Sunday, 04 September 2016 00:00

በአትሌቲክሳችን የባለድርሻ አካላት ውዝግብ፤ ትንቅንቅና ምስቅልቅል በዝቷል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 የ31ኛው ኦሎምፒያድ ክለሳ
በ31ኛው ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያ በ3 የስፖርት አይነቶች 35 ኦሎምፒያኖችን ያሳተፈች ሲሆን፤  1 የወርቅ፤ 2 የብር እንዲሁም 5 የነሐስ ሜዳልያዎች ተገኝተዋል። የሜዳልያ ስብስቡ  ኢትዮጵያን ከ207 አገራት በ44ኛ ደረጃ ከአፍሪካ ደግሞ በ3ኛ ደረጃ  ያስቀመጣት ነበር። ከሜዳልያ ውጤቶቹ  በአልማዝ አያና በ10ሺ ሜትር የተገኘው ብቸኛ የወርቅ ሜዳልያ በኦሎምፒኩ መድረክ የኢትዮጵያ ብሄራዊ መዝሙር ተዘምሮ ባንዲራ የተሰቀለበት ከፍተኛው ውጤት ነበር፡፡  ሁለቱን የብር ሜዳልያዎች ደግሞ ፈይሳ ሌሊሳ በማራቶን እንዲሁም ገንዘቤ ዲባባ በ1500 ሜትር አስመዝግገበዋል፡፡
5ቱ የነሐስ ሜዳልያዎች ጥሩነሽ ዲባባ በ10ሺ ሜትር፤ አልማዝ አያና በ5ሺ ሜትር፤  ማሬ ዲባባ በማራቶን፤  ሃጎስ ገብረህይወት በ5ሺ ሜትር እንዲሁም ታምራት ቶላ በ10ሺ ሜትር የተጎናፀፏቸው ናቸው። ከ31ኛው ኦሎምፒያድ በኋላ በ13 ኦሎምፒያዶች ለመሳተፍ የበቃችው ኢትዮጵያ በአጠቃላይ የሰበሰበቻቸው ሜዳልያዎች ብዛት 53 የደረሰ ሲሆን 22 የወርቅ፤ 9 የብር እና 22 የነሐስ ሜዳልያዎች ሆነው ተመዝግበዋል፡፡ በሌላ በኩል በ2016 የሪዮ አሎምፒክ ከሜዳልያ ውጭ ከ4 እስከ 8ኛ ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች በሚሰጠው የኦሎምፒክ ዲፕሎማ ደግሞ 6 ኦሎምፒያኖች ተሸላሚ ነበሩ፡፡ በወንዶች 10ሺ ሜትር በ4ኛ ደረጃ ይገረም ደመላሽ፤ በሴቶች 1500 ሜትር  በ8ኛ ደረጃ ዳዊት ስዩም፤ በሴቶች 5000 ሜትር በ5ኛ ደረጃ ሰንበሬ ተፈሪ፤ በሴቶች10ሺ ሜትር  በ8ኛ ደረጃ ገለቴ ቡርቃ፤ በሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክል  በ5ኛ ደረጃ ሶፍያ አሰፋ እንዲሁም በሴቶች ማራቶን  በ4ኛ ደረጃ ትርፌ ፀጋዬ ናቸው፡፡ በሌሎች ተሳትፎዎች ሲሆኑ በወንዶች 5ሺ ሜትር  ደጀን ገብረመስቀል 12ኛ ደረጃ፤ በወንዶች 10ሺ ሜትር  አባዲ ሃዲስ 15ኛ ደረጃ፤ በሴቶች 1500 ሜትር  በሱ ሳዶ 9ኛ ደረጃ፤ በሴቶች 5000 ሜትር  አባቤል የሻነህ 14ኛ ደረጃ፤ በሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክል  እቴነሽ ዲሮ 15ኛ ደረጃ አስመዝግበዋል። በወንዶች 800 ሜትር መሃመድ አማን እና በወንዶች 1500 ሜትር የተሳተፉት መኮንን ገብረመድህንና ዳዊት ወልዴ ፤ በሴቶች 800 ሜትር  ሃብታም አለሙ በግማሽ ፍፃሜ ወድቀዋል፡፡ በወንዶች 1500 ሜትር  አማን ወጤ አለመሳተፉ፤ በወንዶች 5ሺ ሜትር  የሙክታር ኢድሪስ ውጤት መሰረዙ፤  በወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል  ሃይለማርያም አማረ፤ ጫላ ባዬና ታፈሰ ሰቦቃ እንዲሁም በሴቶች 800 ሜትር  ትግስት አሰፋና ጉድፍ ፀጋዬ በመጀመርያ ዙር ማጣርያ መውደቃቸው፤ በሴቶች 3ሺ መሰናክል  ህይወት አያሌው ለፍፃሜ አለማለፏ እንዲሁም በሴቶች ማራቶን ትግስት ቱፋ አቋርጣ መውጣቷም ይጠቀሳሉ፡፡ በ20 ኪሎሜትር የርምጃ ውድድር አስካለ ቲኪሳ 61ኛ ደረጃ ስታገኝ የኋላዬ በለጠ በቴክኒክ ችግር ከውድድሩ ውጭ ሆናለች፡፡ ከአትሌቲክስ ውድድሮች ባሻገር በሌሎች ሁለት ስፖርቶች በብስክሌት የጎዳና ውድድር ፅጋቡ ገብረማርያም ውድድሩን አልጨረሰም። በዋና ውድድድር ደግሞ በ100 ሜትር ነፃ ቀዘፋ ሮቤል ኪሮስ 59ኛ እንዲሁም በሴቶች 50 ሜትር ነፃ ቀዘፋ 75ኛ ደረጃ ነበራቸው፡፡
