Sunday, 11 September 2016 00:00

በአዲሱ ዓመት ለፖለቲካዊ ችግሮች - ፖለቲካዊ ውይይት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ግጭቱ ይበርዳል፤ ያልፋል የሚል ተስፋ አለኝ”
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣እንደ ወትሮው ሁሉ በወቅታዊ የአገሪቱ ችግሮችና መፍትሄው ዙሪያ አንጋፋ ፖለቲከኞችን፣ ምሁራንን፣የሃይማኖት መሪዎችንና የአገር ሽማግሌዎችን አነጋግሯል፡፡ የውይይት መድረኩ ዓላማ፣በወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮች ዙሪያ ሃሳቦችን በማንሸራሸር መፍትሄ ማፈላለግና መጠቆም ነው፡፡ እግረ-መንገዱንም እርስበርስ እንድንማማር ዕድል ይሰጠናል፡፡ በአገራችን ለተከሰተው ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ ሁነኛ መፍትሄ አለን የምትሉ፣ሃሳባችሁን በጽሁፍ
(ኢሜይል)፣በስልክ ወይም በአካል (ቢሮ) ብታደርሱን ለማስተናገድ ዝግጁ ነን፡፡

ግርማ ወ/ጊዮርጊስ (የቀድሞ ፕሬዚዳንት)
ወጣቶች ንብረት ማቃጠላቸው በጣም መጥፎ ነገር ነው፡፡ በሚዲያ ሲነገር እንደሰማሁት፤ መንግስት ያሉበትን ችግሮች አርሞ፣ለውጥ ለማድረግ እየጣረ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከዚህ አንፃር ጥያቄዎች መልስ አግኝተው ግጭቱ ይበርዳል፤ያልፋል የሚል ሀሳብ ነው ያለኝ፡፡ መካሪ የማጣትም ሊሆን ይችላል፡፡ በመሸበርና በማሸበር ውስጥ ብዙ ጥቅም የለም፡፡ ጥቅም የሚኖረው ሁሉም ነገር በሰላም ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ወጣቶቹ ይሄን ነገር ለማድረግ ያሰቡበትን ከጀርባ ያለ ምክንያት አናውቅም፡፡ ብናውቅም የምናየው ነገር ደስ አይልም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ወጣቶች ተመክረው ወደየትምህርት ቤታቸው ይመለሳሉ፤ወደየስራቸው ይሄዳሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡
መንግስት የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ይመስለኛል፡፡ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም፤ወጣቱን ሰብስበው አነጋግረዋል፡፡ ነገሮችን በጉልበት ከማድረግና በመግደል ከመመለስ፣በማስተማር ማስታገስና መመለሱ ነው የሚሻለው፡፡
ለመንግስትም ጥሩ የሚሆነው ይህ ነው፡፡ የሚገርመው የኢትዮጵያ ህዝብ በፈጣን የእድገት ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡ 35 ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበትና ድንቁርና እየጠፋ ስልጣኔ የመጣበት ጊዜ ነው፡፡ ድህነትም እንዲህ የሚጠፋ ይሆናል፤ እየጠፋም ነው፡፡ ወጣቶች አንዳንድ አነቃናቂ አግኝተው፣የሚያስቸግሩትን ሃሳብ ማስለወጥና በጥሩ መንገድ እንዲሄዱ ማድረግ ከተቻለ አዲሱ ዓመት ጥሩ ይሆናል፡፡

===================================

“ማንኛውም አለመግባባት በውይይት መፈታት አለበት”

ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ (የኢትዮጵያ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዚደንት)

ባሳለፍነው ዓመት በአገራችን አንዳንድ ቦታዎች የታዩ ውስጣዊ ግጭቶች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ሆኖም እነዚህ ሁኔታዎች ጥፋትና የማህበረሰብ ስሜት ማፋለስ እንዳያስከትሉብን፣ በሰከነ መንፈስ ነገሮች የሚፈቱበት መንገድ እንዲደረግ፣ ቤተክርስቲያን አጥብቃ ትማጸናለች፡፡ ቤተክርስቲያን በሰው ህይወትና በአገር ንብረት ላይ በደረሰው ጥፋት በጣም ታዝናለች፡፡
መንግስት ባለበት የማስተዳደር ኃላፊነት፣ መሰረቱን የጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር በጋራ በመወያየት፣ የግንዛቤ ትምህርቶች በመስጠት፣በጥበብና በማስተዋል በዚህ አዲስ አመት ተግቶ እንዲሰራ፣የአገሪቱንም እድገትና ደህንነት እንዲያስጠብቅ አደራ ትላለች፡፡ ሁላችንም እንደየእምነታችን ክፉውን ከምንወዳት አገራችን እንዲያርቅልን በጸሎት እንትጋ፡፡ መላው የአገራችን ሕዝቦች፤በመካከላችን የሚነሳውን ማንኛውንም አለመግባባት በሰከነ መንፈስ፣ በውይይት የመፍታት ባህል እንዲያዳብሩ፣ በታላቅ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡


================================================

‹‹ኢህአዴግ ብቻውን የችግሩ መፍትሄ ሊሆን አይችልም››

አቶ ገብሩ አስራት
(የቀድሞ አንጋፋ ታጋይ)
የአሁኑ ተቃውሞና ግጭት ባህሪ መንግስት እንደሚለው፣በመልካም አስተዳደር እጦት ብቻ የመጣ አይደለም፡፡ መልካም አስተዳደር ከሃገራችን በርካታ ችግሮች አንዱ ነው፡፡ የተቃውሞ  መነሻ ግን በሰልፎችም ላይ እንደተንጸባረቀው፤የነፃነት፣ የፍትና፣ የዲሞክራሲ እጦት ነው፡፡ ከዚያም ሲያልፍ የኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና የመሬት ዘረፋና የሃብት ክፍፍል፣ የወጣቱ ስራ አጥ መሆን ተደማምሮ ያስነሣው ነው፡፡ ባለፈው አመት የተደረገው ምርጫም የውሸት እንደነበር ያመለክት ነው፡፡ ህዝቡ በግልፅ ነግሮአቸዋል፡፡ እኛ አልመረጥናችሁም፣ በማስፈራራት የተደረገ ምርጫ ነው ብሏቸዋል፡፡
በአጠቃላይ በሃገራችን ያለው ፖለቲካ ከመሠረቱ ኢህአዴግ በሚከተለው አቅጣጫ የተሳሳተ ሲሆን ዲሞክራሲን የሚያፍን፤ ያፀደቀውን ህገ መንግስት እንኳ ሳይቀር የማያከብር፣ የህግ የበላይነት፣ ነፃነት፣ ፍትህ የሌለበት ሃገር መሆኑ ነው መነሻው። ዴሞክራሲና ነፃነት በሌለበት፤ ሚዲያዎች፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት በነፃነት ተንቀሣቅሰው፣የህዝብ ድምፅ መሆን አይችሉም፡፡ ይህ የተጠራቀመ ብሶትን ይወልዳል፡፡ እነዚህ በነፃነት ተደራጅተው ሚዛኑን ሲጠብቁ እንጂ “እኔ ብቻ ነኝ የማውቅልህ” የሚል መንግስት ባለበት፤ሙስና፣ ብልሹ አስተዳደር የሚባሉት መፈጠራቸው አይቀርም፡፡
ኢህአዴግ ላለፉት 25 ዓመታት በራሱ ፍላጎትና መንገድ ብቻ የሚንቀሳቀስ እንጂ በሀገሪቱ ያሉ ባለድርሻዎችን ይዞ መንቀሳቀስ የሚችል ፓርቲ አለመሆኑን አሳይቷል፡፡ እንደ እኔ፤ችግር ፈጣሪው መልሶ ራሱ፣ የችግሩ መፍትሄ ሊሆን አይችልም። ኢህአዴግ፤ የአገር ሽማግሌዎችን፣ ተቃዋሚዎችንና ባለድርሻዎችን ሳያካትት እታደሳለሁ ቢል ጭራሽ የሚሆን አይደለም። መፍትሄም አያመጣም፡፡ እንደውም ዋና የመፍትሄ አቅጣጫ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጥተው ለፀጥታ ኃይሎች የሰጡት ስልጣን ነው፡፡ በግልፅ ያልታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው ያወጁት፡፡ ለችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄ ከመሻት ይልቅ በኃይል ለመፍታት የተዘጋጁበት ሁኔታ ታይቷል፡፡
በሀገራችን በኃይል የሚመጣ መፍትሄ እንደሌለ ብዙ ጊዜ ተሞክሮ ተረጋግጧል፡፡ በግጭቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተው፣መንግስት ኃላፊነት ተሰምቶት ለማጣራት እንኳ አልፈለገም፡፡ ይሄን ሁሉ ገድሎና አስሮ የመፍትሄው ባለቤት ነን ማለት አያስኬድም፡፡ አሁን እየተሄደበት ያለው አቅጣጫ ችግሩን እንደሚፈታም አያመላክትም፡፡ የሚሰጡት ማብራሪያም ሆነ መግለጫ የሚታወቀውን ከመድገም በስተቀር አዲስ ነገር የለውም። ለችግሩ ምክንያት የሆኑት ራሳቸው ሆነው በኢህአዴግ የፖለቲካ ተቋም እንፈታዋለን ማለታቸው የማይሞከር ነው፡፡ በዚህች ሀገር ያገባናል የሚሉ በውጭም በሀገር ውስጥም ያሉ አካላት በመወያየት መፍትሄ እስካላመጡ ድረስ አሁን ኢህአዴግ በሚለው መንገድ የችግሩን 1 በመቶ እንኳ መፍታት አይቻልም፡፡  
እኔ እንደ ፖለቲከኛ መፍትሄው በአንድ ፓርቲ እጅ ብቻ አይደለም እላለሁ፡፡ በዚህች ሀገር የአስተሳሰብ ብዝሃነት አለ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚያው ልክ አሉ። ስለዚህ አንድ ገዥ ፓርቲ የፖለቲካ መፍትሄ ይሰጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ መፍትሄው መነጋገር ነው። ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ መስጠት ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ባለድርሻዎች ጋር ቁጭ ብሎ መወያየት ያስፈልጋል፡፡ የችግሩ ምንጭ የሆነው ፓርቲ ብቻውን መፍትሄ ማምጣት አይችልም፡፡ ስለዚህ ህዝቡ እያቀረበ ያለውን ችግር ረጋ ብሎ አይቶ፣ የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ መፍትሄ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ ለአጭር ጊዜ መፍትሄ ግድያ ማቆም፣ የታሰሩ ፖለቲከኞችን መፍታት፣ ለተጎዱት ካሳ መስጠት ይሄ የአቭር ጊዜ መፍትሄ ነው፡፡ በረጅም ጊዜ መፍሄት ግን ዲሞክራሲ፣ ፍትህ የሚነግስበት ስርአት መቋቋም አለበት፡፡ የአጭር ጊዜውን መፍትሄ እየተገበሩ ዘላቂው መፍትሄ የሚመጣበትን ሁኔታ መፍጠር አለብን።  
 ===================================

