Sunday, 04 September 2016 00:00

ኢህአዴግ፤ ህዝቦችን ከገዛ አመጻቸውም እንኳን ሊጠብቃቸው ሀላፊነት አለበት

Written by  ከበድሉ ዋቅጅራ
Rate this item
(10 votes)

ለወቅታዊው ሀገራዊ ችግር የተሰነዘረ ግላዊ የመፍትሄ ሀሳብ)

በአዲስ አበባ ማስፋፊያ ማስተር ፕላን ሰበብ በኦሮምያ ክልል ህዝባዊ አመጽ ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ ሀገራችን ሰላም አጥታለች፤ በሰላም ነግቶ የሚመሽባት ሀገር መሆንዋ ቀርቶ፣ ወጣቶች ሲነጋ ወጥተው ሲመሽ የማይገቡባት ሀገር ሆናለች፡፡ በኦሮምያ አንድ ያለው የህዝብ ተቃውሞ፣ ወደ አማራ ክልል ተዛምቶ፣ ሀገሪቱ የጦርነት ቀጠና እየሆነች ነው፡፡ የወልቃይትን ጥያቄና የታሰሩ የወልቃይት ኮሚቴዎችን መለቀቅ ጥያቄ ይዞ በጎንደር የተጀመረው ሰላማዊ ሰልፍ፣ መንግስት ጉዳዩን ለመፍታት በመረጠው እልህ የተቀላቀለበት መንገድ የተነሳ እየተባባሰ ዛሬ መላው ጎንደርና ጎጃም መንግስት ስልጣኑን እንዲለቅ የሚጠይቁ መፈክሮችን በአደባባይ እያሰማ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው፣ የሀገሩና የወገኑ ጉዳይ እንደሚያሳስበው አንድ ኢትዮጵያዊ ሀሳቤን፣ ይበጃል ያልኩትን የማቀርበው፡፡
የገጠምን ችግር የተጨማሪ ወገኖቻችንን ህይወት ከመቅጠፉ፣ የብዙዎችን ንብረት ከማውደሙ በፊት ከችግሩ ለመውጣት ምን ቢደረግ ይበጃል? በሚለው ጥያቄ አንጻር ሀሳቤን በቀጥታ ከመሰንዘሬ አስቀድሞ፣ ለምሰነዝረው ሀሳብ ምርኩዝ የሆኑኝን እውነቶች አጠር አጠር አድርጌ ላስቀምጥ፡፡
መንግስት የሀገርና የህዝብ አስተዳዳሪ ነው። አስተዳዳሪ በየትኛውም ደረጃ ያስተዳድር፣ የሚያስተዳድረውን አካል ማዳመጥ አለበት። የሀገራችን ህዝብ ሁል ጊዜ ይናገራል፤ በአፋኝ ስርአት ውስጥም እንኳን መደበኛ መድረክ (ሚዲያ) ቢነፈገው፣ በቀልዱ፣ በዘፈኑና (መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች) መሻቱን ይገልጣል፤ ጥያቄውን ያሳስባል። ኢህአዴግ ግን አንድም አያዳምጥም፤ አልያም ህዝብ የተናገረውን ሳይሆን፣ የህዝቡ ጥያቄ እንዲሆን የሚፈልገውን ያዳምጣል፡፡ በዚህም የተነሳ በችግኝነቱ መመለስ የሚችለውን የህዝብ ጥያቄ ዋርካ ሆኖ እስኪደፈጥጠው ይጠብቃል። የኢህአዴግ መንግስት ህያው ፖለቲካዊ ስርአት ሆኖ ለመቀጠል፣ እራሱን ማደስ፣ ማደግ ሲገባው አርጅቶ እስኪጎብጥ ጠበቀ፡፡ የብርቱካን ዛፍ ሲያረጅ መቆምጠጥ ... መጎምዘዝ ሲጀምር ይገረዛል፤ ያኔ ያረጀው ዛፍ ወጣት ሆኖ ጣፋጭ ፍሬ ይሰጣል፡፡ ኢህአዴግ እራሱን ገርዞ አያውቅም፤ መግረዝ በፖለቲካዊ አስተሳሰብ የማይመስሉትን በየደረጃው ማስወገድ ካልሆነ በስተቀረ፡፡
በዚህም የተነሳ ከሩብ ምእተ አመት በፊት በታላቅ መስዋትነት ደርግን ያስወገዱ ታጋዮች፣ ዛሬም የፖለቲካ ስርአቱ መዳፋቸው ውስጥ ነው፤ በፖለቲካዊ አቋማቸውም ስርነቀል የሚባል ለውጥ አላሳዩም፡፡ ንጉስ ኤዲፐስ፤መከራ ጠሪዋን እንቆቅልሽ መለሰ፤ ግዛቱን ከቸነፈር ታደጋት፤ ነገሰም፡፡ ህዝቡ ከመላእክቱ ቀጥሎ መልአክ አደረገው፡፡ እሱም መልአክነቱን አምኖ ተቀበለ፡፡ ‹‹እኔ ኤዲፐስ! ሴቱም ወንዱም ታላቅ ብሎ የሚጠራኝ›› ብሎ ይፎክር ጀመር፡፡ የአዋቂዎችንና የነብዮችን ምክር ካለመቀበል አልፎ አንቋሸሻቸው፡፡ በመጨረሻ በገዛ ትእቢቱና ማንአለብኝነቱ ተጠልፎ ወደቀ፡፡ ኢህአዴግም ይህን ወቅታዊ ችግር በሰላማዊ መንገድ የማይፈታ ከሆነ ተመሳሳይ ትርክቱን እየጻፈ ይመስለኛል፡፡  
