Sunday, 11 September 2016 00:00

ጀነራል ዋሲሁን ንጋቱ፤ በተለይ ለአዲስ አድማስ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

• መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ‹‹ተልባ ቢንጫጫ በአንድ ሙቀጫ›› ማለት አይገባውም
• ሰልፍ ወጥቶ መብቱን የሚጠይቅ ህዝብ፣መሳሪያ ሊተኮስበት አይገባም
• ህዝቡ ህግ ማክበር አለበት፤ መንግስት የህዝቡን መብት ማክበር አለበት
• ችግሮች በውይይት እንጂ በኃይል እርምጃ ዘላቂ መፍትሄ አያገኙም


ጀነራል ዋሲሁን ንጋቱ፤ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት አንስቶ እስከ ደርግ ውድቀት
ድረስ በጦር አዛዥነት የአገራቸውን ዳር ድንበር በማስጠበቅ ያገለገሉ ሲሆን በአገሪቱ ወቅታዊ
ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር ተነጋግረዋል፡
፡ በአገሪቱ ለተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ መባባስ ህዝብንም መንግስትንም የሚወቅሱት
ጀነራሉ፤በተለይ መንግስት ችግሮችን በብልሃትና በአርቆ አሳቢነት መፍታት ሲገባው የህዝብን አመፅ
በኃይል ጸጥ ለማሰኘት መሞከር ዘላቂነት የለውም ብለዋል፡፡ ጀነራል ዋሲሁን የሰጡት ቃለምልልስ
እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡


በአገሪቱ ለአንድ ዓመት ገደማ ለዘለቀው የፖለቲካ ቀውስ መንስኤው ምንድን ነው?
እኔ በመንግስት የስርዓት ሂደት ውስጥ ስለሌለሁ፣ በትክክል ይሄ ነው ለማለት ይከብደኛል፡፡ ነገር ግን እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ስሰማ፣ ዋናው የችግር መንስኤ የሚመስለኝ የኦሮሚያ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚያ ቀስ በቀስ ወደ አማራ ክልል እየተስፋፋና አስጊ እየሆነ መጣ፡፡ መንግስት ህዝቡ የሚያነሳውን ጥያቄ በአግባቡ ማዳመጥ አለበት፡፡ የህዝብ ጥያቄ ትንሽም እንኳን ቢሆን መናቅ የለበትም፡፡ በመወያየት ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የተከሰተው ችግር የኦባማን ወይም የሂላሪን ምክር የሚያስጠይቅ አይደለም፡፡ አገሪቱ ከዚህ ቀደም ከዚህ እጅግ የከፋ ችግሮችንም አሳልፋለች፡፡ አይደለም የህዝብ የግለሰብ ጥያቄም በአግባቡ መመለስ አለበት፡፡ መንግስት ከላይ እስከ ታች ባሉት መዋቅሮቹ አማካኝነት፣የህዝቡን ችግሮችና ጥያቄዎች በመስማት ምላሽ መስጠት ይኖርበታል፡፡ መቼም አገሪቱ ልትመልስ የማትችለውን ነገር ህዝብ አይጠይቅም፡፡ ሁሉንም ጥያቄዎችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይመልሱታል ማለት አይደለም፤ በተዋረድ የተቀመጡ ሃላፊዎች ችግሮችን ከስር ከስር ከህዝቡ ጋር እየተወያዩ ቢፈቱ፣ ይሄ ሁሉ ቀውስ አይፈጠርም ነበር፡፡ አሁን ችግሩ ትንሽ ስር ሰድዷዋል፡፡ ለዚህ ነው የተለያዩ ችግሮች በየአቅጣጫው እየተደራረቡ የመጡት፡፡
መንግስት ለህዝባዊ ተቃውሞ እየሰጠ ያለውን ምላሽ እንዴት ያዩታል?
