Sunday, 11 September 2016 00:00

‹‹የባለ አደራ መንግስት መቋቋም አለበት››

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ላለፉት 3 ወራት በአሜሪካና ካናዳ ባደረጉት
የሥራ ጉብኝት ከየአገራቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ሰሞኑን ወደ
አገራቸው የተመለሱት ኢ/ር ይልቃል ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር አጭር ቃለ-
ምልልስ አድርገዋል፡፡


የአሜሪካ ጉብኝትዎ አላማ ምን ነበር?
በመጀመሪያ የሄድኩት ወደ ካናዳ ቶሮንቶ ነበር። በዚያ የሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፌስቲቫል ይካሄድ ነበር፡፡ በፌስቲቫሉ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሁኔታ ንግግር እንዳደርግ አንድ ማህበር ጋብዞኝ ነው የሄድኩት፡፡ እኔ ከሄድኩ በኋላ በአጠቃላይ በሃገር ውስጥ ያሉ ነገሮች እየተለዋወጡ መጡ። ስለዚህም ለኢትዮጵያውያን፣ ለአሜሪካና ለካናዳ መንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም ለተለያዩ የሲቪክ ማህበራትና ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፤በኢትዮጵያ እየደረሰ ያለውን የጅምላ እስርና ግድያ እንዲያውቁ አድርገናል፡፡ ለወደፊትም መፍትሄው ምን መሆን እንዳለበት ከሚመለከታቸው አካላት በተለይም የኢህአዴግ ወዳጅ ከሆኑ ከሁለቱ ሃገራት መንግስታት ጋር ለመነጋገር ችለናል፡፡
 ውይይታችሁ ምን ላይ ነበር ያተኮረው?
መንግስት ነገሮች ከቁጥጥሩ ውጪ እየወጡበት እንደሆነ በስፋት ተነጋግረናል፡፡ ቀደም ሲል ስንሄድ የምንነጋገረው ስለ ጋዜጠኞች እስር፣ ስለ ፖለቲከኞች እንግልትና እስር ነበር፡፡ አሁን ግን ተቀይሯል፡፡ በቀን ስንት ሰው ሞተ? የሚል ጥያቄና መረጃ ነው የሚሰማው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የኢትዮጵያ ሁኔታ አሣሣቢ እየሆነ ነው፡፡ አስቸጋሪ ወደ ሆነ ሁኔታ እየገባን ስለሆነ እነዚህን ነገሮች በስፋት አንስተን ተነጋግረናል፡፡ ለካናዳና ለአሜሪካ መንግስታት በዚህ ጉዳይ ላይ እኔም ዶ/ር መረራም በስፋት አስረድተናል። በካናዳ ከውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰዎች ጋር ተነጋግሬያለሁ፣ ከሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋርም ተወያይቻለሁ። በአሜሪካ ከውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰዎችና ከቪዛ ክፍል ሃላፊዎች ጋር ተነጋግሬአለሁ፡፡ በካናዳ የኢትዮጵያ ልማት ተራድኦ ድርጅት ዳይሬክተርንም አነጋግሬያለሁ፡፡ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቋሚ ሴኔት ጋር ለመነጋገር ችያለሁ፡፡ በኋላም ከዶ/ር መረራ ጋር ሆነን፣አትላንቲክ ካውንስል በሚባል የውይይት አደራጅ ቡድን አማካኝነት የአደባባይ ምሁራን ከሚባሉት እንዲሁም ከአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይና ከኮንግረስ የተውጣጡ ሰዎች ሆነው፣ የኢትዮጵያን አጠቃላይ ወቅታዊ ሁኔታና የወደፊት እጣ ፈንታን በተመለከተ ንግግር አድርገናል፡፡ እኔም ዶ/ር መረራም ስለ ጉዳዩ በስፋት አብራርተናል፡፡
የአሜሪካ ባለስልጣናት አሁን ስላለው የሃገሪቱ ጉዳይ ተጨባጭ ዕውቀትና ግንዛቤ አላቸው?