አሁን ለተፈጠረው ችግር ሰላማዊ መፍትሄ መሻቱ በቀጥታ የሚመለከተው መንግስትን ነው። ህዝብ እምቢ ብሎ አምጾአል፤ አመጽ ደግሞ የሚመራበት ህግ የለውም፤ በስሜት ተመርቶ ያልተፈለገ አደጋ ያስከትላል፤ አመጹን በፈለጉት መንገድ ለመምራት ለሚፈልጉ ግለሰቦች እድል ይሰጣል፡፡ መንግስት ግን አመጽ ላይ አይደለም፤ የሚያስተዳድርበት. . . የሚከተለው ህግም አለው። የአመጹትም የሚያስተዳድራቸው ህዝቦች ናቸውና እንዳይጎዱ ይጠብቃቸው ዘንድ ሀላፊነት አለበት። ህዝብን ከገዛ ራሱ አመጽ ይጠብቀው ዘንድ የመንግስት አንዱ ሀላፊነቱ ነው፡፡ መንግስት ህዝብ ላይ እየተኮሰ፣ህዝብን መጠበቅ አይችልም፡፡ ፖሊስ፤ ፌደራል፣ መከላከያ ማንኛውም የታጠቀ የመንግስት አካል፤መሞት ያለበት ህዝብ ላይ እየተኮሰ ሳይሆን፣ ወደ ህዝብ በተተኮሰ ጥይት (ማንም ይተኩሰው) መሆን አለበት፡፡ እንዲህ ሲሆን፣ ስለ ህዝብ ለከፈሉት መስዋእትነት ህዝቡ ራሱ ዘላለማዊ ሀውልት ያቆምላቸዋል፡፡ ስለሆነም ኢህአዴግ፣ አመጹን በአመጽ . . . በተኩስ ለመፍታት መሞከሩን ማቆም አለበት፤ ይህ ለጊዜው ውጤታማ ቢሆን እንኳን ቂም አስቋጥሮ ያልፋልና አድሮ ያው ነው፡፡
ኢህአዴግ የችግሩን ደረጃ አላወቀም፤ ወይ ሆን ብሎ አቃሎታል (እኔ ሆን ብሎ አቃሎታል የሚለውን ማመን ይቀለኛል)፡፡ በሚያስተዳድረው ግዛት ውስጥ በየቀኑ ህይወት እየጠፋ፤ ንብረት እየወደመ፤ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ... እያለ፣ የመንግስት ሚዲያ ስለ ልማት፣ ስለ ሉሲ አሟሟት . . . . . ሲዘግብ መስማት መንግስት ችግሩን ለመፍታት ያለውን የቁርጠኝነት ደረጃ እጅግ ያሳንሰዋል፡፡ አለም አንድ በሆነችበት፣ ቻይና የተፈሳው አዲስ አበባ በሚሰማበት የሉላዊነት ዘመን፣ አፍንጫው ስር ህዝቡ የሚያደርገውን ከራሱ ከህዝቡ ለመሸሸግ መሞከር እውነትን ያለመቀበል ብቻ ሳይሆን፣ ከሉላዊው ዘመን ጋር አለመቀናጀት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከሚመራው ህዝብ ወደ ኋላ እንዲቀር ያደርገዋል፡፡ ኢህአዴግ ህዝባዊ አመጹን አስመልክቶ፣ሰሞኑን ተደጋጋሚ መግለጫዎችን አውጥቷል፡፡ ከመግለጫው ገኖ የወጣው ጠቅላይ ሚንስትሩ የሀይል እርምጃ እንዲወሰድ ትእዛዝ መስጠታቸውን በመግለጽ ያስጠነቀቁበት ነው። ሌላው ፍሬ ሀሳብ በሚመጣው የፓርላማ አመት የአመራር ለውጥ (ስልጣን የራሳቸው ሳይሆን፣ የህዝብ መጠቀሚያ መሆኑን የሚገነዘቡ ባለስልጣናትን) ለማምጣት መታቀዱ መነገሩ ነው። ላለማመን ካልሆነ በቀር ያመጸው ህዝብ ነው፤ ይህ ከሆነ ደግሞ፣ በምንም መመዘኛ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዝ ተጠየቃዊ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ኢህአዴግ እራሱን አንድ ጥያቄ መጠየቅ አለበት፡፡ በየከተማውና የገጠር መንደሩ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የሚተኩሰው የማንን ሰላም ለመጠበቅ፣ የማንን ልማት ለማፋጠን ነው? በጥይት የታፈነ ጩኸት ሰላም . . .  ጸጥታ አይደለም፡፡ ከተኮስንበት ህዝብ ጋር ሀገር ልናለማ አንችልም፡፡ በዚህ መንገድ የሚመጣ ሰላም፣ ለስልጣን ጋት እድሜ ከመስጠት ውጭ ዘላቂ ሊሆን እንደማይችል ኢህአዴግ ይጠፋዋል ብዬ አላስብም፡፡