ኢትዮጵያ በ31ኛው ኦሎምፒያድ  ያስመዘገበችው ውጤት ካለፉት 5 ኦሎምፒያዶች በወርቅ ብዛት ያነሰ ነው። በ1992 እኤአ ላይ በባርሴሎና ኦሎምፒክ በ1 የወርቅ ሜዳልያ ከነበረው ተሳትፎ ጋርም ተነፃፅሯል፡፡ የኦሎምፒክ ተሳትፎው የተያዘ እቅድ ያልተሳካበት፤ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የተሰጡ ግምቶች የተፋለሱበት፤ በታሪካዊ እና አነጋጋሪ አጀንዳዎች የተውተበተበ ነበር፡፡ በተለይ ያልተሳካው የሜዳልያ እቅድ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሲሆን 4 የወርቅ፣ 4 የብርና 4 የነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን ለማስመዝገብ ከኦሎምፒኩ 8 ወራት በፊት በይፋ ተነግሮ የነበረ ነው፡፡ በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት የተሰሩ ትንበያዎች እና የውጤት ግምቶችም ያልተሳኩበትን ተሳትፎ ኢትዮጵያ እንደነበራትም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ኦሎምፒክ ፕሪዲክሽን በተባለ  ድረገፅ  3 የወርቅ፤ 3 የብርና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች በአጠቃላይ 8 የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች  እንደምትሰበሰብ  ተገምቶ ከዓለም 26ኛ ደረጃ በማግኘት  እንደምትጨርስ መገለፁ፤    ኢንፎስትራዳ በተባለው የስፖርት አሃዛዊ መረጃዎች አቀናባሪ ድረገፅ ደግሞ በአጠቃላይ  10 ሜዳልያዎች 3 የወርቅ 3 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያ ተተንብዮላት የነበረ ቢሆንም የተመዘገበው ውጤት ከእነዚህ ቅድሚያ ግምቶች ጋር በፍፁም አልተገናኘም፡፡
በ31ኛው ኦሎምፒያድ የኢትዮጵያ ተሳትፎ አንድ ትልቅ ታሪክ የሠራችው “በጣም ጎበዝ” የተባለችው ወርቃማ ኦሎምፒያን አልማዝ አያና ያስመዘገበችው ነው፡፡ በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ስትጎናፀፍ የዓለም እና የኦሎምፒክ ሪከርድ በማስመዝገብ ሲሆን በ5ሺ ተጨማሪ የነሐስ ሜዳልያ አግኝታለች፡፡ አልማዝ በ10ሺ ሜትር ያስመዘገበችው አዲስ የዓለምና የኦሎምፒክ ሪከርድ  29 ደቂቃዎች ከ17.45 ሰከንዶች ሲሆን ለ23 ዓመታት ሳይሰበር የቆየ ክብረወሰን በ14 ሰኮንዶች አሻሽላዋለች።  በሌላ በኩል 4ኛዋን ኦሎምፒክ የተሳተፈችው ጥሩነሽ ዲባባ በ5ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ በማግኘቷ የምንግዜም ውጤታማዋ የኢትዮጵያ ኦሎምፒያን ለመሆን በቅታለች። ጥሩነሽ  በ4 ኦሎምፒኮች በ10 ሺ ሜትር ሁለት የወርቅና አንድ የነሐስ፤ እንዲሁም በ5 ሺ ሜትር አንድ የወርቅና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎች በመጎናፀፍ ነው፡፡ ባሳየችው አስገራሚ የፅናት ተጋድሎ አድናቆት ያተረፈችው ኦሎምፒያን እቴነሽ ዲሮም ሌላዋ ባለታሪክ ነበረች፡፡ በሴቶች ሶስት ሺ ሜትር መሰናክል የማጣርያ ውድድር የአንድ እግር ጫማዋ ወልቆባት አስገራሚ ፅናት በማሳየት ውድድሯን በ7ኛ ደረጃ የጨረሰችው እቴነሽ፤ በበርካታ የዓለም ሚዲያዎች ለመደነቅ በቅታለች፡፡
