Sunday, 04 September 2016 00:00

ለፖለቲካዊ ችግሮች - ፖለቲካዊ ውይይት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

• የህዝቡን ጥያቄ እንደ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሳንሶ ማየት እብደት ነው
• አሁን መፍትሄው ህዝብን በተለያዩ ስልቶች ማነጋገር ነው
• ሁኔታው ሳይባባስ በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀለት አስጊ ነው

    አሁንም ከመቀዝቀዝ ይልቅ በየጊዜው እየሰፋና እየጋለ ለመጣው ህዝባዊ ተቃውሞና ግጭት ምሁራንና የአገር ዕውቅ ሽማግሌዎች የመፍትሄ ሃሳቦች የሚሏቸውን እየሰነዘሩ ነው፡፡ ሃሳባቸውን
የሚያደምጥ ተገኝቷል ወይ ለሚለው በእርግጠኝነት መመለስ አይቻልም፡፡ አንድ ነገር ግን በእርግጠኝነት እናውቃለን፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሰሞኑን በመፍትሄነት ያቀረበው ውይይትን የሚያካትት አይደለም፡፡ ሰሞኑን ጠ/ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ፤“ሁሉም የጸጥታ ኃይሎች የህግ
የበላይነት እንዲያስከብሩ አዝዣለሁ” ብለዋል፡፡ መንግስት ችግሩን በሰላማዊ መንገድ በውይይት
ከመፍታት ለምን የሃይል እርምጃን መረጠ? ህዝባዊ ተቃውሞው ትዕግስቱን ክፉኛ ተፈታተነው? ወይስ ወደ መፍትሄው የሚያደርስ አቋራጭ መንገድ ይሆን? አሁንም ግን አስተያየት ሰጪዎች የሃይል እርምጃ የትም አያደርስም እያሉ ነው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ዛሬም
አንጋፋ ፖለቲከኞችን፣ ምሁራንንና ታዋቂ ሰዎችን በችግሩና መፍትሄው ዙሪያ አነጋግሯል፡፡ የዚህ
ውይይት ዓላማ፣በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮች ዙሪያ ሃሳቦችን በማንሸራሸር መፍትሄ ማፈላለግና መጠቆም ነው፡፡ በአገራችን ለተከሰተው ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ መፍትሄ የሚሆን ሃሳብ ወይም አስተያየት አለን ለምትሉ ወገኖች መድረኩ ሁሌም ክፍት ነው፡