እውነቱን ለመናገር እያየሁ ያለሁት ነገር በጣም ያሳዝናል፡፡ ህዝቡ የአገሪቱን ህገ መንግስት ተከትሎ፣መሳሪያ ሳይታጠቅ፣በሰላማዊ መንገድ አደባባይ ወጥቶ፣የመብት ጥያቄውን በማቅረቡ መሳሪያ ሊተኮስበት አይገባም፡፡ መሳሪያ ይዞ ንብረት ላውድም፣ ፀጥታ አስከባሪውን ላጥቃ እስካላለ ድረስ ለምን ይተኮሳል?! ህዝቡ ንብረት ማውደምና ፀጥታ አስከባሪ ፖሊስ ላይ መተኮስ ከጀመረ፣ ፖሊስ (ፀጥታ አስከባሪው) አልሞት ባይ ተጋዳይ ስለሚሆን፣ ለመተኮስ ይገደዳል፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ ህዝቡ ሳይታጠቅ ወይም ይተኩስ፤ ተኩሶ መግደል ምን ማለት ነው? መከላከያ ሰራዊትስ ቢሆን፤የፀጥታው ሁኔታ ከአቅም በላይ ሳይሆን፣ ህዝቡም ሳይታጠቅ … ለምን መሀል አገር ይገባል?! እዚያው ባለበት ዳር ድንበሩን በተጠንቀቅ መጠበቅ ነው ያለበት፡፡ የእርስ በእርስ ብጥብጥ ሳይነሳ ወይም ባንክ ሳይዘረፍ መከላከያ ሰራዊት አስገብቶ፣ህዝብ ላይ ማስተኮስ አግባብ ስላልሆነ በአስቸኳይ ሊታረም ይገባል፡፡  ፖሊስን በማጠናከርም ፀጥታ የማስከበር አቅሙን ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡
 ፖለቲካዊ ቀውሱን እንዴት መፍታት ይቻላል ይላሉ?
ዋናው ነገር ሆደ ሰፊ መሆን ነው፡፡ መንግስት ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖቶ አባቶች፣ ጡረታ ከወጡ ባለስልጣናት፣ ልምድ ካላቸው ጀነራሎች (ለምሳሌ እኔና አጠገቤ ያሉት ጀነራል አሰፋ፣ ለአገራችን የሚበጅ የመፍትሄ ሀሳብ ማዋጣትና ተናግረን ማሳመን እንችላለን፡፡)… ጋር  ጥልቅ ውይይት በማድረግና ህዝቡ ለሚያነሳው ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ቀውሱን መፍታት ይቻላል፡፡ እርግጥ ዘግይቷል ቢሆንም ሳይብስ መንግስት በአፋጣኝ ወደ መፍትሄው  መሄድ አለበት፡፡
የሃይማኖት አባቶች፤ገና ክፉ ነገር ሲደረግ ‹‹ይሄ አግባብ አይደለም›› በማለት መገሰፅና ድርጊቱን ማውገዝ አለባቸው፡፡ እነሱ ግን ዝምታን መርጠዋል፡፡ ነገሮች በዚህ ከቀጠሉ  እየተባባሱ ይሄዳሉ፡፡ ባለፈው ጊዜ ባልሳሳት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ቀርበው፤ ‹‹በኦሮሚያ ለተነሳው ችግር በማንም ላይ ጣታችንን አንቀስርም፤ ችግሩ የመንግስት ነው›› በማለት ህዝቡን ይቅርታ ጠይቀዋል፤ ይህንን በጆሮዬ ሰምቼአለሁ፡፡ ‹‹ጥፋቱ የኔ ነው፤ ይቅርታ›› ብለሽ ከጠየቅሽኝ በኋላ፤ አጠፋሁ ያልሽውንና ይቅርታ የጠይቅሽበትን ስህተት መድገም የለብሽም፡፡ መንግስት ግን ስህተቱን እየደገመ ነው፡፡
ከይቅርታው በኋላ ከመንግስት ምን ነበር የሚጠበቀው?
