Sunday, 04 September 2016 00:00

ሽርፍራፊ ሰከንድ

Written by  ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(2 votes)

አባቴ የአውራ ጎዳና መሥሪያ ቤት ተቀጣሪ ነው፡፡ የሥራው ፀባይ አመቱን ሙሉ ከአዲስ አበባ  ያስወጣዋል፡፡ በዓላትን ጠብቆ ካልሆነ በቀር ወደ ቤት ዝር አይልም፡፡ የጂማ-ቴፒ መንገድ ስራ ሲጠናቀቅ አባቴም ቴፒ ላይ ከሌላ ሴት የአንድ ልጅ አባት መሆኑን አጠናቀቀ፡፡ ይህን የሰማችው እናቴም ታናሽ ወንድሜን ተስፉን ይዛ አገሯ ገባች፡፡
የቤቱ ሃላፊ አጎቴ ሆነ፡፡ እድሜውን መገመት ይከብዳል፡፡ ከተፈጠረ መከራረሙ ሃቅ ነው፡፡ እኔን ሁሌም “ቀዥቃዣ” “ክልፍል!!” እያለ ፊቱን ቁጥርጥር ያደርገዋል፡፡ ጨምዳዳ የወየበ ቆዳው፣ ዘመናት ያስቆጠረ ጥንታዊ ብራና ይመስላል - መጽሀፈ ስንክሳር ምናምን የተፃፈበት፡፡
ምሽት አጎቴ ሮንድ ሲዞር አምሽቶ በውድቅት ገባ፡፡
ወደ ጓዳ ገብቶ ሞሰቡን ድስቱን እየከፈተ አየ። የሚላስ የሚቀመስ የለም፡፡ ምናምኒት ፍርፋሪ አላስቀረሁለትም፡፡ ፊቱን ገደል አስመስሎ፡-
“እራት አላስቀረህልኝም?”
“የነበረውን በላሁት”
“መርዝ ብላ!”
አልጋ ውስጥ ቢገባም እርግማኑን አላቋረጠም። “እራስ ወዳድ ሆዳም ትውልድ ….! የስምንተኛው ሺህ መርገምቶች!”
አንድ መላጣ ፂማም ትልቅ ሰው ራት ባለመብላቱ እንዲህ ይበሳጫል ብዬ በፍጹም አልጠበኩም። በማግስቱ ተመላላሽ ሰራተኛ ቀጠረ። ደላላው፤ “አስተማማኝ ሠራተኛ” እያለ ደጋግሞ አሞካሻት። እንጀራ ስትጋግር ይህችው አስተማማኝ ሰራተኛ ትክ ብዬ አየኋት፡፡
 አንገቷ ላይ ፓውሎሲ ኳስ የሚያክል እንቅርት ተንጠልጥሏል፡፡ እንቅርቷን ስላየሁት ተበሳጭታ፡- “ምን ታፈጥብኛለህ አይን አውጣ!” ስትል አምባረቀች፡፡
ይህቺው ተመላላሽ ሠራተኛ አንዳንዴ እንደመቀናጣት ያደርጋታል፡፡ ልብስ በምታጥብ ለት ቀደም ብላ ውሃ እንድናቀራርብ፣ የተወሰኑ ልብሶችን በኦሞ ዘፍዝፈን እንድንጠብቃት ቀጭን ትዕዛዝ ትሰጠናለች፡፡ እግሯ ወጣ ከማለቱ አጐቴ፡- “አንደኛውኑ እኛው አናጥበውም እንዴ!... ነገ ደግሞ አብሲት ጥላችሁ… ምጣድ አስምታችሁ ጠብቁኝ እንዳትለን-የሚያሰማ ያስማትና…. አለሌ…. አበው የታመሰችዋ የሚሏት ዓይነት እኮ ናት…” ሲል መዓቱን ያወርድባታል፡፡
ጠዋት ከሞቀ እንቅልፌ ቀስቅሶኝ ሳሙና እንድገዛ ወደ ሱቅ ላከኝ፡፡ ወደ ያሲን ሱቅ አመራሁ፡፡ ልብስ ሰፊውን ወልዴን አልፌ ያሲን ሱቅ መዳረሻ ላይ የሚገኝ ሰፊ ግቢ ላይ ዓይኔን ጣል አደረኩ፡፡ የቀድሞ ነዋሪዎች ለቀዋል፡፡ በሩ ሁሌም እንደተከረቸመ ነው፡፡ ዛሬ ግን አንድ ልጅ የግቢውን በር ለአመል ከፈት አድርጎ፣ ወጭ ወራጁን ይመለከታል፡፡ እኔንም ሳልፍ እንደ ልዩ ፍጡር ፍጥጥ ብሎ አየኝ። አልፌው ዘወር ስል ምላሱን አወጣብኝ፡፡ ጎንበስ ብዬ ጠጠር አንስቼ ወረወርኩበት፡፡ ግንባሩን ፈነከትኩት፡፡ ወደ ውስጥ ገባ፡፡ አንዲት ሴትዮ አስከትሎ ወጣ። ከግንባሩ ደም እየፈሰሰ ነበር፡፡ ወደኔ ጠቆማት፡፡ ሴትዮዋ ዘወር ከማለቷ በሩጫ ተፈተለኩ፡፡ ማንም እንዳልተከተለኝ ሳውቅ ቆም አልኩ፡፡ ቁና! ቁና! እየተነፈስኩ ቁልቁል አማተርኩ፡፡ ሴትየዋ ልብስ ሰፊው ወልዴን እያናገረችው ነበር፡፡ ሁሉንም አይቷል፡፡ ቤቴን መጠቆሙ አይቀርም- ትክክል!.... ሴትየዋ ልጇን ይዛ እየተጣደፈች ወደ እኛ ቤት አመራች፡፡ በሩን ከፍታ ገባች፡፡
ዓይኖቼን የቤታችን በር ላይ ተክዬ ብቆይም፣ ማንም ከውስጥ የሚወጣ አልነበረም፡፡ ከተወሰነ ደቂቃ በኋላ ሴትየዋ፣ ልጁና አጎቴ ተከታትለው ወጡ፡፡ ሴትየዋ እጇን በዛቻ ታወናጭፋለች፡፡ አጎቴ እጆቹን ወደ ኋላ አጣምሮ፣ እንደ ከዘራ እጀታ አንገቱ ተቆልምሞ፣ በልምምጥ ጠብ እርግፍ ይላል።  በዚህ ሁኔታ ወደ ቤት መመለስ የማይታሰብ ነው፡፡
ቀኑን ሙሉ ላይ ታች ስባዝን ዋልኩ፡፡.…
ደንገዝገዝ ሲል ወደ ሰፈሬ አቀናሁ -ጋሽ ይልማ ቤት፡፡ ጋሽ ይልማ ጐረቤታችን ናቸው፡፡ ልጁን ከፈነከትኩበት ዕለት ጀምሮ ያለውን ውሎዬን ነገርኳቸው፡፡ ከአጐቴ ጋርም እንዲያስታርቁኝ ለመንኳቸው፡፡ ይዘውኝ ወደ ቤታችን አዘገምን፡፡ አጎቴ ኩርሲ ላይ ተቀምጧል፡፡ እርሾ እንደበዛበት ሊጥ ኩፍ ብሎ፡፡ ጋሽ ይልማን ሰላም ብሎ እኔን በሚገሸልጥ ግልምጫ የጐሪጥ እያየኝ፡- “ጉድ ነው! ብለህ ብለህ የባለስልጣን ልጅ ፈነከትክ! ሚስቱ ደንፍታብኝ ነው የሄደችው፤ ካድሬውም መምጣቱ አይቀርም” ሲል የነገር መዓቱን እንደ ዶፍ አወረደው፡፡
ጋሽ ይልማ፡- “ካድሬ ተብዬ ሰውየው ማን ነው?”
አጎቴ፡- “በቀለ አሰፋ”
ጋሽ ይልማ ከአፉ ቀበል አድርገው፡- “በቀለ አሰፋ! ባለፈው ኢህአፓ ተኩሳ የሳተችው”
አጎቴ እራሱን በአዎንታ ነቀነቀ፡፡
“እውነትም ጉድ ነው፤ ከጉድም ጉድ!” ጋሸ ይልማ መቅሰፍት እንደወረደባቸው ክው ብለው ደነገጡ፡፡ ለአፍታም መቆየት አልፈለጉም፡፡ “በል ልጆቼን ላሳድግበት” ብለው ከግቢው በፍጥነት ወጡ - ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ፍጥነት፡፡ ለአፍታም ዞር አላሉም፤እንደ ሎጥ ሚስት የጨው አምድ ሆነው የሚቀሩ ይመስል፡፡
አጎቴ መድረክ ላይ እንዳለ ተዋናይ በረንዳው ላይ እየተንጎራደደ፡- “በጠጠር ግንባሩን ፈነከትከው….ህም! ካድሬው ደግሞ በጥይት ግንባርህን ይበረቅስልሃል…. የእኔንም ጭምር… እናም በቀጥታ…. ወደ ሞት ዋሻ!”
ሰውየው ከአሁን አሁን መጣብን በሚል ስጋት እየተሸማቀቅኩ፣ ሶፋው ላይ በተቀመጥኩበት እንቅልፍ ጭልጥ አድርጎ ወሰደኝ፡፡….