የቁርጠኝነት ጉዳይ ነው እንጂ በቂ ግንዛቤ አላቸው፡፡ ይሄን የሚያውቁበት የተለያዩ መንገዶች አላቸው፡፡ ከኤምባሲው በየቀኑ መረጃ ያገኛሉ፡፡ መድረኩን ልዩ የሚያደርገው በአሜሪካ መንግስት የተለያዩ መዋቅር ውስጥ ሁነኛ ቦታ ያላቸው ሰዎች መገኘታቸውና ሰብሰብ ብለው የኛን ጉዳይ ማዳመጣቸው ሲሆን ይሄም  ጉዳዩ የበለጠ ትኩረት እንዲያገኝ ረድቶታል፡፡ በመድረኩ ላይ ለወደፊት ምን ታስባለችሁ ተብለን ስንጠየቅ፣ የኛ ምላሽ የነበረው አሁን ባለው ሁኔታ ኢህአዴግ ብቻውን የሚፈታው ነገር እንደሌለ፣ ህዝብም በተለያየ ሁኔታ ተቃውሞውን እየገለፀ ያለው ይሄን ችግር ይፍታልን በሚል ሳይሆን ኢህአዴግን ይሁንታ የመንሳት አይነት መሆኑን ጠቁመን፣ ይሄ ደግሞ በቀላሉ የሚታከም ባለመሆኑ፣የባለአደራ መንግስት ተቋቁሞ ለዲሞክራሲ አስፈላጊ የሆነ ተቋማትን ለ1 ዓመት ተኩል ያህል በማስተካከል፣የፖለቲካ ቡድኖች ተወዳድረው ስልጣን የሚይዙበትን መንገድ ማመቻቸት አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የሚደረግ ጊዜያዊ የጥገና ለውጦች አገሪቱ አሁን ላለችበት ችግር መፍትሄ የሚሰጥ እንዳልሆነ ተናግረናል፡፡ ይሄን ሃሳብ በሚገባ እንዲይዙትም አድርገናል፡፡  
የእነሱስ ምላሽ ምን ነበር?
አንድ መገንዘብ ያለብን ነገር፣ የትግሉና የጉዳዩ ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ የእነሡ ድጋፍ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ እኛ ችግሩን በሚገባ ነግረናቸዋል፡፡ “ኢህአዴግ የልብ ወዳጃችሁ እንደሆነ እናውቃለን፤ ‹ኢሳያስና አቶ መለስን ከቅኝ ግዛት በኋላ የመጡ የአዲሱ ትውልድ አመራሮች› እያላችሁ ታሞኳሻቸው ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ኤርትራ የት ነው ያለችው? ኢትዮጵያ ምን ደረጃ ላይ ናት? ይሄን ገምግሙ” ብለናቸዋል፡፡ ኢህአዴግ ብቻውን ያለውን ችግር አይፈታውም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የራሳችሁንም ጥቅም ልታጡ ትችላላችሁ፡፡ የምትረዱን ለኛ ብቻ ሳይሆን ለራሳችሁም ጥቅም ጭምር ነው ብለን አስረድተናቸዋል፡፡ በእናንተ የተለሳለሰ ፖሊሲ ምክንያት ብዙ ሀገር ፈርሷል፡፡ ኢትዮጵያ በቀጠናው ጠንከር ያለ ታሪክ ያለው ህዝብ  ሀገር ነች፤የአህጉሩ መቀመጫ ነች … የዚህች ሀገር መረጋጋት አቅሙ ለእናንተ ነው፡፡ ችግሮች ተባብሰው ሀገሪቱ ከመፍረሷ በፊት አንድ ነገር አድርጉ ብለን በትኩረት ነግረናቸዋል፡፡ እነሱም ጥያቄ እየጠየቁን በጥሞና ሰምተውናል፡፡
ለሀገሪቱ ወቅታዊ ችግር መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?