“መፍትሄው ህዝቡን በቀጥታ ማነጋገር ብቻ ነው”
አቶ አስራት ጣሴ (አንጋፋ ፖለቲከኛ

   በአሁን ጊዜ ህዝባዊ ቅሬታ አለ፡፡ በእርግጥ ገዝፎ የሚታየው በአማራና በኦሮሚያ ክልል ነው፡፡ ይሄ ማለት ግን በሌሎቹ አካባቢዎች የህዝብ ጥያቄ የለም ማለት አይደለም፡፡ እኔ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታን ሳየው፣ይሄ ህዝባዊ አመፅ በጣም የረፈደ እንጂ ከጊዜው ቀድሞ የመጣ አይደለም፡፡ አንድ ሊቅ ምን ይላል፤ በጣም የሚያስፈራው የጥቂቶች ጭካኔ አይደለም፤ በጭካኔው ፊት የብዙዎች ዝምታ እንጂ” ይላል፡፡ ስለዚህ ህውሓት ኢህአዴግ ይሄን እውነታ አምኖ መቀበል አለበት፡፡ በህዝባዊ አመፁ መገረምም መደነቅም የለበትም!ከተገረመም ከተደነቀም እስከ ዛሬ ድረስ በመቆየቱ ነው መሆን ያለበት፡፡ ይሄን እውነታ አምኖ ሲቀበል ነው ወደ ችግር አፈታት የሚኬደው፡፡ ህዝብ ይለወጣሉ በማለት ከበቂ በላይ ጊዜ ሰጥቷቸዋል፡፡ አሁን ያመጸው  ትዕግስቱ በማለቁ ነው፡፡
ህዝቡ እየጠየቀ ያለው የስርአት ለውጥ እንጂ ጥገናዊ ለውጥ አይደለም፡፡ ስርአቱ ሁሉም ለውጥ የሚደረገው በመቃብሬ ላይ ነው” በሚለው ከቀጠለ፣ ለሱም ሆነ ለሀገርም ሰላም የማይበጁ መጥፎ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ የኃይል እርምጃ ደግሞ የትም አያደርስም፡፡ የህዝቡን ጥያቄ እንደ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሳንሶ ማየት እብደት ነው፡፡ ህዝብ አይሳሳትም፡፡ በኦሮሚያ የታየውን እንቅስቃሴ ወደ ማስተር ፕላኑ ዝቅ ማድረግ በጣም ስህተት ነው፡፡ በአማራ ክልልም እምቢተኝነቱን ከወልቃይት ጠገዴ ጋር ብቻ ማያያዝ ለመሰረታዊ ጥያቄው መልስ ላለመስጠት መፈለግ ነው፡፡ ጥያቄው ትልቅ ነው፡፡ ጥያቄው፤የነፃነት የዲሞክራሲና የፍትህ ነው። ጥያቄው፤ ይህቺ ሀገር የማን ናት የሚለው ነው፡፡ ሀገሬን፣ ዜግነቴን መልሱልኝ ነው ጥያቄው፡፡ ጥያቄው የሀብት ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄው የስርአት ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ መፍትሄው ከህዝብ ጋር ፊት ለፊት ቁጭ ብሎ መነጋገር ነው፡፡ ኢህአዴግ አንዴ 99.6 በመቶ፣ ሌላ ጊዜ መቶ በመቶ ድምጽ አግኝቻለሁ በሚል ህዝቡን በፓርላማ ወኪል አሳጥቶታል፡፡ እንግዲህ ይሄን ወኪል የሌለውን ህዝብ ማነጋገር ነው መፍትሄው፡፡
በእኔ እምነት፤በፓርቲ ስም ህዝብን እወክላለሁ ማለት በአሁኑ ሁኔታ ተገቢ አይሆንም፡፡ በምሁርነትም፣ በሀገር ሽማግሌነትም፣ በሃይማኖት መሪነትም ስም ህዝብን እወክላለሁ ማለት አይቻልም፡፡ ያ ጊዜ አሁን አልፏል፡፡ እነዚህ አካላት ገንቢ አስተዋፅኦ አያበረክቱም ማለት ግን አይደለም። ህዝቡን አይተኩትም ማለቴ ነው፡፡ ህዝብ አስተዋይ ነው፤ ራሱ መብቱን ይጠይቃል፡፡ በእኔ እምነት፤ አሁን መፍትሄው ህዝብን በተለያዩ ስልቶች ማነጋገር ነው፡፡ ሀሰትን እንደ እውነት ማመን፣ ለራስ ትልቅ ቦታ መስጠት መቆም አለበት፡፡ መፍትሄው ወደ ህዝብ ሄዶ መነጋገር ብቻ ነው፡፡ አሁን ህዝብን ወክዬ ከመንግስት ጋር እነጋገራለሁ የሚል ካለ ተገቢ አይሆንም፤ መፍትሄውን ያወሳስባል፡፡


=================================
“ህዝብና መንግሥት ይቅር መባባል አለባቸው”
አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ (በሚሊኒየሙ የትውልዱ የክብር አምባሣደር)

አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ
(በሚሊኒየሙ የትውልዱ የክብር አምባሣደር)
ሀገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ እንደ አንድ ዜጋ ያሳስበኛል:: ኢትዮጵያ ነገ ሊቢያ ወይም ሶርያ አሊያም የቀድሞው ሩዋንዳ እንድትሆን ፈፅሞ አልፈልግም፡፡ እናቴ‘ኮ የወለደችኝ ሀገር ቢኖራት ነው፡፡ መንግስትም ህዝብም በእልህ ምንም ነገር እንደማይሆን ማወቅ አለብን፡፡ ይሄን ሁሉ ችግር ያመጣው ጉቦ፣ የኑሮ ውድነት ምሬት ይመስለኛል፡፡ ጥሩ ጥሩ አዋጆች ይወጣሉ፤ነገር ግን እታች ሲወርዱ በተግባር አይውሉም፡፡ እታች ጉቦ አለ፡፡ አድልዎ አለ፡፡ እርግጥ ነው በሀገራችን ብዙ መንገዶች ተሰርተዋል፤የኢንዱስትሪ ፓርኩም የሚደገፍ ነው፡፡ ነገር ግን የህዝብ ኑሮ መወደድ ያስፈራል፡፡ መንገዱ፣ ህንፃው ---- ለህዝቡ ካልሆነ ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው!?
ሌላው “እስከ መገንጠል” የሚለውን የህግ መንግሥቱን አንቀፅ 39 በግሌ አልወደውም። ፓርላማው ለወደፊት ከህገ መንግስቱ ውስጥ ማውጣት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በየትኛውም የሀገሪቱ ከተሞች ማንኛውም ብሄር ብሄረሰብ በነፃነት መኖር እንዲችል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ በየትኛውም ከተማ መኖር መቻል አለበት፡፡ በደም የተዋሃደ፣ በፍቅር የተሳሰረ ዜጋ፤ ለውጭ ጠላት የማይበገር ነው የሚሆነው፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ነች፤ፋሽስትን የተፋለምነው በዚህ መንፈስ ነው፡፡ የመጣውን ወራሪ ጠላት ሁሉ ያባረርነው በአንድነታችን ነው፡፡
በሌላ በኩል ይቅርታ መደራረግ ደግሞ ተገቢ ነው፡፡ ሀገር እናት ነች፤ መንግስት አባት ነው። ስለዚህ ህዝብና መንግስት ይቅር መባባል አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ነገሩ አስጊ ነው፡፡ እርግጥ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ አስተዋይ ነው፡፡ ሀገሩ እንድትከፋፈል አይፈልግም፡፡ ነገር ግን የመንግስት እገዛ ያስፈልጋል። በጎሣና በሃይማኖት የሚመራ መንግስት ከሆነ መከፋፈሉ አይቀርም፡፡ እኔ ደግሞ ይሄን በአይኔ አያሳየኝ ነው የምለው፡፡ እኔ አማራ ነኝ፤ነገር ግን ኦሮሞውም፣ ትግሬውም፣ ጉራጌውም አፋሩም ሱማሌውም ሌላውም ለኔ አንድ ነው፤ ወገኔ ነው፡፡ በየቦታው ጦርነት እየተነሳ የሚራኮት ከሆነና ደም ከፈሰሰ ያሰጋል፡፡ ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንደሚባለው፣መንግስትም ህዝብም ተባብረው ይሄን ነገር ማጥፋት አለባቸው፡፡ እርቅ መውረድ አለበት። ይቅርታ ማድረግ ለመንግስትም ክብር ነው፡፡ መንግስት አጥፍቻለሁ ይቅርታ ካለ፣ ህዝብም ይቅር ማለት አለበት፡፡