ከላይ ከተገለፁት የሜዳልያ፤ የዲፕሎማ፤ የተሳትፎ ውጤቶች እና ከዚያም ካጋጠሙት አዳዲስ ታሪኮች ባሻገር በ31ኛው ኦሎምፒያድ የመክፈቻና የመዝጊያ ስነስርዓቶችም ከኢትዮጵያ ተሳትፎ ጋር በተያያዘ ሁለት አወዛጋቢ ክስተቶችም ነበሩ፡፡ የመጀመርያው በመክፈቻው ስነስርዓት ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ ካነገበው ዋናተኛ ሮቤል ኪሮስ ጋር በተያያዘ የተፈጠሩት አወዛጋቢ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ ሮቤል ኪሮስ በርካታ ታዋቂ አትሌቶች ባሉባት አገር ባንዲራ ይዞ ለመሰለፍ የተመረጠበት ሁኔታ ለብዙዎች አስደሳች አልነበረም፡፡ ለነገሩ ከመጀመርያው የብስክሌት ኦሎምፒያን የነበረው ፅጋቡ ገብረማርያም ባንዲራውን ይዞ እንደሚሰለፍ ተገልፆ ከዚያም መቀየሩ ሌላው ያልተጠበቀ ነገር ነበር፡፡ የባንዲራ ተሸካሚነት ብቻ ግን አልነበረም፡፡ ሮቤል ኪሮስ በተሳተፈበት የ100 ሜትር ነፃ ቀዘፋ የውሃ ዋና ውድድር የተሟላ ብቃት ባለማሳየቱ በከፍተኛ ደረጃ ያወዛገበ ነበር። ሮቤል ለውሃ ዋና ብቁ ስፖርትኛ አለመሆኑ በከፍተኛ ደረጃ ከመተቸቱም በላይ ቦርጫም እና አሳነባሪው ዋናተኛ በሚል በተለያዩ ሃተታዎች ተነቅፏል፡፡ ከሁሉም አስገራሚ የሆነው እና በአወዛጋቢነት እና ልዩ የታሪክ ተሳትፎ በመሆን የሚጠቀሰው  በ31ኛው ኦሎምፒያድ የመዝጊያ ውድድር በነበረው የወንዶች ማራቶን ላይ በመሳተፍ የብር ሜዳልያ ለመጎናፀፍ የበቃው ፈይሳ ሌሊሳ  ያልተጠበቀ  አጨራረስ ነው፡፡ አትሌቱ ውድድሩን ባልተጠበቀ ሁኔታ የተቃውሞ ተግባር በማሳየት መጨረሱ፤ ከዚያም በኋላ በሰጣቸው መግለጫዎች ይህን አቋሙን በማንፀባረቁ እስካሁን እያነጋገረ ይገኛል፡፡
ከ31ኛው ኦሎምፒያድ በፊት የተነሣው ውይይት
በሪዮ ዲጄኔሮ የተካሄደው 31ኛው ኦሎምፒያድ ከመጀመሩ 3 ወራት በፊት ታላላቅ የቀድሞ አትሌቶች እና አሰልጣኞች ከአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ጋር ውይይታቸውን ጀምረው ነበር፡፡ በግንቦት ወር ላይ ለአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት እንዲሁም በግልባጭ  ለኢፌድሪ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር እና ለኦሎምፒክ ኮሚቴ የቀድሞ ታላላቅ አትሌቶች እና አሰልጣኞች ባቋቋሙት ኮሚቴ ‹‹በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን አሰራር እና በሪዮ ኦሎምፒክ ዝግጅት›› ዙርያ በደብዳቤ አመልክተዋል።  በቀድሞ ታዋቂና ታላላቅ አትሌቶች እና አሰልጣኞች የተቋቋመው ጊዜያዊ ኮሚቴ ላይ  ስማቸው የተጠቀሱት የሚከተሉት ሲሆኑ፤  አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ በሰብሳቢነት  እንዲሁም በአባልነት ደግሞ ከአትሌቶች ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም፤  ገዛኸኝ አበራ፤  ቀነኒሳ በቀለ፤  አሰፋ መዝገቡ፤ የማነ ጸጋዬ፤  አሰለፈች መርጊያ ፤  ፋንቱ ሚጌሶ ሲሆኑ ከአሰልጣኞች ኮማንደር አበበ መኮነን፤ ሻምበል ቶሎሣ ቆቱ እና ዳዊት ዘርጋው ናቸው፡፡
የአትሌቶች ጊዚያዊ ኮሚቴ የመጀመርያዎቹ ውይይቶች
‹‹… ወርቃማ የአትሌቲክስ ታሪካችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለና ወደ አስከፊ መንገድ እየተጓዘ መገኘቱ አሳስቦናል ብለው ህብረት የፈጠሩት አትሌቶች ‹‹አትሌቲክስ ምልክታችን ነው፣ አስፈላጊውን ሞያዊና ቴክኒካዊ ድጋፍ ለመስጠት ለአትሌቲክሱ ከአትሌቱ የቀረበ ማንም ባለጉዳይ ሊኖር አይችልም›› በማለት ካንዴም ሁለቴ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይተው ነበር፡፡ በወቅቱ ከተነሱት የመወያያ አጀንዳዎቹ መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ነበሩ፡፡
ሀገራችን ከራሽያና ኬንያ ቀጥላ በአበረታች መድሃኒት መጠርጠርዋን ተከትሎ በአትሌቶቻችን ላይ ሊመጣ የሚችል አደጋን እንዴት እንቅረፍ የሚልና በጉዳዩ ላይ እንዴት አንድ ሀገራዊና የጠራ የጋራ ሀሳብ መያዝ እንችላለን፡፡