መፍትሄው አጭርና ግልፅ ነው፡፡ የባለአደራ መንግስት ማቋቋም ብቻ ነው፡፡ ኢህአዴግ አሁን ከባድ የቅቡልነት ችግር አለበት፤ህዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች “ኢህአዴግ በቃን” ወደሚል ተሻግሯል፡፡ ጥገናዊ ለውጦች አድርጌ የህዝብ ይሁንታ አገኛለሁ እያለ ቢሆንም ህዝቡ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ እየከፈለ ያለው መሰረታዊ ለውጥ ስለፈለገ ነው፡፡ ስለዚህ ሀገሪቱን ከቀጣይ ጥፋት ለማዳን የባለአደራ መንግስት መቋቋም አለበት፡፡ ከዚያ ውጪ የሀገሪቱን ሁኔታ ሊያረጋጋ የሚችል ነገር እንደሌለ እኔ በአፅንኦት ነው የምናገረው፡፡
የባለአደራ መንግስት ሲሉ ምን ማለትዎ ነው? ማን ነው የሚያቋቁመው?
 ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሲቪል ተቋማት፣ ከታዋቂ ሰዎች፣ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ ነው የሚሆነው፡፡ ባለአደራ ማለት ለጊዜው ስልጣኑ በሚመለከታቸው የፖለቲካ ቡድኖች እስከሚያዝ ድረስ ሀገር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስለሆነች፣ የጦር ኃይሉ ባለበት ሆኖ የሲቪል አስተዳደሩ በባለአደራው ይተካል ማለት ነው። በ1 ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ነፃ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብአዊ መብት ተቋማት፣ ነፃ ሚዲያ፣ ነፃ የፖለቲካ ቡድኖች … ይቋቋሙና ሥልጣኑን በምርጫ አሸናፊ ለሆነ ቡድን ያስረክባል ማለት ነው፡፡
ኢህአዴግ ስር ነቀል ህዳሴ አደርጋለሁ፤ ችግሮችንም እፈታለሁ ብሏል፡፡ ይሄንንስ እንዴት ያዩታል?
አሁን ባለው ሁኔታ ሚኒስትር በማባረርና በመሾም የሚለወጥ ነገር የለም፡፡ ጥያቄው መረር ያለ ነው፡፡ ኢህአዴግ በባህሪው የሚታደስ ድርጅት አይደለም፡፡ የመድብለ ፓርቲ ስርአትን በሙሉ ልቡ የተቀበለ ድርጅት ስላልሆነ አይታደስም፡፡ ማዕከላዊነት የበዛበት፣ ተቀናቃኞቹን እንደ ጠላት የሚቆጥር፣ ጠንከር ያሉ ትችቶች የሚያቀርቡ ሚዲያዎችን የዘጋ … ስለሆነ እነዚህ ባህሪያቱ ለመሻሻል እድል አይሰጡትም፡፡ አንድ ስርአት ለመሻሻል ነጻ ሚዲያ፣ የሲቪል ተቋማት፣ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ቡድኖች ነፃነት ---- መኖር አለበት፡፡ ኢህአዴግ እነዚህ ስለሌሉት፣ተጠያቂነትን አስፍኖ ሊሻሻል የሚችል ድርጅት አይደለም፡፡
በአሁኑ ወቅት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚና ምን መሆን አለበት?
እንደዚህ ባለ አስቸጋሪ ወቅት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ፣ ለአለም ማህበረሰብና ለገዥው ፓርቲ ማሳወቅና መፍትሄውን ማመላከት ይጠበቅባቸዋል። ተቃዋሚዎች ሃሳብ ማፍለቅ አለባቸው፡፡ ህዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች የፍልስፍና እና የአይዲኦሎጂ መልክ አስይዞ፣ ምን መሆን እንዳለበት የማመላከት ኃላፊነትም አለባቸው፡፡    

Read 6375 times