Saturday, 10 September 2016 13:41

መጥፎ ቁስል ይድናል፤ መጥፎ ስም ግን ይገድላል

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(7 votes)

     የተገባደደው 2008 ዓ.ም ለሀያ አምስት አመታት በዘለቀው የኢህአዴግ አገዛዝ የታሪክ ማህደር ውስጥ የሚመዘገበው ‹‹ነጃሳ አመት›› ተብሎ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እንደ ዘንድሮው ከትግራይ እስከ ኦሮሚያ፣ ከአማራ እስከ ደቡብ ክልል በተቀጣጠለና ደም ባፋሰሰ ህዝባዊ ቁጣና የተቃውሞ ማዕበል የውጥር ተይዞ አያውቅም፡፡ የኢህአዴግ መበስበስና የአመራር ዝቅጠትም ከመቸውም ጊዜ የበለጠ በገሀድ ተገልጦ የታየው ዘንድሮ ነው፡፡
2008 ዓ.ም ለህዝቡም ቢሆን ተራ የአዘቦት አመት አልነበረም፡፡ ለአመታት የተፈራረቀበትና ወደር በማይገኝለት ትዕግስቱ ተሸክሞት የኖረው ግፍና መከራ፣ጽዋው ሞልቶ የፈሰሰበት አመት ነበር፡፡ አየርላንዶች፤ ‹‹ቀንዳም ላም በጭራዋም የምትማታበት ጊዜ ይመጣል›› እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያ ህዝብም የፈነዳ ቁጣውን በአመጽና በተቃውሞ የገለፀበት፤የታፈነና የተረገጠ መብቱን በአደባባይ የጠየቀበት አመት ነው፡፡ ስመ ጥሩው ግሪካዊ ፈላስፋ ሶፎክለስ፤ ‹‹መልካም ነገርን ከጠላትህም እንኳ ቢሆን በሚገባ አድምጥ›› እንደሚለው፣ኢህአዴግም ሆነ የሚመራው መንግስት፣ ከተለያዩ ወገኖች የሚለገሰውን ምክር ነገሬ ብሎ በመስማት ለህዝቡ ጥያቄ ተግባራዊ መልስ እንዲሰጥና የተነሳበትን ህዝባዊ ቁጣም እንዲያበርድ በተደጋጋሚ ተወትውቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የተጠናወተው የአመራር ዝቅጠት፣ የሌሎችን ምክር መስማት ይቅርና ተራ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን እንኳ መጠቀም እንዳይችል አደርጎታል፡፡ በዚህም የተነሳ መብቱን፣ ነፃነቱንና እኩልነቱን ለመጠየቅ አደባባይ የወጣውን ህዝብ ተቆጣጥሮ፣ አመፁንና ተቃውሞውን ፀጥ እንዲያደርግ የመከላከያ ሰራዊቱን ያለ መደበኛ ስራው አሰማርቶ አረፈው፡፡
“በሽተኛ ወፍ በሽተኛ እንቁላል ትጥላለች እንደሚባለው፣ ይህን የመሰለው የኢህአዴግ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር የመጨረሻ ውጤቱ በውል የማይታወቅ የህይወትና የአካል ጥፋት እንደሚሆን ግልጽ ነበር፡፡ እናም የኢትዮጵያ ህዝብ 2008ን የሸኘው በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች የተገደሉና የቆሰሉ እጅግ በርካታ ልጆቹን፣ “ወዬው!” ብሎ አልቅሶ በመቅበርና “አይዞህ” እያለ በማስታመም ነው፡፡
የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ያመፁት ወይም ቁጣና ተቃውሞአቸውን አደባባይ በመውጣት የገለጹት አመጽና ተቃውሞ ስለሚያዝናናቸው አይደለም፡፡ ይልቁንስ ላለፉት ሀያ አመታት ተስፋ ሳይቆርጡና ሳይሰለቹ ሲያቀርቡ የኖሩት የመብት፣ የነፃነት፣ የእኩልነትና፣ የፍትህ ጥያቄ በገዢው ድርጅት በኢህአዴግና በመንግስቱ ሰሚ ጆሮ ባለማግኘቱና ዘመናት ያስቆጠረው ታላቅ ትዕግስታቸው ተሟጦ በማለቁ ነው፡፡ የሁለቱ ህዝቦች የአመጽና የተቃውሞ እንቅስቃሴ አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ ተጨቁኖ፣ ታፍኖና ተረግጦ የሚኖር የየትኛውም ሀገር ህዝብ፤የግፍና የመከራ ጽዋው ሲሞላ፣ በማናቸውም ጊዜና ቦታ ሊፈጽመው የሚችል ተፈጥሯዊ ድርጊት ነው፡፡
ይሄ ደግሞ ከኢህአዴግ በስተቀር ማንም በቀላሉ የሚረዳው ግልጽ እውነታ ነው፡፡ ኢህአዴግ ለራሱ ያለው የተሳሳተ ግምትና አስተሳሰብ፣ የነገሮችን ሙሉ ስእል አጣርቶ ማየት እንዳይችል ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጥሮበታል፡፡ ያገሬ ሰው፤ ‹‹በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ›› እንደሚለው፤ በዚህ ችግሩ ላይ የተደረበበት የመበስበስና የአመራር ዝቅጠት፣ ይብሱኑ ከገሀዱ እውነት ውጪ እንዲሆንና ከማዕበሉ በተቃራኒ እንዲቀዝፍ አድርጎታል፡፡ ኢህአዴግ፤ “ለዚህች ሀገርና ህዝብ  አለኝታና መድህናቸው እኔና እኔ ብቻ ነኝ” የሚል ስር የሰደደና አመታትን ያስቆጠረ  አስተሳሰብ አዳብሯል፡፡ ይህ የተሳሳተና ፀረ - ዲሞክራሲያዊ የሆነ አስተሳሰቡ ደግሞ በጭቆናና በአመጽ መካከል ያለውን ተፈጥሮአዊ ትስስር በግልጽ ማየትና መረዳት እንዳይችል እንቅፋት ሆኖበታል፡፡ እናም የኢትዮጵያ ህዝቦች ያለሁዋቸው “ብቸኛ አለኝታና መድህን ድርጅት እኔ ስለሆንኩ ምንም ባደርጋቸው በእኔ ላይ ሊያምፁ አይችሉም” ሳይሆን ሊያምፁ አይገባም ብሎ ተፈጥሟል፡፡ አበሻ “የፈሲታ ተቆጢታ” ብሎ እንደሚተርተው፣ህዝቦች በደረሰባቸው ግፍና በደል የተነሳ ተቃውሞአቸውን ሲገልፁ፣ በንዴት እየጦፈ ጠብመንጃውን የሚወለውለው በዚህ የተነሳ ነው፡፡
በየትኛውም አካባቢ ህዝባዊ ተቃውሞ በተነሳ ቁጥር ኢህአዴግ የሚታወቅበት የተለመደ ተግባሩ፣ ችግሩን በሌሎች ላይ በማላከክ ባለ ዕዳ ማድረግ ነው፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን ከተቆናጠጠበት ከዛሬ ሀያ አምስት ዓመት ጀምሮ ላጋጠመው ህዝባዊ ተቃውሞ፣ በጠላትነት የፈረጃቸውን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርቶች ወይም የውጭ አካላት በተለይም አልሸባብና አልቃኢዳ እንዲሁም ሻዕቢያና የኒዎ-ሊበራል ሀይሎችን ተጠያቂ ሳያደርግ የቀረበት ጊዜ የለም፡፡  
ጣሊያኖች እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥማቸው “ሰበብ ጥሩ የሚሆነው ሲሰራ ብቻ ነው” ይላሉ፡፡ ኢህአዴግ እንዲህ ላለው አሪፍ ምክር ላመል ታህል እንኳ ደንታ የለውም፡፡ በየጊዜው በሚያቀርባቸው ሰበቦች ራሱን ማታለሉን እንጂ ለሌሎቻችን መስራት አለመስራቱን ለማረጋገጥ ጊዜውም ሆነ ፍላጎቱ የለውም፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ለሚነሱበት ተቃውሞዎች የሚሰጣቸው ምክንያቶችና የሚያቀርባቸው ሰበቦች እንዲያው ለወጉ ያህል አንድ ወጥ መሆናቸውን ለማወቅ እንኳን አይጨነቅም፡፡ ለምሳሌ በአማራ ክልል የተነሳውን ህዝባዊ አመጽና ተቃውሞ መንስኤ በማስመልከት፣ አንድ የብአዴንና የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሲናገሩ፤ “የዲሞክራሲ ተቋማት አለመጠናከርና የኢህአዴግ የውስጥ ችግሮች ለተከሰቱት ሁከቶች መንስኤ ናቸው” በማለት ከገለጹ በኋላ መለስ ብለው ደግሞ “እየታየ ያለው አካሄድ በህዝብ ጥያቄ ተከልለው ሀገሪቱ ወደ ለየለት የእርስ በርስ ግጭት እንድትገባ የሚፈልጉ ሀይሎች የሚያራመዱት ነው፡፡” ሲሉ ሌሎችን ባለ ዕዳ አድርገዋል፡፡
የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች እያቀረቡት ያለውን የመብት፣ የፍትህ፣ የነፃነትና የእኩልነት ጥያቄ፣ አንድ የኢህአዴግ ባለስልጣን በቅርቡ በተካሄደ የሴቶች የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው፤ “አሁን እየታየ ያለው ሁኔታ ምንም አይነት አጀንዳ የለውም፡፡ የትምክህተኞችና የጠባቦች አጀንዳ ነው፡፡ ሁኔታውና አጠቃላይ ይዘቱ የቀለም አብዮት ነው፡፡” በማለት ገልጸውታል፡፡  
