Sunday, 04 September 2016 00:00

ናይጄሪያ፤ ቦኮ ሃራምን በሳምንታት ውስጥ እደመስሳለሁ አለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

- ፕሬዚዳንቱ ቡድኑን ለመደምሰስ ያቀዱት ከ8 ወራት በፊት ነበር

    የናይጄሪያ የጦር ሃይል ከፍተኛ መሪ ሜጀር ጄኔራል ላኪ ኢራቦር፣ ጦራቸው በአገሪቱ ሰሜን ምስራቃዊ አካባቢዎች የሚገኙትንና በአሸባሪው ቡድን ቦኮ ሃራም የተያዙትን ጠንካራ ይዞታዎች በቁጥጥር ስር በማዋል ቡድኑን በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንደሚደመስስ ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ላለፉት ሰባት አመታት በአገሪቱ የከፉ የሽብር ጥቃቶችን ሲፈጽምና ልጃገረዶችን ሲጠልፍ የቆየውን ቦኮ ሃራም፣ ሙሉ ለሙሉ የመደምሰስ ግብ ይዞ የሚንቀሳቀሰውን ጦር የሚመሩት ሜጀር ጄኔራል ላኪ ኢራቦር ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ፣ቡድኑ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ይደመሰሳል ብለዋል፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙሃሙድ ቡሃሪ እስካለፈው ታህሳስ ወር ቦኮ ሃራምን እንዲደመስስ ለጦር ሃይላቸው ያስቀመጡት ቀነ ገደብ ካለፈ 8 ወራት መቆጠራቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤የጦሩ መሪ ሜጀር ጄኔራል ላኪ ኢራቦር በሰጡት መግለጫ፣ ቦኮ ሃራምን ለመደምሰስ የቀረው የሳምንታት ጊዜ ብቻ እንደሆነ በእርግጠኝነት ተናግረዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ሶስት ያህል ጠንካራ ይዞታዎችን በቁጥጥር ስር አድርጎ እንደሚገኝ የገለጹት ላኪ ኢራቦር፣ የጦር ሃይላቸው በሚወስደው የማያዳግም እርምጃ ቡድኑ ሙሉ ለሙሉ እንደሚደመሰስ ገልጸው፣ በሽብር ቡድኑ ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ከአጎራባች አገራት የጦር ሃይሎች ጋር በተቀናጀ መልኩ እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡
ቦኮ ሃራም እ.ኤ.አ ከ2009 አንስቶ በናይጀሪያ፣ ቻድ፣ ኒጀርና ካሜሩን በፈጸማቸው አሰቃቂ የሽብር ጥቃቶች ሳቢያ ከ15 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውንና 2.3 ሚሊዮን ያህል የአገራቱ ዜጎች እንደተፈናቀሉም ዘገባው አክሎ አስታውሷል፡፡

Read 973 times