በፌዴሬሽኑ እየተተገበረ ያለው የስልጠና ሂደት አለም የደረሰበትንና ጊዜው የሚጠይቀውን ማለትም በሳይንስ በብቁ ባለሞያ የታገዘ ስልጠና ለአትሌቱ እየተሰጠ አይደለም፡፡ ስለዚህ በቀጣይ የስልጠናው ሂደት በተመለከተ ከተለያዩ አካላት ጋር በግልፅ በመመካከርና በመደጋገፍ ዘመኑ ከሚፈልገው በተጨማሪ ተቃራኒቻችንን ለማሸነፍና የማያቋርጥ ድል ለማስመዝገብ የሚያስችል እንዲሆን ምን ማድረግ አለብን፡፡
አሁን ባለው ደረጃ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጽ/ቤት በአግባቡ ስራን ቆጥሮ መስጠትና ቆጥሮ መቀበል ላይ ክፍተት ስላለበት የጽ/ቤት ጉዳይ ለሞያው ተቀራራቢ የሚሆንና በስሩ ያሉትን በአግባቡ የሚመራ ስላልሆነ በዚህ ረገድ ውሳኔ ሊሰጥ ይገባል
የጥላ ፎቁ ምክክርና የአቋም መግለጫ
ከላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተደረጉ ውይይቶች ነገሮቹን ወደሌላ የውዝግብ ምዕራፍ መክተት ሲጀምሩ በተለይ የማራቶን ቡድኖች ምርጫ በከፍተኛ ደረጃ ባወዛገበበት ሰሞን ሌላ ክስተት አጋጠመ፡፡ ይህም ታዋቂ የቀድሞ ታላላቅ አትሌቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ያገባናል በሚል ተነሳሽነት ግንቦት 30 ቀን 2008 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ጥላፎቅ ያደረጉት  ሰፊ ምክክር ነበር፡፡ የምክክሩ ዋነኛ አላማም አትሌቲክሱ እንዴት ወደተሻለ ደረጃ ይድረስ በሚል የሚጠቃለል ሲሆን በተለይም፡- ፌዴሬሽኑ በገንዘብ የተሻለ አቅም እንዲኖረው ማድረግ፤ በተወዳዳሪነት የሚቀርብ ፌዴሬሽን ማድረግ፤ ሙያተኛን የሚያሳትፍ ፌዴሬሽን ማድረግ እንዲሁም ሁሉንም አትሌት በአንድ ሜዳ ላይ የሚሰበስብና የሚያሳትፍ ፌዴሬሽን ከማድረግ አንጻር ምን መሰራት አለበት በሚሉ አጀንዳዎች ያተኮረ ነበር። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ዋና ዋና ጉዳዮች እንዳይቀረፉ እንቅፋት በሆነውና በጊዜያዊነትም ሆነ በረዥም ጊዜ የመጡ ፈተናዎች ላይ ምን ዓይነት አቅጣጫ መከተል ይገባል በሚሉ ነጥቦች ላይ በስፋት ውይይት በተደረገበት በዚህ ምክክር መድረክ አትሌቶችና አሰልጣኞች የጋራ ሀሳብ የያዙባቸው የመወያያ አጀንዳዎች ነበሩ፡፡ በሪዮ ኦሎምፒክ ላይ የተመረጡ አትሌቶች በስልጠናና በስነ - ልቦና ረገድ እንዲሁም ባለው መወዛገብ ምክንያት ከተለያዩ ጫናዎች ነፃ እንዲሆኑን ሀገራዊ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ማስቻል በሚለው ነጥብ ላይ የጋራ ሃሳብ መያዛቸው የመጀመርያው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሙያም ሆነ በአስተዳደራዊ ብቃት ላይ ስላሆነ አትሌቱን በአግባቡ ማገልገል ስላልቻለ የያዘውን ኃላፊነት ለአትሌቱ የሚያስረክብበት ሁኔታ እንዴት መፍጠር ይቻላል በሚል ነጥብ ላይ መወያየት እንደሚያስፈልግ፤ የአትሌቶች ማኅበር ከወከለው አካል ይልቅ ለፌዴሬሽኑ ውግንና ይዟል የሚሉ መላምቶች በመኖራቸው በቀጣይ የማህበሩ ህልውና ላይ መግባባት እንደሚገባ ፤ ፌደሬሽኑ በአቅምም ሆነ በገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ ስላለ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ የጋራ ውሳኔ ማሳለፉ ግድ እንደሚል እና የአትሌቲክስ ሩጫ ከድሮው ጋር ሲነጻጸር በውጤት ደረጃው እያሽቆለቆለ በመምጣቱ ሁሉም አትሌት አምኖበትና የጋራ ሀሳብ ይዞ እንዴት ወደቀድሞው ውጤታማነት መመለስ ይቻላል የሚሉት አጀንዳዎች ዋና ዋናዎቹ ነበሩ፡፡  

ከ31ኛው ኦሎምፒያድ በኋላ
የአትሌቶቹ ጊዚያዊ ኮሚቴ መግለጫ