መንግስት እንደ በቀለ ገርባ ያሉ የፖለቲካ እስረኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ፈትቶ፣ የህዝቡን ቁጣ ማርገብ ነበረበት፡፡ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊዎችም መፈታት ነበረባቸው፡፡ አሁንም ቢሆን መፈታት አለባቸው፡፡ በቀጣይ መንግስት ከወታደሩ፣ ከተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ከምሁራ ጋር ውይይት በማድረግ ችግሩን ለመፍታት መሞከር አለበት፡፡ አንዲትም የህዝብ ጥያቄ ብትሆን በንቀትና በቸልተኝነት ማለፍ፣ የሚያስከፍለውን ዋጋ እየተመለከትን ነው፡፡ ችግሩ እልባት ካላገኘ ከዚህም ይከፋል ባይ ነኝ፡፡ በአፅንኦት መናገር የምፈልገው፤ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቶ መብት የሚጠይቅ ህዝብ መሳሪያ እስካልታጠቀ ድረስ፣ ህገ-ወጥ እንኳን ቢሆን ሊተኮስበት አይገባም፡፡ ይሄ በአስቸኳይ መቆም አለበት፡፡ ህዝብ ወደ ፀጥታ አስከባሪ ከተኮሰ ራስን የመከላከል እርምጃ ሊወስድ ይችላል፡፡ አንድ ምሳሌ ልንገርሽ፡- በ1956 ዓ.ም ሱማሌ ላይ ውጊያ ነበር፡፡ ጃንሆይ ሀረር ከተማ ሰበሰቡንና አማን አምዶምን እንደገና ከሾሙ በኋላ ነው፡፡ (ያኔ እኔ ምክትል መቶ አለቃ ነበርኩ) በስብሰባው ላይ ጃንሆይ ምን አሉ መሰለሽ? ‹‹እኛ ኦጋዴን መሬቱን ብቻ አንፈልግም፤ ህዝቡን በደንብ ያዙ፤ ካልተኮሱባችሁ እንዳትተኩሱ›› ብለው አስጠንቅቀውን ነበር፡፡ የአሁኑ መንግስትም ይህን መርህ ቢጠቀም ጥሩ ነው፡፡ በኦሮሚያም ሆነ በአማራ፤ያለ ህዝቡ መሬቱ ብቻ ለመንግስት ምን ይሰራለታል? ሰዎች መግደል አግባብ አይደለም፡፡ አንድ የቅርብ ወዳጄ የሆነ የዘመኑ ከፍተኛ ባለስልጣን፤ ‹‹ይቅርታ ከጠየቃችሁ በኋላ ለምን እስረኞችን አትፈቱም? ለምን የከፋውን ህዝብ ቀርባችሁ አታወያዩም?” ብዬ ስጠይቀው፣ ምን አለኝ መሰለሽ? ‹‹ጀነራል አያውቁም እንዴ… ፖለቲካ ማለት እኮ ውሸት ነው›› አለኝ፡፡ እውነቴን ነው የምናገረው፤ ይህ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ በሌላ በኩል አንዳንዴ በህዝቡ በኩልም ጥፋት ሊኖር ይችላል፡፡
የህዝቡ ጥፋት ምንድ ነው?
ህዝቡ የመንግስትን ህግ ቢቀበለውም ባይቀበለው ማክበር አለበት፡፡
ምን አይነት ህጎችን ነው ህዝብ ያላከበረው?
ለምሳሌ መንግስትን ሳያስፈቅዱ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ በህጉ የተከለከለ ሆኖ ሳለ፤ ዝም ብሎ መውጣት የለበትም፡፡ አንዳንድ ቦታ መሳሪያ ይዘው የሚወጡ ሰልፈኞች እንዳሉም ሰምቻለሁ፡፡
ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ በቂ እንደሆነ በህጉ ተደንግጓል፡፡  በአብዛኛው የሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ጥያቄዎች ግን ምላሽ እንደማያገኙ ይነገራል…
በጣም ጥሩ፡፡ መልስ ከከለከለ ጥፋቱ የመንግስት ይሆናል፡፡ ህዝቡ ወጥቶ መብቱን በሰላማዊ መንገድ ቢጠይቅ፣መንግስት ምንድነው ጭንቀቱ? ሶማሌና ጣልያን እንደገና መጥተው አይወሩን?! እኛ ነፃ ህዝቦች ነን፡፡ ህዝቡ መብቱን እስከጠየቀ ድረስ ምን የሚያሸብር ነገር አለ?! መንግስት ሀይል አለው፤ ትጥቅ አለው፤ ህዝቡ ቢወጣ ምን አስጨነቀው?!
