Sunday, 04 September 2016 00:00

የአይሲስ ከፍተኛ መሪ ሶርያ ውስጥ ተገደለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


                       - ከአልባግዳዲ ቀጥሎ የቡድኑ ሁለተኛው ቁልፍ ሰው ነበር
      የሽብርተኛው ቡድን አይሲስ ቃል አቀባይ በመሆን ሲሰራ የቆየውና በቡድኑ የአስተዳደር መዋቅር ሁለተኛው ቁልፍ ሰው እንደሆነ የሚነገርለት አቡ ሞሃመድ አል አድናኒ፤ ሶርያ ውስጥ መገደሉን ቡድኑ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡
አይሲስ ግድያውን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ አል አድናኒ ሶርያ ውስጥ በምትገኘው አሌፖ አካባቢ የሚካሄዱ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በሚቆጣጠርበት ወቅት ለህልፈት መዳረጉን ይግለጽ እንጂ፣ የሞቱን ሰበብ በተመለከተ በይፋ ያለው ነገር እንደሌለ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ የሽብር ቡድኑ የአል አድናኒን የሞት መንስኤ ባይናገርም፣ የከፍተኛ አመራሩን ሞት ለመበቀል ቁርጠኛ አቋም መያዙን እንዳስታወቀ የጠቆመው ዘገባው፤ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን፣አል አድናኒ በአልባብ ከተማ በተፈጸመበት የአየር ላይ ጥቃት መገደሉን ባለፈው ረቡዕ ማስታወቃቸውን ጠቅሷል፡፡
አል አድናኒ በሽብር ቡድኑ ታሪክ የተገደለ ከፍተኛው ባለስልጣን ነው ያለው ዘገባው፤ግለሰቡ የአይሲስ መሪ የሆነውን አቡበከር አልባግዳዲን ይተካል ተብሎ የሚጠበቅ ቁልፍ ሰው እንደነበር ጠቁሟል፡፡ ሟቹ የአይሲስ ቀንደኛ መሪ አል አድናኒ፤ የሽብር ቡድኑ አጠቃላይ እንቅስቃሴ መሃንዲስ እንደነበር የጠቆመው ዘገባው፤ከቡድኑ መሪ አቡበከር አል ባግዳዲ ያልተናነሰ ቁልፍ ሚና ሲጫወት እንደነበርና ቡድኑን ለመደምሰስ በተደረጉ ዘመቻዎች በተሳተፉ የተለያዩ አገራት ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ ያስተላለፈውም እሱ እንደነበር ገልጧል፡፡
እ.ኤ.አ በ1977 ሶርያ ውስጥ የተወለደው አቡ ሞሃመድ አል አድናኒ፣ የሽብር ቡድኑ ከቡድንነት አልፎ ራሱን የቻለ እስላማዊ  መንግስት አቋቁሞ የመምራት አላማ ይዞ እንደሚንቀሳቀስ በይፋ ያስታወቀ የመጀመሪያው ሰው እንደሆነም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1231 times