ከሪዮ ኦሎምፒክ ማግስት በአትሌቶች ጊዚያዊ ኮሚቴ በተሰጠው መግለጫ ላይ የተገኙ ከ50 በላይ የመንግስት እና የግል መገናኛ ብዙሃናት በመሆናቸው መግለጫውን በአጋፋሪነት በመሩት አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እና አትሌት ገብረ እግዚ አብሄር ገብረማርያም ‹‹ሁላችንም በአንድ አይነት ስሜት የምንዘምርለት፤ የምንኮራበት የአትሌቲክሳችን ጉዳይ ነው›› የሚለው ስሜት ተንፀባርቋል፡፡  ከ70 በላይ የቀድሞ አትሌቶችና አሰልጣኞች የወከለውን ኮሚቴ በምግለጫው ይዘው የቀረቡት ታላላቆቹ የቀድሞ አትሌቶች ኃይሌ ገብረስላሴ፤ ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም፤ እና ገዛሐኝ አበራ እንዲሁም የቀድሞ የ10ሺ እና 5ሺ እንዲሁም የማራቶን አሰልጣኞች ሻምበል ቶሎሳ ቆቱና ሻምበል አበበ መኮንን ናቸው፡፡
አትሌቶችን ወክለን የተገኘነው ስለ አትሌቲካሳችን ያለፈውን እና የወደፊቱን አሰመልከቶ የስራ እቅዳችንን ለማቅረብ መሆኑን በማስታወቅም፤ ሌላ ምንም አለማ የለንም እከሌን ለማውረድ እከሌን ለመወንጀል አይደለም በሚል ተናግረዋል፡፡ ኮሚቴው ሲንቀሳቀስ  8 ወራት አልፈዋል፡፡ የሚያነሷቸው ጉዳዮች የፌደሬሽኑ አሰራር፤ የዶፒንግ ሁኔታዎች፤ የአትሌቶችአሰለጣጠንና ምልመላ፤ የፌደሬሽኑ የፋይናንስ አሰራር ዋናዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ተገቢ ምላሽ ካገኙ ስፖርቱን መታደግ ይቻላል የሚል እምነት አላቸው፡፡
‹‹ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት ዘርፍ እያስመዘገበች ያለችው ውጤት አስቆጭቶናል። አትሌቲክሱን ስፖርቱን በሚያውቅና ውጤታማ በሚሆን አመራር መደራጀት ይገባዋል፡፡›› ‹‹ተገቢውን ምላሽ የማናገኝ ከሆነ ግን ጉዳዩን እስከ ዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ለማቅረብ እንገደዳለን፡፡››
አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ
‹‹ሩጫ ሩጫ ነው፡፡ ኃይማኖት የለውም ብሄር የለውም ችሎታ ነው፡፡ ያንን ችሎታ ለማምጣት መሰራት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡››
‹‹በአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ፅህፈት ቤት በኩል ብዙ ጉዳዮች ይመጣሉ፡፡ አሁን ያሉት የፅህፈት ቤት ሃላፊ ለስፖርቱ ያላቸው እውቀት እና በዓለም አቀፋዊ ግንኙነታቸው ደካማ ናቸው፡፡ በዚህ ሳቢያም ብዙ ችግሮች እየተፈጠሩ ናቸው፡፡ ፅህፈት ቤቱ በዶፒንግ ዙርያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ ባለመስራቱ፤ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች አፋጣኝ መልሶች ባለመስጠቱ አትሌቶችን መስዕዋትነት አስከፍሏል። ድሮ ዋዳ እና አይኤኤኤፍ በራሳቸው ወጭ አገር ድረስ እየመጡ ምርመራና ክትትል ያደርጉ ነበር። ዛሬ ግን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ከእንግዲህ ይህን ያህል አትሌት ይህን ያህል ጊዜ በራስ ወጭ አስመርምር ተባለ፡፡  በዶፒንግ ምርምራ ለአንድ አትሌት 400 ዶላር መውጣት ግዳጅ ሆኗል፡፡ በተጨማሪም ከዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የተገኘውን እስከ 100ሺ ዶላር የሚደርስ ድጋፍ ተገቢውን የስራ እቅድ ፅህፈት ቤቱ ባለማቅረቡ ማግኘት ሳይቻል ቀርቷል። በፅህፈት ቤቱ ደካማ አሰራሩር የመጣ ነው፡፡…. ‹‹ስለዚህም ስፖርቱን የሚያውቅ፤ በስፖርቱ ያለፈ ይምራው ብለን ነው የምንሟገተው ለዚህ ነው፡፡ የእውቀት ችግር አለብን፡፡››
‹‹ለኦሎምፒኩ ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቷል፡፡ ህንፃ የሰራ ሆቴል የገዛ ፌደሬሽን ቢሆንም በገንዘብ አወጣጡ ላይ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡››
