለ ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የጦርነት ፊልም ሲያሳየን የከረመው፤ አንገታችንን ደፍተን፣ “ዕድሜ ላንተ!” እንድንለው ብቻ ይመስላል፡፡ የጎደለንን ነገር መጠየቅ፣ የተቃወምነውን መናገር “ፀረ ሠላም” የሚል ታርጋ ያስለጥፋል፡፡ የሻዕቢያ ተላላኪም ያስብላል፡፡ ደርግ፤ “የዐረብ ፔትሮ ዶላር ያሰከራቸው ተገንጣይ ወንበዴዎች” ያላቸውን አሁን እነሱ ለሌላው እየደገሙት ነው፡፡
ታዲያ ከዚህ አዙሪት ውስጥ ያለ ጠመንጃ ነፃ አትወጡም! ማለት መጨረሻው ምን ይሆን? እኛ ያየነውን አበሳ፣እኛ ያደናበረንን ጨለማ መጪውንም ትውልድ ማደናበር አለበት? … ይህ ሰዋዊ አስተሳሰብ አይደለም፤ ለገባው ዘመኑን ላወቀ ሰው፤ ኃላቀርነትና ምስኪንነት ነው፡፡ ዛሬም ጠመንጃ ይዞ መሸለል!... ዛሬም በዱላ ማሸነፍ! ዛሬም በሃይል ማስፈራራት! … ዛሬም በቡድንና በጎሳ መከፋፈል! ምን ዓይነት እርግማን ይሆን? … የስናኦር ግንብ ሰዎች ሆነን እስከ መቼ? … እስከ መቼ ቋንቋችን ይደበላለቃል? ጠመንጃ አስቀምጠን፣ ለዕድገት የምንሰራው መቼ ነው? … የትኛው ነቢይ እስኪመጣ ነው የምንጠብቀው ? … መሪዎቻችን በወር አንድ መጽሐፍ እንኳ ቢያነቡ ምናለበት? …ከአሁኑ የተሻለ ለማሰብ ይጠቅማቸው ነበር፡፡  
ገጣሚ ዮናስ ኪዳኔ፤ “የግዜር የብዕር ስም” የግጥም መድበሉ ውስጥ ተመሳሳይ ምሬት ይንጸባረቃል፡፡ እንዲህ፡-
ስብሃት ለዘመኑ
ጭፍኑ ወኔዬ
ሀገር ነው ዝማሬው
ክልል ነው ስሪቱ
ብሄር ነው ቅዠቱ
ድንበር ነው አድማሱ
ኩሬ ውቅያኖሱ
ከንቱነት ነው ምሱ፡፡
ገጣሚው ወደ ሰው ልጅ አንድነት፣ ወደ አዳም ግንድ እንሂድ! ነው የሚለን፡፡ የርሱን ያህል ባንደርስ እንኳን ለምን ፖለቲካችን የሠፈር ይሆናል?... ስልጣናችንን ለምን የጠብ አደረግነው? ዛሬ ጣጣ ውስጥ ለገባንበት ትርምስ አንዱ ምክንያት የኢሕአዴግ ግትርነት-ነው፡፡ የእኔ ሃሳብ ብቻ ይከበር ባይነቱ!... ሌላው ቀርቶ ሰዎች በሠላማዊ መንገድ ትግል ሲያደርጉ እንኳ ትንፋሽ አልተሰጣቸውም። መቶ በመቶ አሸናፊያለሁ ባለበት ብልህነት የጎደለው አነጋገሩ፣ ከጎኑ ሆነው ምርጫውን ያጀቡለትን ነጥ-አልባ ተፎካካሪ ፖለቲከኞች፤ማስርና መደብደብ፣ ማዋከብ ነበረበት? የሠላሙን በር መዝጋትስ የአሁኑን አይነት ዐመፅ ማስነሣቱን ማሰብ ይሳነዋል? ወይስ አንዳች እዚም ወድቆበታል?… ኢህአዴግ ዛሬም በጥንቱ በሬ ለማረስ ይዳክራል፡፡
“የዲያስፖራው ህልም” የሚለው የአሌክስ አብርሃም ግጥም ዓይነት ነው፡-
አበበም እስካሁን የምሳሌ በሶ ያሻምዳል፤
በጨበጠው ጩቤ ጫላ ፍቅር ያርዳል
“አበበ በሶ በላ፤ጫላ ጩቤ ጨበጠ” የሚለውን የመሠረተ ትምህርት ዐረፍተ ነገር ወሥዶ ነው፤ ዛሬም እንደ ሀውልት እዚያው ቆመናል ያለን፡፡ ደግሞም ይሄው ሀገሬ ላይ፡-
የነዳጅ ፅንሠቷ አጥንት ሆኖ ሽሉ..
በየማጀቱ ውስጥ የሰው ደም ይነዳል፤
አንዱ የገነባው በሌላው ይናዳል፤
የመጣው በሄደው ያሻውን ይፈርዳል…
ዛሬ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የሚተርክልንን የሕልም ዓለም ደግሞ እንዲህ ያሽሟጥጣል፡-
ቢሆንም አድገናል!
አደግን እንደናንተ የተባሉ ሁሉ፤
እውነት ነው አድገናል… ግን የናንተን እድገት አላየንም ቢሉ፣
የጠላት ወሬ ነው!!
አዙሪቱ እንዲህ ነው፡፡ በሞታችን ካለቀስን፤ የጠላት ወሬ ነው ይባላል፡፡ ራበን ካልን፣ ረሀብ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ትርጉሙ ምን እንደሆነ ሊያስረዳን፣ካድሬ በባዶ ሆዳችን ይሰበስበናል፤ ስለ ረሀብ ሊተነትንልን፡፡
ሠሚ የለንም እንጂ ሰሚ ኖሮ ቢሆንማ፣ ጉዳያችንን በየቀበሌያችን ጨርሰን ነበርከ፤ዛሬ ከአፈ-ሙዝ ጋር የሞት አፍንጫ ለመላስ የሚያስችል ምሬትስ ከየት ይመጣ ነበር? ሃያ አምስት ዓመታት የተገፉ ጥያቄዎች፤ የታመቁ ብሶቶች ናቸው የፈነዱት።
ሰሚ ቢኖርማ በእንጭጩ፣በየጎጆው ሹክሹክታ ሆነው በቀሩ ነበር!... ሻዕቢያም ሆነ ግንቦት 7 ስማቸው ባልተነሳም ነበር፡፡ ግን ሰሚ የለም፡፡ መቼ ይሆን ጆሮ የምናገኘው?! ሰናይ ጊዜ!!





Read 2253 times