የውጪው በር በሃይል ሲደበደብ ሰምቼ ከእንቅልፌ ነቃሁ፡፡ የማለዳ ጮራ በበሩ ሰርጋ ገብታለች፡፡ አጎቴን ቀስቀስኩት፡፡ በተደጋጋሚ በሩ በሃይል ተደበደበ፡፡ አጎቴ ሱሪውን ለማድረግ ፋታ አጥቶ በጀምስ ሙታንት ብቻ ወደ መስኮቱ ተጠጋ። መጋረጃውን ገለጥ አድርጎ ወደ በሩ አማተረ፡፡
እኔም፡፡
አንድ እጅ በአጥሩ ሾልኮ የአጥሩን መቀርቀሪያ ከፈተው፡፡ በሩም ብርግድ ብሎ ተከፈተ፡፡….ቀይ…. ረጅም ጎልማሳ፣ ልጁን አስከትሎ ገባ፡፡ ልጁ ግንባር ላይ ፕላስተር ተለጥፏል፡፡ አጎቴ “ካድሬው!” ብሎ በድንጋጤ ላብ በላብ ሆነ፡፡ ከመላጣው ላይ ጭስ መሰል እንፋሎት እየተነነ ነበር፡፡
“ይቅር በሉኝ ብለህ እግሩ ላይ ውደቅ… ህይወትህን አድን - የኔንም” ብሎ ወደ ጓዳ ገብቶ ተደበቀ….
ካድሬው ወደ ሳሎን ሰተት ብሎ ገባ - ከእነ ልጁ፡፡
“አንተ ነህ ልጄን የፈነከትከው?” ሲል ጠየቀኝ፡፡
“አ..አ…አ..አዎ” ስል ተንተፋተፍኩ፡፡
“አባትህን ጥራው”
“የለም”
“እናትህን ጥራት”
“ከአባቴ ጋር ተጣልታ አገሯ ገብታለች”
“ያሳዝናል ግን ለምንድን ነው የፈነከትከው!?”
“ምላሱን ስላወጣብኝ” ወደ ልጁ ዘወር ብሎ፤ “ብሩክ፤ ምላስክን አውጥተህበት ነው እንዴ?” ሲል በጥያቄ አፋጠጠው፡፡ ልጁም እየተቅለሰለሰ በአዎንታ ራሱን ነቀነቀ፡፡ ሰውየው ከንዴቱ ሰከን አለ፡፡
ሶፋው ላይ ዘና ብሎ ተቀምጦ፤ “ብሩክ! ሰው ላይ ምላስ ማውጣት ነውር ነው! ለመሆኑ ከማን ተማርከው?“ የልጁን ምላሽ ሳይጠብቅ፤“ምርጥ ማስታወሻ ነው የሰጠህ…. እንደ ፕላምዶ ፕላስተር ለጥፈህ ማሞ ቂሎን መስለሃል” አለውና ከት ብሎ ሳቀ፡፡
“በል ይቅርታ ጠይቀው” ሲል ልጁን አዘዘው። ብሩክ ወደ እኔ ራመድ ባለበት ፋታ … በዚያች የተረገመች ሽርፍራፊ ሰከንድ፣ አጎቴ የነተበ ስስ ካኒቴራና ጀምስ ፓንት ብቻ እንዳደረገ አስፈሪ ጭራቅ መስሎ… ሰውየው እግር ላይ ለመውደቅ ሲንደረደር ከመቅጽበት ሽጉጡን መዞ ግንባሩ ላይ ተኮሰበት፡፡ አጎቴ ወለሉ ላይ ፍግም አለ፡፡
“ማነው?!” ብሎ ሰውየው ሲጠይቀኝ….ከገባሁበት የቅዠት ዓለም ብንን ብዬ፡-
“አጎቴ ነው ይቅርታ ሊጠይቅ… እግርዎት ላይ ሊወድቅ---” እምባዬ ኩልል ብሎ ፈሰሰ፡፡ የሰውየው ቀይ ፊት በአንዴ ገርጥቶ አመድ ሆነ፡፡ ጣእረ ሞት መሰለ፡፡
“በእያንዳንዷ እርምጃ…ደም! ደም! የኢህአፓ ፎቢያ… በልጀ ፊት ደም ላፍስ?!” ብሎ ሳግ እየተናነቀው ምርር ብሎ አነባ፡፡……
“በሉ ልጆች በፍጥነት ውጡ”
ወጣን፡፡
እግራችን ከመውጣቱ፣ ግቢውን ያናወጠ ተኩስ እንደ ነጎድጓድ አስተጋባ…..

Read 1213 times