ኢህአዴግ ሌላው ያላወቀው ጉዳይ ህዝባዊ ቅቡልነቱ፣እንደ ሸረሪት ክር እየሰለለ ወደ መበጠሱ እየተቃረበ መሆኑን ነው፡፡ ዛሬ ኢህአዴግ በሚያወጣው መግለጫና በሚነድፈው እቅድ ልቡ ቦጭ የሚልበት ጥቂት ነው፡፡ ኢህአዴግ ከልቡ... ከቀልቡ ችግርን ለመመለስ ቢሰራ እንኳን ትልቁ እንቅፋት፣ ይህ በየሰበቡ የሸረሸረው ህዝባዊ ቅብልነት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ስርአቱን ለማስተካከል ጥገናዊ ለውጥ ቢያስብ እንኳን ውጤታማ ሊሆን አይችልም።
ምን ሊሆን ይችላል?
በሰሞኑ መግለጫው እንዳስታወቀው፤ኢህአዴግ በሀይል እርምጃው የሚጸናና የሚገፋበት ከሆነ፣ ህዝቡም እምቢታውን ከቀጠለ ውጤቱ አስከፊ ነው፡፡ በመጀመሪያ የሰዎች ህይወት ይጠፋል። ንብረት ይወድማል፡፡ በተለይ ደግሞ እስከ ዛሬ ጎሳን መሰረት አድርጎ የተስፋፋው፣ ለግለሰቦች መብት ትኩረት የማይሰጠው አስተሳሰብ፣ ለአመጹና መንግስት ለሚወስደው እርምጃ የተለየና ጎሳዊ መልክ ሊሰጠው ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በግለሰቦች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ትልቅ ነው፡፡ ግለሰቦች ሰብአዊ መብታቸው ተጠብቆ መኖር አለባቸው። ‹‹የመንግስት ወገን፣ የህዝብ ወገን›› በሚል ጎራ መጠቃቃትን ሊጋብዙ የሚችሉ እርምጃዎችን ከመውሰድ መንግስትም ህዝቡም መጠበቅ አለበት። አሁን እንደተገለጸው በአንድ ክልል ህዝብ ወይም በአንድ ጎሳ አባላት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዝ፣ ኢህአዴግ መሰረት ካደረገው መሰረታዊ የፖለቲካ ስተሳሰብ ጋር የሚቃረን ነው፡፡ በአንዳንድ ቦታ እንደምናየውና በስፋት እንደሚሰማው ህዝብ ታጥቋል፤ መንግስትም የላከው የታጠቀ ሀይል ነው። መንግስት ከሚያስተዳድረው ህዝብ ጋር ጦርነት መግጠም የለበትም፡፡ ህይወት ባስከፈለ ተጋድሎ ደርግን ከህዝብ ትከሻ ላይ ያስወገደው ኢህአዴግ፤ በዚያ ህዝብ ላይ መተኮስን በፍጹም መፍቀድ የለበትም፡፡ ይህን ካደረገ ሀገራችን እንደ ሶርያ ልትሆን የምትችልበት ጥቂትም ቢሆን እድል አለ፡፡
ሌላው ከዚህ አሁን ካለንበት የሀገራችን ሁኔታ ሊጠበቅ የሚችለው መፈንቅለ መንግስት (ኩዴታ) ነው፡፡ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚያሳስቡት፣ አሁን ያለንበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ኩዴታን ሊጋብዝ ይችላል፡፡
ኢህአዴግ እንዳስታወቀው፤የታዘዘው ሰራዊት አመራሮች ትእዛዙን ከተቀበሉ የሚከተለው ውጤት ከላይ ቀደም ብዬ የጠቀስኩት ነው፤ በመንግስት ሀይሎችና በህዝብ መካከል ደም አፋሳሽ እልቂት (መጠኑ በሁኔታዎች የሚወሰን)፡፡ ያ ካልሆነና የሰራዊቱ አመራሮች ትእዛዙን ካልተቀበሉ፣ ወይም ‹‹መንግስታዊ አስተዳደሩ ተዳክሟል፣ መምራት አልቻለም›› ብለው ካሰቡ፣ (ጄነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ ‹‹ደራጋዊነት . . .›› በሚል ርእስ የሰጡትን ትንታኔ ያስታውሷል) መንግስትን በሀይል ለመለወጥ ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ በየትኛውም ሀገር (በተለይ በአፍሪካ) እንዳየነው፣ ከእንዲህ አይነቱ የመንግስት ለውጥ ሰብአዊ መብቶችን የሚያስከብር ዴሞክራሲያዊ ስርአት አይወለድም፡፡
ምን ቢሆን ይበጃል?