በሁሉም በኩል የስልጣን ጉጉት ካለ ደግሞ፣ ከስልጣን በፊት ሀገርን ማስቀደም ያስፈልጋል ባይ ነኝ። በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት አንድ የተፈፀመ ታሪክ አለ፡፡ አንድ ጊዜ ቤተ መንግስት፣ አንድ ሰው በግርፋት ይቀጣ ተብሎ፣ አፄ ምኒልክ፤ አባ መላ ሀብተ ጊዮርጊስን በዚህ ጉዳይ ምን ትላለህ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ አባ መላም፤ አይ አይገረፍም ይላሉ። እንግዲህ በወቅቱ ደም ማፍሰስ ነውር ነበር፡፡ ሰውየውን ምስለኔ አድርገን፣ ወደ ዳር፣ አፋር እንሹመው እንጂ መገረፍ የለበትም ይላሉ፤ አባ መላ። አፄ ምኒልክም፤በአባ መላ ሀብቴ ሀሳብ ተስማምቻለሁ አሉና በዚህ ተለያዩ፡፡ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ወደ ጨቦና ጉራጌ አገር ለስራ ሲሄዱ፣ እዚህ ያለው መኳንንት ሰውየው እንዲገረፍ ያደርጋሉ፡፡ ይሄንን ሀብተ ጊዮርጊስ ሰሙና ተናደዱ። ከስራቸው ሲመለሱ አኩርፈው ቤታቸው ሀብተ ጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ ገብተው ቁጭ ይላሉ። ለስብሰባ ሲጠሩ፣ አልመጣም አሞኛል ይላሉ። ለምኒልክ ይሄ ይነገራቸዋል፡፡ አይ! ተዉት አላመመውም፤ ነገሩ ገብቶናል” ይላሉ፡፡ አንድ ቀን ጠዋት ሚኒልክ ተነስተው፣ በቅሏቸውን አስጭነው፣ መኳንንቱን አስከትለው ሀብተ ጊዮርጊስ ቤት ገስግሰው ማልደው ይደርሳሉ፡፡ ከበቅሏቸው ወርደው ድንጋይ ተሸክመው፣ ሀብተ ጊዮርጊስን ያስጠራሉ፡፡ ሀብተ ጊዮርጊስ በመስኮት ሲመለከቱ፤ ምኒልክ ድንጋይ ተሸክመዋል፡፡ ሰውየው በድንጋጤ ክው አሉ፤ መጥተው ንጉሱ ጫማ ላይ ወደቁ፤ ሁለቱም ተላቀሱ፡፡ በወቅቱ ምኒልክ ምን አሉ? ሰማህ ሀብቴ÷አስቀይሜህ እንጂ ያንተ አንጀት በኔ ይጨክን ነበርን?” ሰው ሁላ ተላቀሰ፡፡
እንግዲህ ከዚህ የበለጠ ምን ድል አለ? ምን ታላቅነት አለ? እና መንግስትና ህዝብ ይቅርታ ቢደራረጉ መልካም ነው፡፡ እስከ አሁን የፈሰሰው ደም ይበቃል፤የበለጠ እንዳይፈስ የሃይማኖት አባቶች ጠንከር ብለው መምከር መዘከር አለባቸው። በመሳሪያ ወይም በኃይል የሚደረግ ማንበርከክ የትም አያደርስም፡፡ ነገ እንደ ብጉንጅ ሊያመረቅዝ ይችላል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ ከሕዝቧ ፍቅር ጋር ለዘለዓለም ትኑር!!