‹‹መንግስት የሌሎችን ሀሳብ መስማት አለበት››
ጠበቃ አመሀ መኮንን

በ2008 ዓ.ም በኑሮዬና በግሌ ብዙ የማማርርበት ነገር አልገጠመኝም፤እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ራሴን ካለኝ ሁኔታ ጋር አጣጥሜ ለመኖር ሞክሬያለሁ፡፡ ነገር ግን በስራዬ በኩል ዓመቱ በጣም የፈተና ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ ከስራዬ ጋር በተያያዘ ደግሞ በቀጥታ እኔ ከያዝኳቸው ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ከአገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዝ፣ ከማረሚያ ቤት የእስረኞች አያያዝና ተያያዥ ጉዳዮች አንፃር አመቱን ስመለከተው፣ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነበር፡፡ በተለይ ሁላችንንም የሚያግባባን፣ቀደም ብሎ በኦሮሚያ ከዚያም በአማራ ክልል ለተነሱት የመብት ጥያቄዎች መንግስት ምላሽ የሰጠበት መንገድ በጣም አሳሳቢ መሆኑ ነው፡፡ በተለይ የፀጥታ ሀይሉ ንፁሀን ላይ ጥይት የመተኮስና መግደል ጉዳይ፣ መንግስት የመጨረሻ ሳይሆን የመጀመሪያ አማራጭ አድርጎ መውሰዱ በጣም ይረብሻል፡፡ አዲሱ አመት መግቢያ ላይ ቆመን ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የደረሰው አሰቃቂ አደጋና እየተሰማ ያለው ነገር ዓመቱን ሲበዛ ፈታኝ ያደርገዋል። በአጠቃላይ ከሙያዬና ከስራዬ አንፃር 2008 እጅግ የፈተና ዓመት ነው፡፡
በአዲሱ ዓመት እንደ ሰው ተስፋ አድርጋለሁ፡፡ በመንግስት በኩል፤ የሌሎችን ሀሳብ ለመስማት ዝግጁ እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ ከመንግስት የተለየ ሀሳብ ያላቸውን እንደ 2008ቱ፣በሀይል ሳይሆን በውይይት የሚፈታበት እድል እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይሄ እንግዲህ ተስፋ ነው፡፡ የህዝቡን ጥያቄ በተመለከተ መንግስት እድገቱ የፈጠረው ነው፤የሚል አከራካሪ ምላሽ እየሰጠ ነው። የሚገርመው አሁን ምላሽ እየተሰጠ ያለበት መንገድ፤ ከ25 ዓመት በፊት ምላሽ ሲሰጥ የነበረበት መንገድ ነው፡፡ የህዝብ ጥያቄ በየጊዜው እንደሚነሳ እየታመነ፣ ለጥያቄው ተመጣጣኝ የሆነ ወቅታዊ ምላሽ መዘጋጀት ነበረበት፡፡ ይህን ግን እያየን አይደለም፡፡ በአዲስ ዓመት የፀጥታ ሀይሉ ንፁሀን ላይ መተኮስን መደበኛ ስራ አድርጎ የማይቀጥልበት እንደሚሆን በጥብቅ እመኛለሁ። የህዝብን ጥያቄ መንግስት በአግባቡ መመለስ አለበት። እንግዲህ ሰው ነኝና፣ምኞትና ተስፋ ነው፡፡ ለሁሉም መልካም አዲስ አመት እመኛለሁ!!

Read 4077 times Last modified on Saturday, 10 September 2016 13:51