ህዝብ ወጥቶ የጎደለውን የአስተዳደር ችግር፣ የመብት ጥሰት-----ሲቃወም መንግስት ከሰላማዊ ሰልፉ ያገኛቸውን አቤቱታዎች እንደ ግብዓት ወስዶ፣ የበታች ሹማምንቶች መፍትሄ እንዲሰጡ ማድረግ ነው ያለበት፡፡ እንደውም ራሱን የሚፈትሽበት መስታወት ነው የሚሆንለት - የህዝብ ተቃውሞ፡፡ በአጠቃላይ መንግስት በህገ መንግስቱ የተቀመጡትን ህጎች ማክበር አለበት፡፡ የህዝብን ጥያቄ “ተልባ ቢንጫጫ በአንድ ሙቀጫ” በማለት ችላ ሊለው አይገባም፡፡ አሁን የተነሳው እንኳን በአንድ ሙቀጫ በብዙም የሚመለስ ስላልሆነ አስቸኳይ መፍትሄ ያስፈልገዋል፡፡ ህዝቡ ህግ ማክበር አለበት፣ መንግስት ደግሞ የህዝቡን መብት ማክበር ይገባዋል፡፡
በአዲስ ዓመት ለአገሪቱ ምን ይመኛሉ?
የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም ፈላጊ ነው፡፡ ሰላም የሚመጣው በመፈክር ሳይሆን በተግባር ነው፡፡ እኔ ወታደር ነኝ፣ ካንቺ ይልቅ እኔ ሰላም ማጣትን እፈራለሁ፤ በጦርነት ውስጥ ተማግጄ የችግሩን ጥልቀት በተግባር አልፌበታለሁና፡፡ በቃ! ጦርነት፤ እርስ በእርስ ግጭት ይበቃናል፡፡ መንግስት እከሌንና እከሌን ከስልጣን በማንሳት ለውጥ እንደማይመጣ አውቆ በአሰራርና፣ በስትራቴጂ፣ ትክክለኛ ለውጥ ሊመጣ የሚልበትን መንገድ መፍጠር አለበት፡፡ ግለሰቦችም ምሁራኖችም የሀይማኖት አባቶችም … ለሰላም ቁርጠኝነት ማሳየት አለባቸው፡፡ በቃ! ጦርነት ይብቃን፤ 37 ኣመት ከኤርትራ ጋር፣ 17 ዓመት እርስ በእርሳችን ተጫረስን፡፡ በቃ! የጦርነት ጦስ የሚያስከትውን ዳፋ ከጎረቤቶቻችን መማር ተገቢ ነው፡፡
 በአገራችን የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ በአዲሱ ዓመት ተስተካክሎ፣ ግድያ ቆሞ፣ አገሪቱና ህዝቦቿ ሰላም ሆነው ማየት እመኛለሁ፡፡ ለዚህ ማዋጣት ያለብኝ ነገር ካለ ዝግጁ ነኝ፡፡ መንግስትም ለሰላም በሩን ክፍት ያድርግ፡፡ ለውይይት ይዘጋጅ፡፡ ቢዘገይም ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ችግሩን በመሳሪያ ከመፍታት ይልቅ በብልሀትና በአርቆ አሳቢነት መፍታት ተገቢ  ነው። በአዲሱ ዓመት መንግስት አሰራሩንና አስተሳሰቡን ለውጦ፣አገሬና ህዝቦቿ ተረጋግተውና ሰላም አግኝተው ማየት እመኛለሁ፡፡







Read 4234 times