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው ነሐሴ 24 ቀን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ለዘመናት የአገሪቱን ውድቀት የሚመኙና ኢትዮጵያ ደካማ ሆና በተፈጥሮ ሀብቷ እንዳትጠቀም የሚፈልጉ አገራት፣ መረጋጋት ለማሳጣት በውጭ ለሚገኙ ጥቂት ጽንፈኛ የዳያስፖራ አባላት ገንዘብ በገፍ በማከፋፈል፣ሁከቱ እንዲስፋፋ እያደረጉ ነው በማለት ተቃውሞና አመጹ የውጭ ኃይሎች እጅ እንዳለበት አስረድተውናል፡፡
በዚህ የኢህአዴግ ድርጊት ውስጥ ያለው አንድ ዋነኛ ጉዳይ፣እኔን በመሰለ መንግስት ላይ ህዝቡ የሚያምፀው በዋናነት በራሱ ተነሳሽነት ሳይሆን በሌሎች ሀይሎች ተገፋፍቶ ነው የሚለው የኢህአዴግ እምነት ነው፡፡ የህዝቡን አመጽና ተቃውሞን በተመለከተ ኢህአዴግ ቀደም ብዬ ካነሳሁት መሰረታዊ አስተሳሰቡ የሚነጭ አንድ ሌላ አመለካከትም አለው፡፡ ኢህአዴግ እሱን በመሰለ ድንቅ መንግስት ላይ የሚደረግን አመጽና ተቃውሞ፤“ቅብጠት ወይም ጥጋብ” አድርጎም ይቆጥረዋል፡፡ በቅርቡ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያወጣው መግለጫ ይህን ጉዳይ በደንብ ይገልፀዋል፡፡
መግለጫው ሰብአዊና ዲሞክራሲዊ መብቶችን በተመለከተ “በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ህገመንግስታዊ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርአት ግንባታ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ በዚህ የዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ ስርአት ግንባታ ሂደት የዜጎችና የልዩ ልዩ ማህበረሰቦች የፖለቲካ መብቶች ህጋዊ እውቅናና ዋስትና አግኝተው ተከብረዋል፡፡” ሲል፤የብሔር ብሄረሰቦችን እኩልነት በተመለከተ ደግሞ “የብሄር ብሄረሰቦችን ማንነት ያስከበረ አዲስ አይነት ፊደራላዊ የእኩልነት ስርአት ተገንብቷል” ይላል፡፡  
የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በተመለከተም፤ ‹‹ኢኮኖሚያችን ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት ባለ ሁለት አሀዝ ተከታታይ እድገት እንዲያስመዘግብ ለማድረግ ችለናል፡፡ ይህን ከመሰለው እድገት ጋር በማይነጣጠል መልኩ የህዝብ ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ ቆይቷል፡፡›› ይላል፡፡
የዚህ ሁሉ ገለፃ ዋናው መልእክት ታዲያ፣ ምን ጎደላችሁና ነው የምታምፁት፤ቀ ብጣችሁ ወይም ጥጋብ ተሰምቷችሁ ካልሆነ በቀር የሚል ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በእጅጉ የከፋው የኢህአዴግ ድርጊት እነ አሞራውን የመሰሉ አልፍ አዕላፍ ታጋዮች በሙሉ ፈቃደኝነት ውድ ህይወታቸውን የሰውለትና ህገ መንግስታዊ እውቅና ያገኘው ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው፣ ነፃነትና እኩልነታቸው እንዲረጋገጥላቸው ለዘመናት ጠይቀው ምላሽ በማጣታቸው ቁጣቸው ገንፍሎ ያመጹና ይህንን ቁጣቸውን ለመግለጽ አደባባይ የወጡ ሰዎች መጨረሻቸው የጥይት ራት እንዲሆን መደረጉ ነው፡፡
ይሄም ሳያንስ ክቡር ከሆነው የሰው ልጅ ህይወት ይልቅ ለተሰበረ ቧንቧና መስታወት ይበልጥ በመጨነቅ የሞቶ ሰዎች ቁጥር ሳይታወቅ የንብረት ውድመት ሪፖርት ይቀርብልናል፡፡ ስኮትላንዳውያን፤ ‹‹መጥፎ ቁስል ይድናል፤መጥፎ ስም ግን ይገድላል›› ብለው የሚተርቱት እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲገጥማቸው ነው፡፡
መልካም አዲስ ዓመት!!!




Read 6000 times