‹‹በኦሎምፒክ መድረክ ባንዲራ ይዞ በሄደው ሰው ጥፋት ተሰርቷል፡፡ ትልቅ ስፖርተኞች መያዝ አለባቸው የሚለውን ፊሎሶፊ ከእውቀት ማነስ የተነሳ አበላሽተውታል፡፡ ከዋናተኛው ሮቤል ኪሮስ ይልቅ ቀነኒሳ ቢሆን ኖሮ ፤ በሮቤል ሳቢያ ኢትዮጵያ አለፈች ብቻ ነው የተባለው፡፡››
አትሌት ገዛሐኝ አበራ
‹‹በፊት እኛ በምንሮጥበት ጊዜ ችግሮች ነበሩ። እንደዚያም ሆኖ የተሻለ ውጤት ይመጣ ነበር።በአሁኑ ወቅት ነገሮች በተሻለ መልኩ ተሟልተው ዝቅተኛ ውጤት መጥቷል›› ብሏል።
‹‹አትሌቲክሱ ቤታችን ነው። አትሌቲክሱን ከውድቀት ለመታደግ  እንጂ፤ ገንዘብና ሥልጣን ከመፈለግ አይደለም’’ ሲልም የኮሚቴውን ፍላጎት ገልጿል።››
‹‹በሪዮ ለጠፋው ውጤት ህዝቡን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ …ብዙ ዓመት ሮጠናል አሁን ከምንሰራቸው ኢንቨስተመንቶች በተጓዳኝ መስራት እንፈልጋለን፡፡››
አሰልጣኝ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ
‹‹በሲድኒና በአቴንስ ኦሎምፒኮች ብዙ ድል አስገኝተናል፡፡ ውጤት ያገኘነው ሰርተን ነው፡፡ አባረሩኝ ውጥ አገር ሰርቼ ስመለስ እና ልስራ ስል አልፈለጉም። ዋናው ነገር ስልጠናው ሙሉ ለሙሉ የተበላሸ ነው። የብሄራዊ ቡድን  አሰልጣኞች እና አትሌቶች ብዙም አይገናኙም፡፡ አትሌቶች ተበታትነው የሚሰሩት፡፡  ባለን እውቀት እንስራ እንርዳቸው ስንል ፍፁም እምቢተኞች ሆነውብናል ፡፡ አታስፈልጉም ነው የተባልነው ፡፡ አሁን በብሄራዊ ቡድን ያሉት አሰልጣኞች በክለብ ደረጃም የተሳካላቸው አይደሉም፡፡ አሰልጣኞቹ ከእኛ ስር የነበሩ ጁኒዬሮች ናቸው፡፡ በአትሌቶች እና በውጤታቸው ላይ ሃላፊነት ወስደው እየሰሩ አይደለም፡፡  …..››፡፡ ‹‹በመስራት ላይ የሚገኙት አሰልጣኞች የአይኤኤኤፍ ላይሰንስ ያገኙ አይደሉም፡፡ መንግስት ካላስተካከለው ውጤቱ የባሰ የወረደ ይሄዳል፡፡››
‹‹በአትሌቲክስ ፕሮጀክቶች እየሰራን ነው ተብሎ በተደጋጋሚ ቢገለፅም፤ በአጋጣሚ ከሚገኙ አትሌቶች በቀር በቂ ተተኪዎች እያፈራን አይደለም።››
‹‹የአዲዳስ እና ሌሎች ድጋፎች ውጤትን መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ውጤት የማይገኝ ከሆነ ገንዘብ  የማግኘት እድሉ እየጠበበ ይመጣል፡፡››
ሻምበል አበበ መኮንን
‹‹በማራቶን ከሯጭነት ጀምሮ ከዚያም በአሰልጣኝነት  ረጅም ዓመት ሰርቻለሁ፡፡ ከፌደሬሽኑ የተባረርኩት መግባባት ባለመቻሌ ነው፡፡ የአትሌቲክስ ስልጠናው ትክክል አይደለም ብዬ በመከራከሬ ነው፡፡ በኦሎምፒክ ዝግጅት ወቅት አትሌቶች ለ3 እና 4 ወራት ካምፕ ገብተው መስራት ነበረባቸው፡፡ ፌደሬሽኑ ፤ አሰልጣኞች እና አትሌቶች ይህን ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ግን ውጤት ተበላሽቷል፡፡ ለምሳሌ ማራቶን በሶስት ቦታ ተሰርቶ ውጤቱ ይምጣል ብሎ መጠበቅ የማይታመን ነው፡፡ ዶክተር ወልደመስቀል በአንድ ላይ ሰባስበው በማሰራት ያስመዘገቡትን ውጤት መጥቀስ ይቻላል። አትሌቶች በራሳቸው ጥረት እንጅ በፌደሬሽኑ ውጤት ለማምጣት ምንም አይነት እገዛ አይደለም፡፡ መስፈርቶች ግልፅ ባለመሆናቸው እና የማያሳምኑ በመሆናቸው የአትሌቶች አመላመል ከፋፋይ ነው፡፡ የምልመላ መስፈርቶች የወጡት አትሌቶች ከሮጡ በኋላ በመሆኑ አትሌቶችን ከፋፈለ የምልመላ መስፈርቶች የወጡት አትሌቶች ከሮጡ በኋላ በመሆኑ አትሌቶችን ከፋፈለ፡፡ በኦሎምፒክ ውድድሩ ላይ አትሌቶች ምንም አይነት መተጋገዝ አላሰሳዩም ከባድ ችግር ነው፡፡የቡድን ስራ ብሎ ነገር የለም፡፡ ለአገር አንድ ዓላማ ይዞ ተደራጅቶ ካልተሰራ ጥሩ ውጤት አይመጣም፡፡ ትልቅ ችግሮች ያሉት በስልጠና እና  በአትሌቶች ምርጫ ነው፡፡››