=================================
“መፍትሄው የሽግግር መንግስት ማቋቋም ብቻ ነው››
ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም (አለማቀፍ የህግ ባለሙያ)

   እንደኔ ከዚህ በኋላ መፍትሄ የሚሆነው የሽግግር መንግስት ማቋቋም ብቻ ነው፡፡ የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት፡፡ በመጀመርያ ግን የፖለቲከኛ እስረኞች በሙሉ መፈታት አለባቸው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ በውጭም ሀገርም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የሲቪል ማህበራት፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች በትልቅ ጉባኤ ተሰባስበው፣አንድ በህዝቡ ተቀባይነት አግኝቶ ሊያረጋጋን የሚችል የሽግግር መንግስት ማቋቋም ያስፈልጋል ባይ ነኝ፡፡ ያ የሽግግር መንግስት በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ምርጫ ማካሄድ አለበት፡፡ ፓርቲዎች በሙሉ ነፃነት በመደራጀት፣ በህዝብ ምርጫ ሀገር የሚመሩበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል፡፡ ይሄ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያካትት መሆን አለበት፡፡ እኔ ከዚህ ውጪ ሌላ ነገር አይታየኝም፡፡
አሁን እንደሚታየው በህዝብ መካከል ከፍተኛ የሆነ ጥላቻ ተሠብኳል፡፡ ይሄ በጣም ያስፈራኛል። የህዝብ ጥላቻ ምን እንደሚያስከትል ከሩዋንዳ ካየሁት ተነስቼ፣በጣም ነው የሚያስደነግጠኝ። ግምቴ ስህተት እንዲሆን እፀልያለሁ፡፡ አሁን ግን የተያዘው አካሄድ ወደዚያ የሚያመራ ነው የሚመስለውና፣ በቶሎ እርምጃ መውሰድ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።
በሩዋንዳ ያ ሁሉ ፍጅት ከመድረሱ በፊት፣ “ይሄ ነገር መጥፎ ነው፤ወደ እልቂት ሊያመራ ይችላል” ብለው ጥቂት ሰዎች አስጠንቅቀው ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች በወቅቱ “ሃገር ከፋፋይ”  ተብለው ተወገዙ፤ ግን ቆይቶ ያሉት ነገር ደርሶ አየነው፡፡ አሜሪካኖች በወቅቱ የዘር ማጥፋት አይደለም በሚል፣እጃችንን አናስገባም ብለው ነበር፡፡ በኋላ ግን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ በአንድ ወቅት ቢል ክሊንተን በሩዋንዳ ጉብኝት ሲያደርግ፣አንድም ሰው ሳይቀበለው ደርሶ ተመልሷል፡፡ በኛም ሃገር ነገሩ በጊዜ ቢደረስበት ይሻላል፡፡ አንዴ ከፈነዳ መመለሻ የለውም፡፡ አሁን መንግስት  መልካም አስተዳደር፣ሙስናን ማጥፋት ወዘተ--- ከሚለው ጉዳይ ህዝቡ አልፎ ሄዷል፡፡ አሁን በህዝቡ ዘንድ ያለው የስልጣን ጥያቄ ነው፡፡ ስለዚህ የግድ የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት፡፡ በዚህ መንገድ ችግሩ ሊቀለበስ ይችላል፡፡