ከገባንበት ችግር ለመውጣት ብቸኛው መፍትሄ ሰላማዊ መፍትሄ መሆን አለበት፡፡ ይህ ሰላማዊ መፍትሄ ደግሞ አሁን ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ ከመገንዘብ የሚመነጭ ሊሆን ይገባል፡፡ መንግስት የቀውሱን መጠንና ስፋት መቀበል አለበት፡፡ በጎንደር ያለው ችግር ሁለት የጎንደር ነዋሪዎች በቴሌቪዥንና በሬድዮ ቀርበው፣ ‹‹ጥቂት ጸረ-ሰላምና ጸረ-ልማት...›› ብለው ከሚገልጹት በላይ ነው፡፡ የአንድን ችግር መግፍኤ ነገር በሚገባ መረዳትና የችግሩን መጠን ማወቅ የምንሰጠውን መፍትሄ ይወስናል፡፡ በመሆኑም ነው ኢህአዴግ ስለ ችግሩ ትክክለኛ ግንቤ መያዝ የሚኖርበት።
የሀገራችን ችግር የመልካም አስተዳደር እጦት ብቻ አይደለም፤ ‹‹ችግሩ መልካም አስተዳደር ነው›› ብለን ብንቀበል እንኳን፣‹‹No problem can be solved from the same level of consciousness that created them.›› እንዲል አልበርት አንስታይን፤ ለዚህ ችግር ማሳውን አለስልሶ፣ ዘርቶ፣ ለፍሬ ያበቃው ኢህአዴግ፤ ብቻውን፣ ችግሩን ባበቀለበት ስርአትና ፖለቲካዊ አስተሳሰብ፣ ለችግሩ መፍትሄ ሊሰጥ ያዳግተዋል፡፡
በመሆኑም፣ ብሄራዊ እርቅ ጠርቶ (ይህንን ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዲፕሎማቶች ባዘጋጀው መድረክ ላይ፣ዲፕሎማቶች እንዳነሱ ከኢቢሲ ሰምቻለሁ) ተቃዋሚዎችንና የሀገር ሽማግሌዎችን ያካተተ ጥምር የሽግግር መንግስት መመስረት አለበት። የሽግግር መንግስቱ በተወሰነ የጊዜ ገደብ፣ በተመቻቸ ዲሞክራሲያዊና ፖለቲካዊ ምህዳር ውስጥ ምርጫ አካሂዶ፣ ስልጣንን በህዝብ ለተመረጠ መንግስት ማስተላለፍ ዋናው ተግባሩ ሆኖ፣ ከዚህ በተጨማሪ በህዝቦች መካከል የተፈጠሩ ችግሮችን በብሄራዊ እርቅ ቀርፎ፣ ከስልጣን ሽግግር በኋላ የሚከተለውን የቂም በቀል እርምጃና መንግስት በተቀየረ ቁጥር የሚከተለውን የአሳሪ - ታሳሪ ትርክት እንዲቀየር መስራት ይጠበቅበታል፡፡
በመሆኑም እንደ አንድ የሀገሪቱ ችግር እንደሚያሳስበው ዜጋ፣ ኢህአዴግ ይህንን ተግባራዊ ቢያደርግ፣ ሀገሬና የሀገሬ ህዝቦች ወደተሻለ ዘመን ይሸጋገራሉ ብዬ አምናለሁ።
ፈጣሪ ሀገራችንንና ህዝቦችዋን ይጠብቅ!!  






Read 7929 times