አትሌት ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም
‹‹የተሰባሰብነው በብሶት ብቻ አይደለም፡፡ በቅን አመለካከት ነው፡፡ ቅንንት ነው ይዘን የመጣነው ስንል ለአፀፋዊ ምላሽ የሚነሱ ከሆነ ተገቢ አይደለም፡፡ የስፖርት ባህርይ ነፃነት ነው፡፡ በተሻለ ስልጠና እና ቴክኒክ እንስራ ነው የምንለው፡፡ቤቱ የኛ ነው፡፡ ለማፅናት እና ለመገንባት እንጅ ለማፍረስ አልመጣንም፡፡  ሙያ ላይ ስንሰለፍ ደጋፊ አንፈልግም፡፡ ደጋፊ ሙያችን ነው፡፡ ስፖርት በስፖርትና በስፖርተኛ ባህርይ መመራት አለበት፡፡ በአትሌቲክሱ ችግሮች እየበዙ መጥተዋል፡፡››
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን
ፌደሬሽኑ  ባዘጋጀው መግለጫ ላይ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ አለባቸው ንጉሴ፤ ፀሃፊው አቶ ቢልልኝ መቆያ፤ ምክትል ፕሬዝዳንቶቹ ዶክተር በዛብህ ወልዴ እና ዶክተር እንጂነር መለሰ ፀጋዬ እንዲሁም የኦሎምፒክ ቡድኑ እና የብሄራዊ ቡድኑ ሁሉም አሰልጣኞች ናቸው፡፡
ይሄው የፌደሬሽን ስራ አስፈፃሚ መግለጫ  በአትሌቶች ጊዜያዊ ኮሚቴ በ1 ሳምንት ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ ይጠራ የሚለውን ጥያቄ ሙለሙሉ ውድቅ ያደረገ ነበር..፡፡‹‹ ጠቅላላ ጉባኤ የሚጠራው ህግና የአሰራር ሂደቱን ተከትሎ ነው፡፡›› በማለት ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአንድ ሳምንት ውስጥ እንደገና እንዲደራጅ የቀረበው ጥያቄ የሕግ አግባብነት የለውም፡፡
የሪዮ ኦሊምፒክ ውጤት ‘’የአገሪቱ አትሌቲክስ ሞቷል ወይም ተቀብሯል’’ አያሰኝም፡፡
የታዋቂ አትሌቶች ጊዜያዊ ኮሚቴ አስቸኳይ ጠቅላለ ጉባዔ እንዲጠራ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ አይችልም፤ጉባዔውንም የመጥራት ሥልጣንም የለውም። የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የዓመቱን ውድድር መርሐ ግብርና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎችን ለማከናወን ጠቅላላ ጉባዔውን በቀጣዩ ወር ይጠራል ብለዋል።
‹‹ችግሩ ከሪዮ ኦሎምፒክ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው ብለን አናምንም’’ የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ኮሚቴው ቀደም ሲልም የቀድሞው የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኃላፊ አቶ ዱቤ ጅሎ ከኃላፊነታቸው ሲነሱ ‘’ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ሥራቸው ይመለሱ’’ የሚል ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡
‹‹በሪዮ የተመዘገበው ውጤት በአጠቃላይ ሲታይ ጥሩ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ነገር ግን በወርቅ ሜዳሊያ ያሰብነውን ያህል አላሳካንም፤በዚህም በጣም አዝነናል››
አሰልጣኞች ፤ በሪዮ ኦሎምፒክ የተሳተፉ ኦሎምፒያኖች በዘመናዊ ስልጠና ያለፉ፣የብቃት ችግር የሌለባቸውና በቡድን ሥራ ውጤታማ ነበሩ ብለዋቸዋል።። ‹‹አትሌቶቻችን ለተፎካካሪዎቻቸው ከባድ ግምት በመስጠታቸው፤ የዶፒንግ ወሬዎች እና ተከታታይ ክትትልና ምርመራዎች መብዛታቸው፤ ከኦሎምፒኩ በፊት ባሉት ወራት እና ከዚያም ከኦሎምፒኩ ማግስት በፌደሬሽኑ ዙርያ ወከባ እና ወቀሳ መብዛታቸው፤ በተወሰኑ ትንሽ ስፖርቶች እየተሳተፍን ሜዳልያ አነሰ ብሎ መገመገም ተገቢ ባለመሆኑ፤ ፌደሬሽኑ ይፍረስ ተብሎ የተጀመረው ዘመቻ በግልፅም በድብቅም የፈጠረው ጫና የአትሌቶችን ሞራል መግደሉ›› ‹‹ከሙስና ጋር በተያያዘ 4 እና 5 አትሌቶች በከፍተኛ ምርመራ ላይ ናቸው፡፡ ከንብረት እና ሃብት አስተዳደር፤ ከአትሌቶች የውጭ ጉዞዎች እና ከሽልማት መኪና ከቀረጥ ነፃ ማስገባት በተያያዘ በርካታ ወንጀሎች ሲሰሩ ቆይቷል፡፡ ስፖርቱ ወደቀ ተብሎ የተነሳው ዘመቻ እነዚህን ሂደቶች ለማስተጓጎል ነው፡፡››