=====================================

‹‹አዕምሮአችንን ማሠራት ካልቻልን ችግሩ ይቀጥላል››
ሠአሊ እሸቱ ጥሩነህ

አሁን አዕምሮ ነው መቅደም ያለበት፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ነገር ተረጋግጦ የታየው፤ ሁልጊዜ ‹‹እኛ ነን ትክክል›› የሚለው አመለካከት ነው፡፡ በኢህአፓና በደርግ የደረሰው ጥፋት በዚህ ‹‹እኛ ነን ትክክል›› በሚለው አመለካከት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አንድ የቻይናዎች ተረት አለ፡፡ ከዚህ ቀደም ህፃን ሆነህ፣ አባትህ የሚለው ነገር ትክክል አይደለም፤ አሁን አባት ሆነህ ልጅህ የሚለው ትክክል አይሆንም የሚል ነው፡፡ ህይወትን እኔ በዚህ መልኩ ነው የማያት፡፡ እና ልጆች ሆነን ድንጋይ ስንወረውር የነበረው፣ስርአቱ ትክክል አይደለም ብለን ነው፡፡ በዘመነ ደርግ፣ እኛ ትክክል ነን፤እናንተ አይደላችሁም በሚለውም ተላለቅን፤አሁን ደግሞ ኢህአዴግ ትክክል የሚለውን መንገድ ይዤ መጥቻለሁ አለ፤ ሌሎች የያዙት ትክክል አይደለም የሚል አካሄድ ነው፡፡ የሚቀጥለውም ቢሆን እንዲሁ ነው የሚለው፡፡ ምክንያቱም አዕምሮ ላይ አይደለም የምንሰራው፡፡ አዕምሮ በሠውነታችን ሰፊ ክፍል ነው፡፡ አዕምሮአችንን ማሠራት ካልቻልን ችግሩ ይቀጥላል፡፡
 ባለፈው ትግራይ ለጉብኝት ስንሄድ የጠየኩት ጥያቄ ነበር፡፡ 60 ሺህ ሰው ደርግን በመጣል አለቀ፤ በመቶ ሺህ የሚሆን ቆሠለ፤ ነገር ግን አዲስ አበባ ከተገባ በኋላ ለከተማው ሰው ይሄንን አላሣያችሁትም፤አያውቀውም፡፡ በነሱ በኩል 60 ሺህ ህዝብ ተቆጠረ እንጂ በዚያም ወገን ያለቀው ኢትዮጵያዊ ወገን ነው፡፡ የገደልነውም የተገደልነውም እኛው በኛው ነው፡፡ ይህ የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ፣ሃዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣም እየተባለ የሚቀመጥ ታሪክ ነው፡፡ ታሪካችን ይሄ ነው፡፡ ብዙ አይነት ቲዮሪዎች (ሃልዮት) ይመጣሉ፡፡ ለኛ ሃገር እንደሚስማማ ማስቀመጥ ካልቻልን፣ማንነታችንን እያጠፋን አይምሯችን የሌላ ሰው ቅኝ ግዛት ነው የሚሆነው። በአካል መገዛት አልተቻለም፤አሁን እየተገዛ ያለው አዕምሮአችን ነው። ችግሮቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት እየተቻለ፣ ወደማያስፈልግ ችግር ውስጥ እየገባን ነው፡፡  
በጥበብ አለም ህሊና፤ ቅንነትና ደግነት ትልቅ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ በሌላውም ይሄ ይመስለኛል የሚያስፈልገው፡፡ ቅንነትና ደግነት ከሌለ ሁሉም ነገር አንፃራዊ ሆኖ ነው የሚቀመጠው፡፡ ሕይወት ሁልጊዜ ጨለማና ብርሃን ነው፡፡ ብርሃን ላይ ስትሆን ጨለማው እንዳለ ማወቅ አለብህ፡፡ ጨለማው ላይ ስትሆን ደግሞ ብርሃን እንዳለ ማወቅ አለብህ፡፡ ሁለቱን አመዛዝነህ ካልያዝክ፣ምንግዜም ብርሃን ከሆነ በራሱ ጊዜ ይጠፋል፡፡ ጨለማም እንዲሁ ነው። አመዛዝኖ መያዝ ካልተቻለ አስቸጋሪ ነው ማለት ነው። በተቻለ መጠን ሠዋዊ አስተሳሰባችን አይጥፋ። ሰው ትልቁ ሃብቱ አዕምሮው ነው፡፡ በአዕምሮው ነው ብዙ ነገር ሊሰራ የሚችለው፡፡ ሃሳባችን ቅን፣ ደግ ካልሆነ፣ ሌላውን በቅንነት መመልከት አይችልም። እንደ አፄ ኃይለ ስላሴ አይነት ሰው 50 ዓመት ሙሉ ሲገዛ፣ እኔ ይበቃኛል ለልጄ ላወርስ አላለም። አሁንም ገዢ ላውርስ ካላለ፣ የሠዎችን አቤቱታ ካልሠማ፣ እንግዲህ የጥንት ሰው የምንላቸው አፄ ሚኒልክ እየበጁን ነው ማለት ነው፡፡ እሳቸው ውስጥ ያለው ደግነት ነበር ኢትዮጵያን ክብር የሠጣት፡፡
እኔ፤ ‹‹መሞት ወይም አለመኖር›› ብዬ በዘመነ ደርግ ስዕል ሰርቻለሁ፡፡ በዚያው በደርግ ዘመን ‹‹ያሸናፊው ምህረት›› የሚል ስዕል ሰርቻለሁ፡፡ አፄ ሚኒልክ ለጣሊያን ያደረጉትን ምህረት በስዕል ገልጫለሁ፡፡ እንደኔ፣ አሸናፊ የሆነ ሁሉ ማወቅ ያለበት ተሸናፊ ሆኖ ማየትን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀላሉ መንገድ፣ ዲሞክራሲ በህዝብ ድምፅ ላይ ነው ያለው ከተባለ፣ ስርአቱን የሚጠብቀው ህዝብ ነው። በኦሮሞ የገዳ ስርአት እድሜን መሠረት አድርጎ፣ ተራ እየሠጠ ስልጣንን የሚቀባበል ነው፡፡ ይህ እጅግ የበለፀገ ሃብታችን ነው፡፡ ይሄን ስርአት ምናለበት ብንቀበለውና ብንተገብረው? ሽማግሌዎች ቀጣዩን እየመረቁ ስልጣን ቢረካከብ ምናለበት? ለእኔ የሚታየኝ ይሄ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ቅንነትና ደግነት ያስፈልጋል፡፡

Read 7413 times