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ
ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተርና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ልዑካን ቡድን መሪ አቶ ታምራት በቀለ  
የአትሌቶች የቡድን ሥራ መጓደልና የብቃት አለመመጣጠን በሪዮ ኦሎምፒክ የሚጠበቀውን ውጤት እንዳይመዘገብ  ማድረጓን በመግለፅ የተያዘ ዕቅድን 66 በመቶ አሳክተናል።
በለንደን ኦሎምፒክ የታዩትን ችግሮች ለመፍታት ጥረት አድርገናል፤  ውጤቱ ግን ህዝቡ የጠበቀውን ያህል ሳይሆን ቀርቷል ብለዋል፡፡
የብሄራዊ ቡድኑ ስልጠና ወጥነት የጎደለው፣ አሰልጣኞች ተነጋግረው የማይሰሩ መሆናቸው፣ የባለሙያዎች አቅም ማነስና አንዳንድ አትሌቶች በግል አሰልጣኝ መሰልጠናቸውም ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡
ኢትዮጵያን ከወከሉ አትሌቶች 70 በመቶ የሚሆኑት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉ ወጣቶች ነበሩ፡፡
በማራቶን የብር ሜዳሊያ ያስገኘው ፈይሳ ሌሊሳ የኦሎምፒክ ቻርተር አንቀጽ 50 ማንኛውም አትሌት ከሃይማኖት፣ ከፖለቲካ ጋር የሚያያዝ ተግባር ማንጸባረቅ የለበትም በሚል የተቀመጠውን  ህግ መጣሱ አንዱ ድክመት ነበር፡፡ አትሌቱ ቻርተሩን አስመልክቶ ዕውቀት እንደሌለው ለዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በማሳወቃችን ሜዳሊያው እንዳይነጠቅ ተደርጓል፤ የቅጣቱና የክሱ ጉዳይ ግን እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።
የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር
ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አንበሳው እንየው በሰጡት መግለጫ
ኢትዮጵያ በሪዮ ኦሊምፒክ ያስመዘገበችው ውጤት የአገሪቱን ስፖርት ውድቀት አያመለክትም፡፡
ኢትዮጵያ በሪዮ ኦሎምፒክ ያገኘቻቸው ሜዳሊያዎች የአገሪቱን የስፖርት ደረጃ መውረድ አያሳዩም። በኦሎምፒኩ የተመዘገበው ውጤት በወርቅ ሜዳሊያዎች ቁጥር ቢቀንስም፤ አገሪቱ በለንደን ኦሎምፒክ ካደረገችው ተሳትፎና የሜዳሊያዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ስለነበር ‘’ስፖርቱ ወድቋል’’ አያስብልም ።
የአገሪቱን ስፖርት በዓይነትና በተሳትፎ መጠን ለማሳደግ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት፣ የስፖርት መሠረተ ልማት ለማስፋፋት፣ በአገር ውስጥ የስፖርት ቁሳቁስ ምርትና የባለሀብቶችን ተሳትፎ ለመጨመር የሚደረገው ጥረት የዕድገቱ መለኪያዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ወደ ሪዮ ለተሰማራው ቡድን ሳይንሳዊና ተጨባጭ ስልጠና አለመሰጠት፣ ካለፉት ኦሎምፒኮች ምርጥ ተሞክሮዎችን አለመውሰድ፣ አትሌቶችን መሰረት ያላደረገ ዕቅድ መውጣቱ ለውጤቱ ማነስ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ስልጠናው በየጊዜው አለመመዘኑ፣ የወርቅ ሜዳሊያ ሊያመጡ የሚችሉ አትሌቶች በቡድኑ አለመካተት፣ በሥነ-ልቦናና የቡድን ስሜት ላይ  አለመሰራቱ፣ ሳይንሳዊ መንገድ የተከተለ አመጋገብ አለመከተል ሌሎቹ ችግሮች እንደሆኑም ገልፀዋል፡፡

Read 2924 times